Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጣሊያን በኢትዮ ኤርትራ የባቡር ፕሮጀክት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት አሳየች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የአዋጭነት ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ አስታወቀ

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኢማኔኤላ ዴል ሪ፣ አገራቸው ኢትዮጵና ኤርትራን በባቡር ትራንስፖርት የሚገናኘውን ፕሮጀክት ለመደገፍ እያሰበች እንደምትገኝ አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያና የጣሊያን የንግድ ፎረም ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደበት ወቅት ምክትል ሚኒስትሯ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዕርቅ መውረዱን ተከትሎ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጣሊያን ትደግፋለች፡፡ በመሆኑም አገራቸው በባቡር ፕሮጀክቱ ልትሳተፍ የምትችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡

ምክትል ሚኒስትሯ ከሌሎች የጣሊያን መንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን 40 ኩባንያዎችን ይዘው በአዲስ አበባ ቆይታ አድርገዋል፡፡ የኢትዮ ጣሊያን የንግድ ፎረም በማካሄድም፣ የጣሊያን ባለሀብቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተወያዩበት ወቅት ፎረሙን መርተዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች የንግድ ፎረም ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የባቡር ትራንስፖርት ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ፕሮጀክት መነደፉን አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ሰሜናዊ፣ ምሥራቃዊና ማዕከላዊ ክፍሎች ከአሰብና ከምፅዋ ወደቦች ላይ ለማገናኘት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ የአዋጭነት ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝና የዓለም ባንክም ድጋፍ እንደሚያደርግበት ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ስለሚያፈልገው የገንዘብ መጠን ሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ከአዋጭነት ጥናቱ በኋላ እንደሚታወቅ ገልጸዋል፡፡

በጣሊያንና በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከል በቅርቡ በተካሄደ ውይይት፣ ጣሊያን ለኢትዮጵያ 140 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኗን አቶ አህመድ አስታውሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ጣሊያን አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአክሱም ጥንታዊ ሐውልቶች ህልውና ለመታደግ ድጋፍ ስለምታደርግበት አግባብ የገለጹት ምክትል ሚኒስትሯ ኢማኔኤላ፣ ሐውልቶቹን በመጎብኘት ስለሚገኙበት ሁኔታና ጣሊያን ድጋፍ ማድረግ ስለምትችልበት አግባብ ምልከታ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ 

በንግድ ፎረሙ ማጠቃለያ ላይ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ እንዲሁም የኤርትራ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ኃላፊና ፕሬዚዳንታዊ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በመሆን የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን አነጋግረዋል፡፡ የሦስቱን አገሮች ውይይት በተመለከተ ሪፖርተር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ጠይቆ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ነገሩ በአጋጣሚ እንጂ ታስቦበት አይደለም፤›› በማለት፣ ከኤርትራ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው ቀድሞ ታስቦበት የተደረገ ውይይት እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ ባለሥልጣናት በአዲስ አበባ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ስብሰባ ለመታደምና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን ለማነጋገር መምጣታቸው ታውቋል፡፡  

በንግድ ፎረሙ ወቅት ማብራሪያ የሰጡት አቶ አህመድ ሺዴ፣ ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ በተለይም በመንገድ፣ በባቡርና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያገናኙ ግንባታዎችን ማካሄዷን አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ከጂቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሌሎችም ጋር ግንኙነት መመሥረቷን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በመንግሥት እየተካሄዱ ስለሚገኙ የፕራይቬታይዜሽንና የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራዎችን በተመለከተም አቶ አህመድ ለጣሊያን የንግድ ልዑካን አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድንና የሎጂስቲክስ ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዛወር ዕርምጃን፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ የስኳርና የኢነርጂ ኩባንያዎችን ወደ ግል የማዛወር እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በአንፃሩ አንጋፋና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመምጣት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶችም ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ የታክስ ማሻሻያና ካገለገሉ ተሽከርካሪዎች የሚወጣውን ብክለት የሚቀንስ አሠራር ይተግበር የሚሉትን ጨምሮ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተቸገሩ የሚገኙ ኩባንያዎችም ጥያቄቸውን ለአቶ አህመድ አቅርበዋል፡፡ በተለይም በፊያት ኩባንያና በኢትዮጵያ መንግሥት ሽርክና መሠረት የ70 በመቶና የ30 በመቶ ድርሻ የተመሠረተው አምቼ ፋብሪካ፣ ለሚገጣጥማቸው ተሽከርካሪዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና እንደሆነበት አስታውቋል፡፡ አቶ አህመድ በበኩላቸው ኩባንያው የመንግሥት ባለቤትነት ድርሻ ያለበት እንደ መሆኑ ችግሩን ከኩባንያው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ዕልባት እንደሚሰጡበት በማስታወቅ፣ የኩባንያው ኃላፊዎችን ቢሯቸው እንደሚያነጋግሯቸው ገልጸውላቸዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ከ590 ሚሊዮን ዩሮ ያላነሰ ካፒታል ኢንቨስት ያደረጉ ነባርና አዳዲስ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ ያሉት፣

የጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት ካርሎ ፌሮ ናቸው፡፡ የንግድ ፎረሙ ለጣሊያን ኩባንያዎች ውጤታማ እንደነበር ለሪፖርተር የገለጹት ሚስተር ፌሮ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግም ሆነ የጣሊያን ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ ለማቅረብ የሚቻልባቸው ሰፊ ዕድሎች እንዳሉ መገንዘባቸውንና ይህም ለጣሊያን ኩባንያዎች መልካም ዕድል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች