Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢኮኖሚውን ለመታደግ የፋይናንስ ሞዴልን መቀየር እንደ አማራጭ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርትና ሪፖርታቸውን ተንተርሶ የሚሰጡት ማብራሪያ ተጠባቂ ነበር፡፡ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሚያቀርቡት ሪፖርት ባለፈም ወቅታዊውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡት ማብራሪያ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነበር፡፡ በተለይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ጫና ያለበት ከመሆኑ አንፃር ወደፊት ለመራመድ መንግሥት ምን እንዳቀደ ለመገንዘብ እንዲሁም የዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ምን ምስል እንዳለው ለመረዳትም ሪፖርታቸው ሲጠበቅ ነበር፡፡   

ከኢኮኖሚ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸውም ሆነ ሪፖርታቸውን ተከትሎ ለተነሱ ጥያቄዎች ከሰጡት መልስ መገንዘብ የሚቻለው፣ መንግሥት በበጀት ዓመቱ በአገሪቱ ላይ ያሉት ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የበለጠ ችግር እንዳይፈጥሩ በማድረግ ሥራ መሥራቱን ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ብለዋል፡፡ መንግሥታቸው በ11 ወራት ከውኗቸዋል ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ ኢኮኖሚው የ9.2 በመቶ ማስመዝገቡን ይገኝበታል፡፡ ባለፉት 11 ወራት 21 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱና ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ20 በመቶ ብልጫ ማሳየቱም ተጠቃሽ ነው፡፡

የሥራ አጥና ኢንቨስትመንትም የሪፖርታቸው አካል ነበር፡፡ በአዲስ አበባ በቢሊዮን የሚገመቱ ወጪዎች የሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው ያስረዱበት ነው፡፡ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም በተመሳሳይ በአኃዝ የተደገፈ ማብራሪያ ጭምር አቅርበዋል፡፡ በተለይ ግን መንግሥት የፋይናንሻል ሞዴሉን መለወጥ አለበት የሚለው የመንግሥታቸውን አቋም የሚያንፀባርቀው ነጥብ በዋናነት ሊታይ ይችላል፡፡ የኑሮ ውድነትን የተመለከቱ ጉዳዮችም በበለጠ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሞኑ ሪፖርታቸው አጉልተው ያመላከቱት አገሪቱ መንግሥት ሲከተል የነበረውን የፋይናንስ ሞዴል መቀየር እንዲኖርበት ያስገነዘቡበት ነው፡፡ የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ መዳከም ይኸው የፋይናንስ ሞዴል ስለመሆኑ ያስረዱ ሲሆን፣ ይህም በመሆኑ የፋይናንስ ሞዴሉን መቀየር አስፈላጊነት ላይ ግልጽ የሆነ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ እስካሁን የነበረውን የፋይናንሻል ሞዴል ይዞ መቀጠል እንደማይችልም ያስታወቁበት ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰውን ተንተርሶ ከምክር ቤቱ አባላት ለማክሮ ኢኮኖሚው አፈጻጸም መዳከም የፋይናንስ ሞዴል ብቻ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳም ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የፋይናንስ ሞዴል ብቻ አለመሆኑን ነገር ግን አናቱ የፋይናንስ ሞዴል በመሆኑ ይህንን መለወጥ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የማይክሮ ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ የመውደቅ ችግር የፋይናንስ ሞዴሉ ስለሆነ እሱን የመለወጥ አስፈላጊነት ላይ ግልጽ የሆነ አቋም መያዙን አስረድተዋል፡፡ ይህንን በማድረግም አብዛኛውን ችግር ሊፈታ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሞዴሉን መለወጥ ሁሉንም ችግር ይፈታል ማለት እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡ ለኢኮኖሚው አፈጻጸም መዳከም በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው እርሳቸው እንዳሉት የአናቱን ችግር መፍታት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ከገለጻቸው መረዳት ይቻላል፡፡  

የፋይናንስ ሞዴሉን መለወጥ አስፈላጊነቱ ላይ አክለው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል የተከተልነው የፋይናንስ ሞዴል በአብዛኛው በብድር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢኮኖሚስቶች ቢግ ፑሽ ይሉታል፡፡ የቆመውን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ ተብሎ ከፍተኛ ብድርና የአገር ውስጥ ሀብት ፈሷል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ አካሄድ በዚያን ወቅት ትክክል እንደነበረ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚያ መንገድ ውጪ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በእኛ ድርብርብ ችግር ምክንያት ተበድረን የጀመርነውን ፕሮጀክት በጊዜ ስለማንጨርስ፣ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን አዋጭነታቸውን በዝርዝር ሳናጠና ብድር ስላገኘን ብቻ ስለገባንበት፣ አሁን ፕሮጀክቶቹ ሳያልቁ ብድር መክፈል ግዴታ ስለሆነብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንደ አስረጅ ያቀረቡትም በ2010 በጀት ዓመት ከአገሪቱ ጠቅላላ በጀት ውስጥ ሦስተኛው ትልቅ በጀት ለዕዳ መክፈያ የሚውል መሆኑን ነው፡፡ በቀደመው የፋይናንስ ሞዴል ምክንያት ለዕዳ ክፍያ እየወጣ ያለውን ወጪ በማሥላት ጭምር ኢኮኖሚውን ለማጎልበት የፋይናንስ ሞዴሉን ከፍ አድርጎ የመመልከቱን ተገቢነት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያዎች አመልክተው፣ ‹‹መሠረታዊ ችግር እሱ ነው፡፡ መሠረታዊ መፍትሔውም እሱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የፋይናንሻል ሞዴል ለውጡ አስፈላጊነት ላይ የተሰጠው ማብራሪያ መለወጥ እንዳለበት፣ እንዲሁም ከዚህ በኋላ በቀደመው መንገድ መጓዝ አይቻልም፣ የሚለውን አጽንኦት የሰጡበት ይመስላል፡፡ ይህ እንደ አንድ የፖሊሲ ለውጥ የሚታየው የመንግሥት አቋም የፋይናንስ ሞዴል ለውጡ ውስጣዊ ይዘት ምን እንደሆነ በዝርዝር ባያመለክትም፣ የተደረሰበት ድምዳሜ አግባብነት እንዳለው ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የፋይናንስ ሞዴል ለውጡን አስፈላጊነት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ላይ አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው መካከል አንዱ የሆኑት ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገለጹት ሌላ በግልጽ የተቀመጠ ዶክመንት አለመውጣቱ በዝርዝር ለመናገር ባይችልም፣ በጥቅል ግን ሲታይ አገሪቱ ትከተል የነበረው የፋይናንስ ሞዴልን መለወጥ አለበት የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የፋይናንስ ሞዴል ለውጥ ይደረጋል ማለት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክና ከሌሎች የፋይናንስ ምንጮች የሚወሰደውን ብድር እየቀነሰ ገበያ መር የሆነ የፋይናንስ አተገባበር መዘጋጀቱን ያሳየ ነው፡፡

ሆኖም ይህ የፋይናንስ ሞዴል ለውጥ እንዴት ነው የሚተገበረው የሚለው ግልጽ ቢሆንም የበለጠ ማስረዳት ይቻላል ያሉት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ሞዴል መለወጥ ግን ምንም ጥርጥር የሌለው ተገቢ ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም የፋይናንሻል ሞዴሉ መለወጥ አስፈላጊ ነው ብቻ ሳይሆን ይህን ሞዴል ከመለወጥ ሌላ ምርጫ የለም በማለት አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም አባባላቸው ማጠናከሪያ ያደረጉት እስካሁን የነበረው የፋይናንስ ሞዴል በመሟጠጡ አዲስ ሞዴል መከተል ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የፋይናንስ ሞዴሉን መለወጥ አንድ ነገር ሆኖ ሌሎች መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የንግድና የኮንትሮባንድን ታክስ ማጭበርበርና የመሳሰሉት ኢኮኖሚውን የሚጎዱና መስተካከል የሚገባቸው መሆኑን በማስታወስ፣ የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማከም ከፋይናንስ ሞዴል አንፃር እኩል ኮንትሮባንድን መቆጣጠር፣ የግብር ገቢ አቅምን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከፋይናንስ ሞዴል ማሻሻል ጋር መሠራት ያለባቸው ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት ጉዳዩ የግል ዘርፉን ማጠናከርና በማነቃነቅ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ማድረግ አስፈላጊነት ላይ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹም ይህንን ሐሳብ ይስማሙበታል፡፡ የግል ዘርፉ ተሳትፎ እንዲያደርግ ዕድል መስጠቱ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከፍተኛ እንደሚያደርገው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ለምሳሌ ሥራውን እዚሁ በማምረት፣ አገራዊ ኢንቨስትመንትና ቁጠባን ማመጣጠን አስፈላጊነቱም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ደግሞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፋይናንስ ሞዴል ለመለወጥ  ማቀድ ተገቢ መሆኑንና ከዚህም ቀደም ብዙ ስንልበት ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን የሚጠበቀው ለውጥ እኔ እንደተረዳሁት እስካሁን በአብላጫው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት እያንቀሳቅሰ የነበረው የመንግሥት ኢንቨስትመንት በመሆኑ፣ ይህንን ደረጃ በደረጃ በማስተካከል የግል ዘርፉን ያሳተፈ ፖሊሲ እንዲኖር ማስቻል ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡  

‹‹በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚው እንዲያድግ የረዳው መንግሥት ከፍተኛ የሆነ ካፒታል በማፍሰስ ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው ደግሞ ተበድሮ ነበር፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ አሁን ይህ ሊቀየር ይችላል የሚል ግምታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አሁንም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንተደመጠው የፋይናንስ ሞዴሉ መታየት አለበት የሚለው ገለጻ፣ ከመንግሥት ጫና ላይ ወርዶ የግል ዘርፉ ኃላፊነቱን ወስዶ ኢንቨስትመንቱን ያካሂድ የሚለው ማብራሪያቸው ትክክል ስለመሆኑም አቶ ዘመዴነህ ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም ይህ የሞዴል ለውጥ መንግሥት ይከተላቸው የነበሩ አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ማለት ሳይሆን ይቀንሳል የሚል እሳቤ እንዳላቸው ያከሉት አቶ ዘመዴነህ፣ የሞዴል ለውጡ አገሪቷ ላይ ያለው የብድር ጫና እንዲቀንስ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በአንፃሩም የግል ዘርፉ ተሳትፎ እየጨመረ ይመጣል፡፡ የታክስ መሠረቱን ያሰፋል፡፡ ብዙ ሥራ ይፈጠራል፡፡ በጥቅል ሲታይም በዚህ ዘርፍ የፖሊሲ ለውጥ የሚደረግ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ የሚጠቁሙት አቶ ዘመዴነህ፣ አሁንም በዚሁ ዙሪያ የፖሊሲ ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም ፕራይቬታይዜሽኑን ነው፡፡

‹‹የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሲበደሩ ያው መንግሥት ተበደረ ማለት ነው፡፡ ወደ ግል ሲዛወሩ ግን የልማት ድርጅቶችን የገዙት የግል ኩባንያዎች ናቸው የሚበደሩት፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ይህ ደግሞ መንግሥት ላይ ያለውን የፋይናንስ ጫና ስለሚቀንስ የፋይናንስ ሞዴሉ መለወጡ ላይ ይስማማሉ፡፡

ቴዎድሮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው የፋይናንስ ሞዴሉን ለመለወጥ መንግሥት ያሰበበት መንገድ ገና ወደፊት የሚታወቅ ቢሆንም፣ እንደ እርሳቸው አቋም ሞዴሉ መቀየሩ አግባብ ቢሆንም በእጅጉ መታሰብ አለበት ብለው ያስቀመጡት ነጥብ አለ፡፡

ገበያውን ነፃ እያደረክ ስትመጣ ቁጥጥሩ መጎልበት አለበት፡፡ በሌሎች አገሮችም ገበያ መር ለማድረግ በነበረው አሠራር ሙሉ በሙሉ አይደለም የለቀቁትና አሁን ያለውን ሞዴል ለመለወጥ ሲታሰብ ተቆጣጣሪ አካላትን ማጠንከር ግድ ይላል ብለዋል፡፡ በተለይ የፋይናንሱ ዘርፍ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ የፋይናንስ ሞዴሉ ሲታሰብ ይህ ጉዳይ በቀዳሚነት ሊታሰብ የሚገባ ነው፡፡

መንግሥት ሲጠቀምበት የቆየው ሞዴል ከብድር ጋር የተያያዘ ብቻ እንዳልነበር ያስታወሱት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ሌሎች ጉዳዮችም መታየት አለባቸው ብለው በእርግጠኝነት ግን መደረግ ካለበት የድሮ የፋይናንስ ሞዴል መቀጠል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም ገበያውም ኢኮኖሚውም እየተናገሩ በመሆኑ በዝርዝር ይዘቱን ይፋ ማድረግና መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡ ሌላው ቢቀር መንግሥት የሚወስደውን ብድር መቀነስ አለበት ብለዋል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የግል ዘርፉ ሚና ከፍ ይላል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ለግል ዘርፉ ሊሰጥ የሚገባው ማበረታቻ ከፍ ማለት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሪፖርታቸው ካካተቱትና ተጨማሪ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ውስጥ ሌላው የዋጋ ግሽበትን የተመለከተ ነው፡፡ ከፓርላማ አባላቱ ይህ ጉዳይ በተለየ መልክ ተጠይቋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው የግንቦት ወር የዋጋ ግሽበት 16.2 በመቶ መድረሱ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ይህ ግሽበት ከፍተኛ የሚባል በሸማችም ሆነ በኢንቨስትመንት ላይ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ፣ አሁን በኢኮኖሚው ውስጥ እንደ ሥጋት የሚታይ ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ያስፈልጋል ሲባል አንዱና ዋናው ነገር ከዋጋ ግሽበት ጋር የሚያያዙ ስለሆኑ በብርቱ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በአኃዝ የተቀመጠው የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ምንድነው ብሎ በደንብ ዓይቶ መፍትሔ መስጠቱ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ባለፉት 13 እና 14 ዓመታት እንደታየው የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በአብዛኛው በባለሁለት አኃዝ ነበር፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ በሠለጠነው ዓለም የዋጋ ግሽበት ከሁለት በመቶ በላይ እንዳያድግ ይሠራል ብለዋል፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ ከአራት እስከ ስድስት በመቶ እንዳይበልጥ የሚደረግ በመሆኑ፣ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት ደረጃ በተለያየ መንገድ በመጠቀም መስተካከል አለበት ይላሉ፡፡  

ለአገሪቱ የዋጋ ግሽበት የምርት እጥረት ብቻ የሚፈጥረው ያለመሆኑን የሚገልጹት አቶ ዘመዴነህ፣ የዘመናዊ ግብይት ዕጦትም ለችግሩ መባባስ መንስዔ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ገበያ 200 እና 300 በመቶ ትርፍ የሚያዝበት ነው፡፡ ይህ በዓለም ላይ የለም፡፡ ይኼ አካሄድም በፖሊሲ ጭምር  ታግዞ ሊስተካከል ይገባል ብለው፣ የዋጋ ግሽበት ከምርት እጥረት ጋር ብቻ ያልተሳሰረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአገሪቷ ገበያ ሥርዓት ዘመናዊ ባለመሆኑ የፖሊሲ ለውጥ ያስፈልገዋል ያሉት አቶ ዘመዴነህ ይህንንም ሲያፍታቱ፣ ‹‹አሁን ውስብስብና ኋላ ቀር የሆነ፣ የገበያ ስርጭት ነው ያለው፡፡ አንዳንድ ቦታ እንዲያውም በሞኖፖል የተያዘ ይመስላል፡፡ በተለይ ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ ገበያው በሞኖፖል ተይዟል፡፡ ስለዚህ ይህንን በመፍታት አዳዲስ ኩባንያዎችን በማስገባት የውድድር ሜዳውን በማስፋት መሠራት አለበት፡፡ ዘርፉን የተቀላቀሉ አዳዲስ ገቢዎችንም ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ከሚታየው አንፃር የዋጋ ግሽበቱ በብዛት ጎልቶ የሚታየው መሠረታዊ በሆኑ የምግብና መጠጥ ነክ ምርቶች ላይ በመሆኑ፣ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚሁ ጉዳይ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤›› ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ሌላው መንገድ በውድድር ዋጋ የሚቀንስበትን መንገድ መፍጠር ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ያነሱትም በሠለጠኑ የሚባሉ አገሮች የትርፍ ሕዳጋቸው ከሰባት በመቶ እንዳይበልጥ ይደረጋል፡፡ ይህ ግን በሕግ የተገደበ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ግን ብዙ ተወዳዳሪ መፍጠር ነው፡፡ የዋጋ ጣራ ማውጣት አትችልም፡፡   ቀልጣፋ የሆነ አቅርቦትና ውድድር ከተፈጠረ የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ይቻላል፡፡

 በዚሁ ጉዳይ ላ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ዋናው ነገር ምርት መጨመር ነው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ለግሽበቱ ዋናው ምክንያት የምርት እጥረት በመኖሩ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን ወደ ኢኮኖሚ ብዙ ገንዘብ ከመለቀቁ ጋር ያያይዙታል፡፡

አቶ ዘመዴነህ ግሽበቱን ለመቀነስ በቂ ምርት ሊኖር ይገባል ከተባለ ደግሞ ሸማቾች የሚጠቀሙባቸው ከአገር ውስጥ ሆነ ከውጭ የሚገኝ ምርት በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ከፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ግሽበቱ የሚታይ ከሆነ በቂ ምርት እንዳይኖር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላልና በቂ የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ እያስተካከሉ መሄድ ይቻላል ይላሉ፡፡ አሁን ያለው አሠራር እየፈጠረ ያለው የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚቀረፀው ፖሊሲ የውጭ ኩባንያዎችንም በማስገባት እንዲረጋጋ ማድረግንም ሊጠይቅ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት አለመተግበር ለዋጋ ግሽበት አንድ ምክንያት ሊሆን ቢችልም ዋነኛ ሆኖ ሊቀርብ እንደማይችል የጠቆሙት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ደግሞ በትንሽ ወጪ ብዙ ነገር ከመሥራት አንፃር የግብዓት ሥርዓቱ የሚያግዘው ነገር ስለመኖሩ ግን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ምርት እጥረት ካለ የቱንም ያህል የግብይት ሥርዓቱ ቢዘምን ዋጋ መጨመሩ አይቀርም ይላሉ፡፡ በእኔ እምነት ግን ከሚለቀቀው የገንዘብ መጠን አንፃር አገሪቱ ውስጥ ያለው የፍጆታ ምርት በቂ አለመሆኑ ስለሆነ ይህንን መጨመር  መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኑሮ ውድነት ላይ የሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ በበጀት ዓመቱ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን የሚያመላክት ነበር፡፡ የኑሮ ውድነትን መፍቻ መንገዱ ጥብቅ የገንዘብ የፊሲካል ፖሊሲዎችን በቅንጅት ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ መንግሥታቸው ከዚህ አንፃር ከሠራቸው ሥራዎች ብለው ከጠቀሱት ውስጥ አያይዘውም፣ በበጀት ዓመቱ ከቀዳሚ ዓመት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ መግባቱን በማስታወስ፣ የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ ብሔራዊ ባንክ ባይዘውና ወደ ኢኮኖሚው ቢያስገባው ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት ብቻ ሳይሆን ውጭ ምንዛሪ ወደ ገበያው ውስጥ ገብቶ ያለውን ሀብት እንዲሰበሰብ ማድረግ አንዱ ግሽበትን የመከላከያ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ በምናገኘው ሀብት ተጨማሪ ፍላጎቶች ማሟያ መንገድ ሰፊ ሥራ መሠራቱም ዕገዛ እንዳደረገላቸው ገልጸው፣ በበጀት ዓመቱ መጀመርያ አካባቢ የዋጋ ግሽበቱ ከ16 በመቶ አካባቢ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በአመዛኙ በዓመት ውስጥ 12 በመቶ አካባቢ እንደነበር በማስታወስ ግንቦት ወር ላይ ግን 16.2 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በሰኔ ወር ግን የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በተሠራው ሥራ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የምግብ ነክ የበጀት ዕቃዎች ላይ የዋጋ ውድነት ስለመኖሩ ያልሸሸጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሰው ገቢ አነስተኛ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ይህንን ለማስተካከል የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶቻችን መጨመር የሚስፈልግ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ሕገወጦችን የመቆጣጠር ሥራ ነው፡፡ ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ምርት የሚያከማቹ ሕገወጦች አሉ፡፡ በምሳሌነት የጠቀሱትም ሲሚንቶ አምራቾችን ነበር፡፡ ከማምረቻ የሕግ ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ገበያ ላይ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ባለው ድርጊት የሚያከማቹ ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ለመቆጣጠርም ተቋቋመ ያሉት ግብረ ኃይል ሥራ ጀምሯል፡፡ አሁንም ያከማቹትን የለየ ሲሆን፣ ወደ ዕርምጃ ይገባልም በማለት የዋጋ ግሽበትን ለማስተካከል እንደ አንድ መፍትሔ ያስቀመጡትን አሳውቀዋል፡፡  

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መንግሥት ከወሰዳቸው ሌሎች ዕርምጃዎች ውስጥ በዚህ ዓመት የምግብና የሸቀጥ ዕጥረትን ለመፍታት 1.3 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከውጭ ማስገባቱ ነው፡፡ ‹‹የገባው ስንዴና እዚህ የተመረተው ስንዴ በአግባቡ በገበያ ውስጥ ቢንሸራሸር ኖሮ፣ የገጠመን ችግር በተወሰነ ደረጃ በቀነሰ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት 263 ሚሊዮን ሊትር ዘይት አስገብተናል፡፡ ስኳር ከ200 ቶን በላይ ገብቷል፤›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ መንግሥት የተለያዩ ድጎማዎችን ማድረጉን ገልጸው፣ እንደ ምሳሌም ለነዳጅ ብቻ አሥር ቢሊዮን ብር መደጎሙን ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ድጋፎችና ድጎማዎች የተደረጉት የታችኛውን የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይጎዱ ለማድረግ ነው ብለው፣ በአሻጥር የሚሠሩትን በተደራጀው ግብረ ኃይል የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ሙከራ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ሌላ አሁን ያለው የዋጋ ንረት የአቅርቦት ብቻ ሳይሆን ስግብግብ ነጋዴዎች ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ዋጋ የሚጨምሩ በመሆኑ፣ በዚህ ዙሪያ ሊሠራ ይገባል ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ያለ ምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሸቀጦችን ዋጋ የሚከምሩ ሕገወጦች ካሉ እንደእነዚህ ዓይነት በአቋራጭ ለመበልፀግ የደሃውን ኅብረተሰብና የአገርን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ የማያደርጉ ምርት የሚያከማቹ ነጋዴዎች ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ለዚህ የተዘጋጀው ግብረ ኃይል ሥራውን ጀምሯል፡፡ ምርት ያከማቹ የተወሰኑትን ስለመለያየታቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጀት ዓመቱ መጀመርያ ላይ በኮንትሮባንድ ላይ እንደተወሰደው ዓይነት ዕርምጃ በእነዚህም ላይ በመተግበር ችግሩን ለማቃለል የሚሠራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ካቀረቡት ሪፖርት በጥቅል ሲታይ ምን ያመላክታል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዘመዴነህ፣ በግሌ እንደ ትልቅ እመርታ የተመለከትኩዋቸው አንኳር ነጥቦች ውስጥ የ2011 በጀት ዓመት የ11 ወራት 9.2 በመቶ እንደሚያድግ መጥቀሳቸው ነው፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ይህንን ያሉበትን ምክንያት ሲያብራሩም በአገሪቱ ውስጥ ከነበረው አለመረጋጋትና በየአቅጣጫው ካሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አንፃር በዚህን ያህል ኢኮኖሚው ማደጉ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት አሁንም በአፍሪካ ፈጣኑ የዕድገት መጠን መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሌላው እንቅስቃሴ ነው፡፡ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከቀዳሚው ዓመት 20 በመቶ የጨመረ ነው፡፡ ይህ የሚያበረታታ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች