Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበርን ካፒታል ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ተወሰነ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኩባንያው በ2.2 ቢሊዮን ብር አዲስ ሕንፃ ይገነባል

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ባለአክሲዮኖች የኩባንያቸውን ካፒታል በእጥፍ ለማሳደግ በቀረበላቸው የውሳኔ ሐሳብ ላይ በመምከር በአንድ ዓመት ውስጥ  የተከፈለ ካፒታሉን በእጥፍ በማሳደግ 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ወሰኑ፡፡ ኩባንያው የሚያስገነባው ሕንፃ 2.2 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል፡፡

ኩባንያው ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው፣ ኩባንያው አሁን ባለበት ደረጃ ካፒታሉን ከ250 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ማሳደግ ግድ የሚለው በመሆኑ፣ ካፒታል የማሳደጉ ጥያቄ ለባአክሲዮኖቹ ሊቀርብ ችሏል፡፡

የ2011 የሒሳብ ዓመት ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንት ሲቀረው በተጠራው ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከዚህ ቀደም የተፈረመ የኩባንያው ካፒታል ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ በመጠናቀቁና ቀደም ሲል ከባለአክሲዮኖች በኩል የኩባንያው ካፒታል እንዲያድግ በተደጋጋሚ ሲቀርብ ለቆየው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳቡን ማቅረቡ እንደ ምክንያት ተገልጿል፡፡

ለኢንቨስትመንትና ለመሰል ሥራዎች የካፒታሉ ማደግ አስፈላጊነት በተለይ የኩባንያውን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በቶሎ ገንብቶ ለማጠናቀቅ የኩባንያውን ካፒታል ማሳደግ ወሳኝ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ማብራሪያ በዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አበራ በቀለ (ኢንጂነር) እና ሌሎች የቦርድ አባላት ቀርቧል፡፡

በዚህ መሠረት ካፒታሉን በ250 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጥሬ ገንዘብ የሚከፈሉ አዳዲስ አክሲዮኖችን በማውጣት የኩባንያው ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን በቀረበው ጥያቄ መሠረት የውሳኔ ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ይህ የዳይሬክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳብ ግን በባለአክሲዮኖች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦበታል፡፡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች የኩባንያውን ካፒታል ማሳደጉ ተገቢ ቢሆንም፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ያስቸግራል የሚል ጥያቄ አጉልተዋል፡፡

‹‹ዛሬ ላይ ያለውን የኩባንያውን ካፒታል 250 ሚሊዮን ብር ለማድረስ አሥር ዓመታት ፈጅቷል፤›› ያሉ አንድ ባለአክሲዮን፣ ይህን ያህል ተጨማሪ ካፒታል በአንድ ዓመት ውስጥ ለማሳደግ አያስቸግርም ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ይህንን ካፒታል ለማፅደቅ እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ ያስረዱት የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ አባል አቶ አቢ ሳኖ፣ በተለይ ኩባንያው ለማስገንባት ያቀደው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ  ዕውን ሊሆን የሚችለው፣ በተጠየቀው መሠረት ካፒታሉን በእጥፍ ማሳደግ ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ያለን አማራጭ ሁለት ብቻ ነው፡፡ አንዱ ካፒታሉን አሳድጎ ግንባታውን ማስቀጠል ወይም የግንባታውን እንቅስቃሴ ማቋረጥ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ከዚሁ ውሳኔ ሐሳብ ጎን ለጎን በአክሲዮን ሽያጭ ዙሪያ ቦርዱ ሥልጣን እንዲሰጠው ጉባዔው ወስኗል፡፡

በንግድ ሕጉ መሠረት ሥልጣን በመስጠት፣ ካፒታሉን በእጥፍ ከማሳደግ ጎን ለጎን የአክሲዮን ሽያጭን በተመለከተ የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም፣ አዲስ አክሲዮኖቹ የሚሸጡበትንና የአክሲዮኖቹ ዋጋ የሚከፈልበትን የጊዜ ሰሌዳ እንዲወሰን፣ ቦርዱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ባለአክሲዮኑ የሚጠበቅበትን ክፍያ ሳይፈጽም ቢቀር የአክሲዮን ድርሻው ለሌላ ነባር ወይም አዲስ ባለአክሲዮን እንዲተላለፍ በሕግ አግባብ መወሰን እንዲችል  ጉባዔው ሙሉ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡  

ኩባንያው በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በተረከበው መሬት ላይ ለሚያስገነባው ባለ 35 ወለል ሕንፃ ግንባታ የተቋራጭ መረጣ ያካሄደ ሲሆን፣ ግንባታውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሕንፃው፣ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ የመድን ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 878 ባለአክሲዮኖችን በአባልነት አካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች