Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘምዘም ባንክ በወለድ አልባ ባንክ ሥራ ለመሰማራት የአክሲዮን ሽያጭ ሊጀምር ነው 

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት በመደራጀት ላይ የሚገኘው ዘምዘም ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ ለመጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ከብሔራዊ ባንክ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ሌሎች ወለድ አልባ ባንኮችም የምሥረታ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

ከዓመታት በፊት ከወለድ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ባንክ ለማቋቋም በሚንቀሳቀስበት ወቅት ክልከላ የተደረገበት የዘምዘም ባንክ አደራጅና የቦርድ ሊቀመንበር ናስር ነሪ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የዘምዘም ባንክን የአክሲዮን ሽያጭ ለማካሄድ የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ረቡዕ ሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. አግኝቷል፡፡

ዘምዘም ባንክ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወን እንዲቻለው ብሔራዊ ባንክ የአክሲዮን ሽያጩ ገቢ የሚደረግባቸውን ባንኮች ሒሳብ ቁጥር በመጥቀስ ለባንኮቹ እንዳሳወቃቸው ከናስር (ዶ/ር) ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹ፈቃድ በማግኘታችን በአጭር ጊዜ የአክሲዮን ሽያጩን እንጀምራለን፤›› ያሉት ናስር (ዶ/ር)፣ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንኩን ለማቋቋም የሚያስችለውን የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከአክሲዮን ሽያጭ እንደሚሰበሰብ ገልጸዋል፡፡

ለምሥረታ የሚያስፈልገውን ግማሽ ቢሊዮን ብር ተሰብስቦ እንዳበቃ፣ የባንኩን ምሥረታ በማሳወቅ ወደ አገልግሎት ለመግባት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ መደረጉን አደራጁ ጠቁመዋል፡፡ ባንኩ ወለድ አልባ አገልግሎቶችን ብቻ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ባንኮች በአሁኑ ወቅት በመስኮት የሚሰጡትን ከወለድ ነፃ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ለዚሁ በተቋቋመና ራሱን በቻለ ባንክ ለማቅረብ መነሳቱን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ዘምዘም ባንክ በድጋሚ አክሲዮን ወደ መሸጥ ከመግባቱ ቀደም ብሎ ቀድሞ በነበረው የባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ባንኩን ለማቋቋም የሚያስችለውን ካፒታል አሰባስቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቱን ለዚሁ ተግባር በተቋቋመ ባንክ  በኩል መስጠት እንደማይችል ከመንግሥት ተነግሮት ያሰባሰበውን ካፒታል ለአክሲዮን ገዥዎች መመለሱ አይዘነጋም፡፡

በወቅቱ የነበረው የብሔራዊ ባንክ ሕግ ባንክ ለማቋቋም ይፈቅድ የነበረው ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል መጠን 100 ሚሊዮን ብር ስለነበር በዚሁ መሠረት ዘምዘም ባንክ 137 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አሰባስቦ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያውን ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት ቢሆንም፣ በወቅቱ አገልግሎቱን የሚገዛ ሕግ ግን አልነበረም፡፡

ወለድ አልባ የገንዘብ አገልግሎት አማራጭ ሆኖ መቅረብ እንደሚችል ዕምነት በማግኘቱ፣ የዘምዘም ባንክ የምሥረታ ጥያቄ ቀርቦ የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል በተረቀቀው ሕግ ውስጥ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን የሚመለከት አንቀጽ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

የባንክ ሥራ አዋጁ በፓርላማ ውይይት ተደርጎበት ሰኔ 2000 ዓ.ም. ፀድቆ ሲወጣ በአዋጁ ከተካተቱት አዳዲስ አንቀጾች ውስጥ በአንዱ ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የሆነ ተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ የባንክ ሥራዎችን ለመቆጣጠር መመርያ ሊያወጣ ይችላል የሚል አዲስ ድንጋጌ አካቶ ነበር፡፡    

ከዚህ አዋጅ መውጣት በኋላ ግን ወለድ አልባ አገልግሎትን እንዲኖር የሚያስችለው ረቂቅ መመርያ የወጣው ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ሕግ ዘምዘም ባንክን ጨምሮ ሌሎችም ለምሥረታ ሲያኮበኩቡ ለነበሩ ባንኮች ወለድ አልባ የባንክ ሥራ ሊጀመር የሚችልባቸው መሥፈርቶችና ለመመርያው መውጣት ግንዛቤ የተወሰደባቸው አምስት መሠረታዊ ነጥቦችን በመግቢያው አስቀምጦ ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የዘምዘም ባንክ አደራጆች በወቅቱ ያቀረቡት ሪፖርት ያሳያል፡፡

በመሆኑም ለወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ጠንካራ የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ በመኖሩ፣ በአንዳንድ ባንኮችና ባለሀብቶች ዘንድም ለወለድ አልባ አገልግሎቱ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኝነቱ በመታየቱ ብሎም፣ ኢትዮጵያ ያለው የፋይናንስ ዘርፍ ልማትና የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን እንደሚያሳድግ ስለታመነበት፣ አገልግሎቱ በአግባቡና ባልተበጣጠሰ አኳኋን መመራት ስላለበት፣ ከወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ጋር ተዛማጅ የሆነ የመቆጣጠሪያ ማዕቀፍ ውስንነት በመኖሩ አገልግሎቱን በቶሎ ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለ የቀረቡ የመንግሥት ሐሳቦች ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥባቸው መንገዶች በመለየታቸውና ተያያዥነት ባላቸው የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች ላይ የተደነገጉ ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ ተሟልተው በሚገኙበት ወቅት፣ ወለድ አልባ አገልግሎት ሊጀመር እንደሚችል መንግሥት አስታውቋል፡፡ በመሆኑም አገልግሎቱን ነባር ባንኮችም በመስኮት በኩል ሊሰጡ እንደሚችሉ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሠማራ ባንክ ማቋቋም እንደሚችሉ የተካተቱበት የሕግ ማዕቀፍ ወጥቷል፡፡

ሁለት ረቂቅ መመርያዎች ወጥተው እንደነበርና የመጀመርያው ከሁለተኛው ብዙም የሐሳብ ለውጥ ሳይደረግበት ቀርቦ እንደነበር፣ የዘምዘም ባንክ ሪፖርት አስታውሷል፡፡ በዓለም ላይ ወለድ አልባ የባንክ ሥራ በሰፊው እያደገ በመሆኑና ለእነዚህ ፍላጎቶችና የለውጥ ሒደቶች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ተገቢ በመሆኑ ወለድ አልባ ባንክ መቋቋም የሚችልባቸው ዕድሎችን አስፍሮ ነበር፡፡ የዘምዘም ባንክ አደራጆች ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች በተነጋገሩባቸው ጊዜያትም አገልግሎቱ አስፈላጊነት በአጽንኦት ተወስቶ ነበር፡፡

ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ ባንክ ለማቋቋም፣ ወይም ነባሩንና መደበኛውን ባንክ ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ አገልግሎት ወደሚሰጥ ባንክ መቀየር ወይም ከመደበኛ የባንክ ሥራ ጎን ለጎን በመስኮት ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የባንክ ሥራ ማካሄድ የሚችልበት ፈቃድ እንደሚሰጥ ተሻሽሎ የወጣው መመርያ አስፍሮ ነበር፡፡

እንዲህ ያለው የሕግ ማዕቀፍ ተደላደሎ ከመጣ በኋላ፣ ሕጉ ለብዙ ጊዜ በረቂቅ ደረጃ ቆይቶ ነበር፡፡ በቅርቡም ሙሉ ለሙሉ ፀድቆ በቅርቡ ዘምዘም ባንክ ወደ ኢንዱስትሪው ለመግባት የሚችልበትን ይሁንታ ከብሔራዊ ባንክ በማግኘቱ እንቅስቃሴውን ጀምሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወለድ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚችልና ራሱን የቻለ ባንክ ማቋቋም ይችላል መባሉን ተከትሎ፣ እስካሁን አምስት ባንኮች ሊመሠረቱ ይችላሉ እየተባለ ነው፡፡ የተወሰኑትም ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች