Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት የግል ባንኮች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝገቡ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዚህ ዓመት ከግል ባንኮች ውስጥ ዓመታዊ ትርፋቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር የቻሉ የግል ባንኮች ሦስት መሆናቸው ታወቀ፡፡

የ16ቱ ባንኮች የ2011 ዓ.ም. ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት፣ ሁሉም ባንኮች አትራፊነታቸውን የሚገታ ጉዳይ አልገጠማቸውም፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻሉ ሦስት አዳዲስ የግል ባንኮች በመካታተቸው፣ ከዚህ ቀደም ከተመዘገቡት ጋር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያተረፉ የግል ባንኮች ብዛት አምስት ይደርሳል፡፡

በ2011 ዓ.ም. ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች ወጪዎች በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ የቻሉት አዳዲሶቹ ባንኮች፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ናቸው፡፡

በ25 ዓመታት የግል ባንኮች ታሪክ እስከ 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለው የነበሩት አዋሽ ባንክና ዳሸን ባንክ ነበሩ፡፡ ሆኖም በ2010 ዓ.ም. ወጋገን ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ ሦስተኛው ባንክ መሆን ችሎ የነበረ ቢሆንም፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን ወጋገን ባንክ ዓመታዊ ትርፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች በመሆኑ በሒሳብ ዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ከቻሉት አምስቱ ባንኮች ውስጥ መቀላቀል አልቻለም፡፡

ከ2011 ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻሉት አምስቱ ባንኮች፣ በጥቅል ከታክስና ሌሎች ተቀናሾች በፊት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ነው፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ ከዓመታት በፊት አንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሻገር የቻለው አዋሽ ባንክ በዚህ ዓመት በግል የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን የ3.3 ቢሊዮን ብር በማትረፍ የመጀመርያውን ረድፍ ይዟል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት ከአዋሽ ቀጥሎ ከፍተኛውን ትርፍ ያስመዘገበው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.4 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት ሁለተኛ ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ዘንድሮ ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር ማሳደጉ የትርፍ መጠኑን ከ450 ሚሊዮን ብር እንዳሳደገ የሚያመላክት ነው፡፡ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2008 ዓ.ም. 325 ሚሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም. 391 ሚሊዮን ብር በማትረፍ፣ የ2010 የትርፍ ምጣኔውን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ ከታክስ በፊት 938 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ሁለተኛውን ከፍተኛ ትርፍ ሲያስመዘግብ የቆየው ዳሸን ባንክ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኘው ትርፍ 1.3 ቢሊዮን ብር ስለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ባንኩ በ2010 ከታክስ በፊት 1.14 ቢሊዮን ብር አትርፎ ነበር፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ የቻለው አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ የዘንድሮ ትርፉ 1.050 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡  ዓመት ከታክስ በፊት ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ 765.7 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማስመዝገብ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ጎራውን የተቀላቀለ ሲሆን፣ 1.05 ቢሊዮን ብር በማትረፍ የተሻለ እንቅስቃሴ አስመዝግቧል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፈው ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኘው ትርፍ 658.75 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ያገኘው የትርፍ መጠን ከ350 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው እንደሆነም አሳይቷል፡፡

የአገሪቱ የግል ባንኮች ዓመታዊ ትርፍ መጠን በዚህን ያህል የሚገለጽ ቢሆንም፣ ይህ ትርፍ ከሌሎች አገሮች ባንኮች ትርፍ አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ የሚባል መሆኑን የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡

አንድ ቢሊዮን ብር ትርፍ ማለት ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ከሌሎች አፍሪካ ባንኮች ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም የትርፍ ክፍፍል ክፍያ ግን ከፍተኛ የሚባል እንደሆነ ሲጠቀስ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

የአገሪቱ የግል ባንኮች በአሁኑ ወቅት ከ140 ሺሕ በላይ አክሲዮኖች ያሉዋቸው ሲሆን፣ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታላቸውም ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠናቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለዋል የተባሉት አምስት ባንኮች በጥቅል ከ20 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያላቸው ናቸው፡፡

ከአምስቱ ባንኮች አዋሽ ባንክ 25ኛ ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ ዳሸን 23 ዓመታት፣ ንብ 20 ዓመታት፣ አቢሲኒያ 21 ዓመታት የያዙ ሲሆን፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ ወደ 11ኛ ዓመት እየተሸጋገረ ያለ ባንክ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች