በአዳማ ከተማ የንግድ ሕንፃዎችን በማስገንባት ላይ የነበረው ግንብ ገበያ አክሲዮን ማኅበር፣ ግንባታዎቹን ላካሄደለት ተቋራጭ በተዋዋለው መሠረት ክፍያዎችን ባለመፈጸሙ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዲከፍል ተወሰነበት፡፡
የፍርድ ቤት ውሳኔ የተላለፈበት ግንብ ገበያ፣ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ወቅት ነበር፡፡ ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ኮራንኮን ኮንስትራክሽን (ጅብሪል ገረሱ) ባቀረበው ክስ መሠረት፣ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንብ ገበያ አክሲዮን ማኅበር በተዋዋለው አግባብ ክፍያ አለመፈጸሙን በማረጋገጥ አክሲዮን ማኅበሩ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ ከእነወለዱ እንዲከፍል ወስኖበታል፡፡
ተቋራጩ ያረቀበው የክስ ጭብጥ እንደሚያስረዳው፣ ከሳሽ በአዳማ ከተማ ለአክሲዮን ማኅበሩ በሁለተኛና ሦስተኛ ዙር የሕንፃ ግንባታ ለማከናወን በገባው ውል መሠረት ግንባታውን እያካሄደ ቢቆይም፣ በውሉ መሠረት ክፍያ ሊፈጸምለት አልቻለም፡፡ ተቋራጩ ለፍርድ ቤት ባሰማው ክስ በሁለተኛውና በሦስተኛው የሕንፃ ግንባታ ውል መሠረት፣ ወለዱና የካሳ ክፍያውን ጨምሮ እንዲከፈለው ያመለከተበት የገንዘብ መጠን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡
በሁለቱም ዙር ግንባታዎች በአማካሪ መሐንዲሱ የፀደቀው ክፍያ በአጠቃላይ 150,970,074.88 ብር በመሆኑ ተከሳሽ ይህ ገንዘብ እንዲከፈለው በክሱ አመልክቷል፡፡ በተጠቀሰው ገንዘብ ላይ አማካሪ መሐንዲሱ ወለዱን ካሰላበት ከኅዳር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያለውን ወለድ የሁለተኛ ዙር ክፍያ በዝቅተኛ የንግድ ባንኮች የብድር ወለድ ተመን ምጣኔ 9.5 በመቶ ሆኖ እንዲከፍል የጠየቀበት፣ እንዲሁም የሦስተኛ ዙር ክፍያውም በውሉ መሠረት በዝቅተኛ የንግድ ባንኮች የወለድ ተመን ሆኖ የ3.5 በመቶ ቅጣት ተጨምሮበት በአጠቃላይ 13 በመቶ ወለድ ታስቦለት እንዲከፈለው ከሳሹ ተቋራጭ ክሱን አቅርቦ ነበር፡፡
ተከሳሽ የሚፈለግበትን ክፍያ ሳይፈጽም ያስገነባውን ሕንፃ ለመረከብ በመንቀሳቀስ በከሳሽ ላይ እያደረሰ ያለውን የሁከት ተግባር እንዲያቆም፣ በክሱ ምክንያት የደረሰበትን ወጪና ኪሳራም ተከሳሽ እንዲተካ በማለት ዳኝነት የጠየቀበት የክስ መዝገብ ያመለክታል፡፡
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤትም በውለታው መሠረት በአማካሪ ድርጅቱ የፀደቁ ክፍያዎች ጊዜውን ጠብቀው ባለመክፈላቸው የግንባታው ውሉም ስለመስተጓጎሉ ጠቅሷል፡፡ ተቋራጩ በውለታው መሠረት እንዲከፈለው በዝርዝር ያቀረበው ገንዘብ በአማካሪ ድርጅቱ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ የክፍያ ጥያቄዎቹ በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘታቸውም ጉዳዩን በሽምግልና ጭምር ዕልባት እንዲገኝበትና ገንዘብ እንዲከፈለው ለማድረግ ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው ታውቋል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል የቀረበውን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ፍርድ ቤትም በሦስትዮሽ የተደረጉ ምክክሮችና በሁለቱ ወገኖች የቀረቡትን ምላሾች በማገናዘብ ክፍያ እንዳልተፈጸመ በማረጋገጥና በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገውን ስምምነት የተጣሰው በአክሲዮን ማኅበሩ እንደሆነ በመጥቀስ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሹም ለቀረበበት ክስ ሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሑፍ መልስ በመስጠት፣ የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያዎቹን ያቀረበ ሲሆን፣ የፌዴራል ጉዳይ ባለመሆኑ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የመዳኘት ሥልጣን የለውም በማለት ተሟግቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የክልል ዳኝነት ሥልጣን የለውም፣ ክስ የቀረበበት ጉዳይ ለዕርቅ የተቀጠረ በመሆኑ ዳኝነት ሊጠየቅበት አይገባም በማለት ተከሳሹ ኩባንያ ተከራክሯል፡፡
ይልቁንም ጉዳዩ በግልግል ዳኝነት የሚታይ በመሆኑ፣ በመደበኛው ፍርድ ቤት ሊታይ አይገባም፣ ጉዳዩም ክስ ለመመሥረት የሚያበቃ ምክንያት የለውም በማለት የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያዎችን በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ በፍሬ ነገር ክርክሩ ወቅትም፣ አማራጭ መልሶቹን አሰምቷል፡፡ ይኼውም ተከሳሹን ድርጅት ሲመሩ የነበሩት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የሥልጣን ዘመናቸው በ2006 ዓ.ም. ካበቃ በኋላ በባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሳይመረጡና ከሦስተኛ ወገን ጋር ውል ለማድረግ የሚያስችላቸው ሥልጣን ሳይኖራቸው ሕገወጥ ውሎችንና ሥራዎችን የፈጸሙ በመሆኑ፣ ከከሳሹ ተቋራጭ ጋር የተደረጉት የግንባታ ውሎችም የዚሁ ሕገወጥ ሥራና ሥልጣን ውጤቶች ናቸው በማለት ተከራክሯል፡፡
ከሳሽ የሥልጣን ዘመናቸው ካበቃው የቀድሞ ቦርድ አባላት ጋር ሕገወጥ በሆነ መንገድ ያለ ጨረታ የግንባታ ሥራውን በመውሰድና ሕገወጥ የግንባታ ሥራ ውል በማድረግ እንዲከፈለው ያቀረበው የይገባኛል ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽም ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ የሁለተኛ ዙር የግንባታ ሥራ ለማካሄድ ውል ከፈጸመ በኋላ በልዩነት የተሠሩ ሥራዎች አሉ በማለት ከጊዜ ወደ ጊዜ ክፍያ ሲቀበል እንደቆየ ተከሳሽ መልስ ሰጥቷል፡፡
ከሳሹ ክፍያ የተቀበለባቸው ሥራዎች እንዳልተሠሩና ክፍያ እንዳልተፈጸመባቸው በማስመሰል በአዲስ መልክ መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጻፈ ተጨማሪ የግንባታ ውል በ50,803,952.11 ብር በሕገወጥ ሁኔታ በመፈራረሙ አሁን ባቀረበው ክስ ይህ ክፍያ ይገባኛል በማለት ጠይቋል በማለት ተከሳሹ ተሟግቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን የጽሑፍ መከራከሪያ ከመረመረ በኋላ፣ ተከሳሽ ያቀረባቸውን መቃወሚያዎች በሙሉ ውድቅ በማድረግ ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃዎች በመመርመር ከሳሽ ከተከሳሽ ጋር ባደረጋቸው የግንባታ ውሎች ከሳሽ በሁለተኛና በሦስተኛ ዙር ላከናወናቸው የግንባታ ሥራዎች ሊከፈለው የሚገባው ክፍያ ምን ያህል ነው? ከሳሽ በእያንዳንዱ ዙር ግንባታ ሥራ ሊከፈለው ከሚገባው ክፍያ ምን ያህል ተከፍሎታል? ያልተከፈለ ቀሪ ክፍያ ካለ ምን ያህል ነው? የሚሉትን ነጥቦች የሚያጣራ ገለልተኛ ባለሙያ ተመድቦ እንዲጣራ አዟል፡፡
ጉዳዩን እንዲያጣራ የተመደበው ገለልተኛ አካል የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርት ውጤት መሠረትም ባደረገው ማጣራትም ተከሳሽ ለከሳሽ የሚገባው የካሳ ክፍያ 110,956,129.90 ብር መሆኑን በመግለጹ በዚሁ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ ለከሳሽ የሚገባውን ክፍያ ለመክፈሉ የሚያረጋግጥ ምላሽ ያላቀረበና ለዚሁ ተብሎ የተደረገ ማጣራትም የሦስትዮሽ ውይይቶች የሚያሳዩትና በአማካሪ ድርጅቱ የቀረቡ ክፍያዎችን በወቅቱ እንዳልከፈለ የሚያስረዱ መሆናቸውን በማረጋገጥ፣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ተከሳሽ ክፍያዎቹን ላለመክፈል የራሱ የሆነ የአመራር ችግር ነበረብኝ በማለት በውይይቱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ ክፍያዎች ግን በወቅቱ መክፈል አለመቻሉን ከቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች ለማረጋገጥ መቻሉን በመግለጽ ውሳኔ እንደተላለፈ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተከሳሽ በአማካሪ መሐንዲሱ ምላሽ አለመስጠቱና ክፍያም አለመፈጸሙ፣ ክፍያ የማይፈጸመው በቂ ምክንያት ሳይኖረው እንደሆነ የሚያመለክትና ያቀረበው ማስረጃም እንደሌለ በማመላከት የግንባታ ሥራውም የተቋረጠው በዚህ ክፍያው በወቅቱ ባለመፈጸሙ ምክንያት በመሆኑ ለግንባታ ሥራው ወይም ለውሉ መቋረጥ ጥፋተኛው ተከሳሽ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል በማለት ወስኗል፡፡
እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በሦስትዮሽ ውይይቶች ተጨማሪ የክፍያ ጊዜ ተሰጥቶት እንኳን ተከሳሽ ያልፈጸመ በመሆኑና ግንባታውም በዚሁ ምክንያት የተቋረጠ በመሆኑ ለውሉ መቋረጥ ጥፋተኛው ወይም ዋናው ምክንያት ተከሳሽ መሆኑን ፍርድ ቤቱ መረዳቱን የውሳኔ መዝገቡ ያመለክታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክርና ማስረጃ በፍርድ ቤት ተመድቦ ጉዳዩን ያጣራው አካል ያቀረባቸውን ሪፖርቶች መሠረት በማድረግ ከሳሽ በግንባታ ውሉ መሠረት ለሠራው ያልተከፈለ ቀሪ ክፍያና ከሳሽ ለሥራው ሌሎች ሥራዎች ተጀምረው ላልተጠናቀቁ ሥራዎች፣ ለግንባታ ሥራ ላቀረቡ ዕቃዎችና የመያዣ ክፍያን በተመለከተ ተከሳሽ ለከሳሽ ሊከፍለው የሚገባውን ክፍያ በማጠቃለል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ይህም ውሳኔ ተከሳሽ ለሁለተኛ ዙር የግንባታ ውል ከሳሽ ለሠራው ሥራ ያልከፈለውን ብር 45 ሚሊዮን የሆነውን ከሚያዝያ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሚታሰብ 9.5 በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፈል ወስኗል፡፡ የሁለተኛው ዙር ግንባታ ሥራ ክፍያ በመዘግየቱ ምክንያት በአማካሪ መሐንዲሱ የተሰላውን የካሳ ክፍያ አምስት ሚሊዮን ብር ጨምሮ ተከሳሹ ለከሳሽ እንዲከፍል፣ የሚያመላክት ሲሆን፣ ይህንን በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን ብር የሆነውን ክፍያ ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ከግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚታሰብ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ጨምሮ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
ተከሳሹ ለሦስተኛው ዙር ግንባታ ውል መሠረት ከሳሽ ለሠራው ሥራ ያልከፈለውን ክፍያ በድምር ሰባት ሚሊዮን ብር ከሚያዝያ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ከሚታሰብ 11 በመቶ ወለድ ጋር ለከሳሽ ሊከፈል ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡
ተከሳሹ ይህ ክፍያ ለዘገየበት ጊዜ አማካሪ መሐንዲሱ ያሰላውን የካሳ ክፍያ 1,589,110.78 ሚሊዮን ብር የሆነው ጨምሮ ለከሳሽ ሊከፈል ይገባልም ብሏል፡፡ በድምሩ 8.8 ሚሊዮን ብር ደግሞ ውሳኔ ከተሰጠበት ከግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ 9 በመቶ ጨምሮ እንዲከፈል ተወስኗል፡፡
ሌሎች በከሳሸ የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ ተከሳሽ 58.39 ሚሊዮን ብር ውሉ ከተቋረጠበት ከግንቦት 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ ሕጋዊ የዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር ለከሳሽ ሊከፍል ይገባል በማለት አክሲዮን ማኅበሩ ወለዱን ሳይጨምር ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍል የፍርድ ቤት ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡