Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤምሬትስ አየር መንገድ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ከዋሉ ፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሠሩ ብርድ ልብሶችን ለተሳፋሪዎች አቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመጪው ዓመት ለብርድ ልብስነት የዋሉ 88 ሚሊዮን ፕላስቲክ ጠርሙሶችን ይጠቀማል

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አየር መንገድ ኤምሬትስከፕላስቲክ ጠርሙሶች መልሰው የተሠሩ ዘላቂ ብርድ ልብሶች ልብሶችን ለተሳፋሪዎቹ ማቅረብ እንደጀመረ አስታወቀ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ከዋሉ ፕላስቲክ ጠርሙሶች የተፈበረኩት ብርድ ልብሶቹ ሙቀት የሚሰጡና ልስላሴ ያላቸው ሲሆኑ፣ ምርቶቹን የታይላንዱ ኢኮትሬድ የተሰኘ ኩባንያ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሆኑ አየር መንገዱ ጠቅሷል፡፡

ብርድ ልብሶቹ በአብዛኛው በረዥም ጉዞዎች ወቅት ለሚደረጉ በረራዎች እንደሚውሉና በኢኮኖሚ ክፍልም እንደሚቀርቡ ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ እያንዳንዱ የኢኮትሬድ ብርድ ልብስም ከ28 ጥቅም ላይ ከዋሉ ፕላስቲክ ጠርሙሶች መልሰው እንደሚመረቱ ተጠቅሷል፡፡

በዘመናዊ ቴክሎጂዎች አማካይነት ፕላስቲክ ጠርሙሶቹ ወደ ቁርጥራጭነት ከዚያም ወደ ክርነት የሚለወጡበት አሠራር፣ ወደ ጨርቅነት ከተቀየረ በኋላ ለብርድ ልብስነት የተዘጋጀው ይኼው ጨርቅ ከዚያው ከፕላስቲኩ በተሠራ ክር እንደሚሰፋ ተብራርቷል፡፡

አየር መንገዱ ለሚያራምደው የአረንጓዴ ዘመቻ ተስማሚ ሆነው ያገኛቸውንና ለአካባቢ ብክለት መቀነስም አስተዋጽኦ የሚያበረክቱትን የፕላስቲክ ጠርሙሶች በሁሉም በረራዎቹ እያቀረበ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ በአሁኑ ወቅትም ከአልሙኒየም ቆርቆሮዎች የተሠሩ መጠጫዎችን የፕላስቲክና የመስታወት ጠርሙስዎች፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ካርቶኖችን ከመሳሰሉ የወረቀት ምርቶች መልሶ በማሠራት እየተጠቀመ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡

2012 ዓ.ም. አጋማሽ የኤምሬትስ ኢኮትሬድ ብርድ ልብሶች 88 ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመጠቀም ወይም በሌላ አገላለጽ 44 የA380 አውሮፕላኖችን ክብደት የሚመዝኑ ፕላስቲኮችን በመጠቀም አካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጫና እንደሚታደግ ይጠበቃል፡፡ ይህን ዓይነት አካሄድ መከተሉም በአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀዳሚ እንደሚያደርገው ኩባንያው አስታውቋል፡፡

መልሰው ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ የፖሊቴሊን ቴሬፓታሌት (ፒኢቲ) የተሰኘ የጨርቅ ምርት ለማምረት ከማስቻላቸው ባሻገር፣ 70 በመቶ የኃይል ፍጆታ ለመቀነስ እንደሚያስችሉ ታምኖባቸዋል፡፡ኢኮትሬድ ምርቶች ‹‹ኢንተርቴክ ግሪን ሊፍ ማርክ›› በተሰኘ ገለልተኛና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጪ አካል በተደረጉ ፍተሻዎች መቶ በመቶ መልሰው ከተሠሩ ቁሳቁሶዎች መፈብረካቸውን አረጋግጧል፡፡

 የኤምሬትስ ኢኮትሬድ ብርድ ልብሶች በኢኮኖሚ ክፍል ብቻም ሳይሆን፣ በአንደኛ ደረጃና ለቢዝነስ ክፍሎችም እንደሚቀርቡ ሲገለጽ፣ ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ ከበግ ቆዳ የተሠሩ ብርድ ልብሶችንም ለአንደኛ ደረጃ ብሎም ቱታዎችንም ለቢዝነስ ክፍል በማለት አስተዋውቋል፡፡

ባለፈውመት ኤምሬትስ ለኢኮኖሚ ክፍልን ለሚጠቀሙ ደንበኞች የተለዩ ምርቶችን አካቶ በተጨማሪም በዓላማችን የመጀመርያው ተግባቢ የዕቃ መያዣ ቦርሳዎችንም ማቅረብ ጀምሯል፡፡

ቦርሳው በእንቅልፍ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል የዓይን መሸፈኛ፣ ድምፅ እንዳይረብሽ የጆሮ መድፈኛ፣ የጥርስ ቡርሽና ሳሙናን ጨምሮ ሌሎችም አቅርቦቶችን በኢኮኖሚ ክፍል እንዳቀረበ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የኤምሬትስ ኢኮኖሚ ክፍሎች 13.3 ኢንች የወንበር ቴሌቪዥን ስክሪኖች በመያዝና 2,500 በላይ ቻናሎችን በማንኛውም ረዥም በረራ ወቅት በማቅረብእንዲሁም አይስ ዲጂታል ዋይድ ስክሪን የተባለውን ተሸላሚ የበረራ መዝናኛ አገልግሎት እንዲቀርብ በማድረግ በአገልግሎቱ ልዩነት እየፈጠረ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ዱባይ በሚደረጉ ጉዞዎች ወቅት፣ የቲኬት ዋጋና ሌሎችም የኤርፖርት አገልግሎቶች ላይ በተለይ ከኢትዮጵያውያን መንገደኞች በየጊዜው ጥያቄዎች ሲነሱ ይደመጣል፡፡ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች ላይ የአየር መንገዱ ኃላፊዎች ከሪፖርተር ተጠይቀው ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች