Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማ ሥራ ላይ መዋሉን ዋና...

የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማ ሥራ ላይ መዋሉን ዋና ኦዲተር ቁጥጥር እንዲያደርግ በድጋሚ ሥልጣን ተሰጠው

ቀን:

የምርጫ ቦርድ አባላትና የዳኞች ሹመት ፀደቀ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማና ልዩ ድጋፍ በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94(2) ላይ በተደረገገው መሠረት፣ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን ኦዲትና ቁጥጥር በማድረግ እንዲያረጋግጥ በሕግ ሥልጣን ተሰጠው።

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ያቋቋመው የቀድሞው አዋጅ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ልዩ ድጎማዎች ኦዲት የማድረግ ሥልጣን ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ በ1998 ዓ.ም. አቅርቦት በነበረው የኦዲት ሪፖርት ለክልሎች የተሰጠው የበጀት ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማረጋገጥ አለመቻሉን ለፓርላማው በማሳወቁ ሳቢያ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።

- Advertisement -

በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ፓርላማ ውስጥ ተቀስቅሶ ለነበረው ውዝግብ በሰጡት ምላሽ የፌዴራል መንግሥት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ ከፈለጉ ‹‹ክልሎች ሊያቃጥሉት ይችላሉ›› ብለው ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ድጎማ ክልሎች እንዴት እንደተጠቀሙበት ወይም በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋሉ የመቆጣጠር ሥልጣን እንደሌለው እሳቸው ከገለጹ በኋላ፣ ዋና ኦዲተሩ ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ የተመለከተ ኦዲት ማድረግ አቋርጦ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል ቀርቦ የነበረው ረቂቅ አዋጅ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94(2) ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ ለኦዲት ክፍተቱ መፍትሔ ለማድረግ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም፣ እንደገና በምክር ቤቱ አባላት መካከል ውዝግብ መከሰቱን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።

 በወቅቱ ቀርቦ በነበረው ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ አንቀጽ 5(2) ላይ ‹‹የፌዴራል መንግሥት ለክልል መንግሥታት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማዎች ኦዲት ያደርጋል፣ ያስደርጋል፤›› የሚል ድንጋጌ የያዘ ነበር፡፡

የ2008 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን አጠናቆ ለእረፍት ተበትኖ የነበረው ፓርላማ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ በተደረገለት ጥሪ መሠረት፣ ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በተሰበሰበበት ወቅት ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል ይህ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያን የሚያሻሽለው ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነበር።

በወቅቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት  መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) በረቂቅ አዋጁ ላይ ያደረጉትን ዝርዝር ምልከታና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ለክልል መንግሥታት የሚሰጠውን ድጎማ ኦዲት የማድረግ ሥልጣኑ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ፣ የረቂቅ አዋጁም ድንጋጌ ከዚሁ ጋር እንዲጣጣም ሆኖ መቅረቡን ገልጸው ነበር።

ነገር ግን ማብራሪያውን ያልተቀበሉ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት፣ ዋና ኦዲተር እንዴት ነፃ የሆኑ ክልሎችን የበጀት አጠቃቀም ኦዲት ሊያደርግ ይችላል የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው አለመግባባት ተከስቶ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት መስፍን (አምባሳደር) ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ በሦስተኛው የፓርላማ ዘመን ተመሳሳይ አለመግባባት ተነስቶ እንደነበር በማስታወስ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለመስጠት ጥያቄውን በመያዝ ከአስረጂ ባለሙያዎች ጋር መወያየታቸውን፣ በውይይቱ ወቅትም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውና ተያያዥ ሕጎችም አብረው መታየታቸውን ገልጸው ነበር።

‹‹በቋሚ ኮሚቴ ደረጃ የደረስንበት ድምዳሜ ማሻሻያ አንቀጹ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተጣጣመ መንገድ እንዲቀመጥ፣ ነገር ግን በሌሎች መንገዶች ክልሎች በራሳቸው የተጠናከረ ኦዲት ሊያደርጉ የሚችሉበትን አሠራር መከተል እንደሚገባ፣ ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር ስምምነት ተደርሷል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተው ነበር።

በወቅቱ በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በጉዳዩ ላይ የሰጡት ማብራሪያ፣ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ የሚያሳይ ነበር። አቶ አስመላሽ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየትም የፓርላማ አባላት ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን፣ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መስፍን (አምባሳደር) በሕገ መንግሥቱ ላይ ድጎማን ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የዋና ኦዲተር መሆኑ በግልጽ ስለመቀመጡ የተናገሩት ልክ መሆኑን በአጽንኦት ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ እንደ ሙሉ ማዕቀፍ (Package) ነው መታየት ያለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተመሠረተው በፌዴራሊዝም መርህ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ሁሉ ነገር መነሻ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የተመሠረተው ክልሎች ቆርሰው በሰጡት ሥልጣን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያው ጀምሮ የክልሎችን ነፃነት፣ እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥትም ሥልጣን የሰጡት እነሱ መሆናቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሰጠውን ድጎማ እየሄደ ኦዲት ያደርጋል የሚለው ትክክል አለመሆኑን፣ ለምክር ቤቱ አስረድተው ነበር፡፡ በማከልም፣ ‹‹የቀረበው ማሻሻያ አዋጅ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የሚለው ዋና ኦዲተር ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማና ድጋፍ በክልል ኦዲተሮች ኦዲት እየተደረገ መሆኑን በመተባበር ክትትል ያደርጋል ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተስማማነውም በዚህ መልኩ ነው፤›› በማለት የመንግሥታቸውን አቋም ስለማብራራታቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡

 ክልሎች ራሳቸውን የቻሉ ብሔራዊ መንግሥታት መሆናቸውን፣ ነፃ ሆነው ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉት ራሳቸው ባወጡት ሕግና አሠራር ብቻ እንደሆነም አቶ አስመላሽ በወቅቱ ተናግረው ነበር። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መስፍን (አምባሳደር) ይኼንኑ የአቶ አስመላሽ ማብራሪያ፣ ‹‹በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ማስተካከል ይቻላል፤›› በማለት የተቀበሉት ሲሆን፣ ምክር ቤቱም አቶ አስመላሽ የሰጡትን ማስተካከያ ሐሳብ ተቀብሎ ረቂቅ አዋጁን አፅድቆት ነበር።

የፀደቀው አዋጅ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲታይ ግን ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍና ልዩ ድጎማ ኦዲት ስለማድረግ የቀረበው ሐሳብም ሆነ፣ አቶ አስመላሽ ያቀረቡት ማሻሻያ ሐሳብ አብሮ አለመታተሙ ተስተውሏል። ይኼንን ስህተት ለመሙላት መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በ2008 ዓ.ም. የፀደቀውን የዋና ኦዲተር አዋጅ ላይ የተወሰኑ አንቀጾችን የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ የቀረበ ሲሆን፣ ይኸውም ዋና ኦዲተር ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጋፍና ድጎማ ላይ ኦዲትና ቁጥጥር እንዲያደርግ የሚፈቅድ ነው።

ይህ ማሻሻያ ለዝርዝር ዕይታ የተመራለት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል። ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ እንደገለጸው በቀደመው የዋና ኦዲተር ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጋፍና ድጎማ ላይ ዋና ኦዲተር ኦዲትና ቁጥጥር እንዲያደርግ ሥልጣን ቢሰጠውም፣ አዋጅ ቁጥር 982/2008 ላይ ይህ ድንጋጌ ሳይካተት በመቅረቱ ያጋጠመውን ችግር ድንጋጌው እንደገና እንዲካተት በማድረግ ክፍተቱን ማስተካከል እንደሚያስችል ገልጿል።

በቀደሙት ዓመታት እንደተነሳው ዓይነት የክርክር ሐሳብ በተመሳሳይ የቀረበ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል።

ምክር ቤቱ በዚህ ቀን ሌሎች አዋጆችንም ያፀደቀ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል መንግሥት በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ላይ የነበረውን የብቸኝነት ሚና ወይም የገበያ ሞኖፖሊ የሚያስቀርና የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች እንዲሳተፉ የሚፈቅደው አዋጅ ይገኝበታል። በተጨማሪም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ አዋጅ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡ አራት የቦርድ አባላት ሹመት በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ስምንት ዕጩዎች መካከል የአራቱ ሲፀድቅ፣ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በቦርድ ሰብሳቢነት ቀጥለዋል፡፡ በተጨማሪም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋናና ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ዳኞች ሹመት በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡ ሁሉም ተሿሚዎች በምክር ቤቱ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...