Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹አቧራችንን ካራገፍን ብዙ የሚሸጡ ሀብቶች ስላሉን ሀብቶቹን ለማየት ልቦናችን ቀና መሆን አለበት››...

‹‹አቧራችንን ካራገፍን ብዙ የሚሸጡ ሀብቶች ስላሉን ሀብቶቹን ለማየት ልቦናችን ቀና መሆን አለበት›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ከአጭር ጊዜ ዕቅድ አንፃር የቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተደርጎበታል

መንግሥት ከዋጋ ግሽበት አንፃር የቤት ኪራይ ዋጋን ለመቆጣጠር አቅዷል

 በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የመለወጥ ዕድል መኖሩንና ይህንን ዕድል ለመጠቀምም አቧን ማራገፍና በቅን ልቦና ብቻ ማየት እንደሚጠይቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

- Advertisement -

‹‹አቧራችንን ካራገፍን ብዙ የሚሸጡ ሀብቶች አሉን›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እነዚህን ሀብቶች ለማየት ልቦናችን ቀና መሆን አለበት፤›› ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፣ የ2012 ዓ.ም. በጀት ለማፀደቅና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕቅዳቸውን በተመለከተ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ አንፃር በቀጣዮቹ ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶት የሚተገበረው የቱሪዝም ዘርፍ ልማት እንደሆነ ገልጸዋል።

አርባ ምንጭን የመሰለ የምድር ገነት እያለ የቱሪዝም ሀብት ማመንጨት አለመቻሉን የነቀፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአርባ ምንጭ አንድ ትልቅ ሪዞርት በመገንባት ትልቅ ሀብት ለማመንጨት ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ድርድር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ብዙ የሚሸጡና ገቢ ማስገኘት የሚችሉ ያልታዩ ሀብቶች መኖራቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ የሰበሰቧቸውና ይጠቀሙባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎች እንደ ተራ ነገር አቧራ ወርሷቸው በመጋዘን ተቆልፎባቸው መቀመጣቸውን ጠቁመዋል።

‹‹አቧራችንን ካራገፍን ብዙ የሚሸጡ ሀብቶች አሉን›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ የቆዩ፣ ያለፈውን ዘመን የዓለም የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ደረጃ የሚያስታውሱና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ይጠቀሙባቸው የነበሩ የቤተ መንግሥት ተሽከርካሪዎች ለቱሪስቶች ዕይታ ክፍት በማድረግ፣ የማይናቅ ሀብት ማመንጨት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ለዚህም ሲባል የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥትና መኖሪያን በማደስ በቀጣዩ ዓመት ለቱሪዝም ክፍት እንደሚደረግ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቢሮና መኖሪያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደሚገኙበት የምኒልክ ቤተ መንግሥት እንደሚዘዋወር አስረድተዋል።

የምኒልክ ቤተ መንግሥት ከፊል ይዞታ በማስዋብ የኢትዮጵያ መንግሥታትን ታሪክ መዘከሪያ ሙዚየም ለመቀየር የተጀመረው ፕሮጀክትም፣ በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ተጠናቆ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ የተመጀመረው የተፋሰሶች ልማትና ፓርክ ግንባታ፣ በምኒልክ አደባባይ የተጀመረው የዓድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት፣ በለገሃር አካባቢ የሚጀመረው የሪል ስቴትና የከተማ ልማት ተደምረው ከአዲስ አበባ ብቻ ላቅ ያለ የቱሪዝም ሀብት ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከእነዚህ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሒደትና ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩም ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለከተማዋ ወጣቶች እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ እንደያዘ፣ በአዲስ አበባ የተጀመሩት የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች፣ እንዲሁም 20 ሺሕ ሰው ማስተናገድ የሚችል የብሔራዊ ላይብረሪ ግንባታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጭምር ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ወጣቶችን በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች አሠልጥኖ ወደ ውጭ ለመላክ ከተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ጋር ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በተደረገው ድርድርም 50,000 ወጣቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ሠልጥነው ወደ ዱባይ በቀጣዩ በጀት ዓመት እንደሚላኩ ተናግረዋል፡፡

የኃይልና ሌሎች የመሠረተ ልማት አቅርቦት በማሟላት በርካታ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በቀላሉ ማፍሰስ እንዲችሉ፣ በዚህም የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ለማዕድን ዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥና በዚህም የአገሪቱን የፖታሽ፣ የወርቅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብቶች በማልማት ሀብት የማመንጨት ሥራ በጥንቃቄ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ አካባቢ ዳግም ያገረሸው የሸቀጦች ዋጋ ግሽበትን ለማስተካከልም ኮሚቴ መቋቋሙንና የግሽበት ሒደቱን ለመቆጣጠርም፣ ከማክሮና ከፊስካል ፖሊሲ አኳያ አፋጣኝ መፍትሔዎች እንደሚቀመጡ ገልጸዋል። የመሠረታዊ ፍጆታዎችን በማቅረብ እጥረቱን የመቅረፍና ዋጋን የማረጋጋት ተግባርም እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የዋጋ ግሽበቱን እያበረታቱ የሚገኙ ሌሎች ምክንያቶችን ማለትም የሎጂስቲክስ ዘርፉ እየፈጠረ ያለው መሰናክል መፍትሔ እንዲያገኝ እንደሚደረግ፣ እንዲሁም የከተማ የቤት ኪራይ ዋጋን በጥናትና ሕግን መሠረት ባደረገ መንገድ መንግሥት መቆጣጠር እንደሚጀምር ገልጸዋል።

በዘንድሮ ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደው የታክስ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ ሳለ፣ ለቀጣዩ ዓመት ከቀረበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ በዚህ ዓመት ከተሰበሰበው በእጅጉ የሚልቅ ገቢ ከታክስ እንደሚሰበሰብ ታሳቢ የመደረጉ ተገቢነት፣ የአገሪቱ የውጭ ክፍያ ሚዛን ከፍተኛ መሆንና የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሽቆልቆል በኢኮኖሚው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ጫናን የተመለከቱ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ቀርቦላቸዋል።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሲያድግ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በመጠቆም፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር የአንድ ቢሊዮን ዶላር ልዩነት ያለው መጠባበቂያ ክምችት መኖሩን አስረድተዋል።

በብድር የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ የብድር መክፈያ ጊዜ መድረስ እንደሌለበት ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መሰል ችግሮችን ለማስተካከል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውንና ውጤት መገኘቱን፣ ከእነዚህም መካከል ከአበዳሪ መንግሥታት ጋር በመደራደር የክፍያ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን፣ እንዲሁም ኮንሴሽናል (በገበያ የሚወሰን የወለድ ክፍያ የሚጠይቁ) የውጭ ብድሮችን መበደር እንዲቆሙ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ሆነ በቀጣዩ በጀት ዓመት ለዕዳ ክፍያ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከ2012 ዓ.ም. በጀት ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ወጪ (25 ቢሊዮን ብር) ለዕዳ ክፍያ እንደሚውል አመልክተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጤናማ እየሆነ መምጣቱን፣ በቀጣዮቹ ዓመታት የወጪ ንግድ ዘርፉን በማጠናከር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ ከተቻለ የአበዳሪ አገሮችንና ተቋማትን እምነት ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

 ምክር ቤቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ካፀደቀ በኋላ ለ2012 በጀት ዓመት የቀረበውን 386.9 ቢሊዮን ብር በጀት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራትና አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸሙን በመገምገም የሥራ ዘመኑን አጠናቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...