Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የደቡብ ግሎባል ፕሬዚዳንት ባንኩንም ኢንዲስትሪውንም ተሰናበቱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደቡብ ግሎባል ባንክን ለአምስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ አዲሱ ሃባ ኃላፊነታቸውን ለቀቁ፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንትነትም ያስረክባሉ፡፡

አቶ አዲሱ ከደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው በፍላጎታቸው እንደሚለቁ የሚጠይቅ ደብዳቤ ሰኞ፣ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ለባንኩ እንዳስገቡ ታውቋል፡፡ ከባንኩ መልቀቅ የፈለጉት በፈቃዳቸው እንደሆነ ለሪፖርተር የገለጹት አቶ አዲሱ፣ ቀድሞም ባንኩን የተቀላቀሉት ለተወሰነ ጊዜ እንደሚያገለግሉ በመስማማት እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የኃላፊነት ቆይታቸውን እንዳራዘሙና በአሁኑ ወቅት ግን የሚተኳቸው ባለሙያ በመዘጋጀታቸው፣ ከባንኩ የቦርድ አመራሮች ጋር በመግባባት መልቀቂያ እንዳስገቡ አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ግሎባል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የአቶ አዲሱን መልቀቂያ በመቀበል፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በመቆየት ኃላፊነታቸውን ለሚተኳቸው እንዲያስረክቡ ተስማምቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኩን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ የሚገኙት ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) ተጠባባቂ የባንኩ ፕሬዚዳንት በመሆን የአቶ አዲሱን ቦታ እንዲረከቡ ቦርዱ እንደወሰነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአቶ አዲሱ ከፕሬዚዳንትነት የመልቀቃቸው ምክንያቱ፣ ከባንኩ ቦርድ በመጣ ግፊት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ አቶ አዲሱ ግን ቀደም ብሎ በነበረ ስምምነት በመግባባት የተፈጸመ ስንብት እንደሆነ በመግለጽ፣ ግፊት ተደርጎባቸዋል መባላቸውን አስተባብለዋል፡፡

ባንኩን በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የታጩትና ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ አዲሱን ተክተው በፕሬዚዳንትነት የሚሰየሙት ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር)፣ በተጠባባቂነት የሚያገለግሉት በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ሹመታቸው እስኪፀድቅላቸው ድረስ ነው፡፡ ተጠባባቂው ፕሬዚዳንት ደቡብ ግሎባል ባንክን የተቀላቀሉት፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተሹመው እንደነበር ይታወሳል፡፡

አዲሱ ተሿሚ ደቡብ ግሎባል ባንክን ከመቀላቀላቸው በፊት፣ በዘመን ባንክ የዕውቀትና የምርምር ግኝት (ኢኖቬሽን) ሥራ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪው ከ15 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱት ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ከ34 ዓመታት በላይ በኢንዱስትሪ የቆዩትን የአቶ አዲሱን ቦታ ተረክበው ሥራ ለመጀመር ጥቂት ሳምንታት ይጠብቃሉ፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች ዘግይተው ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ ሦስት ባንኮች አንዱ ነው፡፡ ከባንኩ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው በቀደመው የ2010 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 142 ሚሊዮን ብር አትርፎ ነበር፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ ከ2009 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ 252 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የ2011 የሒሳብ ዓመት የዘጠኝ ወራት ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ባንኩ በዘጠኝ ወራት ከታክስ በፊት ከ215 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አዲሱ ከደቡብ ግሎባል ባንክ መልቀቃቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንትነታቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚለቁ ታውቋል፡፡ የባንኮች ማኅበር ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አዲሱ፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት ማኅበሩን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከባንክ ሥራ ውጪ በሆነ የሙያ መስክ ለመሥራት በመፈለጋቸው፣ ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በኋላ የማኅበሩን ኃላፊነትም ለምክትላቸው ያስተላልፋሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ፣ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ፕሬዚዳንቱ ከሌለ ምክትሉ ተክቶ ስለሚሠራ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ ኃላፊነቱን ተረክበው ይሠራሉ፡፡

አቶ አቢ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዳዚንት ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት ከስድስት ወራት በፊት ነበር፡፡ የማኅበሩ ታሪካዊ ዳራ እንደሚያመለክተው የማኅበሩ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት የቀድሞ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ለይኩን ብርሃኑ ናቸው፡፡ በእሳቸው እግር ደግሞ የቀድሞው የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ሲሆኑ፣ አቶ ብርሃኑ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ሲለቁ አቶ አዲሱ ተክተዋቸዋል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ከ34 ዓመታት በላይ ከቆዩበት የባንክ ኢንዱስትሪ ከወጡ በኋላ ቀጣይ ማረፊያቸውን ባይወስኑም በግላቸው ለመሥራት የሚሹ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የ62 ዓመቱ ጎልማሳው አቶ አዲሱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከወጡ በኋላ ሥራ የጀመሩት በቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ነበር፡፡ በዚሁ ባንክ ውስጥ ከጀማሪ የባንክ ባለሙያነት እስከ ፕሬዚንትነት ባሉት መስኮች አገልግለዋል፡፡

ለሁለት ዓመታት በምክትል ፕሬዚዳንት፣ ለስምንት ዓመታት ደግሞ በፕሬዚዳንትነት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን የመሩት አቶ አዲሱ፣ ከባንኩ ከለቀቁ በኋላ ወደ አቢሲኒያ ባንክ በማቅናት ለአምስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መርተውታል፡፡

2011 ዓ.ም. በባንክ ኢንዱስትሪው በተለያዩ ባንኮች ውስጥ አዳዲስ ለውጦች የታዩበት ነበር፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግል ባንኮች የተደረጉ የአመራር ለውጦች ባንኮች አዳዲስ ፕሬዚዳንቶች የተሾሙበት ሆኗል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ አዳዲስ ፕሬዚዳንቶችን ከሾሙት መካከል ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ዘመን ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ወጋገን ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ባንኮች ውስጥ አቢሲኒያ ባንክ፣ ወጋገን ባንክና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አዲሶቹ ፕሬዚዳንቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚዳንት ሲያገለግሉ የነበሩ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲሠሩ የቆዩትና በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ በመሆን ተሹመው የነበሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ የምክትል ገዥነት ሹመት በመተው የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች