Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የ51 በመቶ ድርሻ በመያዝ ኢትዮ ቴሌኮምን እንደሚሸጥና ሁለት የኔትወርክ ኦፕሬተሮችን እንደሚያስገባ አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ ግል ይዛወራሉ

ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታ ይዛወራሉ ከተባሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት ዘርፍ እንደሚደራጅና 51 በመቶ ድርሻ መንግሥት በመያዝ፣ የተቀረውን ድርሻ ለመሸጥ የገንዘብ ሚኒስቴር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ሌሎች ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮችም ወደ ዘርፉ በጨረታ ተወዳድረው እንደሚገቡ መንግሥት በማስታወቁ፣ ፍላጎት ያሳዩ የውጭ ኩባንያዎች የሽያጭ ሒደቱን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

 ከ60 የማያንሱ የውጭ ኩባንያዎች በጨረታ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ተገልጾ፣ በተለይም በኔትወርክ መስክ በ3G እና በ4G ኔትወርክ ዝርጋታ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ይመረጣሉ ተብሏል፡፡ የዓለም ባንክ የሽያጭ ሒደቱን በማማከር እየተሳተፈ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ዓርብ ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በዘርፉ ያለውን የኦፕሬተርነት ሥራ ይይዛል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተሮችም በመጪው ዓመት መጨረሻ ሩብ ዓመት ውስጥ እንዲገቡ የሚችሉበት ሥራ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ በመጋራት ከሚገባው ኩባንያ ባሻገር፣ የራሳቸውን የቴሌኮም መስመር የሚያስተዳድሩ ሌሎች ሁለት ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ሥራ ይጀምራሉ፡፡ 

 በቴሌኮምና በስኳር ፋብሪካዎች የሽያጭ ሒደት ላይ እየተከናወኑ ስላሉ ሥራዎች መግለጫ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ኢትዮ ቴሌሎም በሁለት ምድብ እንደሚከፈል ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በመሠረተ ልማት አውታር ወይም በቴሌኮም መስመሮች ዝርጋታና በአገልግሎት አቅራቢነት ይካፈላል፡፡

እንደ ኢዮብ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ በመስመር ዝርጋታው መስክ ዓለም አቀፍ መገናኛዎች፣ አገር አቀፍ ፋይበር ኦፕቲክ፣ የሞባይል ኔትወርክ ማማዎችን የመገንባት ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በአገልግሎት መስክም የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የመበደኛ ስልክ የችርቻሮ ሽያጭ የሚያከናውን ተቋም ከኢትዮ ቴሌኮም ተለይቶ በመውጣት ለብቻው ይመሠረታል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የሚገዙ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት፣ የቴክኒክ ምዘና የሚካሄድበት፣ በሒደትም ግልጽ የጨረታ አሠራር የመከተልና በሒደቱ የተመረጡትን በማሳወቅ ግዥውን የማስፈጸም ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ 

ከፍተኛ አትራፊ ከሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ለሽያጭ እንደሚቀርብ ይፋ ከተደረገ በኋላ ቮዳፎን፣ ኤምቲኤን፣ እንዲሁም ኦሬንጅ የተሰኙት ታዋቂ ኩባንያዎችን ጨምሮ ሌሎችም ፍላጎት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ዕዳዎቹን እየከፈለ፣ የመንግሥት ዋስትና ሳያስፈልገው 300 ሚሊዮን ዶላር ለመበደር መዘጋጀቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቴሌኮም መስክ ተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው፣ በዓለም ባንክ ሥር የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ማጥናቱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡ 

ከቴሌኮም ዘርፉ ባሻገር በስኳር ኢንዱስትሪው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ 13 የመንግሥት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል የማዛወር እንቅስቃሴ ተጀምሮ፣ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች የማመልከቻ ቅጽ ሞልተው ለሚኒስቴሩ እንዲያስገቡ ተደርጎ እስካሁን አሥር ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ማሳወቃቸው ታውቋል፡፡ ፍላጎታቸውን ከገለጹ መካከል አንዳንዶቹ አዳዲስ ፋብሪካዎችን የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው፣ ሌሎቹም ነባሮቹን የመግዛት፣ በሽርክና ገብተው መሥራት የሚፈልጉም ሐሳባቸውን ለመንግሥት ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም፣ ያላቸው ንብረትና የዋጋ መጠን፣ እንዲሁም ፋብሪካዎቹ በተቋቋሙበት አካባቢ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተፅዕኖና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከ13 ፋብሪካዎች ስድስቱ ከስድስት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ግል እንደሚዛወሩ ተገልጿል፡፡ ይሁንና ኢዮብ (ዶ/ር) እስካሁን ፍላጎታቸውን የገለጹ የስኳርም ሆኑ የቴሌኮም ኩባንያዎች እነማን እንደሆኑ ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች