Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወንጂና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት የተነሳው ኩባንያ መንግሥት የእኩል ተወዳዳሪነት ዕድል እንዲሰጠው ጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር መንግሥት ወደ ግል ሊያዛውራቸው ይፋ ካደረጋቸው 13 የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ በተለየ ፍላጎት ወንጂና መተሐራ ስኳርን ለመግዛት መነሳቱን ለዚህም የገንዘብ አቅሙና የሰው ኃይል ብቃት እንዳለው በማስታወቅ መንግሥት የእኩል ተወዳዳሪነት ዕድሉን እንዲያስጠብቅለት ጠየቀ፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ፣ የፋብሪካዎቹን ሠራተኞች፣ በወንጂና መተሐራ ከተማ የሚኖሩ ገበሬዎች፣ የአካባቢው የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች በባለአክሲዮንነት የሚሳተፉበት እንደሆነ በመግለጽ መንግሥት ለውጭ ኩባንያዎች ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ አክሲዮን ማኅበሩም በውድድሩ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚሳተፍበትን ዕድል እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤርሲዶ ሌንደቦ (ዶ/ር) ከኩባንያው የቦርድ አባላትና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ስድስት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመሸጥ መነሳቱ ሥጋት አሳድሮባቸዋል፡፡ ይኸውም በተለይ ወንጂና መተሐራ ፋብሪካዎችን ለመግዛት ኢትዮ ስኳር የተነሳው ፋብሪካዎቹ ካላቸው ታሪካዊ ማንነት፣ በኢትየጵያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ካላቸው ተቀዳሚነት ብሎም፣ አክሲዮን ማኅበሩን በመሠረቱት ባለሙያዎችና በፋብሪካዎቹ አካባቢ የሚኖረው አብዛኛው ሕዝብ ከፋብሪካዎቹ ጋር ካለው የረዥም ጊዜ የኑሮ ቁርኝት አኳያ ፋብሪካዎቹ ለሌሎች ከሚሸጡ ይልቅ ኢትዮ ስኳር ቢገዛቸው የሚኖራቸው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን በማመላከት መንግሥት የመዳደሪያ ዕድሉን በአቻ ሜዳ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ፋብሪካዎቹን ለመግዛት የድርድር ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ምክትል ፕሬዚዳንቱና የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢተው ዓለሙ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ጥያቄውን እንደሚያጤነው ከመግለጽ በቀር መንግሥት እሺም እምቢም አለማለቱ፣ ይብሱኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሽያጭ የሚያቀርባቸው ስድስት ፋብሪካዎች እንደሆኑ ማስታወቁ ሥጋት እንዳሳደረባቸው የኩባንያው ኃላፊዎች አልሸሸጉም፡፡

ይህም ሆኖ ከአገር ውስጥ ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትልውደ ኢትዮጵያውንን ከማሳተፍ በተጓዳኝ፣ ኤችቪኤ የተሰኘውና ወንጂና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ከ60 ዓመታት በፊት የመሠረተው የሆላንድ ኩባንያ ጥያቄው ቀርቦለት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣትና በኢትዮ ስኳር ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት በማሳደሩ በጥቅምት ወር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ በኩባንያው ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ሌሎች የውጭ ኩባንያዎችም ፍላጎት በማሳየታቸው ድርድር እየተካሔደ በመሆኑ፣ በኢትዮ ስኳር ኩባንያ ውስጥ እስከ 60 ሺሕ የሚደርሱ ባለአክሲዮኖች የሚሳተፉ በመሆኑ ጭምር መንግሥት ሒደቱን በሚገባ እንዲያጤነው ተጠይቋል፡፡

እንደ ኤርሲዶ (ዶ/ር) ማብራሪያ ከሆነም፣ ከወዲሁ ሦስት ባንኮች 60 ሺሕ ለሚደርሱት ባለአክሲዮኖች በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር በማመቻቸት አክሲዮን የሚገዙበትን ገንዘብ ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም ከወዲሁ አክሲዮኖች እየተሸጡ እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡ በኩባንያው የቦርድ አባልና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ እሸቱ ገለቱ በበኩላቸው፣ የስኳር ምርት የሚጣል ነገር እንደሌለው በተለይም ተረፈ ምርቶቹ ለእንስሳት መኖ፣ ለኢታኖል ምርት፣ ለኃይል ማመንጨት፣ ለሽቶ ማምረቻነት፣ ለከረሜላና ለሌሎችም በርካታ ምርቶች ግብዓት የሚሆኑ የተረፈ ምርት ውጤቶች የሚያመነጭ አትራፊ ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሰው ሁለቱ ፋብሪካዎች ልምዱ፣ ፍላጎቱና አቅሙ ባላቸው የአገር ውስጥ ባለሙያዎችና ባለአክሲዮኖች እንዲያዙ ቢደረግ ለታሪክም ለመንግሥትም ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጡ አብራርተዋል፡፡

ወንጂና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ብቻም ሳይሆኑ፣ ደስታ ከረሜላ ይመረትባቸው የነበሩ፣ ሽቶና ከሰል ማምረቻዎችም የነበሯቸው የበርካታ ኢንዱስትሪዎች መነሻ፣ በኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉ የኢንዱስትሪ ማዕከላት ውስጥ መነሻዎች በመሆናቸው ወደፊት የስኳር ኢንዱስትሪ ቱሪዝም፣ የስኳር ዓውደ ርዕይና ፌስቲቫሎችን ጭምር ጎን ለጎን የማስተዋወቅ ፍላጎት እንዳላቸው ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው (ዶ/ር) በርከት ያሉ ኩባንያዎች በቀረበላቸው የፍላጎት መግለጫ ሰነድ አማካይነት የግዥ ፍላጎታቸውን ማሳወቃቸውን ገልጸው፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችና ባለሀብቶችም በሽያጭ ሒደቱ እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በፍላጎት ማሳወቂያ ሰነዱ ውስጥ ኩባንያዎች ካቀረቧቸው ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ በስኳር ምርት ተጓዳኝ ተብለው የተዘረዘሩ ሐሳቦች በኢትዮ ስኳር ኃላፊዎች የተጠቀሱት ተረፈ ምርቶች ይገኙባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች