Friday, June 21, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ቁርስ እየበሉ ልጃቸው መጣች]

 • ደህና አደርክ ዳዲ፡፡
 • ሰላም ነኝ፡፡
 • ትንሽ ጊዜ አለህ?
 • የምን ጊዜ?
 • ላወራህ የምፈልገው ነገር ነበር፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • እንዳትቆጣኝ ግን?
 • ውጤት ተሰጣችሁ እንዴ?
 • ኧረ ገና ነው ዳዲ፡፡
 • ታዲያ ምንድነው?
 • ቃል ግባልኛ?
 • መጀመሪያ ነገሩን ንገሪኛ፡፡
 • አየህ ልትቆጣኝ አስበሃል ማለት ነው?
 • ምን አጥፍተሽ ነው?
 • አጥፍቼ አይደለም ዳዲ፡፡
 • ታዲያ ምንድነው?
 • ፍቅር ይዞኝ፡፡
 • ምን?
 • በቃ አደገኛ ፍቅር ይዞኛል ዳዲ፡፡
 • ገና ልጅ እኮ ነሽ፡፡
 • ፍቅር እኮ ዕድሜ አይመርጥም፡፡
 • ለሁሉም ጊዜ አለዋ፡፡
 • ያልተነካ ግልግል ያውቃል አሉ፡፡
 • ተረት ደግሞ ማን አስተማረሽ?
 • ያው ፍቅር ሲይዝህ ፈላስፋ ትሆን አይደል?
 • ለማንኛውም እንደዚህ ዓይነት ቀልድ አቁሚ፡፡
 • የምን ቀልድ ነው ዳዲ?
 • ይኼ ፍቅር ምናምን የምትይውን ነዋ፡፡
 • ምን ችግር አለው ዳዲ?
 • እንዴት ችግር የለውም ተማሪ እኮ ነሽ?
 • ተማሪ ፍቅር አይዘውም እንዴ?
 • ነገርኩሽ እኮ አንቺ ስለፍቅር ማሰብ ያለብሽ ትምህርትሽን ከጨረሽ በኋላ ነው፡፡
 • ምን ሆነሃል ዳዲ?
 • ምነው?
 • ልጁን በጣም ነው የወደድኩት እኮ?
 • ተማሪ ነሽ እያልኩሽ እኮ ነው፡፡
 • ብሆንስ ዳዲ?
 • እንደዚህ ዓይነት ነገር ሁለተኛ እንዳልሰማ፡፡
 • ተው እንጂ ዳዲ፡፡
 • ምን?
 • እንዲያውም እውነቱን ልንገርህ?
 • ንገሪኝ፡፡
 • ልጁን ማግባት እፈልጋለሁ፡፡
 • ምን አልሽ?
 • የልጆቼ አባት እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡
 • እ…
 • ባይሆን አንድ ነገር ዕርዳኝ፡፡
 • ምን?
 • አሁን ነው መውለድ የምፈልገው፡፡
 • እኔ ጠፋሁ፡፡
 • ፍቅሩ ስላየለብኝ ከእሱ ሳልወልድ አንድ ወርም መቆየት የምችል አይመስለኝም፡፡
 • የት ነው በአንድ ወር ውስጥ ሲወለድ ያየሽው?
 • እናንተ ልታስወልዱ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡
 • በአንድ ወር ምንድነው የምናስወልደው?
 • ክልል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የፖለቲካ ተንታኝ ጋር ስብሰባ ላይ ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ላወራዎት እፈልጋለሁ፡፡
 • ስለምን ጉዳይ?
 • ስለወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ፡፡
 • ይቻላል፡፡
 • እዛ ጋ ሻይ ቡና እያልን እናውራ፡፡
 • ጥሩ ነው፡፡
 • ቡና ይሻልዎታል ሻይ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔስ ቡና ነው ምርጫዬ፡፡
 • ስኳር ስንት ላድርግልዎት?
 • እንኳን ስኳር ጨምሬበት ፖለቲካው ራሱ ደም ግፊቴን ጨምሮታል፡፡
 • ታዲያ ባዶውን ይጠጡታል?
 • እሱ ይሻለኛል፡፡
 • ግራ ተጋባን እኮ ክቡር ሚኒስትር?
 • በምኑ?
 • በሰሞኑ ፖለቲካችን ነዋ፡፡
 • ማን ግራ ያልተጋባ አለ ብለህ ነው?
 • ለመሆኑ ምንድነው የተፈጠረው?
 • የፖለቲካ ተንታኝ ነኝ ብለሃል አይደል እንዴ?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የተፈጠረው ብለህ እንዴት ትጠይቀኛለህ?
 • ግራ ስለተጋባን ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው ግራ ያግባህ?
 • የወሬው ብዛት ነዋ፡፡
 • ሚዲያ መቼም ተከታትለሃል?
 • አንዱም አልቀረኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ስለተፈጠረው ነገር እኮ በዚያ በኩል በሚገባ ተናግረናል፡፡
 • ያው መንግሥት የሚለውን ሙሉ ለሙሉ ለማመን ይከብዳል፡፡
 • ምኑ ነው የከበደህ?
 • ያው የእንግሊዝ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መንግሥትን ማመን ቀብሮ ነው ብለዋል፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅዎታል?
 • አይ የዘመኑ ፖለቲካ ተንታኝ፡፡
 • እንዴት?
 • ትራምፕ የትኛውን አገር እንደሚመራ የማታውቅ ጥራዝ ነጠቅ ነህ፡፡
 • ለማንኛውም መንግሥት የሚናገረውን ሁሉ ማመን ሞኝነት ነው፡፡
 • ለምን?
 • አዩ እንደ ፖለቲካ ተንታኝ የተለያዩ ሐሳቦችን ማየቱ መልካም ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋላ፡፡
 • የምን ጥያቄ?
 • የሰሞኑ የፖለቲካ ክስተት እንዴት ተከሰተ? ለምን ተከሰተ? በማን ተከሰተ? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
 • ጥያቄ መጠየቅ ጥሩ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንደ ፖለቲካ ተንታኝነቴ ነገሮችን ሰነጣጥቄ ነው ማየት ያለብኝ፡፡
 • ምን አየህ ታዲያ?
 • ያው እንደሚያውቁት ፖለቲከኞቻችን ሴረኞች ስለሆኑ፣ በዋናነት መመልከት ያለብን ከክስተቱ ጀርባ ያለውን ሴራ ነው፡፡
 • እኮ ምን አገኘህ?
 • እሱን እኮ እንዲያጫውቱኝ ነበር እናውራ ያልኩዎት?
 • ለመሆኑ ትንተናህን ምን ላይ ነው የምታቀርበው?
 • በራሴው ሚዲያ ላይ፡፡
 • የራስህ ሚዲያ አለህ?
 • ማኅበራዊ ሚዲያውን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
 • እናንተ ናችሁ እኮ ሕዝቡን የምታጫርሱት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የፖለቲካ ተንታኝ እንደ መሆኔ መተንተን እንጀራዬ ነው፡፡
 • አንተና መሰሎችህ የፖለቲካ ተንታኝ አትመስሉኝም፡፡
 • ታዲያ የምን ተንታኝ ነን?
 • የሴራ ተንታኝ፡፡
 • ይተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም በቅርቡ ፍርዳችሁን ትቀበላላችሁ፡፡
 • ከማን?
 • ከእግዚአብሔር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የእግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ስልክ ይደውልላቸዋል]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • ምን አደረግናችሁ?
 • ምነው?
 • ፍልስፍናችን መደመር ነው አላላችሁም ነበር እንዴ?
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ታዲያ ለምን እኛን ለመቀነስ አሰባችሁ?
 • ምን አድርገን?
 • ይኸው በአደባባይ ስፖርት የለም እያላችሁ አይደል እንዴ?
 • ተሳሳትን እንዴ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • እንዲህ የምንለፋው እኮ እግር ኳሳችን በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ነው፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅዎታል?
 • ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • የዓለሙን ተወውና በአገር ውስጥ በታወቃችሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለውጥ በአንድ ጀንበር አይመጣም እኮ፡፡
 • እሱማ ልክ ነህ፡፡
 • ስለዚህ እኛም እንደናንተው በለውጥ ውስጥ ነን፡፡
 • ስንት ዘመናት አሳልፋችሁ ለውጥ ላይ ነን ስትሉ አታፍሩም እንዴ?
 • ምኑ ያሳፍራል?
 • ለዘመናት ለውጥ ውስጥ ነኝ እያልክ መቀጠል ይቻላል?
 • ምን ችግር አለው?
 • ባይሆን አሁን ጥሩ ትምህርት ሰጠኸኝ፡፡
 • እንዴት?
 • እኛም ለውጥ ላይ ነን እያልን ለዘመናት መቀጠል እንችላለና፡፡
 • እ…
 • ከኳሱ ይልቅ አሁን ለፖለቲካው አንድ ጥሩ ነገር አበርክተሃል፡፡
 • ኧረ እኔን ፖለቲካ ውስጥ አይክተቱኝ?
 • ቀድሞውኑም ቢሆን ኳስ ሜዳዎቹን የፖለቲካ መጫወቻ አደረጋችኋቸው የምንለው ለዚህ ነው፡፡
 • እ…
 • እናንተ እኮ ከስፖርቱ ለፖለቲካው ነው ቅርብ የሆናችሁት፡፡
 • እኔ ግን ቅር ብሎኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው ቅር ያለህ?
 • ስፖርት የለም የሚለው ነዋ፡፡
 • ታዲያ በየጨዋታው የፖለቲካ መፈክር እያሰማችሁና እየተበጣበጣችሁ ስፖርት አለ እንበል?
 • እ…
 • ለማንኛውም በቅርቡ ስታዲየሞቻችንን እንዘጋቸዋለን፡፡
 • ለምን?
 • ያው በአገራችን ሁለት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል እንደታቀደ ታውቃለህ አይደል?
 • ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡
 • ስለዚህ ስታዲየሞቹን ችግኝ እናፈላባቸዋለን፡፡
 • ምን?
 • ምነው?
 • እኛስ?
 • እናንተም በአንድ ልብ ትቀላቀላላችሁ፡፡
 • ምኑን?
 • ፖለቲካውን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ለምን አታምኑም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን ነው የምናምነው?
 • አገር ማስተዳደር እንዳቃታችሁ፡፡
 • ቢያንስ ከእናንተ እንሻላለን፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • እኛ ስናስተዳድር እኮ ኮሽ የሚል ነገር አልነበረም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሕዝቡን በብረት እየገዛችሁት ስለነበረ ነዋ፡፡
 • እናንተ በምንድነው የምትገዙት?
 • በፍቅር ነዋ፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • እናንተም እኮ ሮማንሱን ጨርሳችሁ ወደ አክሽን ፊልም ከገባችሁ ቆያችሁ እኮ፡፡
 • ምን?
 • ይኸው አመራር ሳይቀር እየተገደለ ሮማንስ ላይ ነን ስትሉ አታፍሩም?
 • ምንም አላችሁ ምን እናንተ እንደሆነ ተመልሳችሁ አትመጡም፡፡
 • እንግዲያው በአገሪቱ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ይቀጥላል በሉኝ፡፡
 • እናንተ እኮ የሁሉም ችግር ምንጭ እንደሆናችሁ ግልጽ ነው፡፡
 • መቼ ይሆን እኛ ላይ ጣት መጠቆም የምታቆሙት፡፡
 • ለማንኛውም በጊዜ መንገዳችሁን ብታስተካክሉ ጥሩ ነው፡፡
 • የምን መንገድ?
 • የለውጡን መንገድ ተቀላቀሉ፡፡
 • እርሱን ይርሱት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለነገሩ የእናንተን ምርጫ እናውቀዋለን፡፡
 • ምንድነው?
 • ለውጥ ሳይሆን…
 • እ…
 • ነውጥ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...