Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የቡና ዋጋ ቢወርድም እስካሁን ከ200 ሺሕ ቶን በላይ ወደ ውጭ ተልኳል›› አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተቋሙን መምራት የጀመሩት አዱኛ (ዶ/ር) ቀደም ብሎ እንደ አዲስ የተዋቀረውን የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንትና የሆርቲካልቸር ባለሥልጣንን፣ በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሥራ በማስጀመርና በኃላፊነት በመምራት ቆይተዋል፡፡ በቡናው ዘርፍ አዳዲስ ክስተቶች መታየት መጀመራቸው ብቻም ሳይሆን ቀድሞ ለበርካታ የዘርፉ ተዋንያን፣ በተለይም ለላኪዎችና ለመንግሥት ራስ ምታት የነበረው የቅሸባ ወይም የሥርቆት ተግባር መልኩን ቀይሮና ተራቆ፣ በአሁኑ ወቅት የታሸገ ኮንቴይነር በማያስታውቅ መንገድ በመቅደድ የላኪዎች ቡና በየመንገዱ መዘረፍ ጀምሯል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው የዓለም የቡና ዋጋ በዚህ ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካቶች የገቡትን የሽያጭ ኮንትራት ማክበር እስከሚቸገሩ ድረስ ኪሳራ እያደረሰባቸው እንደሆነ ታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ ያገዳቸው ከ80 በላይ ላኪዎች እንደነበሩም ዋና ዳይሬክተሩ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ችግሮች የሚገነዘበው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለመፍትሔዎች እየሠራ ስላለው ጉዳይ፣ በአፍሪካ የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታን በመጨመር በዓለም የቡና ዋጋ መዋዠቅ ሳቢያ የሚደርሰውን ኪሳራ ለማካካስ ስለሚቻልበት መንገድ የሚመክር ጉባዔም በቡናና ሻይ አስተናጋጅነት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር፡፡ ስለዚህና ስለቡና ዘርፍ እንዲሁም ስለሻይና ቅመማ ቅመም እንቅስቃሴ ብርሃኑ ፈቃደ ከአዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም የቡና ዋጋ ችግሮች ሳቢያ በአፍሪካ አገሮች ውስጥ የቡና ፍጆታ እንዲጨምር የሚያሳስብ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ ሆኖም የቡና ምርት ካለው ፍላጎት አንፃር አነስተኛ በሆነበት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥም፣ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ይልቅ ለወጪ ንግዱ ቅድሚያ በሚሰጠበት ወቅት የአገር ውስጥ ፍጆታን ማበረታታት ለምን ትኩረት ተሰጠው?

አዱኛ (ዶ/ር)፡- ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው ከኢትዮጵያ ልምድ ለማግኘት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ከሚመረተው 50 በመቶውን ይሸፍናል፡፡ ከዚህ በላይ ግን መሄድ አንችልም፡፡ ይህንን በመገንዘብ ኢትዮጵያ እንዴት በዚህ ደረጃ የቡና ፍጆታዋ እንዳደገ፣ ምን ዓይነት ልምድ መቅሰም እንደሚቻል ለመረዳት በማሰብ ነው ይህ ኮንፈረንስ የተዘጋጀው፡፡ ኬንያ ከምታመርተው ቡና አምስት በመቶው ብቻ ነው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው፡፡ 95 በመቶው ወደ ውጭ ይላካል፡፡ ሩዋንዳ 99 በመቶውን ቡና ወደ ውጭ ትልካለች፡፡ ኡጋንዳም 90 በመቶውን ወደ ውጭ ትልካለች፡፡ ይህ ማለት የቡናን ዋጋ መወሰን አይችሉም ማለት ነው፡፡ ወደ ውጭ ሲልኩ ዋጋው በቀነሰ ቁጥር በወረደ ዋጋም ቢሆን ቡናውን የመጣል ያህል ለመሸጥ ይገደዳሉ፡፡ ይህ ሲሆንም የቡናውን ማምረቻ ዋጋ እንኳ በማይሸፍን ዋጋ ይሸጣሉ፡፡ አማራጭ ስለሌላቸው ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በአገር ውስጥ ፍጆታችን 50 በመቶ ስለደረስን የቡናው ዋጋ እጅግ ቢወድቅ እንኳ፣ ቡናውን የሚታደግ የአገር ውስጥ ተጠቃሚ አለን፡፡ ይህንን ልምድ ለሌሎች አገሮች እያካፈልን ነው፡፡ የአፍሪካ አምራቾች የአገር ውስጥ ፍጆታቸውን መጨመራቸው ለእኛ ጥሩ ዕድል ነው፡፡ ውድድሩን ይቀንስልናል፡፡

ለምሳሌ ኬንያ የአምስት በመቶ ፍጆታዋን ወደ 50 በመቶ ከፍ ብታደርግ፣ ከምታመርተው ቡና ግማሹን ብቻ ለዓለም ገበያ ማቅረቧ ለእኛ ቡና የበለጠ ዓለም አቀፍ ገበያ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ በአፍሪካም አዳዲስ ገበያ እንድናገኝ ያግዘናል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የእርስ በርስ ግብይቱ ከአሥር በመቶ አይልጥም፡፡ ይህ ማለት አንዱ የአፍሪካ አገር ከሌላው ቡና እየገዛ ወይም እየሸጠ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ የገበያ ዕድል ነው የማየው፡፡ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የቡና ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርግ ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ አዳዲስ ገበያም እንድናገኝ ያግዘናል፡፡ አፍሪካ አምራች እንጂ የቡና ተጠቃሚ ባለመሆኗ፣ አሁን የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ሲስፋፋ ተጨማሪ የአፍሪካ ገበያዎችን እንድናገኝም ስለሚያግዘን ጥሩ ዕድል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዓለም ዋጋ ላይ የራሳችን ድርሻ እንዲኖረን ይረዳናል፡፡ እንደ በፊቱ በተገኘው ዋጋ መሸጥ ብቻ ሳይሆን፣ የምንሸጥበትን ዋጋ መወሰን የምንችልበትን ዕድል የሚፈጥርልን የአፍሪካ ቡና ተጠቃሚነት መጨመሩ ነው፡፡ ስለዚህ በብዛት በአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ከተስፋፋ፣ ወደ ምዕራቡ ዓለም እየላክን በዚያ ገበያ የሚወሰነው የቡናችን ዋጋና ጥገኝነታችን ሊቀንስ ስለሚችል፣ ለኢትዮጵያ በተለይ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ እንቅስቃሴ መቼ ዕውን ሊሆን ይችላል? እርግጥ ምልክቶች እየታዩ ነው?

አዱኛ (ዶ/ር)፡ ጅምር ሥራዎች እየታዩ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታን ለማስፋፋት እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች በዩኒቨርሲቲዎቻቸው በኩል ተጠቃሚዎችን ለማብዛት የዘመቻ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ወጣቶችን ቡና መጠጣት እያለማመዱ ነው፡፡ አርሶ አደሮችም በዩኒየኖቻቸው በኩል ቡናቸውን በጥሬው ከመላክ ይልቅ፣ ቆልተውና አዘጋጅተው የሚልኩበትን ዕድል እያመቻቹላቸው ነው፡፡ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ የአፍሪካ የልዩ ጣዕም ቡናዎች ማኅበር (አፍካ) በበኩሉ የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታ በአፍሪካ እንዲጨምር የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞችን እያካሄደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተካሄደውንም መድረክ ያዘጋጀው አፍካ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የሚገኘውን ልምድና ተሞክሮ ወደ ኬንያ፣ ዛምቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ሴራሊዮን ብሎም ወደ ሌሎች አገሮች በመውሰድ የቡና የአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲስፋፋ በማድረግ፣ የቡና ዋጋ መዋዠቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተጀመረው ባለፈው ግንቦት ነው፡፡ በመጀመሪያ በፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ውስጥ ተካሂዶ ነበር፡፡ በእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች መካከል የሚካሄደውን ስብሰባ ኢትዮጵያ በማስተናገድ አስጀምራለች፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በቀጥታ ባይያያዝም የኢትዮጵያ ላኪዎች በቡና ስርቆትና ዝርፊያ አዲስ ክስተት እንዳጋጠማቸው በመግለጽ ክፉኛ እያማረሩ ነው፡፡ ይኸውም ከኮንቴይነር በረቀቀ ዘዴ የሚፈጸም ዝርፊያ ነው፡፡ ከሰሞኑ ሁለት ኩባንያዎች ይህ ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል፡፡ ጉዳዩ አገር አቀፍ አደጋ ከመሆኑ በፊት ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው? 

አዱኛ (ዶ/ር)፡- ይህ ረቀቅ ባለ መንገድ እየመጣ ያለ የቡና ቅሸባ ተግባር ነው፡፡ በሞጆና በጂቡቲ መካከል ባለው ጉዞ ወቅት ነው ይህ ችግር እየተከሰተ ያለው፡፡ ላኪዎቹ አምነው ነው ቡናቸውን የሚያጓጉዙት፡፡ ከዚህ በፊትም ይህ ዓይነቱ ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ኩባንያዎች አሉ፡፡ ለፖሊስም ለሚመለከተው አካልም ጉዳዩን አቅርበናል፡፡ እኛም እየተከታተልነው ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት ጊዜ ወዲህም ሁለት ኩባንያዎች ላይ ስርቆት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ይኼንን ችግር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚመራው የወጪ ንግድ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አቅርበናል፡፡ ኮሚቴው ይህንን ብቻም ሳይሆን የኮንትሮባንድ ንግድ የሚከታተል ግብረ ኃይል አቋቁሟል፡፡ ይህ ግብረ ኃይል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን የሚመራና የደኅንነት መሥሪያ ቤት፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተካተቱበት ግብረ ኃይል በመሆኑ በቀጥታ ወደ ዕርምጃ በመግባት ችግሩን እንደሚፈታው ይታመናል፡፡ የቡናና ሻይ ባለሥልጣንም የዚህ ግብረ ኃይል አባል በመሆን እየተሳተፈ ስለሚገኝ፣ ችግሩ ሙሉ በሙሉ በቶሎ ባይቀረፍ እንኳ በመሠረታዊነት እንዲቀንስ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በላኪዎች ዘንድ ከሚጠቀሱት መካከል ሁለት ጉልህ የመፍትሔ ሐሳቦች አሉ፡፡ አንደኛው በተሽከርካሪ የተጫነ ዕቃን በዲጂታል ዘዴ የመከታተያ ሥርዓት፣ ወይም ካርጎ ትራኪንግ የሚባለውና በጂቡቲ ወደብ ሚዛን ማስቀመጥ ላይ መንግሥት ትኩረት ቢሰጥ በማለት ላኪዎች ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡

አዱኛ (ዶ/ር)፡- የካርጎ ትራኪንግን እኛም እንደ አንድ ዓብይ ጉዳይ አንስተነዋል፡፡ የተዘረጋ ሥርዓት ነበር፡፡ በመካከል ተቋርጦ ቢቆይም በአሁኑ ወቅት መልሶ ሥራ እንዲጀምር ስምምነት ተደርጓል፡፡ በጂቡቲ ሚዛን ማስመቀጡም አንዱ አማራጭ መፍትሔ ነው፡፡ ሆኖም ለትግበራ ካርጎ ትራኪንግ የሚቀድም ይመስለኛል፡፡ ትራንስፖርት ሚኒስቴርና ገቢዎች ሚኒስቴርም የካርጎ ትራኪንግ ሥርዓትን እንደ አዲስ በማስጀመር እንዲያስተገብሩ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– ከሁለት ዓመት በፊት ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ይታወሳል፡፡ ዘንድሮስ ምን ይጠበቃል?

አዱኛ (ዶ/ር)፡- ዘንድሮ የቡና ዋጋ እጅግ ወርዷል፡፡ አንድ ፓውንድ ወይም 2.2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቡና በ80 የአሜሪካ ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡ ይሁንና አንዱን ኪሎ ቡና ለማምረት ቢያንስ ከአንድ ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን 2.2 ኪሎ ግራም ቡና እየተሸጠ ያለው ከአንድ ዶላር በታች በመሆኑ፣ ይህ ሁኔታ ባለበት ወደ ውጭ ወስዶ መሸጡ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህ ችግር ባለበት ወቅትም ላኪዎቻችን የዋጋውን መውረድ ሥጋት በመጋፈጥ ቡና እየላኩ ነው፡፡ የቡና ዋጋ ቢወርድም እስካሁን ከ200 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ተልኳል፡፡ በዋጋ አንፃር እንደ አምናው ላይገኝ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አምና እስከ ሦስት ዶላር ሲሸጥ የነበረው ቡና ዘንድሮ ወደ 80 ሳንቲም (በዶላር) ወርዷል፡፡ ይህ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ ይህንን ለማካካስ በመጠን ከፍ አድርጎ ለመሸጥ ተሞክሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በፀጥታ ችግር ሳቢያ ያልወጣ ቡና እንዳለ ይነገራል፡፡

አዱኛ (ዶ/ር)፡- በፀጥታ ችግር ሳቢያ በተለይ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ፣ በከፋና ሚዛን ቴፒ አካባቢ የሚመረቱ ቡናዎች ሙሉ በሙሉ ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ይህም ለቡናው አፈጻጸም ሌላው ችግር ሆኗል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሲስተካከሉ በሚመጣው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በወጪ ንግዱ ላይ ግብርና ሚኒስቴር፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይሳተፋሉ፡፡ የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት አሰጣጥ ላይ በተለይ በቅመማ ቅመም መስክ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ ቡናም ላይ ይህ ችግር እየታየ ነው፡፡ አንዴ ቡናና ሻይ አንዴ ግብርና ሚኒስቴር ሂዱ እየተባልን የጥራት ማስረጃ ሰነድ ለማግኘት ተቸግረናል የሚሉ የበርበሬ ላኪዎች፣ ከዚህ ቀደም ያነሱት የነበረው ችግር አሁን ደግሞ ወደ ቡናውም እየመጣ ነው፡፡ የሚታየው አለመናበብ ከምን የመጣ ነው?

አዱኛ (ዶ/ር)፡- በቅንጅት የመሥራት ክፍተት ላይ ለሚነሳው ያው እንግዲህ ሁሉም የየራሱ ኃላፊነትና ድርሻ አለው፡፡ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ላኪዎች ፈቃድ እንዲያገኙ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት አንዱ ነው፡፡ ላኪው ቡና ለመላክ የሚያስፈልጉ መመዘኛዎችን ያሟላል ወይ? ለወጪ ንግድ ሥራው ብቁ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ መሥፈርቶችን በመያዝ፣ የላኪውን አቅምና የአሠራር ሥርዓት በቦታው በመገኘት ካረጋገጠ በኋላ ብቁና ወደ ውጭ መላክ የሚችልበት አቅም አለው ብለን ስናምን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደብዳቤ እንጽፋለን፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም እኛ የሰጠነውን የብቃት ማረጋገጫ ሰነድ ሲያገኝ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ፈቃድ የማግኘት መብት ስላለው ሚኒስቴሩ ይህንኑ በመከተል፣ ተፈላጊዎቹ መሥፈርቶች መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ ፈቃድ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ተገቢውን መሥፈርትና መመዘኛ ሳያሟሉ ፈቃድ አያገኙም፡፡ በመሥሪያ ቤታችን የብቃት ማረጋገጫ ኮሚቴም ስላለን፣ በቦታው ተገኝቶ ተገቢውን መሥፈረትና መመዘኛ ያሟሉትን በመፈተሽ የብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ምናልባት ይህንን በተገቢ ደረጃ ሳያሟሉ ቀርተው ቅሬታ የሚያቀርቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኛም የተቀመጠውን መሥፈርት መቶ በመቶ እንዲያሟሉ ሳይሆን፣ ቢያንስ ከ80 በመቶ በላይ ተፈላጊውን መሥፈርት ሲያሟሉ ፈቃድ እንዲያገኙ እናግዛቸዋለን፡፡ በዚህ አግባብ ስለምንሠራ ይህ ችግር ሆኖበት ቅሬታ ያቀረበ ላኪ አላጋጠመንም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓመት ያገዳችኋቸው ላኪዎች እንዳሉ ሰምተናል፡፡ አንዳንዶቹም ታዋቂ ላኪዎች ናቸውና ችግሩ ምንድነው?

አዱኛ (ዶ/ር)፡- ይህ የሆነው አብዛኞቹ የገቡትን ኮንትራት ባለማክበራቸው ነው፡፡ አንድ ላኪ  ከቡና ገዥው ጋር ኮንትራት በፈረመ በ90 ቀናት ውስጥ ቡናውን ማቅረብ አለበት የሚል አሠራር አለ፡፡ በገባው ኮንትራት መሠረት ቡናውን የማይልክ ነጋዴ ሲኖር፣ ኮንትራቱን የሰጡት ገዥዎች በእኛ ላይ እምነት ያጣሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ወደ ሌሎች አገሮች ፊታቸውን ያዞራሉ፡፡ ይህ የአገርን ገጽታ ያበላሻል፡፡ በመሆኑም በገቡት ኮንትራት መሠረት ቡናውን በወቅቱ መላክ ያልቻሉትን ሰዎች ለይተን ከአንዴም ሁለት ጊዜ በማስታወቂያ ብንጠራቸውም ሊገኙልን አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ንግድ ሥራው ላይ ይኑሩ ወይም ከሥራው ይውጡም ስላላወቅን፣ ለጊዜው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይት እንዳይፈጽሙና ቀርበው ችግራቸው ምን እንደሆነ እስኪያስረዱ ድረስ 81 ላኪዎች ታግደው ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ30 በላይ የሚሆኑት ቀርበው ችግራቸውን በማስረዳት፣ ዳግመኛ በመላክና ያላከበሩትን ኮንትራት በማደስ ወደ ግብይት እንዲገቡ የተደረጉ አሉ፡፡ በዚህ ዓመት ከወጣው ከዚህ ዕግድ ውስጥ እስካሁን 50 ያህል ዕግዱ እንደፀናባቸው ይገኛሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት መሥሪያ ቤት ሻይና ቅመማ ቅመምንም ከቡናው ጋር በማጣመር የግብይትና የልማት ሥራዎችን ይመራል፡፡ በዚህ ዘርፍ ምን ለውጥ እየታየ ነው?

አዱኛ (ዶ/ር)፡- ቅመማ ቅመም ላይ እንደ ቡናው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት አይደለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የአሠራር መመርያዎች ማዘጋጀት የግድ በማለቱ ነው፡፡ ሕጎችና ደንቦች መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለቡና የአሠራር ሕጎች እንደ አዲስ ወጥተውለታል፡፡ ለቅመማ ቅመም ዘርፉም የአሠራር ሥርዓት እየዘረጋን ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በዘርፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ከየክልሉ ጠርተን፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በዘርፉ የሚሠሩ ሰዎችን በማግኘት ሰነድ አዘጋጅተን እያስገመገምን ነው፡፡ እንደ ጨረስን ወደ ሥራ እንገባበታለን፡፡ የሻይ ምርትን ፋብሪካዎች በገበሬዎች በማስመረት (አውት ግሮወርስ ስኪም) ምርት ማብዛት የሚችሉበትን ዕቅድ አውጥተናል፡፡ የተለያዩ አማራጮችንም እየተቀጠምን እንገኛለን፡፡ በዚህ አግባብ ችግሮችን እንደምንፈታ አስባለሁ፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...