Friday, May 24, 2024

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ማሻሻያና ይዞት የመጣው ጦስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሥራ ላይ ከዋለ 24 ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ ተቃርኖ ያላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሻሻል፣ የተቀሩት ደግሞ ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበሉትና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበትና የሚቀበሉት አዲስ ሕገ መንግሥት ይጠይቃሉ፡፡ ይህ የሚሆንበትንም ወቅት ይናፍቃሉ። የሕገ መንግሥቱ አመንጪ የሆነው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በበኩሉ፣ ሕገ መንግሥቱ ምሉዕ እንደሆነና ከ16 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውበት የበለፀገና ብሔር ብሔረሰቦች ለህልውናቸው ሲሉ ፈቅደው ይሁንታቸውን የሰጡት የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን በመግለጽ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ ለድርድር እንደማይቀመጥ በተደጋጋሚ በይፋ የሚገልጸው የዓመታት አቋሙ እንደነበር ይታወሳል።

ሕገ መንግሥቱ ስለሚሻሻልበት ሁኔታ ወይም የማሻሻያ ሥነ ሥርዓቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሠፍረው የሚገኙ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ ጉዳዩን አስመልክቶ በይፋ በሚገልጸው የፀና አቋሙ ምክንያት ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚፈልጉ ፖለቲከኞች ሕጋዊ የማሻሻያ ሥነ ሥርዓቶችን በመከተል ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እንኳን ሞክረው አለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከገዥው ፓርቲ በወጡ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች አመንጪነት ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ እንደሚያውቅ ሞግተው አያውቁም። በእርግጥ ሕገ መንግሥቱ የተሻሻለበት መንገድ የተድበሰበሰና እስከ ዛሬም ድረስ የተሻሻለውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አለመውጣቱ ስለሕገ መንግሥቱ መሻሻል ዜጎች መረጃም ሆነ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው አድርጓል።

 የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ እንዴትና መቼ ተሻሻለ?

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ንዑስ አንቀጽ አምስት ላይ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ እንደሚካሄድ ተደንግጓል። በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ሦስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ የነበረበት በ1997 ዓ.ም. ነበር። ይሁን እንጂ በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በዚያው ዓመት ከሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በመገጣጠሙና ሁለቱንም ኃላፊነቶች በአንድ ዓመት ለማካሄድ የሚጠይቀውን ከፍተኛ የበጀት ፍላጎት መንግሥት ወጪ ለማድረግ አቅም ያልነበረው በመሆኑ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በመንግሥት ይወሰናል። ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) መሠረት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ እንዲካሄድ የተደነገገ በመሆኑ፣ በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበትን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወደ ሌላ ጊዜ ለመግፋት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ማሻሻል የግድ ይጠይቅ ነበር። በመሆኑም ይኼንን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ በ1996 ዓ.ም. እንዲሻሻል ተደርጓል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 105

የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች እንዲሻሻሉ ባስፈለገበት ጊዜ የሚሻሻሉባቸውን ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቶች በግልጽ ደንግጓል። በዚህ አንቀጽ ከተደነገጉት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥነ ሥርዓቶች መካከል በንዑስ አንቀጽ ሁለት ሥር የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበትን የጊዜ ወሰን በተመለከተ የሠፈረውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) ለማሻሻል የሚጠቀስ ነው።

ይህ ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩትን መብቶችና ነጻነቶች እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል የሚገልጸው አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን ድንጋጌዎች ለማሻሻል የሚቻለው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁትና ከፌዴሬሽኑ አባል ክልል ምክር ቤቶች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁት እንደሆነ ይደነግጋል።

በ1996 ዓ.ም. የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከላይ የተገለጸውን መሥፈርትና ሥነ ሥርዓት ስለማሟላቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሒደቱን የተከታተሉ የሕግ ባለሙያ እንደሚሉት፣ የተጠቀሰውን አንቀጽ የተሻሻለው በጥድፊያ እንደነበርና ሥነ ሥርዓቱ እንዲሟላ ሲባል ብቻ የክልል ምክር ቤቶች በቅጡ በጉዳዩ ላይ ሳይመክሩ የማሻሻያ ሐሳቡን በመቀበል ውሳኔ ማሳለፋቸውን የሚገልጽ ኦፊሴላዊ ደብዳቤ ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መላካቸውን፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ የክልል ምክር ቤቶች በጉዳዩ ላይ ስለመወያየታቸው ይጠራጠራሉ። በዚህ መንገድ በጥድፊያ ሥነ ሥርዓቱን ለማሟላት ሩጫ ከመደረጉ በዘለለ ግንዛቤ የተሞላበት ምክክር ተደርጓል ማለት እንደማይቻል ያስታውሳሉ።

 በመሆኑም የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም የሁሉም ክልሎች ምክር ቤቶች በተናጠል ባካሄዱት ስብሰባ የቀረበላቸውን የውሳኔ ሐሳብ በማፅደቅ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበት የጊዜ ወሰንን በተመለከተ የሚደነግገውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) እንዲሻሻል አድርገዋል።

ነባሩ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5)፣ ‹‹የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል። በውጤቱም መሠረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስናል፤›› የሚል ሲሆን፣ ማሻሻያው ደግሞ ‹‹የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል፣ ሆኖም ቆጠራውን ለማካሄድ ከአቅም በላይ ችግር ስለመኖሩ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ ካረጋገጡ የቆጠራው ዘመን እንደ ሁኔታው ሊራዘም ይችላል፤›› በማለት የአንቀጹን ይዘት አሻሽሏል።

ጉዳዩን በጥልቀት የተከታተሉት እኚሁ የሕግ ምሁር ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ በወቅቱ የተደረገው ማሻሻያ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ሕገ መንግሥታዊ መሥፈርት ተከትሏል ለማለት እንደማይቻል ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም አንድ አዋጅ ሲወጣም ሆነ ሲታወጅ ሕዝብ ሊያውቀው ስለሚገባ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ በመንግሥት ላይ የሕግ ግዴታ መጣሉን በመከራከሪያነት ያቀርባሉ።

ከሞላ ጎደል በአገሪቱ የወጡት ሕጎች በሙሉ የመጨረሻ ገጾቻቸው ላይ ‹‹በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል›› የሚል ድንጋጌ የሚይዙት፣ በዚህ መርህ መሠረት መሆኑን በማንሳት ይከራከራሉ።

ክርክራቸውን ለማጠናከርም በ2008 ዓ.ም. ተሻሻሎ በድጋሚ የታወጀውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 ይጠቅሳሉ።

በዚህ ደንብ አንቀጽ 59 ላይ፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚኖርበት ጊዜ እያንዳንዱ ማሻሻያ ቁጥር ተሰጥቶት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ መታተም ይኖርበታል፤›› የሚል ድንጋጌ መያዙን፣ በቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ ሥር ደግሞ፣ ‹‹እያንዳንዱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚታተመው ሕገ መንግሥት መጨረሻ ላይ ‹ማሻሻያ› የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ይካተታል፤›› የሚል ድንጋጌ መቀመጡን፣ ነገር ግን ከ13 ዓመታት በፊት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) ላይ የተደረገው ማሻሻያ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሠረት የታተመ ነጋሪት ጋዜጣ፣ ወይም ማሻሻያው ተካቶበት የታተመ ሕገ መንግሥት አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበትን የጊዜ ወሰን የተመለከተው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የተሻሻለበት መንገድ፣ ሕጋዊ ቅቡልነት ነበረው ለማለት እንደሚቸገሩ የሕግ ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ሦስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለሁለት ዓመት ያህል ተገፍቶ በ1999 ዓ.ም. ተካሂዷል።

በአንቀጹ መሻሻል የተከተለው ጦስ

ከላይ የተገለጸውን ሒደት አልፎ ሦስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. በመካሄዱ፣ ቀጣዩና አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተሻሻለው አንቀጽ መሠረት ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ካልተፈጠረ በ2009 ዓ.ም. ሊካሄድ ይገባው ነበር። ነገር ግን አገሪቱ በሕዝባዊ የፖለቲካ ጥያቄዎችና ከዚሁ ጋር ተቆራኝቶ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረው የውስጥ ትግል ምክንያት፣ በ2009 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበትን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ያስታወሰው የመንግሥት አካል አልነበረም ማለት ይችላል፡፡ ይህን ማለት ስህተት ከሆነ ደግሞ በተሻሻለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ መሠረት ቆጠራውን በ2009 ዓ.ም. ለማካሄድ ነባራዊ ሁኔታው አይፈቅድም ተብሎ፣ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ሊራዘም ይገባ ነበር። ነገር ግን ይህ በ2009 ዓ.ም. አልሆነም። ዘግይቶሞ ቢሆን ቆጠራውን ለማካሄድ ሥልጣን የተሰጠው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ በ2010 ዓ.ም. እንደሚካሄድና ለዚህም የሚረዳ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ አስታውቆ ነበር። ቢሆንም በኢሕአዴግ ውስጥ የተቀሰቀሰው ፖለቲካዊ ትግል ተቀጣጥሎ የመጨረሻ ውጤቱ ኢሕአዴግ ውስጥ ተወልደው ባደጉት ተራማጅ ኃይሎች ድል አድራጊነት በመጋቢት 2010 ዓ.ም. እስኪጠናቀቅ ድረስ ቆጠራው መቼ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

የኢሕአዴግ ፈጣሪና ጭንቅላት እንደሆነ የሚነገርለት የሕወሓት ስብስብ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በኢሕአዴግ ውስጥ ይዞ የቆየውን የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና፣ በመጋቢት በተጠናቀቀው የውስጥ ትግል በፓርቲው ተራማጅ ኃይሎች መነጠቁ ይታወሳል። ድሉን የተቀዳጀው ተራማጅ ኃይል ሥልጣን በያዘ ማግሥት በቅድሚያ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራን ጉዳይ መልክ ማስያዝ አንዱ ነበር። የተሰጠው ትኩረት ግን ሕጋዊነትን የተመለከተ እንጂ፣ ቆጠራው በዚያው ዓመት እንዲካሄድ የሚያስችል አልነበረም። በመሆኑም በ2010 ዓ.ም. ይካሄዳል የተባለው የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲራዘም የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ በኮሚሽኑ አማካይነት፣ ሚያዚያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ለውሳኔ እንዲቀርብ ተደርጓል። ኮሚሽኑ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ቆጠራውን ለማካሄድ ሙሉ በሙሉ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ገልጾ፣ በአገሪቱ ያለው ነባራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋትና በዚህም የተነሳ በበርካታ አካባቢዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከዬአቸው በመፈናቀላቸው፣ እንዲሁም በወቅቱ በመንግሥት ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ቆጠራውን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ዓለም አቀፍ መሠረት ባለመሟላቱ ቆጠራው ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲተላለፍ የሚጠይቅ ነበር።

 ኮሚሽኑ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ለመወሰን ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔያቸውን ከማካሄዳቸው በፊት፣ በተናጠል በየራሳቸው ምክር ቤት ጥያቄውን በያዘው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይተው የነበር። ሁለቱም ምክር ቤቶች በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ውይይት ጎልቶ የተነሳው የክርክር ሐሳብ፣ ኮሚሽኑ ቆጠራው የሚካሄድበት ጊዜ እንዲተላለፍለት ስላቀረባቸው ምክንያቶች አሳማኝነት ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ቆጠራው የሚካሄደው በየአሥር ዓመቱ መሆኑን ደንግጎ ሳለ ቆጠራውን ለማስተላለፍ እንዴት እንደሚቻል ነበር። ይህም ማለት ቆጠራ የሚካሄድበትን የጊዜ ወሰን የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ስለመሻሻሉ በቂ መረጃ እንዳልነበራቸው የሚያስረዳ ነው። በወቅቱ በተለይም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተካሂዶ የነበረው ውይይት ጠንከር ያለ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። በፌዴሬሽን ምክር ቤት በወቅቱ የተካሄደው ውይይት በ1997 ዓ.ም. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) ላይ የተደረገው ማሻሻያ ሕግ ሆኖ ባለመፅደቁ፣ አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲራዘም በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ምክር ቤቱ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ንዑስ አንቀጽ አምስት ሊያሻሻል እንደሚገባ ክርክር ቀርቦበት ነበር።

 በተነሳው ክርክር መግባባት ባለመቻሉ ወደ ድምፅ መስጠት ሒደት ተሸጋግሮ ቆጠራው ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲተላለፍ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በ90 ድጋፍ፣ በአሥር ተቃውሞና በሦስት ድምፀ ተዓቅቦ መፅደቁን መዘገባችን አይዘነጋም።

በተመሳሳይ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብና የቤት ቆጠራን ወደ 2011 ዓ.ም. ለማራዘም በቀረበው የኮሚሽኑ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተመሳሳይ ክርክር ተደርጎበታል። በምክር ቤቱ የተነሳው ክርክር በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተደረገው ጋር ተመሳሳይ የነበረ ሲሆን፣ ይኸውም በ1997 ዓ.ም. የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕጋዊ አለመሆኑን በማውሳት ክርክር የተደረገበት ነበር። ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሟላት ስለሚገባቸው የሕግ ሥነ ሥርዓቶች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መሥፈሩን ያነሱ አንድ የምክር ቤቱ አባል፣ በ1997 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱ የተሻሻለበትን መንገድና መሻሻሉ በነጋሪት ጋዜጣ ባለመታወጁ እንደማይቀበሉት ገልጸው፣ ‹‹ፓርላማው ነው ለሕገ መንግሥቱ ተጠሪ? ወይስ ሕገ መንግሥቱ ነው ለፓርላማው ተጠሪ የሆነው?›› ሲሉ ተቃውሟቸውን በጥያቄ አቅርበው ነበር።

 በወቅቱ የፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አማኑኤል አብረሃ ማሻሻያው አለመታተሙ ስህተት እንደሆነና በፍጥነት እንዲታተም እንደሚደረግ፣ ነገር ግን ማሻሻያው በሕጉ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል። የፓርላማው የተናጠል ስብሰባ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በሦስት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል። ከዚህ ሒደት በኋላ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበትን ጊዜ ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ቀርቦ፣ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ መፅደቁ ይታወሳል።

 ይህ አወዛጋቢ ሒደት ከታለፈና 2011 ዓ.ም. ከጠባ በኋላ የሕዝብና ቤት ቆጠራው በመጋቢት ወር እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት፣ ቆጠራውን ለማካሄድ የሚረዱ የሎጅስቲክስ ሥነ ሥርዓቶች ተፈጽመው ቆጠራውን ለማካሄድ ከሁለት ሳምንት ያጠረ ጊዜ ሲቀረው፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በድጋሚ ቆጠራውን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን በመግለጽ እንዲተላለፍ ወስኗል።

 በተሻሻለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) መሠረት ቆጠራ የሚካሄድበትን ጊዜ የማስተላለፍ ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ በመጋቢት ወር ቀን የተቆረጠለትን ቆጠራ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ እንደሌለ በመወሰን ያሳለፈው ውሳኔ፣ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ እንዲፀድቅለት ጥያቄውን ያቀረበው ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር።

ሁለቱ ምክር ቤቶች ኮሚሽኑ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የጋራ ጉባዔ ከማካሄዳቸው በፊት በተናጠል በየምክር ቤቶቻቸው መክረውበታል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቆጠራው ወደ 2012 ዓ.ም. እንዲራዘም በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ባደረገው ውይይት የተደመጠው የልዩነት ድምፅ ቆጠራውን ወደ 2012 ዓ.ም. ማራዘም በዚያው ዓመት ከሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲጋጭ የሚያደርገው በመሆኑ ውድቅ ሊሆን ይገባል የሚል ነበር። ይህ የልዩነት ሐሳብ የተደመጠው ሕወሓትንና የትግራይ ክልልን በወከሉ ምክር ቤት አባላት ነው። ቆጠራው ሊራዘም አይገባም ያሉት እነዚህ ተወካዮች ቆጠራው እንዲራዘም የተፈለገው በ2012 ዓ.ም. የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በወቅቱ እንዳይካሄድ የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል። በተጨማሪም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) ተሻሽሏል ቢባል እንኳን ስለመሻሻሉ በነጋሪት ጋዜጣ ባለመታወጁ ሕጋዊ ተቀባይነት እንደማይኖረውና ምክር ቤቱ የቀረበውን ውሳኔ መቀበል የለበትም በማለት የተከራከሩ ቢሆንም፣ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የምክር ቤቱ አባላት አቋም በድምፅ እንዲለይ ተደርጎ በስምንት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው የተናጠል ውይይት የትግራይ ክልልን የወከሉ የሕወሓት አባላት ተመሳሳይ መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል። ይኸውም የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ መሆኑንና እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚመለሱ የሰላም ሚኒስቴር መግለጹን በማስታወስ፣ ቆጠራው መራዘም እንደሌለበት ተከራክረዋል። በዋናነት የነበረው መከራከሪያ ቆጠራውን ወደ 2012 ዓ.ም. ማራዘም በዚያው ዓመት ከሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር ተደርቦ በመንግሥት ላይ ጫና ይፈጥራል፣ ይህም ምርጫውን ለማራዘም የተጠነሰሰ ተንኮል አድርገው እንደሚገነዘቡት በማውሳት ተከራክረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ያደረገውን ውይይት የቋጨው በ24 የተቃውሞ ድምፅና የሶሕዴፓ ተወካዮች በሆኑ ሁለት የምክር ቤት አባላት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ነበር።

በመቀጠልም ሁለቱ ምክር ቤቶች በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ባደረጉት የጋራ ጉባዔ ተመሳሳይ ክርክር፣ ከትግራይ የሕወሓት ተወካይ ሌላ ሐሳብ ተነስቷል። የሕወሓት አባል የሆኑት የትግራይ ክልል ተወካይ አድሀነ ኃይሌ (ዶ/ር) ባቀረቡት ለየት ያለ ሐሳብ ቆጠራውን ማራዘም ከምርጫ ማራዘም ጋር ተገናኝቶ በተደጋጋሚ መነሳቱ ትክክል አለመሆኑን፣ እንዲሁም ሁለቱ ሁነቶች የሚገዙት ራሳቸውን በቻሉ የሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አንቀጾች እንደሆነ አስረድተዋል። ቆጠራው ከምርጫው መከናወን ጋር ቀጥተኛ የሆነ ቁርኝት እንዳለው በሕግ አለመቀመጡን አውስተው፣ የጋራ ምክር ቤቱ በዚህ ላይ የሚታየውን ብዥታ በዚሁ አጥርቶ እንዲያልፍ ጠይቀዋል።

ይኼንን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የተነሳው ሐሳብ ትክክል እንደሆነ፣ የጋራ ምክር ቤቶቹ የቀረበላቸው የውሳኔ ሐሳብ ቆጠራውን ስለማራዘም ብቻ እንደሆነና ምርጫን አስመልክቶ የሚቀርብ ነገር ካለ በወቅቱ እንደሚታይ አስረድተዋል።

በስተመጨረሻ ክርክሩ በድምፅ እንዲቋጭ ተወስኖ ቆጠራው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በ30 ተቃውሞ፣ በሦስት ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -