Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርናው የኋላ ታሪክና የወደፊት ተስፋ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ የመንግሥት ኃላፊዎች ንግግር ውስጥ የሚደመጠው ለግብርናው ከሌላው ጊዜ የተሻለ ትኩረት እንደተሰጠው የሚጠቁም ነው፡፡ መንግሥት ለሜካናይዜሽን በተለይም ለመስኖ እርሻ ሥራዎች ቦታ መስጠቱን በየመድረኩ እያስታወቀ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን የመስኖ ልማት ሽፋን ለማሳደግ የተፈጠሩ የመስኖ ውኃ አማራጮች በመጠቀም፣ በ4.8 ሚሊዮን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አማካይነት 2.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሊለማ መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር የስምንት ወራት ሪፖርት በቅርቡ አትቷል፡፡ ይህም ከሚኒስቴሩ ዕቅድ አኳያ 68 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ በቆላማ የኢትዮጵያ ክፍሎችም 3,500 ሔክታር ያለበሰ መሬት በመስኖ መልማቱን፣ ሆኖም 1‚210 ከፊል አርብቶ አደሮችና 18 ለንግድ ሥራ የገቡ ባለሀብቶች በመስኖ አማካይነት ያረሱት መሬት ነው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ካላት 112 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ከ70 በመቶ ያላነሰው በሚገባ ሊለማ እንደሚችል መንግሥትም የዘርፉ ባለሙያዎችም ደጋግመው የሚገልጹት ነው፡፡

የግብርናው የኋላ ታሪክና የወደፊት ተስፋ

 

ይህም ሆኖ በዘርፉ ሲታይ የቆየውም ሆነ ሲመዘገብ የከረመው ውጤት፣ ትርፍ ምርት ሊያስገኝ ቀርቶ የአገሬውን ሆድ ሊሞላ ባለመቻሉ፣ ከፍተኛ ወጪ በየዓመቱ ለስንዴ ግዥ እየዋለ ይገኛል፡፡ ሰፊው ለም ሁዳድ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ ትርፍ እንዲመረትበት የሚያስችል አካሔድ ባለመፈጠሩ፣ ከ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያላነሰ ስንዴ በሚሊዮን ዶላሮች ከውጭ እየተገዛ ይገባል፡፡ በመጪው ዓመት በኢትዮጵያ ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው የ6.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የስንዴ ፍጆታ ውስጥ፣ ከ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከውጭ በተለይም ከሩማንያ፣ ከአሜሪካ፣ ከሩስያ፣ ከዩክሬን፣ ከቡልጋርያና ከሌሎችም አገሮች ተገዝቶ እንደሚገባ የአሜሪካ የግብርና መሥሪያ ቤት መረጃዎች ይፋ አድርገዋል፡፡

መንግሥት ይህንን አካሔድ ለመቀየር መነሳቱንና ስንዴን ብቻም ሳይሆን፣ ዘይትና መሰል የምግብ ምርቶችን ከውጭ ከማስመጣት ይልቅ እዚሁ ለማምረትና የአገር ውስጥ ፍላጎትንና ፍጆታን በአገር ውስጥ ምርት ለማሟላት እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲሁም የግብርና ዘርፉን የሚመሩ ሹማምንት ደጋግመው የገለጹበትን መድረክ መታዘብ ተችሏል፡፡

ይህንን ለማድረግ ያስችላሉ ተብለው ለሙከራ በአራት ክልሎች የተጀመሩ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ፓርኮች ሲገነቡ ታሳቢው ከየተገነቡበት አካባቢና በአቅራቢያቸው ከሚገኙ አምራቾች ምርት በገፍ እየቀረበላቸው አቀነባበረው ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ህላዌ ለመፍጠር ነበር፡፡ በትንሹ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ ግንባታቸው እየተገባደደ ይገኛሉ፡፡ ተቋማቱ ከአራት ወራት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ ይህ ይባል እንጂ ወደ ፓርኮቹ የሚገባና የሚቀነባበር የግብርና ጥሬ ምርት አቅርቦት ጉዳይ ሥጋት መፍጠሩ ታውቋል፡፡

በቅርቡ በአዳማ ከተማ በተካሔደው የግብርናው ዘርፍ አመራሮች በተለይም ከወረዳና ቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው ከፍተኛ አመራሮች ድረስ የተሳተፉበት የሁለት ቀናት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስብሰባ በተካሔደበትና ከ1‚500 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ወቅት፣ የዘርፉ አመራሮች የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት ሊያገኙ እንደማይችሉ በማሳሰብ የመፍትሔ ያለህ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያን ጉዳይ ከቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት አኳያ በማስተያየት የድሮና ዘንድሮውን የሁለቱን አገሮች ግብርና መመልከቱ ለዛሬው ግብርና ዘርፍ ይበጅ እንደሁ በማለት ከዚህ ቀደም ሪፖርተር አንድ ሐተታ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ ሐተታ ለዳግም ትውስታ ጥቂቱ ተቀንጭቦ ቀርቧል፡፡

የቀድሞዋ ሶሻሊስታዊቷ ሶቪዬት ኅብረት የአሁኗ ሩስያ ሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ42 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ በማረስ ከፍተኛ የግብርና ውጤት እንዳገኘችበት ስለሚነገርለትና የድንግል መሬቶች ዘመቻ ወይም ‹‹ዘ ቨርጂን ላንድስ ካምፔይን›› ስለሚባለው ግዙፍ የእርሻ ልማት አብዮት፣ የቀድሞው የሩስያ ፕሬዚዳንት ሊዮኔድ ኢሌዪች ብሬዥኔቭ በዘመቻው ስያሜ ‹‹ዘ ቨርጂን ላንድስ›› የሚል መጽሐፍ ጽፈው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ እ.ኤ.አ. በ1978 በጻፉት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ ከ20 ዓመታት በላይ ወደኋላ ተጉዘው፣ ያልተነኩና ያልታረሱ ድንግል እንዲሁም የተተዉ መሬቶችን በማረስ፣ እርሻዎችን በማስፋፋት የያኔዋን የሶቪዬት ኅብረትን የምግብ ሰብል እጥረት ለመቅረፍ የምትችልበትን መንገድ እንዲያስፈጽሙ የተደረገበትን ታሪክ ይዘክራሉ፡፡ ትንሿ መጽሐፋቸው ከ40 ዓመታት በኋላ ቆይታም በአማዞን ድረ ገጽ ሽያጭ ላይ ትገኛለች፡፡ በበርካታ ቋንቋችዎች ተተርጉማ በሽያጭ ላይ ትገኛለች፡፡ በእኛም አገር በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉማ ለንባብ በቅታ እንደነበር መረዳት ተችሏል፡፡

ብሬዥኔቭ በጉልምስናቸው ወቅት ያልተነኩ የሩስያ መሬቶችን በእርሻ እንዲያጥለቀልቁ ከተመደቡባቸው ግዛቶች መካከል በካዛኪስታን ሪፐብሊክ ውስጥ በሁለት ዓመታት ውስጥ የሠሩት ውጤታማ ሥራ ተዘክሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ራሷን የቻለች ነፃ አገር የሆነችው ካዛኪታን ሰሜናዊ ክፍልን በእርሻ ማሳያዎች ለማጥለቅለቅ የዘመተው የሶቪዬት ወጣት፣ 250 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ወይም ታላቋ ብሪታኒያን በሙሉ የሚሸፍን መሬት ወደ እርሻነት እንዲቀይር ይጠበቅ ነበር፡፡ አሳካው፡፡ ወጣቶች ለእርሻ ሥራው ከሚፈለገው በላይ እየተመሙ በመምጣታቸው እነሱን ማስተዳደሩ፣ በተለይም ሴቶች ወጣቶች ወደ አዳዲሶቹ የእርሻ ማሳያዎች መትተማቸው አሳስቧቸው እንደነበር ብሬዥቭ በመጽሐፋቸው ገልጸውታል፡፡

ወደ ነገረ ጉዳዩ እንመለስና በመላው ሩስያ እ.ኤ.አ. ከ1954 እስከ 1955 በነበረው ጊዜ ውስጥ ከታረሰው አዳዲስ የእርሻ መሬት ውስጥ አብዛኛው የሚገኘው በካዛኪስታን ግዛት እንደነበር የሚያወሱት ብሬዥኔቭ፣ በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ለእርሻ ሥራ ከተዘጋጀው 42 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 25 ሚሊዮን ሔክታሩ በካዛኪስታን ግዛት ውስጥ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ሶቪዬት ኅብረት ወደ መጠነ ሰፊ የእርሻ ማሽፋፊያ ዘመቻ ከማምራቷ በፊት፣ እ.ኤ.አ. በ1953 31 ሚሊዮን ቶን እህል ይመረት ነበር፡፡ ሆኖም የምግብ እህል ፍጆታዋ 32 ሚሊዮን ቶን ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ብሬዥኔቭ በጠቀሱት አኀዝ መሠረት ነው፡፡

ይሁንና የአገሪቱን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ በወቅቱ የሶቪዬት ፕሬዚዳንት ኒኪታ ክሩሽቼቭ አመራር ጸድቆ ወደ ተግባር ለገባው ዕቅድ መተግበሪያ፣ በአራት ዓመታት ውስጥ 30 ሚሊዮን ሩብል ወይም በአሁኑ ምንዛሪ ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብታወጣም ከ7.6 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ48.8 ቢሊዮን ሩብል በላይ ግምት ያለው የምግብ ሰብል ማምረት መቻሏን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ምንም እንኳ ያልታረሱና ያልተነኩ መሬቶችን በሰፊው የማልማቱ ዕርምጃ ከጅምሩ በሶቪዬት ፖለቲከኞችና ምሁራን ዘንድ ትችት ቢሰነዘርበትም፣ ክሩሽቼቭም ሆኑ ብሬዥነቭን የመሳሰሉ ደጋፊዎቻቸው ዕቅዱን ለማስፈጸም ተፍ ተፍ በማለት የአገሪቱን የምግብ እህል እጥረት ለመቅረፍ በቅተዋል፡፡ አካሔዱ ግን በክፉም በበጎም ዛሬም ድረስ ይነሳል፡፡ በትንሹ ከ300 ሺሕ በላይ ወጣቶች የእርሻ ልማት ማስፋፊያ በሚካሔድባቸው ክልሎችና ግዛቶች ተሰማርተዋል፡፡ የወጣቶቹ ከወታደራዊ ተልዕኮ ያልተናነሰ ዘመቻ አዲዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና ኢንዱስሪዎች እንዲስፋፉ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ሆኖም ዘመቻው በርካቶችን ለሞት ዳርጓል፡፡ በርካቶችንም ለከፋ ውድቀት አብቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሩስያ ታላቋ ሩስያ የሆነችበትን ትልቅ ዕርምጃ ያስመዘገበችው ውጤት አመላክቷል፡፡

እንደ አገር የማይቻለውን የሚችልና ለድል የሚተጋ ሕዝብ ያላት ታላቅ አገር መሆኗን ያሳየችበት የታሪክ ምዕራፍ ስለመሆኑ ብሬዥኔቭ በኩራት ጽፈዋል፡፡  ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ የያኔዋ ሩስያ፣ እንደ ግዙፉ የእርሻ ዘመቻ የገባችው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በጦርነቱ ወቅት ከ20 እስከ 27 ሚሊዮን ወታደራዊና ሲቪል ዜጎቿን ያጣችው ሩስያ፣ 32‚000 ፋብሪካዎቿ፣ 17‚000 ከተሞቿና 70‚000 መንደሮቿ በጦርነቱ ወድመውባት ነበር፡፡ ይሁንና ጦርነቱ ባከተመ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ አስገራሚ ውጤት ያስመዘገበችበትን የግብርና ዘመቻ በማካሔድ የምግብ ሰብል እጥረቷን አልፋ ፋብሪካዎቿን መመገብ የቻለ ትርፍ ምርት አስመዝግባለች፡፡

የሶቪየት ኅብረትና የኢትዮጵያ ውድጅት

ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ ስለአገራቸው የእርሻ ስኬቶች ብቻም ሳይሆን፣ ስለአገራቸው ሕዝብ ታላቅ ተጋድሎ ባወሱበት ክታብ፣ ከጠቀሱት ውስጥ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ትራክተርና ኮምባይነር ማግኘት ከባድ በነበረበት ወቅት እንኳ፣ ዶማና አካፋ በመያዝ በርካታ መሬት በማረስ ሰብል ማምረታቸውን ይተርካሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ካዛኪስታንን ጨምሮ አብዛኞቹ አዳዲስ የእርሻ ቦታዎች ከባድ ድርቅ የሚታይባቸው፣ ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚያስተናግዱ ነበሩ፡፡ እንደውም የእርሻ ዘመቻው በታወጀበት ወቅት ከባድ ድርቅ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የነበረበት ወቅት እንደነበር ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም በሁለት ዓመታት ውስጥ ታርሶ የተመረተው ምርት ከሚጠበቀው በላይ ከፍተኛ በመሆኑ ሳቢያ ምርቱን ከማሳ ሰብስቦ ወደ ፋብሪካ ለመውሰድ ፈታኝ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም በሰው ጫንቃና በእንስሳት ሸክም ወደ መኪኖች እየተጫነ ምርቱን ወደሚፈለግበት መውሰድ ግዴታ ስለነበረበት ሁኔታም አስታውሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ብሬዥኔቭ ስለአገራቸው የእርሻ ልማት ብቻ አልነበረም የሚታወሱት፡፡ እሳቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት በኢትዮጵያም የደርግ መንግሥትን ይመሩ ለነበሩት ለኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወዳጅ እንደነበሩ የሚዘክሩ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ጋዜጠኛዋ ሚሼላ ሮንግ ስለሁለቱ የኮሚዩኒስት መሪዎች ግንኙነት ‹‹አይ ዲድንት ዱ ኢት ፎር ዩ›› በተሰኘውና በአብዛኛው ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ በሚተርከው መጽሐፏ የጠቀሰችው ታሪክ ይገኝበታል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ብሬዥኔቭን ‹‹እንደ አባቴ የማየው ወዳጄ›› እንደሚሏቸውና ብሬዥኔቭም ከአፍሪካ መሪዎች ምሳሌ የሚያደርጓቸው የልብ ወዳጃቸው እንደሆኑ የተናገሩትን በመጽሐፏ አስፍራለች፡፡

ጸሐፊዋ የሁለቱ ርዕሰ ብሔሮች የግል ግንኙነት ብቻም ሳይሆን፣ የየአገሮቹን ግንኙነት በምትጠቅስበት ምዕራፍም ሶቪዬት ኅብረት፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ምሳሌና ሞዴሏ ለማድረግ የነበራትን ጉጉት ትተርካለች፡፡ አገሪቱ ለኢትዮጵያ በየዓመቱ ስትመድብ በነበረው ገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ኃይል ሆና እንድትወጣ፣ በዚህም የሶቪዬት ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ከካፒታሊዝም የሚልቅበት ጉልበቱን በአፍሪካ የማሳየት ፍላጎት እንደነበራት ጋዜጠኛዋ ትተነትናለች፡፡ በየጊዜው እያደገ ሔዶ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሰው የገንዘብ ድጋፍ ግን፣ ለኢኮኖሚ ልማት ከመዋል ይልቅ ለጦርነት መማገዱ የኋላ ኋላ ሶቪዬቶችን እንዳላስደሰታቸው ተጽፏል፡፡

ግብርናችንና የሶቪዬት የእርሻ ዘመቻ

ከሶቪዬቶች ግዙፉ የእርሻ ዘመቻ ትይዩ በኢትዮጵያም በሜካናይዜሽን የታገዘ የሰፋፊ እርሻዎች ፕሮግራም ዳዴ ማለት ጀምሮ ነበር፡፡ የዚህ ሥራ ጅማሮን በሚመለከት የወቅቱን ሁኔታ የሚዘግቡ ድርሳናት እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የምግብ እህል ከውጭ ገዝታ ማስገባት የጀመረችበት ወቅት ነበር፡፡ በእርሻው መስክ የአገሪቱን የምግብ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በማሰብ የጭላሎ ግብርና ልማት ቡድን፣ የአርሲ ግብርና ልማት ቡድን፣ የወላይታ ግብርና ልማት ቡድንና ሌሎችም ዘመናዊ የግብርና ፕሮግራሞች ብቅ አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ተኮር ተቋማዊ ሥርዓት እ.ኤ.አ. በ1907 እንደተመሠተ ስያሜውም፣ የግብርና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይባል እንደነበር ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) በቅርቡ ባሳተሙት ‹‹ኦቨር ካሚንግ ፉድ ኤንድ አግሪካልቸራል ክራሲስ ኢን ኢትዮጵያ›› በተሰኘው መጽሐፍ ጠቅሰውታል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ ብሔራዊ የሰብል ምርት ድርጅት፣ የአምቦ እርሻ ትምህርት ቤትና ሌሎችም እ.ኤ.አ. በ1940ዎቹ ጀምሮ ነበር የተመሠረቱት፡፡ ይብሱኑ የአሁኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ እ.ኤ.አ. በ1945 ሲመሠረት ዋና ዓላማው ግብርናን በገንዘብ እንዲያግዝ ተብሎ ስያሜውም የኢትዮጵያ ግብርና ባንክ የሚል ነበር፡፡ እርግጥ በየጊዜው ስያሜውና ተግባሩ እየተሻሻለ መጥቶ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የግብርና ልማት ቡድኖችም በተለያየ አካባቢ ተመሥርተው ዘመናዊ እርሻን ለማስፋፋት ጅምሮች ታይተው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ፕሮግራሞችና ተቋማት የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ይህም ሆኖ በአርሲ አካባቢ የተጀመረው ሥራ መጠነኛ ውጤት እንዳሳየና ዛሬም ድረስ በአካባቢው የሚታየው የግብርና ሥራ በሜካናይዜሽን የተቃኘ የመሆኑ ምሥጢር መነሻው በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት የተጠነሰሱት እነዚህ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራዎች ያመጡት ተፅዕኖ እንደነበር ከሚጠቅሱት ምሁራን መካከል ጌታቸው  (ዶ/ር) ይጠቀሳሉ፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ጌታቸው (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ግብርና እጅጉን ኋላቀር ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረግጠው ጽፈዋል፡፡

በመጽሐፉ ዙሪያ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታም፣ ‹‹መጽሐፉን የጻፍኩት ከቁጭት በመነሳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ጥንት በኒዮሊቲክ ዘመን ከነበሩ አሠራሮች አኳያ ሲታይ ብዙም ለውጥ አለማሳየቱ ያስቆጫል፤›› በማለት ከ60 ዓመታት ቀደም ብሎ በአርሲ በተለይም እሳቸው ተወልደው ባደጉባት የዶሻ ቀበሌ ውስጥ ሕይወት ለነዋሪዎቿ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ፣ በእነኚህ ዓመታት ውስጥም የታየው ለውጥ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ አበክረው ገልጸዋል፡፡

የአርሲ ገጠር ግብርና ልማት ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ የመጀመሪያ ተጠቃሚዋ ዶሻ ቀበሌ እንደነበረ የሚያብራሩት የግብርና አኮኖሚ ባለሙያው ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ቀበሌየግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማግኘት ከቻሉ የዚያን ጊዜ አካባቢዎች የመጀመሪያዋ ልትባል እንደምትችልም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ይህ ሁሉ ተደርጎም የዶሻ ነዋሪዎች ሕይወት አልተሻሻለም፡፡ ጥሩ የኑሮ ደረጃ ስለሚባለውና የዶሻ ነዋሪዎች ሕይወት ከነበረው በምንም መልኩ ለምን እንዳልተለወጠ እንመለከታለን፡፡ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪ ቤተሰቦች ብዛት በሦስት እጥፍ ጨምሯል ማለት ይቻላል፡፡ አካባቢው፣ የደኑ ይዞታ፣ የዱር እንስሳቱ በሙሉ ሙልጭ ብለው ጠፍተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመሬት እጥረት ትልቁና ዋናው ፈተና ነው፡፡ ወጣቶች ወደ ከተማ አካባቢ ለትምህርትና ለሥራ ፍለጋ ይሰደዳሉ፡፡ ነዋሪዎች የባንቧ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች በማሳቸው ያመረቱትን በአህያ፣ በፈረስ ሲከፋም በትከሻቸው ተሸክመው ወደ ገበያ ቦታ ይሔዳሉ፡፡››

ምሁሩ ይህንን ካነሱ በኋላም እንዲህ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያውያን ቁልፉ ጥያቄ የሚሆነው በእንዲህ ያለው ሁኔታ እስከመቼ እንቀጥጣለን? የሚለው ነው፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ መንደሮች አኳያ ስትታይ ዶሻ የምግብ እጥረት ላይታይባት ይችላል፡፡ ይህ በአወንታዊነት ሊታይ ቢችልም ድህነቱ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ሕዝቡ ወደ ዕርዳታ ተቀባይነት እያዘገመ መሆኑ ነው፡፡ የሰብል ምርት ችግር ውስጥ ከገባ ዶሻ የእህል ዕርዳታ መፈለጓ አይቀሬ ነው፤›› በማለት ሊመጣ ያለውን ሥጋት አመላክተዋል፡፡ እንደ ጌታቸው (ዶ/ር) ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ግብርና አሁንም ድረስ ከ10 ሺሕ ዓመታት በፊት በነበረ የእርሻ መሣሪያዎች የሚታገዝ፣ የበሬና የገበሬ ጉልበት የሚፋተጉበት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ዘርፍ መሆኑን  ቀጥሏል፡፡

በ2007 ዓ.ም. እንደሁም በ2009 ዓ.ም. ሁለት የዳጎሱ ሙያዊ መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁት ሌላው የግብርና ኢኮኖሚ ምሁር ደምስ ጫንያለውም (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለገበሬዎቿ የሰጠችውን አነስተኛ ትኩረት ይተቻሉ፡፡ ገበሬው ከመንግሥት ጥገኝነት ተላቆ፣ ያሻውን አምርቶ፣ ባሻው ጊዜ በገበያ ሸጦና ለውጦ ለመኖር የሚችልበትን አቅምና ዕድል አላገኘም የሚሉት ደምስ (ዶ/ር)፣ ገበሬው በግሉ እንደማንኛውም ነጋዴ ወይም አምራች አካል ከመታየት ይልቅ በግብርና ሥራው ላይ ያለመንግሥት ድጋፍ ምንም ማድረግ የማይችል አልሚ ሆኖ መቅረቱን ይሞግታሉ፡፡ ማዳበሪያ ለማግኘት የመንግሥትን እጅ መጠበቅን ጨምሮ የኤክስቴሽን አገልግሎት ለማግኘት፣ ምርጥ ዘርና ሌላውንም አቅርቦት ለማግኘት የመንግሥት እጅ የሚጠብቅበት አሠራር መለወጥ እንዳለበትም ‹‹ዘ ኩዌስት ፎር ቼንጅ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲሁም 900 ገጾችን ባካተተው ‹‹ኢትዮጵያስ ኢንዲጂኒየስ ፖሊሲ ኤንድ ግሮውዝ፡ አግሪካልቸር፣ ፓስቶራል ኤንድ ሩራል ደቨሎፕመንት›› በተሰኘው መጽሐቸው ሰፊ ሐተታዎችን አቅርበዋል፡፡  

ነገሮች እንዲህና እንዲያ ቢጠቀሱም፣ የአገሪቱ የምርት መጠን በዚህ ዓመት 400 ሚሊዮን ኩንታል ወይም 40 ሚሊዮን ቶን እንዲደርስ መታቀዱን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን አስታውቀዋል፡፡ ይህ መጠን እ.ኤ.አ. ከ1954 በፊትም ስታመርተው ከነበረው ጋር እኩል ነው፡፡ ሩስያ የእርሻ ማስፋፊያ ዘመቻ ከመጀመሯ ቀድሞ 31 ሚሊዮን ቶን ታመርት እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ለፍጆታ የሚውለው ግን 32 ሚሊዮን ቶን ስለነበር፣ ይህንን ክፍተት መድፈን ብቻም ሳይሆን፣ ለምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደልብ የሚበቃ የተትረፈረፈ የግብርና ምርት ማምረት ችለዋል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓይነቱ አቅመ ግብርና አልበቃችም፡፡ ደምስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብትና የግብርና አቅም ከ600 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማምረት እንደምትችል በመግለጽ የመንግሥት ዕቅድ እንዲስፋፋ ይጠይቃሉ፡፡

መንግሥት ግብርናው ከምንጊዜውም ይልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል በማለት፣ ለመስኖ እርሻ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መበጀቱን አስታውቋል፡፡ በአንፃሩ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ የዕለት ደራሽ ምግብ የሚፈልጉ ዜጎች አሉ፡፡ ከአንድ አምስተኛ ያላነሰ ሕዝብ ለምግብ ዕርዳታ በሚሰለፍባት ኢትዮጵያ፣ ግብርናውን ፈታኝ የሚያደርገው ጉዳይ የመሬት ሥሪቱና የአነስተኛ ገበሬዎች የመሬት ይዞታ አንዱ እንደሆነ የሚጠቅሱት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ከ40 በመቶ በላይ አነስተኛ አርሶ አደሮች ከ0.23 ሔክታር ያነሰ የእርሻ መሬት አላቸው፡፡

ከግማሽ ሔክታር ከፍ ያለ ወይም 0.6 ሔክታር የሚያርሱት 23 በመቶ፣ እንዲሁም 2.6 ሔክታር የሚያርሱት 23 በመቶ፣ 1.2 ሔክታር የሚያርሱ 12 በመቶ ሲሆኑ፣ ትክክለኛውን የአነስተኛ አርሶ አደሮች ትርጓሜ የሚያሟሉት ያላቸው የመሬት ይዞታ 4.4 ሔክታር ሲሆን፣ የእነዚህ ብዛት ግን ከ1.25 በመቶ ወይም ከ220 ሺሕ ቤተሰቦች ያልበለጠ ነው፡፡

እንዲህ ባለው ሥሪት መንግሥት የሚያስበው በምግብ ሰብል ራስን የመቻል ዘመቻና የመስኖ እርሻ ሥራ ውጤታማነት ሊታሰብበት እንደሚገባ ምሁራን ያሳስባሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጉዳይ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥናት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአገሪቱን የግብርና ምሁራን ያካተተ አገር አቀፍ የአማካሪዎች ቡድን ተመሥርቶ የግብርና ሚኒስቴርንና ሌሎችም ከፍተኛ ሹማምንትን ማማከር እንደጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ጅምር ከቀድሞው የተሻለ ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ ከ70 ዓመታት በፊት በሩስያ ከታየውም የላቀ ለውጥ ይታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ይታይ ይሆን?

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች