የአገሪቱን ከፍተኛ የቢራ ገበያ እንደያዘ የሚታመነውን የቢጂአይ ኢትዮጵያ የማርኬቲንግ ዘርፍ ኃላፊ በመሆንና ኩባንያውን በመወከል ከሦስተኛ ወገን ጋር በመደራደር የሚታወቁት አቶ ኢሳያስ ሃደራ ከኃላፊነት መልቀቃቸው ተሰማ፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከማርኬቲንግ ኃላፊነታቸው በተጨማሪ፣ ኩባንያውን በመወከል በተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ኃላፊነት እንደነበራቸው የሚነግርላቸው አቶ ኢሳያስ፣ ከቢጂአይ ኩባንያ ጋር የነበራቸውን የሥራ ውል ያቋረጡት በገዛ ፈቃዳቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በቢጂአይ ኢትዮጵያ ከ21 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አቶ ኢሳያስ፣ ከሥራ ስለለቀቁበት ምክንያት ባያብራሩም በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ ስለጉዳዩ ከሪፖርተር ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል፡፡
ከቢጂአይና ከእህት ኩባንያዎቹ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ውስጥ ከነበራቸው ኃላፊነቶች መካከል በተለይ ቢጂአይ ኢትዮጵያ የራያ ቢራ አክሲዮኖችን በግዥ ከመጠቅለሉ ቀደም ብሎ ቢጂአይን በመወከል በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚጠቀስ ነው፡፡
የራያ ቢራ አክሲዮኖች በሽያጭ ወደ ቢጂአይ ኢትዮጵያ እንዲዘዋወሩ ስምምነት እስከተደረሰበት ጊዜ ድረስም ቢጂአይ ኢትዮጵያ በራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ የ42 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንደነበረው ይታወሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቢጂአይ ኢትዮጵያና እህት ኩባንያው ካስቴል ግሩፕ፣ የራያ ቢራና የዘቢዳር ቢራ ፋብሪካዎችን አክሲዮኖች ለመጠቅለል በተደረጉ የሽያጭ ድርድሮች ውስጥ ዓይነተኛ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አቶ ኢሳያስ፣ ከሥራ የመልቀቃቸው አጋጣሚና ድንገተኛ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ እርሳቸው ግን ከሥራ መልቀቃቸው እርግጥ ቢሆንም፣ የሚለቁት በግላቸው ለመሥራት በመፈለጋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ ከቢጂአይና ከእህት ኩባንያዎቹ ጋር በተያያዘ በነበራቸው ኃላፊነትም ከፍተኛ ተከፋይ እንደነበሩ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም በኩባንያዎቹ ውስጥ ከነበራቸው ኃላፊነትና የሥራ ግንኙነት አኳያ በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን ይለቃሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ምንጮች ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የአቶ ኢሳያስን መልቀቅን ተከትሎ ቢጂአይ ኢትዮጵያ አዲስ የማርኬቲንግ ዘርፍ ኃላፊ መሰየሙ ታውቋል፡፡ በፈረንሣዩ ካስትል ግሩፕ የሚተዳደረው ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ በቢራ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሲሰማራ የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ ነው፡፡ ኢንዱስትሪውንም የተቀላቀለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካን ከመንግሥት በአሥር ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ቢጂአይ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ የሚገኘውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ከማስፋፋቱም ባሻገር፣ በኮምቦልቻና በሐዋሳ ፋብሪካዎችን ገንብቷል፡፡ ካስትል ወይን ፋብሪካም በካስትል ግሩፕ ሥር የሚተዳደር ነው፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ በቢራ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ ለማስፋት በራያ ቢራ ውስጥ ከነበረው የ42 በመቶ ድርሻ በተጨማሪ የተቀሩትን የራያ ቢራ አክሲዮኖች ለመጠቅለል ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ግዥ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
ዘቢዳር ቢራ አክሲዮን ማኅበርንም ለመግዛት ባደረገው ጥረት ካስትል ግሩፕ የዘቢዳር ቢራን 60 በመቶ ድርሻ ይዞ ከነበረው የቤልጂየሙ ዩኒ ቢራ ኩባንያ አክሲዮኖችን መግዛቱም ይታወሳል፡፡ በቢጂአይ ስም 40 በመቶውን የዘቢዳር ቢራ ድርሻ ለመግዛት ከ1.37 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ሰጥቷል፡፡ የግዥ ሒደት በተለይም የቀረበው ዋጋ አንሷል የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይዘነጋም፡፡