Tuesday, March 28, 2023

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ተግዳሮቶችና መፃኢ ዕድሎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ከምዕራባዊያን አገሮች ፈልቀው በመላው ዓለም የተዳረሱት የዴሞክራሲ ሥርዓት መርሆዎችና ሥነ ሥርዓቶች በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ባህል ውስጥ ተስማሚና ትክክል ሆነው መቆም የሚችሉ፣ በውጤታቸውም የየትኛውንም ማኅበረሰብ ሕይወትና አኗኗር በማሻሻል ከፍ የሚያደርጉ አይደሉም፤›› በሚል እምነታቸው የሚታወቁትና አመዛኙን ዘመናቸውንም ይኼንን እምነታቸው በተግባር ጭምር በማሳየት የሚታወቁት፣ የምሥራቅ እስያዋን ሲንጋፖር ለረዥም ዓመታት አስተዳድረው እ.ኤ.አ. በ2015 ያለፉት የቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን ናቸው፡፡

ከምዕራባዊያን የፈለቀው ዴሞክራሲ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ማኅበረሰቦች ጋር ፈጽሞ የሚጣጣሙ እንዳልሆነ በስፋት በመናገር የሚታወቁት የቀድሞው የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን፣ የማኅበረሰብን ሕይወት ጥያቄዎች በመመለስ ወደ ብልፅግና ጫፍ ለማድረስ የሚቻለው የማኅበረሰብን ፍላጎት የሚረዳ፣ ለዚህ ፅኑ አቋም ያለውና የሚተጋ መልካም መንግሥት መኖር መሠረታዊ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

የመንግሥት ቀዳሚ መሠረታዊ ኃላፊነትና ተግባር የተረጋጋና ሥነ ሥርዓት ያለው ማኅበረሰብን በመፍጠር፣ የአገሪቱ ነዋሪዎች መሠረታዊ ፍላጎቶች የሆኑትን የምግብ፣ የመጠለያ፣ የሥራ ዕድልና ጤና በመጠበቅ ማገልገል መሆኑን ያምናሉ፡፡

‹‹ዴሞክራሲ ይኼንን (ከላይ የተጠቀሱትን) መፈጸሚያ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ምርጫ የሌለበት መንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት ወደ መጨረሻው የማኅበራዊ ሕይወት ልዕልና ለማድረስ ተስማሚ ከሆነ፣ እኔ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባላንጣ ነኝ፡፡ ይኼንን ሥነ ሥርዓት በመጥላትና ሌላውን ተስማሚ በመምረጥ ረገድ የሞራል ጥያቄም ሆነ ወቀሳ ሊነሳ አይገባም፤›› ሲሉ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1959 ጀምሮ እስከ 1992 ድረስ ሲንጋፖርን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩትም በዚህ መርሐቸው ሲሆን፣ በአመራር ዘመናቸውም መንግሥትን የመቃወምምና የመናገር ነፃነትን በሕግ የከለከሉ፣ በሲንጋፖር የአንድ ፓርቲ መንግሥትን ለዘመናት በማስረፅ የገዙ ብቻ ሳይሆን፣ ማስቲካ ማኘክን በሲንጋፖር  የከለከሉ፣ ማኅበራዊ እሴቶችንና ሥነ ሥርዓቶችን በጣሱት ላይም አካላዊ ቅጣት የሚቀጡ መሪ ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ መንገዳቸው ሲንጋፖርን ከድህነት አረንቋ በማውጣት፣ አሁን በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ኢኮኖሚ ከገነቡት ተርታ እንድትሠለፍ አድርገዋል፡፡ ሊ ኩዋን ወደ ሥልጣን በመጡበት እ.ኤ.አ. በ1959 የነበረው የሲንጋፖራዊያን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 400 ዶላር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የሲንጋፖራዊያን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 60 ሺሕ ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይህ የሲንጋፖር የቀድሞ መሪ ፍልስፍና በአካባቢው በሚገኙ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ላይ ብቻ አልነበረም ተፅዕኖውን ያሳደረው፡፡ ተፅዕኖው ካረፈባቸው አገሮች መካከል የምሥራቅ አፍሪካዋ ኢትዮጵያም ትገኝበታለች፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዚህ ፍልስፍና ተፅዕኖ ሥር ወድቀው፣ በ1990ዎቹ አጋማሽ መግቢያ ኢትዮጵያን አስተዳድረውበታል፡፡

አቶ መለስ ይኼንን መርህ ወደ ኢትዮጵያ ሲያመጡ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲጣጣምና የዴሞክራሲ ዘውግ የፍልስፍናው አካል እንዲሆን ለማድረግ፣ ‹‹የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት›› መርህን ተከትለዋል፡፡ ይህ የአመራር ፍልስፍና በኢትዮጵያ በተተገበረባቸው ዓመታት ኢኮኖሚው ከፍተኛ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ ሲገለጽ፣ ይኼንን የአመራር ፍልስፍና የማይቀበሉት የምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ያጠላባቸው እንደ የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ያሉት ተቋማት ጭምር በይፋ አረጋግጠዋል፡፡

ነገር ግን አቶ መለስ በተከተሉት የአመራር ፍልስፍና ከሲንጋፖር የተለየ ያደርገዋል የተባለው የዴሞክራሲ ዘውግ ሙሉ በሙሉ ወደፊት ባለመውረዱ አልያም ከማኅበረሰቡ ፍላጎት (Expectation) ጋር መጣጣም ባለመቻሉ የተፈጠረ ሕዝባዊ ንቅናቄ ተቀጣጥሎ፣ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወር በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ በትግል ውጤት የተጠናቀቀ የአመራር ለውጥ አስከትሏል፡፡

የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ማዕበል (PDC) ዴሞክራሲ በመላው ዓለም እንዲስፋፋ የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ከተቋቋመው ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ (ኔድ) ከተባለው የፋይናንስ ድጋፉን ከአሜሪካ ኮንግረንስ ከሚያገኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም ጋር በመተባበር፣ ከሰኔ 12 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት ባካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጉዞ›› የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኔድ ሊቀመንበር፣ በሩቅ ምሥራቋ አገር ሲንጋፖር የቀድሞ መሪም ሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ የተከተሉትን የአመራር ፍልስፍና በመቃረን አስተያየታቸውን ለውይይት መድረኩ አጋርተዋል፡፡

የኔድ ሊቀመንበር ካርል ግረሽማን በሁለቱ መሪዎች የአመራር ፍልስፍና ላይ የተቃርኖ አስተያየታቸውን ለማቅረብ መንደርደሪያ ያደረጉት፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ ሐሳብ የማያራምደውን ህንዳዊ ኢኮኖሚስትና ተመራማሪ አማርተያ ሴን ለዓለም ማኅበረሰብ ያቀረበውን ሙግት ነበር፡፡ የሲንጋፖሩ መሪ ሊ ኩዋን የዴሞክራሲ መርሆዎች ለሁሉም የዓለም ማኅበረሰብ ተስማሚ እንዳልሆኑና በየትኛው ቦታና አካባቢ ውስጥ የሚሠሩ አይደሉም ማለታቸው ስህተት እንደሆነ የሚናገረው ህንዳዊው ምሁር፣ ‹‹የዴሞክራሲ መርሆዎች ለአንዱ ማኅበረሰብ ባህልና ነባራዊ ሁኔታዎች ተስማሚ፣ ለሌላው ግን ተስማሚ ላይሆኑ ይችላሉ ለማለት አይቻልም፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት አንድ አገርና ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ አልፎ ከመርሆዎቹ ጋር ተስማምቶ ይቆማል ነው፤›› ማለታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

ይኼንንም ሲያብራሩ አንዳንድ ሕዝቦችና ባህሎች ለዴሞክራሲ ተስማሚ መሆን ሳይችሉ ቀርተው ሳይሆን፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ አልፈው ከዴሞክራሲ መርሆዎች ጋር ተለማምደውና ተስማምተው እንዲቆሙ ያልተፈቀደላቸው የመሆናቸው ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ማኅበረሰቦችም ሆነ ግለሰቦች ነፃነታቸውን ሲያጡ ነፃነትን እንደሚናፍቁ የተናገሩት የኔድ ሊቀመንበር ሚስተር ካርል፣ ኢትዮጵያውያንም በርካታ ዓመታትን በዚህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥማት ውስጥ ከፊውዳላዊው የመንግሥት ሥርዓት አንስቶ በአምባገነኑ ደርግ ተጨቁነው፣ የቀይ ሽብርን ሰቆቃና የመለስ ዜናዊን ጨቋኝ ልማታዊ መንግሥት አልፈው ዛሬ የዴሞክራሲ አማራጭ እየፈለጉ እንደሚገኙ አውስተዋል፡፡

የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ተግዳሮቶችና ዕድሎች

በመድረኩ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ ዴሞክራሲ ትላንት፣ ዛሬና ወደፊት በኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ ምን እንደ ገጠመው፣ መፃኢ ዕድሎቹ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉና እንደሚገባ ለመመልከት ተሞክሯል፡፡

በውይይቱ ላይ በፓናሊስትነት (የመወያያ ሐሳብ አቅራቢነት) የተገኙት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሚኒስትር ዴኤታ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ መንግሥትን በመወከል የቀረቡ ነበሩ፡፡

እሳቸው የውይይት ሐሳባቸውን የጀመሩት ዴሞክራሲን እንዴት እንደሚገነዘቡት በመግለጽ ነበር፡፡ ዴሞክራሲ ማለት በአንድ ማኅበረሰብ ወይም ቡድን ውስጥና በመንግሥታዊ ሥርዓት በየፊናቸውና በተናጠል፣ እንዲሁም በሚጋሩዋቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ የሚያሳልፉበት መንገድ ወይም የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት አድርገው እንደሚገነዘቡት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ጉዞ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጀመረ እንዳልሆነ የጠቀሱት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የነበረው የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደት፣ የዘውዳዊው ሥርዓት በ1960ዎቹ አጋማሽ አብዮቱ እንዲያበቃ የተደረገበት፣ እንዲሁም ኢሕአዴግ የመጣበት መንገድ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ትውልዶች ያሳረፉት አሻራ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በዚህ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ጉዞ ውስጥ የነበረው የትውልዶች ቅብብሎሽ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የተሄደበት መንገድ፣ ጎዶሎዎች እንደነበሩትና ከዚህም መማር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የዴሞክራሲ ፍለጋ ጉዞ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ጎዶሎ ‹‹አንድ ችግር አለ የማለት ችግር›› እንደሆነ የራሳቸውን ምልከታ አካፍለዋል፡፡

ይህ ችግር አንድ ችግር አለ ተብሎ አንድ ችግር ላይ ብቻ የማተኮር እንደሆነ፣ ሌላውን ችግር ማኅበረሰቡም ሆነ ልሂቃኑ እንዳያስተውሉ የከለለና የሚከልል፣ በሁሉም ትውልዶች ጥረት ውስጥ የተስተዋለ ጉድለት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሌላው ጉድለት ደግሞ የመርህ ሚዛንን ያለመጠበቅ እንደሆነ አክለዋል፡፡ ይኸውም አንድ ችግር አለ ተብሎ ተለይቶ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት አዋጭ የሆነው መንገድ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ መፍትሔውን ፍለጋ ሁሉም በየፊናው ስምምነት ከተደረገበት መንገድ ወጥቶ የመሄድ ችግር በትውልዶች የዴሞክራሲ ጉዞ ውስጥ የተስተዋለ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ሌላው የውይይት ሐሳብ አቅራቢ የነበሩት የመብት ተሟጋችና የሕግ ባለሙያው አቶ ቁምላቸው ዳኜ ናቸው፡፡

በእሳቸው ዕይታ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ጉዞ በፖለቲካ ቁርጠኝነት ብቻ የሚመጣ አለመሆኑን፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ መሠረታዊ ችግር ደግሞ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል አለመኖር ነው፡፡

አንደኛው ሥልጣን ለመያዝ ሌላኛውን የማጥፋት ባህል ላይ የተመሠረተ ጉዞ በትውልዶች ውስጥ ጎልቶ የሚታይ፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግም የዚሁ ባህል ወራሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደዚህ መጠፋፋት የሚከተው ሌላው ተያያዥ ችግር የፖለቲካ ሥልጣንን እንደ ርስት የሙጥኝ ማለትና ለማስተላለፍ ያለመፈለግ አባዜ መሆኑንም አቶ ቁምላቸው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ጉዞ ታሪክ ላይ የተለየ አስተያየት የሰጡት የሰብዓዊ መብት ተከላካይና የሕግ ባለሙያው አቶ አምሐ መኰንን ናቸው፡፡

ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም ኢትዮጵያ ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲ መንገድ የገባችው ከአንድ ዓመት በፊት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ጥረት ላይ ነች ሲባል ወይም የተለየና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች አሉ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ በትክክል ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ያሸጋግራታል? የሚለው ሌላው በመድረኩ ውይይት የተደረገበት ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡

ይኼንን በተመለከተ የመንግሥታቸውን አቋም ያንፀባረቁት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር የሚደረጉ ሙከራዎች ምን እንደሆኑና ምን እንደሚሉ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል አንዱ መንግሥት አፋኝ ሕጎችን ለማሻሻል እያደረገ ያለው ጥረት አንዱ ነው፡፡

መንግሥት የፀረ ሽብር ሕጉን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ አጠናቆ ለሕግ አውጪው እንዳቀረበ የተናገሩት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ መንግሥት ይኼንን ሕግና መሰል ሕጎኝን ሲያሻሽል ሕጎች የነፃነትና የደኅንነት ሚዛንን የጠበቁ መሆን እንዳለባቸው እየተናገረና ይህም አቋሙ እንደሆነ እያሳወቀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅን ሲያሻሽል ሥልጣን በቀደመው መንገድ አይያዝም፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት መከበር አለበት ማለቱ እንደሆነ፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን ለማሻሻል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰና ይኼንን ሲያደርግም መንግሥት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን አስከብራለሁ እያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ኢትዮጵያን ለማሸጋገር የሪፎርም (የለውጥ) ዕርምጃዎችን እያደረገ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብቻውን የተባለውን ውጤት እንደማያመጣ፣ ለዴሞክራሲ ሽግግር ወሳኝ የሆኑ አላባዊያን በሙሉ በአንድ ዓይነት ጉልበትና ንቃት፣ እንዲሁም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ካላደረጉ ድካም ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ለውጡን እየመሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና ቡድናቸው በመንግሥትና በፓርቲ መካከል የነበረውን መደበላለቅ መለየታቸው፣ በኢሕአደግ ውስጥ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑን አቶ ቁምላቸው አውስተዋል፡፡

በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎች መካከል ፍጥጫ ማየሉን፣ ይህ ፍጥጫና ቅራኔ ካልተፈታና የአገሪቱ ልሂቃንም ወደሚያስማማቸው አንድ ማዕከል ለመምጣት ድርድር ካላደረጉ ሽግግሩ የትም ሊደርስ ይችላል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተጀመረው ሪፎርም ሽታ የሚያውደው የፌዴራል መንግሥት አካባቢ እንጂ፣ ወደ ጎን መስፋትና በክልል ደረጃ መታየት አለመጀመሩ ሌላው ሥጋታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል ሊገነባ የሚችለው በመንግሥት ሳይሆን በሲቪል ማኅበረሰቡ የተግባር ተሳትፎ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ሲቪል ማኅበራት ቀድሞ በደረሰባቸው አፈና ምክንያት ከተኙበት እንቅልፍ አለመንቃታቸው የዴሞክራሲ መሠረቱን ጎደሎ እንዳደረገው ገልጸው፣ ይህም ሥጋታቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሚዲያው በተለየ ሁኔታ ተነቃቅቶ ቢታይም ድሮውንም በብቃት ላይ የተመሠረተ ዘርፍ ባለመሆኑ፣ አሁን በፅንፈኞች ቁጥጥር ሥር መውደቁና ወገንተኛ መሆኑ ሌላው የለውጥ ሒደቱ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -