Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ ከታክስ በፊት ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አገኘ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሃያ አምስተኛ ዓመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኘው አዋሽ ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር ያለውን ልዩነት በማስፋት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት፣ ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡ ተመለከተ፡፡

ባንኩ በ2011 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው 3,329,766,285 ብር ትርፍ በግል ባንኮች የትርፍ ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ የ1.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ70 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን ከባንኩ የ2011 ዓ.ም. ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባንኩ ባለፈው ሒሳብ ዓመት በኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ተብሎ የተጠቀሰውን ሁለት ቢሊዮን ብር ማትረፉ የሚስታወስ ሲሆን፣ በዘንድሮ የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ግን ከሌሎች ባንኮች ጋር የነበረውን ልዩነት ያሰፋበት እንደሆነ ግርድፍ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የባንኮችን የ2011 የሒሳብ ዓመቱ አፈጻጸም የሚያሳዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ ትርፍ ተብሎ የተመዘገበው 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አዋሽ ባንክ በትርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ከግል ባንኮች በቀዳሚነት የሚያስቀምጡት አፈጻጸሞች ያስመዘገበበት ነው ተብሏል፡፡ ከባንኩ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው በደንበኞች ቁጥር፣ በተከፈለ ካፒታልና በመሳሰሉት ከግል ባንኮች የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ሊያስቀምጠው የሚችል አፈጻጸም ማስመዝገቡን፣ ከባንኩ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት ታውቋል፡፡

በመረጃው መሠረት ባንኩ በ2011 የሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ከ62.2 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ36 በመቶ ወይም የ16.3 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳያል፡፡ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥርም ከ2.7 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ታውቋል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን በ51 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ባንኩ የሰጠው ብድር ከ47.1 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ነው፡፡ ካፈለው ዓመት የብድር መጠን አንፃር ሲታይ በ2011 የሒሳብ ዓመት የሰጠው ብድር በ15.8 ቢሊዮን ብር ብልጫ የታየበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባንኩ ዓመታዊ ገቢም ስምንት ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የሚያመለክተው ይኸው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት፣ ከቀዳሚው ዓመት 2.5 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡ በቀዳሚው ዓመት ኦዲት የተደረገው የባንኩ ዓመታዊ ገቢ መጠን 5.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በተከፈለ የካፒታል መጠንም በ2011 የሒሳብ ዓመት የተሳካ አፈጻጸም እንዳሳየ አኃዛዊ መረጃው የሚጠቁም ሲሆን፣ ባንኩ በግል ባንኮች በተከፈለ ካፒታል መጠን የመጀመርያውን ደረጃ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ በ2011 ሒሳብ ዓመት ብቻ የተከፈለ ካፒታሉን በ49 በመቶ በማሳደግ ከ4.3 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም በአንድ ዓመት ውስጥ የተከፈለ ካፒታሉን በ1.4 በሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን የሚያመለክት ነው፡፡ በ2010 የሒሳብ መዝጊያ ላይ የባንኩ የተከፈለ ከፒታል መጠን 2.94 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ከባንኩ ዓመታዊ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ ዓመታዊ ወጪውም በ35 በመቶ ጨምሯል፡፡ በዘንድሮ የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ ጥቅል ወጪ 4.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ1.18 ቢሊዮን ብር የጨመረ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ወጪ 3.44 ቢሊዮን ብር እንደነበር፣ ኦዲት የተደረገው የባንኩ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት ያሳያል፡፡

አዋሽ ባንክ ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ የመጀመርያው የግል ባንክ በመሆን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለ ሲሆን፣ በመጪው ኅዳር 2012 ዓ.ም. የ25 ዓመት የምሥረታ በዓሉን ከእህት ኩባንያው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ባንኩ ከ25 ዓመታት በፊት ሲመሠረት 4,863 ባለአክሲዮኖችን ይዞ በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ሥራ የገባ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 4,380  ሆኖ የተፈቀደ ካፒታሉ ስድስት ቢሊዮን ብር፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 4.38 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አሁን ዓመታዊ ትርፉን 3.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለው አዋሽ ባንክ፣ ሥራ በጀመረ በመጀመርያው ዓመት ትርፍ አምስት ሚሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በ410 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ የሠራተኞች ቁጥር ከዘጠኝ ሺሕ በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች