Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሁለት ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እንደሚኖረው የሚጠበቅ የ‹‹ስታርት አፕ›› ፈንድ ሊመሠረት ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ‹‹ኤንጅል ኢንቨስተርስ›› ጥምረት ተመሥርቷል

በቅርቡ በብሉሙንና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ትብብር የተካሄደው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ መርሐ ግብር በቋሚነት እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ፣ ለመነሻው እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ተቋም ‹‹ስታርት አፕ ፈንድ›› በሚል ስያሜ እንደሚመሠረት ተሰማ፡፡

የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር)፣ ከሁለት ዓመታት በፊት የመሠረቱት ‹‹ብሉሙን›› የተሰኘው የፈጠራ ሥራ ሐሳብ አመንጪ ወጣቶች ድጋፍ መስጫ ተቋምንም በመምራት ላይ ይኛሉ፡፡ ከዚህ ተቋም ጎን ለጎን የተመሠረተው፣ የጀማሪ ኩባንያዎች ማበልጸጊያ ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› የሚል ስያሜ ያለው ተቋምም በቴክኖሎጂ መስክ በተለይ ክህሎቱና የፈጠራ ሐሳብ ያላቸውን ወጣቶች አቅሙ ካላቸው ባለሀብቶች ጋር በማገናኘት ሐሳቡን ወደ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት መቀየር የሚቻልበትን ዕድል እያመቻቸ ይገኛል፡፡

በዚሁ መሠረትም ከጥቂት ቀናት በፊት ከተካሄደውና ‹‹ኢኖቬት ኢትዮጵያ›› ከተሰኘው ዓውደ ርዕይ ጎን ለጎን፣ 3,000 ታዳሚዎች የተሳተፉበት ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› የተሰኘው መድረክ የተሰናዳው እሌኒ (ዶ/ር) በሚመሩት ተቋም አማካይነት ነበር፡፡ ስታርት አፕ ኢትዮጵያ፣ የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ወጣቶች በገንዘብ ዕጦት ችግር ፈቺ ሐሳቦቻቸው መና እንዳይቀሩና በተግባር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማገዝ የሚያስችል እንቅስቃሴ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡

በመሆኑም በመድረኩ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና ሐሳቦችን በማቅረብ በመድረኩ እንዲሳተፉም ለወጣቶች ጥሪ ቀርቦ ነበር፡፡ ለመወዳደር ከተሳተፉ 2,300 ወጣቶች መካከል 283 በላይ ስለፈጠራ ሐሳቦቻቸው የሚዘረዝሩ የውድድር ማመልከቻዎች አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 120ዎቹ ተመርጠውና ሥልጠና ወስደው ከተለዩ በኋላ ዙር ውድድር ካለፉት 50 ተወዳዳሪዎች መካከል አሥሩ በውድድሩ አንደኛ ለሚጣውና አንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት ለሚያስገኘው የመጨረሻ ዙር ታጭተው ነበር፡፡

የውጭ ዳኞች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር አንደኛ በመውጣት የገንዘብ ሽልማቱን ያገኙት፣ ግሪን ቢን ማኑፋክቸሪንግ የተሰኘውን አክሲዮን ኩባንያ የመሠረቱት ሁለት ወጣቶች፣ የቡና ማድረቂያ ማሽን በመፈብረካቸው አሸንፈዋል፡፡ እግዜርያለው አየለና አንዱአምላክ መሐሪ የተባሉት ሁለቱ የፈጠራ ሥራ ባለንብረቶች፣ ቡና ለማድረቅ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ይፈጅ የነበረውን፣ ወደ 24 ሰዓት በማሳጠርና የቡናው ጥራት ሳይጓደል የሚያደርቅ ማሽን በመሥራታቸው ተሸላሚ ለመሆን የበቁበት መድረክ ነበር፡፡

ወጣቶቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመስከረም ወር አሥር የቡና ማድረቂያ ማሽኖችን ሠርተው ለማስረከብ ከወዲሁ ትዕዛዝ ተቀብለዋል፡፡ ከሦስት ቶን እስከ አሥር ቶን ቡና በአንድ ጊዜ ማድረቅ የሚችለውን ማሽን ሐሳብ የጠነሰሱት የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርታቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማጠናቀቅ በተቃረቡበትና ለመመረቂያ በሠሩት ፕሮጀክት አማካይነት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉትን ጨምሮ በርካታ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሐሳቦችን ከተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር ላቀረቡ ወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድሎችን የሚያስገኙ ግንኙነቶች የተፈጠሩበት መድረክ እንደነበር ያወሱት እሌኒ (ዶ/ር)፣ በቴክሎጂው መስክ ግዙፉ ስም ያካበቱ የ11 ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ኩባያዎች ተወካዮች መገኘታቸውም ለስታርት አፕ ኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነበር ብለዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ሚና ብሎም በወጣቶች ሥራ ፈጠራ ዙሪያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በመንግሥት ታምኖበት፣ በጥቂት ወራት ውስጥ የስታርት አፕ ፈንድ ወይም ጀማሪ የፈጠራ ሥራ አፍላቂዎችን ፕሮጀክቶች በፋይናንስና በቴክኒክ የሚደግፍ ፈንድ እንዲመሠረት ተወስኗል ያሉት እሌኒ (ዶ/ር)፣ ለዚህ ፈንድ መንግሥት ለመነሻ የሚሆን ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚመደብ ያላቸውን ተስፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሌሎች አገሮች እንደሚታየው፣ በኢትዮጵያ ጀማሪ የፈጠራ ሥራ ሐሳብ አፍላቂዎችን የሚደግፍ መሠረተ ልማት ገና መጀመሩ ቢሆንም፣ በአፍሪካ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለዚህ መስክ ድጋፍ እንደሚደረግ አጣቅሰዋል፡፡ በዚህ መስክ እስራኤል ከ300 ሚሊዮን ዶላር ተነስታ በአራት ዓመታት ውስጥ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ የስታርት አፕ ፈንድ ማቋቋሟን፣ ኢትዮጵያም እንዲህ ያለውንና ቬንቸር ካፒታል የተሰኘውን ዓይነት ፈንድ በማቋቋም በርካታ ሐሳብና የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች መደገፍ እንድትጀምር ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውና የአዲስ አበባ ‹‹ኤንጅል ኢንቨስተርስ›› ጥምረት መመሥረቱም በስታርት አፕ ኢትዮጵያ መድረክ ከታዩ አዳዲስ ክስተቶች አንዱ ነበር፡፡ የጥመረቱ መሥራችና በካናዳ ለዓመታት የኖሩት አቶ ሸም አስፋው፣ በአሁኑ ወቅት በራይድ ታክሲና በብሉሙን እንዲሁም በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ በኤንጅል ኢንቨስተርነት መሳተፍ ከጀመሩ አራት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ በካናዳ ቆይታቸው ከሐሳብ ጀምረው እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር አቅም የሚኖረው የቴክኖሎጂ ድርጅት የመፍጠር ተልዕኮ በመወጣት ውጤታማ ሥራ እንዳከወናወኑ የገለጹት አቶ ሸም፣ በውጭ ቆይታቸው ያካበበቱትን ጥሪት ወደፊት ሊያተርፉ በሚችሉ የፈጠራ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

እንደ እሳቸው እንዲህ ባለው መንገድ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ‹‹ኤንጅል ኢንቨስተሮችን›› በማሰበሳብ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁን ላይ ሰባት የደረሱት እነዚህ ባለሀብቶች ወደፊት 30 እስኪሞሉ ድረስ መሰባሰብ የሚችሉበትን የአዲስ አበባ የኤንጅል ኢንቨስተሮችን ጥምረት ከወዲሁ እውን አድርገዋል፡፡ ይህ ጥምረት ኢንቨስት የሚያደርጉባቸው የፈጠራ ሐሳቦች ሳይሳኩ ቢቀሩና አክሳሪ ቢሆኑ፣ በባለሀብቶቹ ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ በመጋራት ሥጋቱን የሚቀንሱበት፣ አትራፊ ቢሆኑም ከትርፉ የሚቋደሱበት ስብስብ ነው፡፡ ይህ ጥምረት ለአሁኑ ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ካለው የኤንጅል ኢንቨስትሮች ጥምረት ጋር ከወዲሁ ትስስር ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች