Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› በሕገወጥ ንግድ ላይ በጠራው ጉባዔ ስለኢትዮጵያ የቀረቡ አኃዞች አነጋገሩ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጨርቃ ጨርቅ፣ ትንባሆና የመድኃኒት ምርቶች ከፍተኛ ሕገወጥ ንግድ የሚፈጸምባቸው ተብለዋል

በሕገወጥ የንግድና የኢኮኖሚ እንስቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረውና የኢኮኖሚኒስት መጽሔት አካል በሆነው ዘ ኢኮኖሚስት ኢንጀሊጀንስ ዩኒት የተሰኘው ተቋም በኩል የተካሄደው ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ትምህርት ኮሌጅ ባልደረባ ያቀረቧቸው የጥናት አኃዞች አነጋግረዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ ማንደፍሮ ባቀረቡት ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ በሁሉም የንግድ መስኮች ከሚታየው እንቅስቃሴ 40 በመቶው በሕገወጥ ንግድ መስክ የሚመደብ ነው፡፡ በተለይም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክ፣ በመድኃኒትና በትንባሆ ምርቶች ላይ የሚታየው ሕገወጥ የአገር ውስጥ ንግድ ከፍተኛ ደረጃ የያዘ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ የ48 በመቶ የአገር ውስጥ ሕገወጥ ንግድ ድርሻ እንደያዘ ሲገለጽ፣ ትንባሆ የ45 በመቶ እንዲሁም የመድኃኒት ዘርፉ 30 በመቶ የሕገወጥ ንግድ የተስፋፋበት እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ አቅርበዋል፡፡

በጥናቱ መሠረት የአምስት ዓመታት ዋጋው እንደተሰላ አብራርተው፣ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2017/18 ባለው ጊዜ ውስጥ የ18 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሕገወጥ የገቢ ንግድ እንደተመዘገበ ግምታዊ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ብቻ የዘጠኝ ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2016 በነበረው ጊዜ ውስጥም ከ17 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል መታጣቱ እንደሚገመት ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳ ምሁሩ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ሥጋት የደቀነ የሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ በአገሪቱ እንደሚታይ ቢያመላክቱም፣ ከጠቀሷቸው አኃዞች መካከል በተለይ በመድኃኒት ዘርፉ ላይ የቀረበው አኃዝ ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸውና እንደማይስማሙበት ለሪፖርተር ያብራሩት፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አማካሪ አቶ ጥላሁን እስማኤል ካሳሁን ናቸው፡፡

እንደ ከፍተኛ አማካሪው ከሆነ፣ ከ70 በመቶው ከውጭ የሚገባው መድኃኒት በመንግሥት በኩል በተለይም በመድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ በኩል በሕጋዊ መንገድ እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቀሪውን 30 በመቶ አቅርቦት በአብዛኛው የሚሸፍኑት የአገር ውስጥ አምራቾችና አስመጪዎች እንደሆኑ አቶ ጥላሁን አብራርተው፣ በኢትዮጵያ 30 በመቶው መድኃኒት በሕገወጥ መንገድ የሚገባ ነው መባሉን እንደማይስማሙበት አስታውቀዋል፡፡ በጨርቃ ጨርቅና በትንባሆ ምርቶች ላይ በረዳት ፕሮፌሰር ማንደፍሮ የቀረቡት አኃዞች ከሞላ ጎደል ሊያስማሙ እንደሚችሉ ገልጸው፣ በጠቀሰው መጠን መሆኑ ላይ ግን ጥያቄ እንዳደረባቸው አልሸሸጉም፡፡

ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣው የሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ሳቢያ በተለይ በመድኃኒት፣ ጨርቃ ጨርቅና ትንባሆ ምርቶች ላይ ከሚታየው የሕገወጥ ንግድ በተጨማሪ በሕገወጥ መንገድ ከሚገቡት የትንባሆ ምርቶች መካከል 90 በመቶ በላይ ተመሳስለው የተሠሩ እንደሆኑ ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ እሳቸው በአኃዝ የጠቀሷቸው ተመሳስለው የተሠሩና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችም በገበያው በብዛት እየታዩ መሆናቸው አሳሳቢ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ለመጣው የሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ሦስት ዋና ዋና አመቺ መንገዶች አስተዋጽኦ አድገዋል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በመደበኛውና በኢመድበኛው ንግድ መስክ የተሰማሩ ነጋዴዎች ትክክለኛውን ምርት ከተጭበረበረውና ሕገወጥ ከሆነው በመቀላቀል የሚፈጽሙት ማጭበርበር አንደኛው ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት መንስዔ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በደኅንነትና በፀጥታ ሠራተኞች ብሎም፣ በጉምሩክ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ከለላ እየተሰጣቸው በወታደራዊ አጀብ ጭምር ታግዘው የሚገቡ የሕገወጥ ምርቶችም በአገሪቱ እየተስፋፋ ለመጣው የሕገወጥ ንግድና እንቅስቃሴ ወቀሳ ከሚቀርብባቸው መካከል እንደሚመደቡ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ሁሉ አሁንም ድረስ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ከሚገኘው የሙስና ተግባር ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን ከምንጊዜውም ይልቅ ተጋላጭ እያደረጋት እንደመጣ ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ ገልጸዋል፡፡

ጉባዔውን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽር ደበሌ ቅባት በከፈቱበት ወቅት እንደተናሩት፣ በሕገወጥ ንግድ አማካይነት ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገሮች ከሚጓዙት ሸቀጦች ውስጥ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የቁም እንስሳት፣ ወርቅ፣ ሳፋየርና ሌሎችም በገፍ እየወጡ ነው፡፡ በመሆኑም የድንበር ንግድን በሕጋዊ መንገድ ለማካሄድ ከጎረቤት አገሮች ጋር ስምምነት ማድረግ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ፣ የንግድ ሸቀጦችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን በዲጂታል መንገድ መከታተል የሚቻልበት የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት መዘርጋት ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ የተሰኘው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ግልጽነት ተቋም ከሚያወጣቸው መረጃዎች እንደሚታየው፣ እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ1.2 ቢሊዮን እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ ንግድ ብሎም በተጭበረበረ የንግድ ሰነድ አማካይነት ወደ ውጭ ሲሸሽባት ቆይቷል፡፡ ይህ አኃዝ በአሁኑ ወቅት ከዚህም በላይ እየጨመረ እንደሚመጣ ይታመናል፡፡ የተጠቀሰው አኃዝ በየዓመቱ የኢኮኖሚዋን 2.2 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ሲገለጽ፣ የዓለም ባንክና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተለያየ ወቅት በተጭበረበሩ የንግድ ሥራዎች፣ ስምምነቶችና ሰነዶች በተለይም ገቢና ወጪን በማዛባት (ወጪን በማናርና ገቢን በማሳነስ) የሚፈጸሙ የንግድ ወንጀሎች እየተበራከቱ እንደመጡ በተለያየ ጊዜ ያወጧቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን የዳሰሰው የኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት የኢትዮጵያ ጉባዔ በሌሎች ሦስት አገሮች ውስጥ ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያ አራተኛውን ጉባዔ ያስተናገደች ሲሆን፣ በዝግጅቱም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢኮኖሚስት መጽሔት ጋር በመተባበር ዝግጅቱን እንዳሰናዱት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ የተከሰተው የሰሞኑ ቀውስና የባለሥልጣናቱ ግድያን ተከትሎም የተዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት ተፅዕኖ ያሳደረበት ጉባዔ ቢስተናገድም፣ ከሚጠበቀው ያላነሰ ተሳታፊ መገኘቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ጉባዔውን ስኬታማ እንደሚያሰኘው ጉባዔውን የመሩትና በኢኮኖሚስት መጽሔት፣ የእስያ ማኔጂንግ ኤዲተርና በመጽሔቱ ዓለም አቀፍ የንግድና የግሎባሊዜሽን ኤዲቶሪያል ዘርፍ ኃላፊ ክሪስቶፈር ክሌግ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች