የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሽምብራን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በማካተትና በማገበያየት የምርቶቹን ብዛት ወደ ዘጠኝ ከፍ አደረገ፡፡ ምርት ገበያው ከምሥረታው ጀምሮ ከ225 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጡ የግብርና ምርቶች አገበያይቷል፡፡
በተገባደደው የ2011 በጀት ዓመት ወቅት አኩሪ አተርን ወደ ዘመናዊ ግብይቱ ያስገባው ምርት ገበያ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮም ሽምብራን በማካተት በዓመቱ ሁለተኛውን ምርት ወደ ዘመናዊ ግብይቱ አካቷል፡፡ የውጭ ገበያ ፍላጎት የሚታይበት ሽምብራን ወደ ግብይት ሥርዓቱ በማምጣት አርሶ አደሩ፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ብሎም አገሪቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ የግብርና ምርቶች አንዱ ነው ያሉት የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ፣ የሽምብራ ምርት ከሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ በምርት ገበያው ማዕከላት ግብይቱ መካሄድ እንደጀመረ አስታውቀዋል፡፡ ምርት ገበያው በአምስት ቅርንጫፎቹ ሽምብራን እየተቀበለ እንደሚገኝና አቅራቢዎችም ከወዲሁ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ተጠቅሷል፡፡
የሽምብራ ምርት በዓለም ገበያ ተፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በ2010 ዓ.ም. 49 ሺሕ ቶን ሽምብራ ወደ ውጭ ተልኮ ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ሽምብራ በዘመናዊ ሥርዓት በኩል ግብይቱ መፈጸሙ ለወጪ ንግዱም ሆነ ለአገር ውስጥ ገበያ አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖርና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለመገበያየትና ለመላክ ከማስቻሉ ባሻገር፣ አቅራቢዎችም ግብይት በተፈጸመ ማግሥት የምርታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ እስካሁን የሽምብራ የወጪ ንግድ ግብይት ከምርት ገበያው ውጪ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዘመናዊ ግብይቱ በኩል ግብይቱ መፈጸሙ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡
የሽምብራ በአማራጭነት ግብይቱ እንዲፈጸም ቢወሰንም በአርሶ አደሩና በአቅራቢዎች ዘንድ በምርት ገበያ በኩል ግብይቱ እንዲከናወን ያለው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ምርቱ በብዛት ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡ ምርት ገበያ ካሉት 23 ቅርንጫፎች ውስጥ በአዲስ አበባ ሳሪስ፣ አዳማ፣ ቡሬ፣ ኮምቦልቻና ጎንደር ምርት መቀበያ ቅርንጫፎች ለመቀበል ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አኩሪ አተርና ሽምብራ ወደ ምርት ገበያ ሥርዓት በመግባታቸው የግብይት ምርቶች ቁጥር ወደ ዘጠኝ እንዳደገ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምርት ገበያው ቡና፣ ሰሊጥ፣ ቀይ ቦሎቄ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ ማሾና አኩሪ አተር ሲገበያይ ቆይቷል፡፡ እንደ ምርት ገበያው መረጃ ከሆነም፣ እስከ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 100,657 ኩንታል አኩሪ አተር በ1.22 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የአኩሪ አተር ምርት እያደገ በመምጣቱና ተፈላጊነቱም በመጨመሩ ወደ ማዕከል የሚገባው የምርት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ምርት ገበያ አስታውቋል፡፡ ምርት ገበያ የቅበላ አቅሙን በማስፋት በቡሬ፣ በጎንደር፣ በፓዌ፣ በሳሪስና በነቀምት በሚገኙ የምርት መቀበያ መጋዘኖች ምርቱን እየተረከበ ይገኛል፡፡
ምርት ገበያው አሁንም አዳዲስ ምርቶችን ወደ ምርት ገበያው ለማስገባት ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ በተለይ የኑግ ምርትን በጥቂት ወራት ውስጥ የግብይት ሥርዓቱን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም ምርት ገበያው ተደራሽነቱን ለማሳደግ በቅርቡ በሑመራ አካባቢያዊ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል በመክፈት ሥራ አስጀምሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡና በማምረትና በመገበያየት ላይ ለተሰማሩ ሴቶች የሚሰጠው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በማጠናቀቅ ማስመረቁ አስታውቋል፡፡ ምርት ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና አምራችና ላኪዎች ማኅበር አባላት በቡና አዘገጃጀት ላይ ለሁለት ሳምንት በንድፈ ሐሳብና በተግባር የታገዘ ሥልጠና በመስጠት ያስመረቃቸው እንስቶች፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ ለአነስተኛና መካከለኛ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አባላት ይህን መሰል ሥልጠና ያለ ክፍያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ከጀመረበት ሚያዝያ 2000 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ 225.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 5.6 ሚሊዮን ቶን የግብና ምርቶችን እንዳገበያየም አስታውቋል፡፡ .