Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፀረ ሙስና ኮሚሽን ባንኮች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን መረጃ እንዲሰጡት ጠየቀ

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባንኮች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን መረጃ እንዲሰጡት ጠየቀ

ቀን:

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በመንግሥት በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ሲያገለግሉ የነበሩና በማገልገል ላይ ያሉ 78 ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው፣ በባንኮች ያላቸውን የገንዘብ መጠንና የአክሲዮን ድርሻም ካላቸው ተጣርቶ በአምስት የሥራ ቀናት እንዲቀርብለት ባንኮችን መረጃ ጠየቀ፡፡

ኮሚሽኑ በተለይ ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ለሁሉም ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ፣ በባንኮቹ ውስጥ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦችና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም የተገዙ የአክሲዮን ድርሻዎች ስለመኖራቸው ተጣርቶ እንዲቀርብለት ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 688/2002 መሠረት በማድረግ መረጃው እንዲሰጠው በጠየቀበት ደብዳቤ በአዋጁ መሠረት የመንግሥት ተሿሚዎች፣ የሕዝብ ተመራጮችና ምዝገባው የሚመለከታቸው የመንግሥት ሠራተኞችንና የሥራ ኃላፊዎችን ሀብት እንደሚመዘግብ፣ የተመዘገበን የሀብት ምዝገባ መረጃ እንደሚያረጋግጥ በሕግ ስለመደንገጉ በማስታወስ ነው፡፡

ኮሚሽኑ መረጃዎቻቸውን በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ እንደሚፈልግ ከጠቀሳቸው የቀድሞ ባለሥልጣናት መካከል የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳና ቤተሰቦቻቸው ተካትዋል፡፡ የቀድሞ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ሳልኬ፣ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀና የቀድሞ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ከእነ ቤተሰቦቻቸው ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ አቶ ተፈራ ደርበው፣ አቶ ሽፈራው ጃርሶ (አምባሳደር)፣ ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በስም ዝርዝሩ ውስጥ ከእነ ቤተሰቦቻቸው ተካተዋል፡፡ የቀድሞ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ፣ የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ በርሄ፣ የቀድሞ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉና ቤተሰቦቻቸው አሉበት፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት አቶ ድሪባ ኩማ፣ የፕላን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ መኮንን ማንያዘዋል ከእነ ቤተሰባቸው ተካተዋል፡፡

በሥራ ላይ ካሉት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) እና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከእነ ቤተሰቦቻቸው ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ስማቸው የተጠቀሱት የቀድሞና አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ሹማምንት መረጃ የተጠየቀባቸው፣ በባለቤቶቻቸውና በልጆቻቸው ስም ያለ በባንክ የተቀመጠ ገንዘብና የአክሲዮን ድርሻ ካለ ይህንኑ ከዝርዝር መረጃ ጋር እንዲቀርብ በኮሚሽኑ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ኮሚሽኑ እንዲህ ያሉ የመንግሥት ሹማምንትና ቤተሰቦቻቸውን የባንክ ሒሳብና በባንኮች ውስጥ አክሲዮን ካላቸው ይህንኑ የሚገልጽ መረጃ መጠየቁ አዲስ ባይሆንም፣ በአንዴ በዚህን ያህል መጠን የሹማምንቱንና የቤተሰቦቻቸውን መረጃ መጠየቁ ትንሽ ለየት ያደርገዋል፡፡

የመረጃ አሰባሰቡ ባለሥልጣናቱና ቤተሰቦቻቸው በኮሚሽኑ ካስመዘገቡት ሀብት መጠን ጋር ለማመሳከር እንደሆነ ቢነገርም፣ ከኮሚሽኑ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች በሥልጣን ላይ የነበሩ ሹማምንትና የመንግሥት ሠራተኞችም በተመሳሳይ መረጃ እንዲሰበሰብባቸው፣ ተጨማሪ የስም ዝርዝሮች ለባንኮች የደረሳቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...