Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ላኪዎች ከታሸገ ኮንቴይነር የሚፈጸም ዝርፊያ በመባባሱ የወጪ ንግዱን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት አደጋ ተደቅኗል አሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁለት ላኪዎች ብቻ 400 ኩንታል ገደማ መዘረፋቸውን አስታውቀዋል

ከአገር ውስጥ ታሽጎ ከሚወጣ ኮንቴይነር ውስጥ በማያስታውቅ መንገድ ሲካሄድ የነበረው የተቀነባበረ የቡና ዝርፊያ ወይም ቅሸባ ለወራት ጋብ ብሎ ቢሰነብትም፣ ዳግም ተባብሶ  በማገርሸቱ ላኪዎች የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ቡና አደጋ ተጋርጦበታል አሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ገልጿል፡፡

ሄድ መለስ በማለት የሰነበተው ቅሸባ በኮንቴይነር ታሽጎ ወደ ውጭ የሚላከውን ቡና በረቀቀና በማያስታውቅ መንገድ በመክፈት ከውስጡ በርካታ ኬሻ ቡና በመስረቅ መልሶ እንደነበር በማሸግ ወደ ወደብ እንዲደርስ እየተደረገ፣ ከዚያም ቡናውን ወደገዙት አገሮች እንደሚላክ የገለጹ ላኪዎች፣ የቡናው መጉደል ተቀባዩ ዘንድ ከደረሰ በኋላ እንደሚታወቅ፣ በዚህም ሳቢያ የኪሳራ ጉዳት ክፍያ ጥያቄን ጨምሮ ዳግም ቡና የማይገዙበት፣ የኢትዮጵያንም ስም በመጥፎ ሊያስነሳ የሚችል ዝርፊያ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ከሦስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሦስት ጊዜ ዝርፊያ እንዳጋጠማቸው ያስታወቁት የታደሰ ደስታ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ደስታ ወደ ሩሲያ፣ ፖርቹጋልና ታይዋን ከተላኩ ቡናዎች ውስጥ በሦስት ኮንቴይነሮች ላይ ቅሸባ መፈጸሙን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይኸውም ወደ ሩሲያ ከተላከ ቡና መካከል ከአንድ ኮንቴይነር ውስጥ ባለ 60 ኪሎ ግራም 70 ኬሻ መወሰዱን፣ ወደ ፖርቹጋል ከተላከው ቡናም ከአንድ ኮንቴይነር ብቻ 64 ኬሻ ባለ 60 ኪሎ ግራም ቡና መጉደሉን፣ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ወደ ታይዋን ከተላከ የልዩ ጣዕም ቡና ውስጥ ከአንድ ኮንቴይነር በ30 ኪሎ ግራም መጠን የታሸገና ብዛቱ 124 ኬሻ እንደተወሰደ አቶ ታደሰ ገልጸተዋል፡፡ አንድ ኮንቴይነር በአብዛኛው 320 ኬሻ ቡና እንደሚይዝ ያብራሩት አቶ ታደሰ፣ ከአንድ ኮንቴይነር ግማሽ ያህል ቡና መዝረፍ የተጀመረበት ክስተት መታየቱ፣ ቅሸባው አደጋ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል፡፡ ከሦስት ኮንቴይነሮች ውስጥ የተዘረፈው ቡና መጠን በኩንታል ሲገለጽ 135 ኩንታል እንደሚሆን፣ መሸጫ ዋጋውም እስከ 42 ሺሕ ዶላር እንደሚደርስ ተጠቁሟል፡፡

በአብዛኛው በአስመጪና በላኪነት ንግድ ሥራ ከሚታወቀው ከታደሰ ደስታ በተጨማሪ፣ ትራኮን ትሬዲንግ ኩባንያም ተመሳሳይ ዝርፊያ እንፈተፈጸመበት ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡ የኩባንያው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ኡመር እንደገለጹት፣ 100 ሺሕ ዶላር የሚያወጣ 250 ኩንታል የኤክስፖርት ቡና ተዘርፏል፡፡

አቶ ታደሰም ሆኑ አቶ ኤልያስ እንደሚገልጹት፣ የቡናው መዘረፍ በኩባንያዎቹ ላይ ከሚያደርሰው ኪሳራ በላይ በአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ላይ የሚያሳድረው አደጋ አሳሳቢ ነው፡፡ ይኸውም ገዥዎች እንዲላክላቸው ላዘዙት ቡና ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም በተስማሙት መጠን እንደሚደርሳቸው የሚጠብቁት ቡና መጠኑ ጎድሎ ሲደርሳቸው፣ ከሚጠይቁት የማማካሻና የተመላሽ ሒሳብ ባሻገር ዳግመኛ ከኢትዮጵያ ላኪዎች ላለመግዛት እንዲወስኑ ሊያደርጋቸው የሚችል ወንጀል እንደሆነ በመግለጽ፣ መንግሥት የወጪ ንግድ መስመሮችን ከቅሸባና መሰል ዝርፊያዎች ነፃ እንዲያደርግ ጠይቀው፣ አጥፊዎችን ተከታትሎ ለሕግ እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት ሪፖርተር ባስነበበው ዘገባ ከ150 ኩንታል በላይ የተዘረፉ ኩባንያዎች ለመንግሥት አቤቱታቸውን አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውም ተገልጾ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዝርፊያው ተባብሶ በመቀጠሉና ይባስ ብሎም አንድ መኪና እስከጫነው ሙሉ ቡና የተሰወረበት አጋጣሚ በላኪዎች ዘንድ በቅርቡ ዳር እስከ ዳር ሲያነጋግር የሰነበተ ክስተት ነበር፡፡ ይህ በሆነበት ወቅትም ቢያንስ ታደሰ ደስታና ትራኮን ትሬዲንግ ኩባንያዎች ላይም ዝርፊያው እንደተፈጸመ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገኝ፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣንም ሆነ ላኪዎች ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ በዚያም ላይ በዘርፉ የሚታዩ በርካታ ማነቆዎችን እየተቋቋሙ ደኅንነቱ የተረጋገጠ እንደሆነ በሚታመን የአላላክ ዘዴ ላኪ፣ አሽከርካሪ፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች የጭነቱን ትክክለኛነት አረጋግጠውና ተፈራርመው በኮቴይነር አሽገው በሚልኩት ቡና ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ እየተባባሰና አደገኛ እየሆነ መምጣቱ ሊገታ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡ 

ምንም እንኳ ከኮንቴይነር በረቀቀ መንገድ ዝርፊያው ይፈጸም እንጂ፣ እንደ መተሐራና አዳማ ባሉ ነገር ግን ቡና አምራች ባልሆኑ ከተሞች አንደኛ ደረጃ የኤክስፖርት ቡና መደበኛው ቡና ከሚሸጥበትም ባነሰና በቅናሽ በአደባባይ እየተሸጠ ባለበት አገር ውስጥ፣ ዘራፊዎቹን በቀላሉ መያዝና ቅሸባን ማስቆም አለመቻል ግራ እንደሚያጋባ ላኪዎች ይገልጻሉ፡፡ ዝርፊያውና ዘራፊዎቹ በዚህ አያያዘቸው ከቀጠሉ ግን ላኪዎችን ብቻም ሳይሆን፣ ኢትዮጵያንም ከዓለም የቡና ገበያ ሊያስወጡ የሚችሉበት አደጋ እንደተጋረጠ ይገልጻሉ፡፡ የቡና ላኪዎች ማኅበርም አጥፊዎች በአብዛኛው ሾፌሮች እንደሆኑና ዕርምጃ መውሰድ የሚገባው የሕግ አካልም ተገቢውን ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅበት አሳስቧል፡፡ 

ከኮንቴይነር የሚፈጸመው የቡና ዝርፊያ በአብዛኛው ከሞጆ እስከ ጂቡቲ ባለው መስመር እንደሚካሄድ ይታመናል ያሉት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት በሁለት ኩባንያዎች ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸው፣ ይህንኑ ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚመራው ብሔራዊ የወጪ ንግድ አስተባባሪ ኮሚቴ ማስታወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮሚቴው ባለሥልጣኑን ጨምሮ በንግዱ መስክ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩ በአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በመገንዘብ፣ ተቋርጦ የቆየው በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የታገዘ የጭነት መከታተያ (ካርጎ ትራኪንግ) ሥርዓት ዳግም እንዲጀመር ባለሥልጣኑ ጥያቄ ማቅረቡን ጠቁመው፣ ይህንኑ ለማስፈጸም የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የገቢዎች ሚኒስቴር ኃላፊነቱ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጂቡቲም የክብደት መለኪያ ሚዛን እንዲገጠም በማድረግ ችግሩን መቆጣጠር እንደሚቻል ላኪዎቹ በመፍትሔነት አሳስበዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት ተመሳሳይ የኮንቴይነር ቅሸባ ካጋጠማቸው መካከል ቴስቲ ኮፊ ትሬዲንግ፣ ሙለጌ፣ ሲዳማ ቡና አምራቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን፣ አባሃዋ ትሬዲንግና ፋህም ጄኔራል ትሬዲንግ ከታሸገ ኮንቴይነር ውስጥ ቡና እንደተወሰደባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከስድስቱ ኩባንያዎች የተዘረፈው ቡና መጠኑ 150 ኩንታል እንደሚደረስ ተዘግቧል፡፡ ይሁንና ታደሰ ደስታና ትራኮን ትሬዲንግ ብቻቸውን 400 ኩንታል የሚጠጋ ዝርፊያ ተፈጽሞብናል ብለዋል፡፡

ይህ አድራጎት ቸል በመባሉ እየተባባሰ እንደመጣ ከሚገልጹት መካከል የአካካስ ሎጂቲክስ ኩባንያ የመርከብና የወጪ ንግድ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ቡታ ናቸው፡፡ አቶ ግርማ እንደሚሉት፣ ከኮንቴይነር ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ በሾፌሮችና መጋዘን ባላቸው ወይም በሚያከራዩ፣ እንዲሁም በጋራዥ ቤቶች ትብብር ሊሆን የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በተመሳሳይ መንገድ ወደ ውጭ በመጓጓዝ ላይ የነበረና የከሰረው የአይካ አዲስ ኩባንያ ንብረት የሆነ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ጭነት ዘርፈዋል በተባሉ አስምት ሾፌሮች ላይ፣ የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስከ 25 ዓመታት በሚደርስ እስራትና እስከ 20 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት በመወሰን ያስተላለፈው ውሳኔ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች በአጥፊዎች ላይ መወሰድ እንዳለባቸው የሚያሳስቡት አቶ ግርማ፣ መንግሥት ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት የማያዳግም መፍትሔ እንዲያበጅለት ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች