Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቱሪዝም ኢትዮጵያ በጎብኚዎች ላይ የቁርጥ ግብር በመጣል ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለኮከብ ሆቴሎች ቢቀበሉትም በፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ የገበያ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በሚል ስያሜ ከአራት ዓመታት በፊት የተመሠረተውና በአሁኑ ወቅት ከስያሜው ጀምሮ የተቋቋመበት አዋጅ በማሻሻል ብሎም ረቂቅ ደንብ በማዘጋጀት ባለኮከብ  ሆቴሎችን ያወያየው ይህ ተቋም፣ በቱሪስቶች ላይ የቁርጥ ግብር ለመጣል ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌንሳ መኰንን የባለኮከብ ሆቴሎች ባለንብረቶችንና ሥራ አስኪያጆችን ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በመጥራት ስለተረቀቀው ደንብና እየተቋቋመ ስላለው የቱሪዝም ፈንድ ከተቋሙ ሕግ ክፍል ዳይሬክተር ወይዘሮ ለምለም ካሳ ጋር በመሆን አብራርተዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይቋቋማል የተባለው የቱሪዝም ፈንድ ዓላማው ቱሪዝም ኢትዮጵያ የሚያጋጥመውን የገንዘብ እጥረት ከመንግሥት በጀት ባሻገር በሌሎች የገንዘብ ምንጮች በተለይም ከቱሪስቶች ቁርጥ ግብይ (ታክስ ሌቪ) ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውቋል፡፡ ይህ የቱሪስት ታክስ፣ ተቋሙ በሕግ ለተሰጡትና ኢትዮጵያን ለዓለም ቱሪዝም ገበያ የማስተዋወቅ ብሎም መዳረሻዎችን ለማልማትና ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በገንዘብ ለመደገፍ ያለመ ነው፡፡

ምንም እንኳ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከመንግሥት ቋት የሚለቀቅለት በጀት ቢኖረውም፣ በቂ ስለማይሆን ከሌሎች የገቢ ምንጮች ሥራዎቹን ለመደጎም በማሰብ የቱሪዝም ፈንድ ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሌንሳ ጠቅሰዋል፡፡ ተቋሙ ከሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ከሚሰበስባቸው የተለያዩ የገቢ ምንጮች ባሻገር ሆቴሎችና ሌሎችም የቱሪዝም ዘርፉ ተዋንያን ከተጠቃሚው እየሰበሰቡ ገቢ የሚያደርጉለትን የቱሪስት ታክስ በተመለከተ ያቀረበው ሐሳብ በአብዛኛው በባለኮከብ ሆቴሎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶለታል፡፡

ምንም እንኳ ከሁሉም ክልሎችና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ባለኮከብ ሆቴሎች ይሳተፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው የሆቴል ባለቤቶችና ሥራ አስኪጆች በስብሰባው ተገኝተዋል፡፡ አብዛኞቹም ሐሳቡን ተቀብለው ትግበራው ግን እንዲዘገይላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከበርካቶቹ ሆቴሎች ሲደመጥ የነበረውም በአሁኑ ወቅት የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ያመላከተ ነበር፡፡ አብዛኞቹ በአገሪቱ ክልሎች አካባቢ እየተባባሰ ባለው የፀጥታና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ ገበያ በማጣታቸው፣ የብድር ዕዳም ሆነ የሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈል መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ ምንም ዓይነት ተነሳሽነት እንደማይታይበት፣ የብድር ዕፎይታ እንደማይሰጣቸው፣ አብዛኞቹም ብድር ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሚገኙ፣ ከግል ባንኮች ‹‹የአራጣ ያህል›› ለወለድ እስከ 18 በመቶ እየተጠየቁ መቸገራውን በመግለጽ መንግሥትን ኮንነዋል፡፡ ሌሎችም ከሥልጠናና ከአቅም ግንባታ አኳያ በተለይም የሆቴል ባለሙያዎችን ወደ ውጭ በመላክ ለማሠልጠን የሚፈልጉ ሆቴሎች ለሠልጣኞች የሚያወጡት ወጪ በመንግሥት ስለማይታሰብላቸው ባለሙያዎች ዕድሉን እያጡ መቸገራቸውንም አንስተዋል፡፡

በሆቴሎቹ የተነሱት ጥያቄዎች አሳሳቢነት መገንዘባቸውን ያስታቁት ወይዘሪት ሌንሳ፣ ከሌሎች ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን ለመፍትሔው እንደሚነጋገሩት ለባለሆቴሎቹና ሥራ አስኪያጆቹ ገልጸዋል፡፡

እንደ አዲስ ራሱን አደራጅቷል የተባለው ቱሪዝም ኢትየጵያ፣ በየሦስት ዓመቱ የሚሾሙለት የቦርድ አመራር አባላት እንደሚኖሩት፣ ተቋሙን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ኃላፊዎችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሾሙ፣ የተቋሙ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደሚሆን በሚሻሻለው አዋጅ ተካቷል፡፡ ቱሪዝም ኢትዮጵያ የንግድ ተቋም ባህርይ እንደሚኖረውና በአብዛኛው የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ እንደሚያተኩር፣ የፖሊሲና የቁጥጥር ሥራዎች በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል እንደሚከናወኑ አደረጃጀቱን በማስመልከት አብራርተዋል፡፡ አዲስ የሚቋቋመውን የቱሪዝም ፈንድ ተቋምንና የሚያሰባስባቸውን ገቢዎች የማስተዳደርና የመቆጣጠር ድርሻ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ይሆናል፡፡

ስምምነት የተደረገበት የቱሪዝም ቁርጥ ታክስ ገቢ፣ ምጣኔው በመቶ ይሁን ወይም ከጠቅላላ ገቢ በቁርጥ ተቀናሽ (ፍላት ሬት) የሚለውን ጨምሮ፣ መቼና እንዴት ይጀመር፣ እነማን ይካተቱ የሚለው ላይ ዝርዝር ጥናት እንደሚካሔድ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሆቴሎች በበኩላቸው ምጣኔውም ሆነ ገቢው ታሳቢ የሚደረግበት አግባብ በሚገባ እንዲጠና ጠይቀው፣ እንግዶች በሚከራዩት ክፍል ሒሳብ ላይ እንጂ በምግብና መጠጥ ላይ ታሳቢ መደረግ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ ምግብ አክሳሪ በመሆኑ ተጨማሪ ወጪ ተጠቃሚው ላይ መጣል አይቻልም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአስጎብኝ ድርጅቶችን ጨምሮ፣ የትራንስፖርት ኩባንያዎችና ሌሎችም በቱሪዝም መስክ የሚተዳደሩ ሁሉ ቁርጥ ታክስ የመሰብሰብ ግዴታው እንዲጣልባቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህም ይባል እንጂ ሆቴሎቹ ተጨማሪ ውይይቶች በየክልሉ እንዲካሔዱና ባለንብረቶችም እንዲጋገሩበት ዕድሉ እንዲመቻችም አሳስበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች