Monday, May 27, 2024

ኢኮኖሚው ወዴት እያመራ ነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም ከ1996 ዓ.ም. አንስቶ በነበሩት አሥር ዓመታት ባለ ሁለት አኃዝ አማካይ ዕድገት በማስመዝገብ የተፈጥሮ ሀብትና የባህር ወደብ ከሌላቸው የአፍሪካ አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡት መካከል በግንባር ቀደምትነት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ሲነገርለት እንደነበረ ይታወቃል፡፡

በተጠቀሱት ዓመታት ለተመዘገበው ዕድገት የግብርናው ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ ያበረከቱ መሆኑን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ አሥር ዓመታት ውስጥ በመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት የአገልግሎት ዘርፍ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ፣ የግብርናውን ዘርፍ ድርሻ በመብለጥ ቀዳሚ መሆን እንደቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የአገልግሎት ዘርፍ ለአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ቀዳሚውንና ትልቅ ድርሻ ማበርከት በመጀመሩ የኢኮኖሚ መዋቅሩ እየተዛባ መሆኑን የተረዳው በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት፣ በግብርናው ዘርፍ ላይ መሠረቱን ጥሎ የተዋቀረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለዓመታት ሲያስመዘግብ የነበረውን ዕድገት ጠብቆ የመዋቅር ሽግግር በማድረግ የቀዳሚነት ሚናውን ለኢንዱስትሪው ማስረከብ እንደሚገባ በማመን በቀረፀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ያስተዋለውን መፋለስ ለማስተካከል፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተባለ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የዚህ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ዋነኛ ዓላማ በግብርና ላይ የተዋቀረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ እርስ በርሱ እየተመጋገበ በኢንዱስትሪ ዘርፍ መሠረት ላይ እንዲዋቀር ማድረግና ለዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ሳይስተጓጎል የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በቀጣይም ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገቡን እንዲቀጥል ማድረግ፣ በውጤቱም አገሪቱን በሁለት የአምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች የመካከለኛው ኢኮኖሚ የታችኛው እርከን ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ነበር፡፡

ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ተግባራዊ የተደረገው የአምስት ዓመት መርሐ ግብር በዋነኛነት የታቀደውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል የኢንዱስትሪ መሠረት ለመጣል እንቅስቃሴ የተደረገበት፣ ለዚህም ሲባል ከፍተኛ የአገር ውስጥና ከውጭ የተገኘ ሀብት በመንግሥት አማካይነት ጥቅም ላይ የዋለበት መሆኑ ይታወሳል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ የባቡር መሠረተ ልማቶች፣ የስኳር ፋብሪካዎችና የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ የአምስት ዓመት መርሐ ግብር ውስጥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የታቀደውን ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት ማለትም ዝቅተኛው አማካይ 11.4 በመቶ፣ ወይም በከፍተኛው የዕድገት አማራጭ 14 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት ባይቻልም፣ የአምስት ዓመቱ አማካይ 10.6 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይሁን እንጂ በመጀመርያው የአምስት ዓመት መርሐ ግብር ለተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት በተለዋዋጭነት ትልቁ አበርክቶ ያስመዘገቡት፣ የግብርናውና የአገልግሎት ዘርፍ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጠናቀቅን ተከትሎ፣ ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም. ተግባራዊ የሚደረግ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ አራተኛው ዓመት ተገባዷል፡፡

ሁለተኛው የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ መርሐ ግብር መሠረታዊ መርሆዎችም ከሞላ ጎደል ከመጀመርያው ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ፣ ዓላማቸውም የኢኮኖሚ መዋቅሩ ከግብርና መሠረት ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሽግግር እንዲያደርግ ያለመ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የሁለተኛው የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር በታቀደው መሠረት መሄድ አልቻለም፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚም ቀደም ሲል ሲመዘገብ ከነበረው ባለሁለት አኃዝ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት አሽቆልቁሎ ዕድገቱ በመቀዛቀዝ ላይ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተመዘገበውም ዕድገት ከቀደሙት ዓመታት የተገኘውን ጉልበት በመጠቀም የተገኘ ለመሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ 

የ2012 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥትን ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ያቀረቡት ሪፖርትም ይህንኑ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝና ማሽቆልቆል የሚያመለክት ነው፡፡

‹‹የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመርያዎቹ ሦስት ዓመታት የተመዘገበው አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት 8.6 በመቶ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. የተመዘገበው ዕድገት በነጠላው ሲታይ 7.7 በመቶ እንደሆነ፣ በጥቅሉ በተጠቀሱት ዓመታት የተመዘገበው ዕድገት በዕቅዱ ከተያዘው የ11 በመቶ ግብም ሆነ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አምስት ዓመታት ከተመዘገበው የ10.1 በመቶ አማካይ ዕድገት ያነሰ ነው፤›› በማለት ለምክር ቤቱ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

የኢኮኖሚ ቀውስ አዙሪት?

ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል ለመመዝገቡ የገንዘብ ሚኒስትሩ በጥቅሉ ያስቀመጧቸው ምክንያቶች፣ ሁለተኛው የአምስት ዓመት መርሐ ግብር ሥራ ላይ መዋል ከመጀመሩ አንስቶ በአገሪቱ የተከሰቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመረጋጋቶችና በኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን ክፍተት ናቸው፡፡

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ መሠረታዊ ግብም እንደ ቀደመው የአምስት ዓመት ዕቅድ ሁሉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከግብርናው ዘርፍ ጥገኝነት ቀስ በቀስ ተላቆ፣ ሽግግሩን ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲያደርግ የታለመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ግብርናው አሁንም ከዝናብ ጥገኝነት ባለመላቀቁና የዘመናዊ የእርሻ ግብዓት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ባለመሆኑ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን መግቦ የኢኮኖሚ መዋቅሩን ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሊያሸጋግር ይቅርና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅም መፍጠር አለመቻሉን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያ ከሚጠቀሱት መካከል አገሪቱ የዳቦ ስንዴ ከውጭ በከፍተኛ ደረጃ በውጭ ምንዛሪ እያስገባች የምትገኝ መሆኗ፣ እንዲሁም ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ግብዓት የሆነው የጥጥ ምርትም በተመሳሳይ በውጭ ምንዛሪ እየገባ መሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡

‹‹የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የኢንዱስትሪ ዘርፉ በየዓመቱ ከሃያ በመቶ ያላነሰ ዕድገት እንዲያስመዘግብ በዕቅድ የተመለከተ ቢሆንም፣ በተለይም ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚጠበቀው እሴት የመጨመርና የኤክስፖርት ዘርፉን የመደገፍ ግብ መሻሻል ባለመሳየቱ በኢኮኖሚው የሚጠበቀው መዋቅራዊ ሽግግር ሳይሳካ ቀርቷል፤›› በማለት የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ዕድገት ግብዓቶችን በማቅረብና የወጪ ንግድ ዘርፉን ለመደግፍ ከተወሰኑ የተለመዱ የኤክስፖርት ምርቶች ተላቆ በዓይነት፣ በጥራትና በመጠን የተሻለ በማምረት ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እንዲደግፍ በሁለቱም የአምስት ዓመታት የኢኮኖሚ መርሐ ግብሮች ግብ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም መሳካት አልቻለም፡፡

ለአብነትም ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. ከግብርና ዘርፍ ምርቶች ኤክስፖርት በውጭ ምንዛሪ የተገኘው ገቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው 2.15 ቢሊዮን ዶላር፣ 2.17 ቢሊዮን ዶላርና 2.11 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የኤክስፖርት ንግድ በተጠቀሱት ዓመታት የተገኘው ገቢ (ግብርናን ጨምሮ) እንደ ቅደም ተከተላቸው 2.83 ቢሊዮን ዶላር፣ 2.83 ቢሊዮን ዶላርና 2.7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም. አሥር ወራት ውስጥ የተገኘው የኤክስፖርት ዘርፍ ገቢ ደግሞ 2.09 ቢሊዮን ዶላር ስለሆነ፣ በቀረው ጊዜም ተዓምራዊ ለውጥ ይመጣል ተብሎ የማይጠበቅ በመሆኑ የዘንድሮው አፈጻጸም ካለፉት ዓመታት ያነሰ ስለመሆኑ መረጃው ያመለክታል፡፡

ከኤክስፖርት ዘርፍ መገኘት የነበረበት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለው፣ መንግሥት የኤክስፖርት ዘርፉን ለማበረታታት የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ካደረገ በኋላ መሆኑ ቀውሱን የተለየ ያደርገዋል፡፡

የኤክስፖርት ዘርፉ አፈጻጸም ስኬት ወይም ጎዶሎነት በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ የተፈጠረውን መዛነፍ ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ለዚህ የሚዘረዝሩት ምክንያት የአገሪቱ የአምስት ዓመት መርሐ ግብር መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣት የግብርናው ዘርፍ ምርቶች በዓይነትና በጥራት ጨምረው ለኢንዱስትሪው ግብዓት የማቅረብና ከግብርና ምርቶች ኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ በመሆኑና እንዲሁም የተሻሻለ የግብርና ግብዓቶችን የሚያገኘው የኢንዱስትሪ አምራች ዘርፍ ግብም እሴቶችን በመጨመር ለኤክስፖርት ገበያው ምርቶችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ የዕቅዱ መሠረታዊ ምሰሶ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከሁለቱ ዘርፎች በዕቅዱ መሠረት በድምር የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ መልሶ ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት ለሚያስፈልገው የውጭ ግዥና የውጭ ዕዳዎች በማዋል፣ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ሚዛን በመቀነስ ተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ማስፋፊያ የሚውል የውጭ ፋይናንስ በብድር ለማግኘት ማመቻቸት በመሆኑ፣ በኤክስፖርት ዘርፉ ላይ የሚታይ ስኬትም ሆነ ጉድለት የኢኮኖሚ ዘርፎቹ በታቀደላቸው መስመር ውስጥ መሆንና አለመሆን መገለጫነቱን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የዓለም የሸቀጦች ዋጋ መቀነስና የበለፀጉት አገሮች ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የማፍራት አቅም ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ ከፍተኛው ድክመት ግን የመንግሥት ውስጣዊ ችግር ነው፤›› ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የተጠቀሱት ምክንያት ለኤክስፖርት ዘርፉ የገቢ ዕድገት መሠረት የሆኑት የግብርናና የኢንዱስትሪ (ማኑፋክቸሪንግ) ዘርፎች ዕድገት አዝጋሚ መሆኑ አንዱ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ መሠረት ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው፣ የመንግሥት ግዙፍ አምራች ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ማምረት አለመቻላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ ያመጣውን የኢኮኖሚ ቀውስ በተመለከተም የገንዘብ ሚኒስትሩ ሲያስረዱ፣ ‹‹የወጪ ሸቀጦች ገቢ ማሽቆልቆል ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈታኝ የሆነው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳይቀረፍ አድርጓል፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ የውጭ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ አምራቾች ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት በሚጠበቀው ደረጃ ማሟላት አልተቻለም፤›› ሲሉ ችግሩ በዚህ አያበቃም የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዚህ የተነሳም በአገር ውስጥ የማይመረቱ መሠረታዊ ዕቃዎች አቅርቦትን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ አልተቻለም፡፡ ይህ ደግሞ በአንዳንድ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ግሽበት እያስከተለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ የኤክስፖርት ገቢው መዳከም በአገሪቱ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ላይ የራሱን ተፅዕኖ በማሳደሩና የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና ሥጋት እንዲጨምር በማድረጉ፣ ተጨማሪ የልማት ብድር ለማግኘት እንዳልተቻለና ይህም መንግሥት የጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን እንዳስተጓጎለ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ችግር አዙሪት ውስጥ ለመውጣት ከባድ ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ዝቅተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ዘርፎች በበኩላቸው የውጭ ምንዛሪውን ሙሉ በሙሉ ወደ ራሳቸው ኪስ ለማስገባት ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱን ወደ ጎን አድርገው፣ በሕገወጥ የወጪ ንግድ ላይ መሰማራታቸውን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን ዘንድሮ 26 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከገባበት የቀውስ አዙሪት ለመውጣት የመንግሥት ኢንቨስትመንቶች እንዲገደቡና የውጭ ብድርም እንዲቆም ያደረገ ሲሆን፣ ያለውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በሥነ ሥርዓት ለመጠቀም ሲባልም የገቢ ዕቃዎች መቀነሳቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የራሱ ዕድልና ፈተና ይዞ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡

በመልካምነት የሚጠቀሰው የተወሰደው ዕርምጃ በመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ጫና እንዲቀንስ ማድረጉ ሲሆን፣ የመንግሥት ኢንቨስትመንትና የውጭ ብድር እንዲያዝ መደረጉ ደግሞ የአገሪቱ የውጭ ብድር ጫና ባለበት እንዲረጋ አስተዋጽኦ ማድረጉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በየዓመቱ 25 ቢሊዮን ብር ለውጭ ዕዳ ክፍያ ብትመድብም የውጭ ብድሩ የዋለባቸው ፕሮጀክቶች ግን መጠናቀቅ አለመቻላቸው ይታወቃል፡፡

በፈተናነት የሚጠቀሰው ደግሞ መንግሥት የገቢ ዕቃዎች መጠንና የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ በማድረጉ፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የታክስ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስና ኢኮኖሚው እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ሆኗል፡፡

ለአብነት ያህል በ2011 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ በአዋጅ ከፀደቀው 211 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ ውስጥ፣ በአሥር ወራት ውስጥ መሰብሰብ የተቻለ 143.5 ቢሊዮን ያህሉን እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በ2003 ዓ.ም. 58.9 ቢሊዮን ብር የነበረው የአገሪቱ ታክስ ገቢ በ2008 ዓ.ም. 190.5 ቢሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም. 210.2 ቢሊዮን ብር፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ 235.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር መረጃው ያሳያል፡፡

በመሆኑም የአገሪቱ የታክስ ገቢ መጠን መቀነስ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ማሳያ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -