Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምግብ ዋጋ ግሽበት ከዓምናው ሰኔ ወር በ19 በመቶ ሲያሻቅብ ዘንድሮ በ13 በመቶ ከፍ ብሏል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከባድ መኪኖች ዕገዳ ምግብን ጨምሮ የሸቀጦችን እጥረት እንዳያባብስ ሥጋት አሳድሯል

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ወርኃዊ የሸማቾች የዋጋ መመዘኛ ሪፖርት፣ በሰኔ ወር የተመዘገበው ተንከባላይ የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ በ13.1 በመቶ ዕድገት ማሳየታቸውን ቢያስታውቅም፣ ይህ የዋጋ ግሽበት ከዓምናው የሰኔ ወር አኳያ በ19 በመቶ ጭማሪ እንደታየበት አመላክቷል፡፡

አብኛዛኛውን ጊዜ የዋጋ ግሽበት የሚለካው በአንድ ዓመት ውስጥ የሸቀጦችና አገልግሎቶችን የዋጋ ሁኔታ በማጥናት ሲሆን፣ በተለይም የ12 ወራት ተንከባላይ የዋጋ ግሽበት በአማካይ ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ ግሽበት እንደሚባል የኤጀንሲው ሪፖርት ያሳያል፡፡ በመሆኑም በዓመቱ በሰኔ ወር የታየው ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት 12 በመቶ ገደማ ሲሆን፣ ምግብ ነክ የሆነው የዋጋ ግሽበት ግን ከ13 በመቶ በላይ አስመዝግቧል፡፡

ከዚህም ባሻገር በዚህ ዓመት ሰኔ ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር የተነፃፀረበት የዋጋ ግሽበት መመዘኛ እንደሚያሳየውም፣ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር አኳያ ዘንድሮ የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 15.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥም በተለይ የምግብ ነክ ሸቀጦች ጭማሪ ወደ 19.8 በመቶ አሻቅቦ መታየቱ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም በዚህ ዓመት ግንቦት ወር የታየው የዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር ላይ የበለጠ የዋጋ ጭማሪ ሲያሳይ ከእነዚህ መካከል ጤፍ፣ ሩዝ፣ ገብስ፣ ማሽላና በቆሎ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከሌሎች የእህል ሰብሎች የበለጠ ጭማሪ ስለመሆኑ ኤጀንሲው አመላክቷል፡፡ በአትክልት ዋጋም ላይ ጭማሪው ጉልህ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሸቀጦች ዋጋ በግንቦት ወር ከነበረውም በላይ በሰኔ ወር ብቻ የ1.5 በመቶ ጭማሪ በማሳየት እየተባባሰ ለመጣው የዋጋ ግሽበት መንስዔ ሆነዋል፡፡ ወርኃዊ የዋጋ ግሽበት የአጭር ጊዜ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ሲሆን፣ በአብዛኛው የአጭር ጊዜ ክስተትን ያመላክታል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች አባላት የመንግሥታቸውን የዚህ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት አንዱ አጀንዳቸው ይኸው የዋጋ ግሽበት ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እስከ ግንቦት ወር ድረስ እያሽቆለቆለ መምጣቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጸው የዋጋ ግሽበት፣ በሰኔ ወር ዳግም እንዳገረሸም ተናግረው ነበር፡፡

ለዋጋ ሽግበቱ መባባስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ጉዳዮችም በአዲስ አበባ ሥጋት መፍጠር እንደጀመሩ እየተሰማ ነው፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር የጀመረው የሞተር ብስክሌቶች ክልከላና የከባድ ተሽከርካሪዎች በምሽት ካልሆነ በቀር በቀን እንዳይነቀሳቀሱ መታገዳቸው ከወዲሁ የሸቀጦች እንቅስቃሴን እየገታ እንደመጣ ታውቋል፡፡ በርካታ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችም በከተማው ዳርቻዎች ታይተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንደሚሉት መመርያው፣ የትራፊክ ፍሰትን ማስተካከል ላይ ያነጣጠረ እንጂ በሸቀጦች ትራንስፖርት ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ በአግባቡ ያልታየ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ የሚገባውም ሆነ የሚወጣው ሸቀጥ ላይ ትልቅ ጫና አሳርፏል፡፡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ በከተማው አስተዳደር የተላለፈውን ውሳኔ ማስተግበር እንደጀመረና ከወዲሁም በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ይታዩ የነበሩ መጨናነቆች መስተካከል እንደጀመሩ፣ አሽከርካሪዎችም እፎይታ እያገኙ መምጣታቸውን የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጄሬኛ ሐርጳ ለሚዲያ አካላት በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች በሌሊት ጭነት የማይጫንና የማይራገፍ በመሆኑ፣ ሸቀጦቹ ሌሊቱን ይጫኑ ቢባል እንኳ እንደማያልቅና ቀን በቀን ማጓጓዝ ግድ የሚል በመሆኑ አስተዳደሩ ውሳኔውን ለማጤን የሚገደድበት ጫና እንደሚፈጠር አሽርካሪዎች ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ የትራፊክ ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ግን መመርያው ሳይዛነፍ እንደሚተገበር አስታውቀዋል፡፡ መመርያው ተላልፈው በቀን ሲሽከረከሩ የሚገኙ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከመስመር እንዲወጡ ተደርገው አሽከርካሪዎቹም ከአንድ ሺሕ ብር ያላነሰ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህንን ቅጣት ሽሽት፣ የከባድ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ከወዲሁ ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች ፊታቸውን እያዞሩ መጥተዋል፡፡ 

ይህ በመሆኑም በርካታ ተሽከርካሪዎች ሞተር ብስክሌቶችን ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን የጭነት አገልግሎት ወደ ክልል ከተሞች እያዛወሩ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ በዚህ ሳቢያ ሊከሰት የሚችል የሸቀጥ እጥረት ከወዲሁ ታስቦበት መፍትሔ ካልተሰጠው የዋጋ ንረትንም ሆነ ግሽበትን በማባባስ የኑሮ ውድነቱን ጣሪያ እንዳያስነካው ሥጋታቸውን የሚገልጹ ተበራክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች