Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ11 ወራት ከታቀደው የቡና ወጪ ንግድ ከ287 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳየ ገቢ ተገኘ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሻይና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ከ679 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተመዝግቧል

በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ 264 ሺሕ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የገቢ መጠን ከ955 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም፣ በአፈጻጸሙ ግን ከ287 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ የተመዘገበበትን ገቢ ማስገኘቱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባወጣው ወርኃዊ ሪፖርት መሠረት፣ እስከ ግንቦት 2011 ዓ.ም. ባሉት 11 ወራት ውስጥ ከቡና ይጠበቅ ከነበረው ገቢ 70 በመቶ ገደማ ወይም 668.58 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የዘርፉ ገቢና አፈጻጸም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከቡና ብቻ ከተገኘው የ740 ሚሊዮን ዶላር የቡና ገቢ አኳያም፣ 72 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡

በዚህ ዓመት ለታየው የቡና አፈጻጸም መዳከም ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ቀርበዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የዓለም የቡና ዋጋ በ20 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን በውጫዊ ምክንያትነት ያጣቀሰ ሲሆን፣ ቡና አምራች አገሮች በርካታ የቡና ምርት ማቅረባቸው፣ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ ደንበኞች ግዥ ከመፈጸም መዘግየታቸውና አምና ከነበራቸው ክምችት አኳያ የግዥ ፍላጎታቸው መቀነሱ ከቀረቡት ምክንያቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡

በአንፃሩ ከውስጣዊ ችግሮች መካከል የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከዓለም ዋጋ ጋር ባለው ልዩነት ሳቢያ ላኪዎች የውል ስምምነታቸውን ማክበር አለመቻላቸው አንዱ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በየጊዜው መቆራረጡ ቡናውን በወቅቱ አዘጋጅቶ ለመላክ እንዳላስቻለና የኮንቴይነር ዕጥረት መታየት በምክንያትነት ቀርበዋል፡፡

የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከሻይና ከቅመማ ቅመም ምርቶች ጋር ተዳምሮ 209,407.76 ቶን ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ አኳያ የ74.84 በመቶ መጠን በመላክ በጠቅላላው የ679 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት ሊጠናቀቅ ከሁለት ሳምንት ያነሰ ዕድሜ የቀረው የበጀት ዓመት አገባዷል፡፡

እስካለፈው ግንቦት ወር በነበረው የዚህ ዓመት የቡና ወጪ ንግድ አፈጻጸም ከመዳረሻ አገሮች አኳያ ሲታይ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በ40,432 ቶን ወይም በ20 በመቶ ድርሻ ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ ተብላለች፡፡ በገቢም የ107.76 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ16 በመቶ ድርሻ ነበራት፡፡ አሜሪካ በ20,222 ቶን ወይም በ10 በመቶ ድርሻ፣ በ106.32 ሚሊዮን ዶላር ወይም በ16 በመቶ የገቢ ድርሻ ሁለተኛውን ደረጃ ይዛለች፡፡ ጀርመን የ29,049.53 ቶን ወይም የ14 በመቶ የመጠን ድርሻ ያለውን ቡና በ83.89 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ሦስተኛዋ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሆናለች፡፡

የተቀሩት አገሮች በገቢ ቅደም ተከተል ሲቀመጡ ጃፓን አራተኛ፣ ቤልጅየም አምስተኛ፣  ደቡብ ኮሪያ ስድስተኛ፣ ጣሊያን ሰባተኛ፣ ሱዳን ስምንተኛ፣ አውስትራሊያ ዘጠነኛ፣ እንዲሁም እንግሊዝ የአሥረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡  በጠቅላላው አሥሩ አገሮች 84 በመቶ የቡና መጠን እንደሚገዙና 82 በመቶ ገቢም ከእነዚህ አገሮች እንደሚመነጭ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሪፖርት ያብራራል፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች