Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያን በቅርቡ የተቀላቀለው አኩሪ አተር በ100 ቀናት ግብይት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አስመዘገበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቅርቡ ወደ ግብይት ሥርዓቱ ያስገባው አኩሪ አተር፣ በ100 ቀናት ውስጥ የ5,700 የግብይት ዝውውሮች አማካይነት 76 ሺሕ ቶን ምርት በ1.05 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን አስታወቀ፡፡

ምርት ገበያው የአኩሪ አተርን የ100 ቀናት የግብይት ክንውንና የግንቦት ወር አጠቃላይ የግብይት አፈጻጸሙን በማስመልከት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው መረጃ፣ ወደ ግብይት መድረኩ ከመጣ የወራት ዕድሜ ያስቀጠረው አኩሪ አተር በአጭር ጊዜ ቆይታው ከአንድ ቢሊዮን ብር ላይ የግብይት ክንውን ማስመዝገብ እንደቻለ ይገልጻል፡፡ በ100 ቀናት ውስጥ ከተገበያየው ጠቅላላ የአኩሪ አተር ምርት ውስጥ፣ 48 ሺሕ ቶን የጎጃም አኩሪ አተር በ668 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ፣ 24 ሺሕ ቶን የአዶሳ አኩሪ አተርም በ353 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ አራት ሺሕ ቶን የጎንደር አኩሪ አተር በ58 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ስምንት ቶን የወለጋ አኩሪ አተር በ79 ሺሕ ብር ተሸጧል፡፡

የአኩሪ አተር ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ እያደገ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚገባው የምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቅበላ አቅሙን በማጠናከርም በቡሬ፣ በጎንደር፣ በፓዌ፣ በሳሪስና በነቀምት በሚገኙት የምርት መቀበያ መጋዘኞች ምርቱን እየተቀበለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በግንቦት ወር 14,583 ቶን አኩሪ አተር ለግብይት ቀርቦ በ231.29 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ በግብይቱም የጎጃም አኩሪ አተር 63 በመቶ የግብይት መጠንና የግብይት ዋጋን በማስመዝገብ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው፡፡ አማካይ የአኩሪ አተር የግብይት ዋጋ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር 15.43 በመቶ ከፍ ማለቱንም የምርት ገበያው መረጃ ያመለክታል፡፡

ምርት ገበያው በግንቦት ወር 29,382 ቶን ቡና፣ 14,583 ቶን አኩሪ አተር፣ 8,902 ቶን ሰሊጥና 2,213 ቶን ነጭ ቦሎቄ በአጠቃላይ 55,080 ቶን ምርት በ2.79 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡ ቡና 53 በመቶና 70 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ የወሩን የግብይት ድርሻ ይዟል፡፡ የቡና የግብይት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ0.66 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በወሩ ሁሉም የቡና ዓይነቶች ግብት የተከናወነ ሲሆን፣ ለውጭ ገበያ የቀረበ ቡና 69 በመቶ የግብይት መጠንና 67 በመቶ የግብይት ዋጋ በመያዝ የግብይት ድርሻውን ሸፍኗል፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ ቡናና ስፔሻሊቲ ቡና ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለውጭ ገበያ የቀረበ ያልታጠበ 19 ሺሕ ቶን ቡና ለግብይት ቀርቦ በ1.2 ቢሊዮን ብር ሲገበያይ፣ ከዚህ ውስጥ በግብይት መጠን የጊምቢ ቡና 21 በመቶ እንዲሁም የቄልም ወለጋ ቡና 18 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው ታውቋል፡፡

እንዲሁም 1,468 ቶን ለውጭ ገበያ የቀረበ የታጠበ ቡና በ87.97 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ በግብይት መጠን የሲዳማ ቡና 37 በመቶ፣ የይርጋ ጨፌ ቡና 25 በመቶ፣ የምዕራብ አርሲ ቡና 12 በመቶ በማስመዝገብ ተከታታይ የግብይት ድርሻን ይዘዋል፡፡

በተጠቀሰው የግንቦት ወር በ340 ሚሊዮን ብር ከተገበያየው 4,125 ቶን የስፔሻሊቲ ቡና ውስጥ 1,025 ቶን ያልታጠበ ቡና በ110.9 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 3,101 ቶን ያልታጠበ ስፔሊቲ ቡና በ229 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡

በምርት ገበያው መረጃ መሠረት 21 የግብይት ቀናት በነበሩት የግንቦት ወር 8,902 ሰሊጥ ለግብይት ቀርቦ በ563.46 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ በወሩ ውስጥ ለግብይት ከቀረበው የሰሊጥ ምርት ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ የያዘው የሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ ነው፡፡ ከጠቅላላ ግብይት ከተፈጸመበት የሰሊጥ ምርት ውስጥ 72 በመቶ የግብይቱን መጠን የያዘው የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ ሲሆን፣ አጠቃላዩ የሰሊጥ ግብይት ከተፈጸመበት ዋጋ ውስጥ ደግሞ 74 በመቶ የሚሆነውን የግብይት ዋጋ ሊያዝ ችሏል፡፡

የግንቦት ወር የሰሊጥ ግብይትና የግብይት ዋጋ ቅናሽ አለው፡፡ የሰሊጥ የግብይት መጠንና ዋጋ ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ54 በመቶና በ45 በመቶ ቅናሽ ቢያሳይም፣ አማካይ የግብይት ዋጋው ግን 18 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የሰሊጥ የግብይት ዋጋ በ44 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም፣ የግብይት መጠኑ ግን የስድስት በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ እንዲሁም አማካይ የግብይት ዋጋው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ53 በመቶ ጭማሪ እንደነበረው ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በወሩ ውስጥ 2,213 ቶን ድቡልቡል ነጭ ቦሎቄ በ48.52 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በግብይት መጠንና ዋጋ በ43 በመቶና በ34 በመቶ ቅናሽ ቢያስመዘግብም፣ አማካይ የግብይት ዋጋው ግን በ14.86 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የቦሎቄ አማካይ የግብይት ዋጋ 39 በመቶ እንደጨመረ መረጃው ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች