Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለት ዓመታት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ዝግጅት መጀመሩ ተሰማ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለስድስት ዓመታት የተቋረጠው የድርድር ሒደት ዳግም ተጀምሯል

ከ15 ዓመታት በላይ ሲጓተት የቆየው የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሒደት እንደ አዲስ ተጀምሮ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መጀመሩ ተሰማ፡፡ ኢትዮጵያ የሸቀጦች የቀረጥ ጣሪያን ጨምሮ በአራት መስኮች የመደራደሪያ ሰነዶች ላይ ዝግጅት ጀምሯለች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪና ኢትዮጵያን በዋና ተደራዳሪነት ለመወከል የተሰየሙት አቶ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱ፣ አሥር አባላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ እንደ አዲስ ተዋቅሮ ሥራውን በይፋ መጀመሩንና የመጀመርያውን ስብሰባ ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ማካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከፕላንና ልማት ኮሚሽን፣ እንዲሁም ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ ሥራውን መጀመሩን ያስታወቁት አቶ ማሞ፣ ለስድስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ድርድር ለማስጀመር ቴክኒካዊ ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም አስረድተዋል፡፡

አቶ ማሞ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ሦስት የድርድር ምዕራፎች ወቅት የፖሊሲና የቴክኒክ ሰነዶች ለዓለም ንግድ ድርጅት ተደራዳሪዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ድርድር ከስድስት ዓመታት በፊት ተካሂዶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ የተጀመረው የድርድር ሒደት በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ፣ በመንግሥት ካቢኔ በኩል ውሳኔ እንደተላለፈ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን በተመለከተ አቶ ማሞ በግልጽ አልተናገሩም፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴውም የመክፈቻ ንግግራቸውን ካደመጠ በኋላ በዝግ ተወያይቷል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማሞ ሲሆኑ፣ ምክትላቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አረጋ (አምባሳደር) ናቸው፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴው ስብሰባ በዕቃዎች የቀረጥ ጣሪያ ወይም ‹‹ጉድስ ኦፈር››፣ ለውድድር ክፍት በሚደረጉ የአገልግሎት መስኮች ወይም ‹‹ሰርቪስ ኦፈር›› ላይ ተወያይቶ ማፅደቅ ሲሆን፣ በተለይም በሸቀጦች የታሪፍ ጣሪያ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አቶ ማሞ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም አራተኛው የድርድር ሒደት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር፣ ለዚህም የድርድር ሰነዶችና የአገሪቱን የንግድና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ከዓለም ንግድ ድርጅት ሕግጋትና አሠራሮች ጋር የማጣጣም ሥራዎች መከናወን መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአራት መስኮች ማለትም በንግድና በአገልግሎት መስክ ከምትደራደርባቸው በተጨማሪ፣ በአዕምሯዊ ንብረቶችና በሌሎችም የንግድ መስኮች ላይ የድርድር ሒደቶችን እንደምትጀምር ይጠበቃል፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ዩኒት ስብሰባ ላይ የተገኙት የዓለም ንግድ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ዮኖቭ ፍሬድሪክ አጋህ (ዶ/ር)፣ ስለአባልነት ሒደቱ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያ በትክክለኛው መንገድ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት ሰነዶችን ለድርጅቱ ማስገባቷን ገልጸው፣ ድጋፍ በጠየቀች ጊዜም የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት ፈተና የአገሪቱን ሕጎችና ፖሊሲዎች ከዓለም ንግድ ድርጅት ሕግጋት፣ የንግድና የኢኮኖሚ መርሆዎች ጋር ማጣጣም ላይ እንደሚሆንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በአሁኑ ወቅት የዓለም ንግድ ድርጅት ታዛቢ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድርጅቱ ሲመሠረት በአባልነት እንድትካተት የቀረበላትን ጥያቄ ወደ ጎን ማለቷን የሚያስታወሱ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የሚደረገው ጉዞ ውስብስና ፈታኝ እየሆነ መምጣቱ ቢታይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኃያላኑ አገሮች መካከል እየተካረረ ያለውና በታሪፍ ላይ የተመሠረተው የዓለም የንግድ ጦርነት የዓለም ንግድ ድርጅትን ሚና እየተፈታተነው እንደሆነ የመስኩ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች