Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ አገር የጭነት ተሽከርካሪዎች ኢትዮጵያ ጭነት ይዘው መግባትና መውጣት የሚያስችላቸው አሠራር ሊፈቀድ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ተሽከርካሪ ለጉብኝት ከአገር መውጣት እንዲችሉ ሊፈቀድ ነው

የውጭ ጎብኚዎችም በተሽከርካሪዎቻቸው ኢትዮጵያ መግባት ሊፈቀድላቸው ነው

የውጭ አገር የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ጭነት ይዘው እንዲገቡ በሕግ ሊፈቀድ ነው፡፡ ጭነታቸውን ካራገፉ በኋላ በልዩ ሁኔታ ተፈቅዶ ለመቆየት ካልሆነ በስተቀር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደማይፈቀድላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የትራንስፖርት ወይም የሎጅስቲክስ አገልግሎት ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀደና ጥበቃ የሚደረግለት ዘርፍ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ክልከላ በተወሰነ ደረጃ ለማላላትና ለመፍቀድ፣ በሥራ ላይ የሚገኘውን የጉምሩክ አዋጅ ለማሻሻል ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል።

የውጭ አገር የንግድ ማጓጓዣ ወደ አገር ውስጥ በጊዜያዊነት ሊገባ የሚችለው፣ ማጓጓዣው በተመዘገበበት አገርና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት ወይም የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሲፈቅድ ብቻ እንደሚሆን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አመልክተዋል፡፡

በዚህ ፈቃድ መሠረት ወደ አገር ውስጥ የገባ የውጭ አገር የንግድ ማጓጓዣ በአገር ውስጥ ጭነትና በወጪ ዕቃ ትራንስፖርት አገልግሎት መሰማራት እንደማይችል የገለጹት ምንጮች፣ በልዩ ሁኔታ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አገር ውስጥ የገባ የውጭ አገር የንግድ ማጓጓዣ ሕጋዊ የወጪ ዕቃ ጭኖ ከአገር እንዲወጣ ሊፈቅድ እንደሚችል፣ ይህም በጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የሚካተት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

 በጊዜያዊነት ወደ አገር ውስጥ የገባ የውጭ አገር የንግድ መጓጓዣ በተወሰነለት ጊዜ ተመልሶ ከአገር ያልወጣ እንደሆነ፣ ወይም በአገር ውስጥ ጭነትና በወጪ ዕቃ ትራንስፖርት አገልግሎት ተሰማርቶ የተገኘ እንደሆነ አስተዳደራዊ ቅጣት ተፈጽሞበት ከአገር እንዲወጣ የሚደረግበት የቁጥጥር አሠራር እንደሚበጅ ታውቋል።

በሌላ በኩል በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የአገር ውስጥ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በጭነት ተሽከርካዎች ላይ ጠቋሚ መሣሪያው (ካርጎ ትራኪንግ) ላይ እንዲገጥሙ የሚደነግግ ቢሆንም፣ ድንጋጌው አስገዳጅ ባለመሆኑና ወጪ ለማውጣት ባለመፈለግ ምክንያት አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻሉን ምንጮች ገልጸዋል።

 ይህንን ችግር ለማስቀረትና የመከታተያ መሣሪያው በሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ላይ የሚያበረክተውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በመገንዘብ፣ የማጓጓዣ ባለንብረቶች መሣሪያውን ገዝተው እንዲገጥሙ የሚያስገድድ ድንጋጌ ማሻሻያነት እንዲገባ የሚደረግ መሆኑንና መሣሪያውን ያልገጠመ የመጓጓዣ ባለንብረት የወጪና ገቢ ዕቃ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጥ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በሥራ ላይ ያለው የጉምሩክ አዋጅ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ይዘዋቸው ለሚገቡ ንብረቶች ዋስትና እንዲያስይዙ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ቱሪስቶችን ደግሞ ዋስትና እንዲያስይዙ ማስገደድ ያልተለመደና የአገሪቱን የቱሪዝም መርህ ሊጎዳ የሚችል እንደሆነ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቱሪስቶች ተሽከርካሪን ጨምሮ በጊዜያዊነት ለሚያስገቡት ዕቃ ዋስትና ሳያቀርቡ እንዲያስገቡ የሚያስችል ማሻሻያ እንደሚደረግ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

 በዚህ መሠረት ተሽከርካሪም ሆነ ሌሎች ንብረቶችን ይዞ የገባ ቱሪስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ ያገኘ እንደሆነ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባው ዕቃ የመኖሪያ ፈቃድ በተገኘበት ቀን ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ተቆጥሮ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት በመፈጸም፣ ቀረጥና ታክስ ከፍሎ ዕቃው አገር ውስጥ እንዲቀር የሚፈቀድበት ሕጋዊ አሠራር በማሻሻያው እንደሚካተተም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በውጭ አገር ፕሮጀክት ያላቸው የኢትዮጵያ ነዋሪዎች፣ ወይም ለጉብኝት ወደ ጎረቤት አገር ወጣ ብለው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን፣ ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ተሽከርካሪን ጨምሮ በጊዜያዊነት ዕቃ ይዘው እንዲወጡ የሚፈቅድ ማሻሻያ የሚደረግ መሆኑንም ምንጮች አመልክተዋል። ሌላው በማሻሻያው ይካተታል ተብሎ የሚጠበቀው በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ ዕገዳ የተደረገበት የቀረጥ ነፃ መብት ጉዳይ ነው። በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የቀረጥ ነፃ መብት እንዲፈቅዱ ለተለያዩ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤትች የሰጠውን ሥልጣን በማሻሻል፣ ይህ ሥልጣን ለንዘብ ሚኒስቴር ብቻ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

 በማሻሻያው እንደሚካተት የሚጠበቀው ሌላው ጉዳይ እየተስፋፋ የመጣውን የጉምሩክ ታክስ ስወራ ለመከላከል የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ለጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም በቀረበ የዕቃ ዲክላራሲዮን ላይ ያልተመዘገበን ዕቃ መግለጫ በቀረበባቸው በሕጋዊ ዕቃዎች ከለላነት ወደ አገር የማስገባት ድርጊትን ለመከላከል የሚያስችለው ማሻሻያ ተጠቃሽ ነው።

 በሚደረገው የሕግ ማሻሻያ ውስጥ ማንኛውም ሰው ትክክለኛ መግለጫ ያልተሰጠበት ዕቃ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት በሕጋዊ ዕቃ ከለላነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ወይም ከአገር እንዲወጣ ያደረገ ወይም የሞከረ እንደሆነ፣ ቀረጥና ታክስ የመክፈል ግዴታው እንደተጠበቀ ሆኖ ሸሽጎ ለማስገባት በተጠቀመበት ዲክላራሲዮን ላይ ለተመዘገቡት ዕቃዎች መከፈል ከሚጠበቅበት ቀረጥና ታክስ ከሃምሳ በመቶ የማይበልጥ ክፍያ እንዲከፍል የሚደረግ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በጉምሩክ አዋጅ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ በዋናነት ንግድን ከማሳለጥ አንፃር የተቀረፀና በመንግሥት ፕሮግራም ውስጥ ቅድሚያ የተሰጠው በመሆኑ፣ ፓርላማው በሰኔ ወር መጨረሻ ለእረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ካልሆነም በመጪው የሥራ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንዲፀድቅ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች