Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች በክሪፕቶከረንሲ ሥጋት ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ሽኝት ተደረገላቸው  

የባንክ አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ ካልተተገበረ ለወደፊቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ፈታኝ እንደሚሆን ተሰናባቹ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ዛባ ገለጹ፡፡

አቶ አዲሱ ይህንን የገለጹት፣ ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሒልተን ሆቴል የደቡብ ግሎባል ባንክ ባዘጋጀላቸው የሽኝት ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ ስለባንክ ኢንዱስትሪው ቀጣይ ዕጣ ፈንታን አጽንኦት ሰጥተው ለመናገር የወደዱት በተለያየ አቅጣጫ እየታየ ያለውን በቴክኖሎጂ የታገዘ ድንበር ተሻጋሪ ገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎቶች ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የፌስቡክ ክሪስቶክረንሲን በዋቢነት በመጥቀስ ነው፡፡ ፌስቡክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጀምር ያቀደው የአንድ ገንዘብ የክፍያ ዘዴ፣ ከሰው ወደ ሰው የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራን የሚያስተጓጉል በመሆኑ ባንኮች እንዲህ ያለውን ድንበር ተሻጋሪ የፋይናንስ አገልግሎት ለመቋቋም የሚችሉበት ሥርዓት መከተል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ፌስቡክ አገልግሎቱን 2.3 ቢሊዮን በሚደርሱ ደንበኞቹ አማካይነት በአነስተኛ የአገልግሎት ዋጋ የገንዘብ ማስተላለፉን ሥራ ለመጀመር መነሳቱ፣ በተለመደው የባንክ አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ማስተር ካርድና ቪዛ ካርድን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ተቋማትን ይዞ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ፣ እስካሁን በገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር የሚታወቁት ኩባንያዎችም ከገበያ ውጪ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል፡፡ አገልግሎቱ ከባንኮች ውጪ የሚቀርብ በመሆኑም ማዕከላዊ ባንኮች የገንዘብ ዝውውሩን ለመቆጣጠር የሚቸገሩበት ደረጃ ሊኖር ስለሚችል፣ የዚህ አገልግሎት መጀመር በብዙ አቅጣጫ የባንክ ኢንዱስትሪውን ሊፈትን እንደሚችል ሥጋት ማሳደሩን አቶ አዲሱ አብራርተዋል፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስም ፌስቡክ ለመተግበር ያሰበውን አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት እንዴት ልንቆጣጠረው እንችላለን የሚል ሥጋት በማሳደሩ፣ ከሪዘርቭ ባንክ ኦፍ አሜሪካ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ አገልግሎቱ ለጊዜው እንዲዘገይ እንደተደረገ ያስታወሱት አቶ አዲሱ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ማዕከላዊ ባንኮችም ብርቱ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ያሳያል ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥጋቶችን ለመቋቋም የኢትዮጵያ ባንኮች ለቴክኖሎጂ ያደላ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ አዲሱ፣ ከቅርንጫፎች ማስፋፋት በመለስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም አቅምና ችሎታ ተስፋፍቶ ካልተተገበረ በቀር፣ ተወዳዳሪ ሆነው መዝለቃቸው ፈታኝ ይሆናል ብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው አንዳንድ ባንኮች፣ እርስ በርስ በመዋሃድ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩሩ እንዳደረጋቸው በቅርቡ ሦስት የጣሊያን ባንኮች ያደረጉትን ውህደት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥም እኛ ፈለግነውም አልፈለግነው እንዲህ ያለው ነገር እየመጣ ነው፤›› ያሉት አቶ አዲሱ፣ ‹‹የደንበኞቻችንን ልብ ለመያዝ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በቀዳሚነት ሊተገበር ይገባል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ለራሳችንም ለፋይናንስ ኢንዱስትሪውም ሥጋት የሆነውን በመጠቀም የአገራችን ባንኮች በቴክኖሎጂ ታግዘው አቅማቸውን አደራጅተው መንቀሳቀስ ካልቻሉ ሊፈተኑ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የክሪፕቶከረንሲ አካሄድ በጣም አደገኛ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አዲሱ፣ የባንኮች አልፎ የሚሄድ በመሆኑም ይህ አዲስ የገንዘብ ማስተላለፍ ዘዴ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ለብዙ ሥጋቶች የሚያጋልጥ ነው፡፡ ነገር ግን ፌስቡክ ይህንን አገልግሎት በይፋ እንደሚጀምር አረጋግጧል፡፡

ከባንኪንግ ሲስተም ውጭ የሚሠራ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ሥጋት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ባንኮች ኮርስፖንደት የሚጠቀሙባቸውን ባንኮች ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል መሆኑን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ ትራንዝ አክሽኖችን ፌስቡክ የሚያከናውን ከሆነ ከኮርስፖንደት ባንኮች ጋር ሊኖር የሚችለውንም ግንኙነት ሊያስቀር የሚችል በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የባንኮች ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች በሙሉ በድምር ያላቸው ካፒታል አውሮፓ ወይም መካከለኛው ምሥራቅ ካለ አንዱ መካከለኛ ባንክ ያለውን ካፒታል እንኳን አያህልም፤›› ያሉት አቶ አዲሱ፣ የባንኮች ውህደትም ጠቃሚ ሊሆን መቻሉም ሳያስታውሱ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ከዚህ ጋር ተያይዞ የባንኮች ውህደትም ሊመጣ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ ውህደቱን መቀበል ካልተቻለ እንኳን አቅሙን ከድርጅቱ ቢሆንም ዘርፉ ራሱን ማስተዳደር የግድ ነው ይላሉ፡፡ ፌስቡክ ዓለምን ለመቆጣጠር የጀመረው ይህ እንቅስቃሴ እንደ ዌስተርን ዩኒየንና መኒ ግራም ያሉ ገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎችን የሚያጠፉ በመሆኑ፣ ከእነዚህ ተቋማት ጋር ይሠሩ የነበሩ ባንኮች በገንዘብ ማስተላለፍ ሥራቸውን ያገኙ የነበረውን ጥቅም ያሳጣቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ አዲሱ ሽኝት ፕሮግራም ላይ ደቡብ ግሎባል ባንክ  ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ አቶ አዲሱ ባንኩን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን አወል፣ አቶ አዲሱ አበርክተዋል ያሏቸውን መልካም ተግባራት በሰፊው አብራርተዋል፡፡

በደቡብ ግሎባል ባንክ የአምስት ዓመት ቆይታቸውን በማጠናቀቅ የተሸኙት አቶ አዲሱን በባንክ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽ ግማሽ ሚሊዮን ብር የተበረከተላቸው ሲሆን፣ የወርቅ ሀብልና አበርክቶአቸውን የሚገልጽ ሰርተፍኬት ከባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እጅ ተረክበዋል፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲሱ በባንኩ ቆይታቸው አበረከቱ ያሏቸውን አስተዋጽኦ በሰፊው ያብራሩ ሲሆን፣ በእሳቸው አመራር ባንኩ ከፍተኛ እመርታ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የባንኩ ትርፍ መቶ በመቶ በላይ መጨመሩን ለአብነት ያነሱ ሲሆን፣ ባንኩን በማሳደጉ ረገድ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አቶ አዲሱ በመሪነት ኃላፊነታቸውን ስለመወጣታቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ አዲሱም ሥራቸውን ለመሥራት ቦርዱ የሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የቻሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በደቡብ ግሎባል ባንክ ቆይታቸው አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ስለማበርከታቸው የተናገሩት አቶ አዲሱ፣ ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተደረጉ ጥረቶችን ግን አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በተለይ የባንኩን ካፒታል ወደ 500 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ የወጣውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ለማሟላት የነበረውን ተግዳሮት ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን የካፒታል መጠን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ለማሟላት ፈተና በነበረበት ወቅት ብሔራዊ ባንክ ቀን እንዲጨምርልን ጠይቀን እንኳን አልፈቀደልንም፡፡

ሆኖም ከባንኩ ጋር የሚሠሩና በስም የጠቀሷቸው ባለሀብቶችና ኩባንያዎች፣ እንዲሁም ባለአክሲዮኖች በወሰዱት ዕርምጃ ካፒታሉን ማሟላት አስችሏል፡፡ አሁን ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉ 775 ሚሊዮን ብር የደረሰ መሆኑንም ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ወቅት የባንኩ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን በዕጥፍ ለማሳደግ የወሰኑትን ውሳኔ በማስታወስ ባንካቸው የሚፈለገውን ካፒታል አሟልቶ እንዲቀጥል አስችሏቸዋል፡፡ የተለያዩ የአሠራር ሥልቶች የሚተገበሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ አሳታፊ የአመራር ስልትን የመከተል ልምድ ያላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አዲሱ በዚህም ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀጣዩ ማረፊያቸውን በተመለከተ በመጠኑ በገለጹት ማብራሪያ ንባብ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ሆኖም አነስ ያሉ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡  

‹‹ለዓመታት ለቤተሰቤ ጊዜ አልሰጠሁም፤›› ያሉት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት፣ በዚህ እንደ ዕረፍት በሚቆጥሩት ቀጣዩ ጊዜ ለቤተሰቤም የነፈግሁትን ጊዜ የምንሰጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡

አቶ አዲሱ ከአምስት ዓመት በፊት ለአምስት ዓመት አገልግለውበት ከነበረው አቢሲኒያ ባንክ በተመሳሳይ መንገድ በተዘጋጀላቸው የሽኝት ፕሮግራም አቢሲኒያ ባንክ 500 ሺሕ ብር አበርክቶላቸው ነበር፡፡ አቶ አዲሱ ባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሠሩባቸውን የኃላፊነት ቦታዎች የሚጠቁመው መረጃ በኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በክሬዲት መምርያ ሥራ አስኪያጅ፣ በምክትል ፕሬዚዳንትና በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ የአቢሲኒያና የደቡብ ግሎባል ባንኮችን በፕሬዚዳንትነት (አሥር ዓመት) መርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንትና በሌሎች መንግሥታዊና የግል ተቋማት ውስጥ በቦርድ አባልነት ያገለገሉና በማገልገል ላይ መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች