Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለጋራ ቤቶች ግንባታ አዲስ አማራጭ ይዞ የመጣው ድርጅት ከወዲሁ ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ማዘጋጀቱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግንባታ ሥራው በከተማው ቤቶች ልማት ትብብር በሁለት ዓመታት ውስጥ ይተገበራል ተብሏል

ጎጆ ማርኬቲንግ ሰርቪስ የተሰኘውን ድርጅት በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩትና “ቤዝ ሶሉሽን ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የጋራ ቤቶች ልማት በግለሰቦች ይዞታ ላይ በስምምነት ለመገንባት የታቀደበትን ሐሳብ ያመነጩት ግለሰብ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በትብብር ለሚካሄደው የቤት ግንባታ ሥራ ከ1,700 ባለይዞታዎች ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ከወዲሁ መሰባሰቡን አስታወቁ።

አቶ ናደው ጌታሁን የጋራ ቤቶች ፕሮጀክቱ ሐሳብ አመንጪና የጎጆ ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ቤዝ ሶሉሽን ፕሮጀክት በጅምሩ ከ200 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ቤቶችን በግል ባለይዞታዎች ቦታ ላይ በመገንባት አንዱን ቤት እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እስከ ሁለት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ማግኘት የሚችሉበትን አሠራር ይዞ መጥቷል። በአንድ ባለ 500 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ከ60 ያላነሱ ቤቶች ሊገነቡ እንደሚችሉ፣ የአርታማዎቹ ከፍታም 12 ወለልና ከዚያ በላይ እንደሚሆን ተጠቅሷል።

እንደ ቶ ናደው ከሆነ በስምንት ወራት ውስጥ በተካሄደ እንቅስቃሴ ከ1,700 ባለይዞታዎች ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ለግንባታ ስምምነት ተደርጎበት ለከተማው አስተዳደር ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ከናሙና ዲዛይን ጋር በማያያዝ የቦታዎቹን ሰነድ አስገብቷል። አስተዳደሩ ከጎጆ ማርኬቲንግና ከባለይዞታዎቹ ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት በመፈረም ወደ ግንባታ ሥራው ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ እንደሚገባ አቶ ናደው አስታውቀዋል። የቤቶቹ ዋጋ 1.5 ሚሊዮን ብር ጣሪያው ቢሆንም፣ ወደፊት ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል። ከዚህ ባሻገር በዝቅተኛው ከተቀመጠው 500 ካሬ ሜትር ጀምሮ እስከ 63 ሺሕ ካሬ ሜትር ይዞታ ያላቸው 1,700 ባለይዞታዎች መካተታቸው ተገልጿል።

የባለይዞታዎቹን ተጠቃሚነት በተመለከተ እንዳብራሩትም፣ በፕሮጀክቱ መካተት የሚችሉበት የይዞታቸው ዝቅተኛው የቦታ ስፋት 500 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ በዚህ ይዞታቸው ላይ ከሚገነባው አፓርታማ አምስት ቤት የማግኘት መብታቸው አንደኛው ተጠቃሚነታቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪም በ1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚሸጥ ከተገለጸውና በባለይዞታው ቦታ ላይ ከሚገነባው እያንዳንዱ ቤት ላይ 200 ሺሕ ብር ተቀንሶ ለባለይዞታዎች ይከፈላል። ባለይዞታዎች በዚህ ከተስማሙ በኋላ የይዞታ ማረጋገጫቸው ስለሚመክንና ወደ አዲሱ አካል ስለሚዛወር የቤት ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስም በኪራይና በሌሎች አማራጮች መቆየት እንደሚችሉ ተብራርቷል። “ጠቀም ያለ ገንዘብ ስለሚያገኙ በሚመቻቸው አማራጭ መጠቀም ይችላሉ፤” ብለዋል።

ለቤቶቹ ግዥ የተቀመጡ መሥፈርቶች፣ የአከፋፈል ሥርዓቱ በምን አግባብ እንድሚካሄድ፣ የምዝገባም ሆነ መሰል ጉዳዮች የሚመለከቱት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እንደሆነ ተገልጾ የኤጀንሲው ኃላፊ ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ እንደሚሰጡ በዕለቱ ሲጠበቁ፣ ወደ ውጭ የሚወስዳቸው ድንገተኛ የሥራ ጉዳይ በመምጣቱ ሳይገኙ መቅረታቸውና ወደፊት ሌላ መግለጫ እንደሚሰጡበት ተነግሯል። የከተማ ልማት ሚኒስቴርም ለፕሮጀክቱ መሳካት ድጋፉን እንደሚሰጥ ማስታወቁን አቶ ናደው ገልጸዋል። ይህም ሆኖ ቤት ፈላጊዎችን የሚመዘግበውና የክፍያውን ሒደት የሚወስነው የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ እንደሆነ አቶ ናደው አስታውቀዋል።

ይህ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ለመንግሥት ከሚያስገኝለት የቤት ጥያቄ እፎይታ በተጨማሪ፣ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከሊዝ ሽያጭና ሌሎችም ክፍያዎች መንግሥት የሚያገኘው ገቢ ከ2.1 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት ከ1.2 ሚሊዮን ያላነሰ ቤት ፈላጊ በአዲስ አበባ ዛሬ ነገ ቤት ለማግኘት እንደሚጠባበቅ መረጃዎች ያመላክታሉ። 

መንግሥት በከፊልም፣ ሙሉ በሙሉ ክፍያ ተፈጽሞለትም የ40/60ም የ20/80 የጋር ቤቶችን ለፈላጊው ማዳረስ አልቻለም። የጋራ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ከተጀመረበት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ለተመዝጋቢውና በልማት ለተነሳው ነዋሪ የተላለፉት ቤቶች ብዛት ከ150 እንደማይበልጡ ይገመታል።

በሌላ በኩል አቅሙና ገንዘቡ ኖሯቸው፣ ልክ እንደ ቤዝ ሶሉሽን ፕሮጀክት የሰው ይዞታ ጭምር እየገዙ ቤት የሚገነቡ የሪል ስቴት ኩባንያዎች በስድስት ዓመታት ውስጥ ከ3,000 ያነሰ ቤት ሲገነቡ ታይተዋል።

ይህ በሆነበት አግባብ፣ አዲሱን ፕሮጀክት በምን የተለየ ሆኖ ነው እስከ 300 ሺሕ ቤት ሊያስገነባ የሚችለው? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ ናደው በሰጡት ምላሽ፣ የቁጠባ ቤቶቹም ሆኑ ሌሎቹ ፕሮጀክቶች የየራሳቸው ድክመት ነበረባቸው በማለት ይጀምራሉ። በአዲሱ ፕሮጀክት ነዋሪዎች ከኖሩበት ቀዬ ሳይፈናቀሉ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ፣ ቤት ገዥዎችም ከወዲሁ በተረጋገጠ ይዞታና እየተከለሰም ቢሆን ቀድሞ በተዘጋጀ ፕላን፣ በተመረጡ፣ ልምዱ፣ አቅሙና ብቃቱ ባላቸው ሥራ ተቋራጮች ሙሉ ግንባታውና ግብዓት አቅርቦቱ ስለሚካሄድ የፕሮጀክቱ መጓተት ሥጋት እንደማይኖር ተናግረዋል።

በነዋሪዎች ይዞታ ላይ የባለይዞታዎቹ ተጠቃሚነት በሚገባ ተረጋግጦ እንደሚተገበር የተነገረለትን ፕሮጀክት የነደፉት አቶ ናደው፣ ካዛንቺስ አካባቢ ከነበራቸው ይዞታ በልማት ተነሺነት ካሳደረባቸው ጫና በመነሳት ማንም ሳይጎዳ ቤት ማግኘት ይቻላል የሚለውን ሐሳብ እንዳመነጩት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አምሃ ስሜ ስለፕሮጀክቱ ሐሳብ ሲገልጹ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ላይ በተመሠረተ አካሄድ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት የእስካሁኑን የጋራ ቤቶች ወይም ኮንዶሚኒየም ግንባታን በቀየረ አካሄድ የሚተገበር ሲሆን፣ ተቋራጩ በራሱ ግብዓት እያቀረበ የሚገነባው ፕሮጀክት በመሆኑ ስኬታማ እንደሚሆን ገልጸዋል።

አቶ ናደው ከዚህ ቀደም “ጎጆ ዕቁብ” በማለት ያስጀመሩት የቁጠባ ተጠቃሚነት የንግድ ሐሳብ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ እንደነበር ቢታይም፣ ከጅምሩ በመንግሥት ሹማምንት ትዕዛዝ ተሰናክሎ እሳቸውንም ለእንግልት ዳርጓቸው ሳይተገበር መቅረቱ ይታወቃል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች