Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቆዳ ኢንዱስትሪው በመንታ መንገዶች መካከል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቂት ቀናት በፊት በአገሪቱ የቆዳ ኢንዱስትሪ ላይ ውይይት ተካሄዶ ነበር፡፡ የውይይቱ መነሻም መንግሥት ለዘርፉ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን በማስመልከት በረቂቅ ሰነዱ ላይ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ለመመካከር የጠራው ስብሰባ ሲሆን፣ በቆዳ ኢንዱስትሪው መስክ በተለይ የእሴት ጭማሪ ፖሊሲ መውጣቱን ተከትሎ በዘርፉ የታዩ ችግሮች ላይ የተደረገው ክርክር ሰፊ ቦታ ወስዷል፡፡

በሚያዝያ ወር መካተቻ ሳምንት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተጠራው ስብሰባ፣ በሚኒስቴሩ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የተሳተፉበት ፍኖተ ካርታ ጭምቅ ሐሳብ ቀርቦም ነበር፡፡ በውይይቱ ወቅት በሁለት ጎራ ያከራከረው የመንግሥት የእሴት ጭማሪ ፖሊሲ ከስድስት ዓመታት በላይ በሥራ ላይ ቢቆይም፣ መንግሥት ፖሊሲ ላይ ለውጥ ማድረጉና ከስድስት ዓመታት በፊት የነበረውን አሠራር በከፊል ለመመለስ የተገደደበት ችግር ውስጥ መግባቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የእሴት ጭማሪ ፖሊሲው ከኢትዮጵያ በከፊል የተዘጋጀ ቆዳ ብሎም ጥሬ ቆዳና ሌጦ ወደ ውጭ እንዳይላክ የሚከለክል ነበር፡፡ ክልከላውም በታክስ አማካይነት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በከፊል የተዘጋጀ ወይም ክረስት እየተባለ የሚጠራው የቆዳ ዓይነትን ጨምሮ ከጥሬ ቆዳና ሌጦ በመጠኑ የተዘጋጁ ዌት ብሉና ፒክል የተሰኙ የበግና የፍየል ቆዳዎችን ወደ ውጭ መላክ የሚፈልግ ቆዳ ፋብሪካ በእያንዳንዱ የምርት ዓይነት ላይ የ150 በመቶ ታክስ እንዲከፍል የሚያስገድድ ፖሊሲ ሲተገበር ቆይቷል፡፡

የፖሊሲውን መውጣት ተከትሎም ቆዳ ፋብሪካዎች ተቃውሞ ሲያቀርቡ፣ አንዳንዶቹም ህልውናቸው ማብቃቱን ሲያስታውቁ ተደምጠዋል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በቀላል ማኑፋክቹሪንግ ዘርፍ በተለይም በቆዳና በቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የቀላል ኢንዱስትሪ ማዕከል የመሆን ህልሟን ለማሳካት እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ማምረቱ ላይ እንደምታተኩር ሲገለጽና ሲነገር ቆይቷል፡፡

በቆዳ ኢንዱስትሪው ላይ የእሴት ጭማሪ ፖሊሲው ሲተገበር ታሳቢ የተደረጉ ወሳኝ ጉዳዮች ባለመሟላታቸው ሳቢያ ፖሊሲው የሚፈለገውን ውጤት እንዳያስገኝ እንቅፋት ሆነውበታል የሚሉ በአንድ ወገን፣ የለም ፖሊሲው በተለይም የአገር ውስጥ ቆዳ ፋብሪካዎችን እንዲዘጉና ከገበያው እንዲወጡ በማድረግ ለውጭ ኩባንያዎች ያደላ አሠራር ለማስፈን የመጣ ነው የሚሉት በሌላ ረድፍ ሆነው በተከራከሩበት መድረክ ላይ መንግሥት በተለይም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፖሊሲ ለውጡን ይፋ አድርጓል፡፡

ከስድስት ዓመታት በላይ ሲሠራበት የቆየው የምርት እሴት መጨመሪያ ፖሊሲ፣ በአሁኑ ወቅት ማሻሻያ ተደርጎበት በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወይም ክረስት በአገር በቀል አምራቾች አማካይነት ወደ ውጭ እንዲላክ መፍቀዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረኢየሱስ አስታውቀዋል፡፡ የመንግሥት ዕርምጃ በዚህ ብቻ ላይወሰን እንደሚችል ይልቁንም በከፊል የተዘጋጀ ቆዳና ሌጦም የ150 በመቶ ታክስ ተነስቶለት እንደ ቀድሞው ወደ ውጭ ሊላክ በሚችልበት አግባብ ላይ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ቢባል ቆዳና ሌጦ መፈቀድ የለበትም፣ አለበት የሚል ክርክር መነሳቱንና የዘርፉ ተዋንያን በሚስማሙበት ሐሳብ መንግሥትም እንደሚስማማ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

ከቆዳ ኢንዱስትሪው ተዋንያን መካከል አንዳንዶቹ ዘርፉ ‹‹ሞቷል፡፡ ቆዳው ሞቶ ተቀብሯል፡፡ በወር እስከ 70 ሚሊዮን ብር እናገኝበት ነበር፡፡ ግን ያለቀለት ቆዳ ብቻ ወደ ውጭ ይላክ በመባሉ ቆዳው ወድቋል፤›› ያሉት የኮልባ ቆዳ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ አየለ ደጀኔ ናቸው፡፡ ኮልባ ቆዳ ፋብሪካ በቀን ከ6,000 በላይ የበግ ቆዳ (ፒክል) እና የፍየል ሌጦ (ዌትብሉ) በማዘጋጀት ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ቢኖረውም፣ በመንግሥት ፖሊሲ ሳቢያ ይህንን ማከናወን ሳይቻለው እንደቆየ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት መንግሥት በከፊል ያለቀለትን ቆዳ ብቻም ሳይሆን፣ የበግ ቆዳና የፍየል ሌጦም ወደ ውጭ እንዲወጣ መፍቀድ እንዳለበት አቶ አየለ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥትም የቀድሞውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመቀየር የተገደደበትን ምክንያት በፍኖተ ካርታው ባሰፈረው መሠረት፣ ‹‹ፖሊሲው የተተገበረው አጋዥና ደጋፊ ማበረታቻዎች ሳይደረጉ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ አምራቾች ከለውጡ ጋር መጓዝ ባለመቻላቸው ቀስ በቀስ እየሞቱ ነው፤›› በማለት የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ እንዳስፈለገው ገልጿል፡፡ በዚህም ሳያበቃ፣ የቆዳ ፋብሪካዎች ሲተገበር በቆየው ፖሊሲ ሳቢያ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ ብሎም የወጪ ንግዱ ዘርፍ በየጊዜው እየተዳከመ በመምጣቱ የቀድሞውን ክልከላ ማንሳት እንዳስፈለገው አብራርቷል፡፡

በዚህ ሐሳብ ከሞላ ጎደል የሚስማሙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በአሁኑ ወቅት የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የፕሮጀክት አስተባባሪ በመሆን በሙያቸው እየሠሩ የሚገኙት አቶ ወንዱ ለገሠ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪው ‹‹ሞቷል፣ ተቀብሯል›› የሚለውን እንደማይቀበሉት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ወንዱ መከራከሪያ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪው የሚጠበቅበትን ያህል ላለማደጉ መሟላት የሚገባቸው ድጋፎችና ማበረታቻዎች አለመቅረባቸው እንጂ የእሴት ጭመራ ፖሊሲው ችግር የለበትም፡፡ እንደውም ፖሊሲው በመተግበሩ ምክንያት የአገሪቱ የቆዳ ውጤቶች የምርት አቅም መጨመርና የውጭ ኢንቨስተሮች መምጣት ቁልፉ ያለቀለትና እሴት የተጨመረበት ቆዳ እንዲመረትና ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ በመደረጉ ነው ይላሉ፡፡ ዋቢ የሚያደርጉትም የአገሪቱን የጫማ፣ የጓንትና የቆዳ አልባሳት የወጪ ንግድ መጠን ነው፡፡

የቆዳ ኢንዱስትሪውን ለማሻሻል የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር በ1991 ዓ.ም. ገደማ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረቡን ያወሱት አቶ ወንዱ፣ ዘርፉ ወዳለቀለት ቆዳ፣ ጫማ ወደ ማምረት መሄድ ሲችል መሠረታዊ ለውጥ እንደሚመጣ ባለሙያዎቹ ያመላከቱባቸውን ሰነዶች እያጣቀሱ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹና ማኅበራቸው ያቀረቡት የፖሊሲ ሐሳብ በመንግሥት ተቀባይነት ያገኘው ግን ከ12 ዓመታት በኋላ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የቆዳ ዘርፉ የወጪ ንግድ ለመጀመሪያ ጊዜ 100 ሚሊዮን ዶላር ማስገኘት የቻለው በ2000 ዓ.ም. እንደነበርና ይህም ከምንጊዜውም የዘርፉ አፈጻጸም አኳያ በከፍተኛነቱ የተመዘገበ እንደነበር አቶ ወንዱ አውስተዋል፡፡ የእሴት ጭማሪ ፖሊሲው ሲተገበር ግን በመጀመሪያው የትግበራ ዓመት የወጪ ንግዱ ገቢ ወደ 75 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱንም አስታውሰዋል፡፡ ይብሱን ወደ 56 ሚሊዮን ዶላርም ወርዶ እንደነበርና፣ ‹‹ይህ እየሆነም ግን በከፍተኛ ገቢነት የተመዘገበችውን የ100 ሚሊዮን ዶላር መጠን እንደሚያልፋት እናውቅ ነበር፤›› ያሉት አቶ ወንዱ፣ በሦስተኛው ዓመት ወደ 112 ሚሊዮን ዶላር እንዳንሰራራ፣ ከዚያም ወደ 119 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ 123 ሚለዮን ዶላር፣ ብሎም ወደ 135 ሚሊዮን ዶላር ማደግ እንደቻለ  አብራርተዋል፡፡ ይህን ያመጣው የእሴት ጭማሪው ነው ቢሉም፣ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ቀውስ በገባበት ወቅትና ጫናውም እየረበታ በመጣበት ጊዜ የጫማ ፋብሪካዎች እንደሚፈለገው መጠን ከውጭ ሳይመጡ እንደቀሩ በማጣቀስ የዘርፉ አፈጻጸም ወደ ታች እንወረደና እውነታውም ይኸው እንደሆነ ሞግተዋል፡፡ ይህም ይባል እንጂ መንግሥት ከቆዳና ከቆዳ ውጤቶች የወጪ ንግድ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያቀደው የገቢ መጠን 500 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በሁለቱም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ይህ ገቢ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት አቶ ወንዱ ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 30 እና 40 በመቶ ወደ 70 ወይም 80 በመቶ ለማሳደግ፣ ለዚህም በሁለት ፈረቃ እስከ 16 ሰዓታት በቀን እንዲያመርቱ ማድረግ፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችም በፍጥነት ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ የሚሉና ሌሎችም ታሳቢዎች እንደነበሩት አስታውሰው፣ እነዚህ ባለመሠራታቸው የታሰበው ገቢ ሊሳካ እንዳልቻለ አቶ ወንዱ ይገልጻሉ፡፡

በዚያም ላይ ለዘርፉ የታሰበው የጋራ የፍሳሽ ማጣሪያና በሞጆ ከተማ ሊተከል የታሰበው የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማዕከልም፣ በመሬት ችግር ሳቢያ ባለመተግበሩ፣ አገር በቀል ቆዳ ፋብሪካዎችን ለአካባቢ ብክለት ተጋላጭ በማድረግና ከውጭ የመጡም ቢሆኑ እንዲዘጉ ያስገደደበትን ተፅዕኖም አቶ ወንዱ አልዘነጉም፡፡ በሱሉልታ ከተማ የተገነባውና በአሁኑ ወቅት የተዘጋው ቻይና አፍሪካ የተሰኘው የቆዳ ፋብሪካ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡

በእንዲህ ያሉ ችግሮች የሚናጠው የቆዳው ዘርፍ፣ በአገር ውስጥም በውጭ የገበያና የዋጋ ችግሮችም እየተፈተነ ባለበት ወቅት እንኳ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ተስፋ መሆኑ አላከተመም፡፡ መንግሥት ከውጭ እንዲገቡ በብዙ ማበረታቻ ያመጣቸው የውጭ ኩባንያዎች የእሴት ጭማሪ ፖሊሲው በመለወጡ ሳቢያ ተደናግጠዋል ያሉት አቶ ወንዱ፣ ይህ ጉዳይ ይባሱኑ ወደ በግ ቆዳና የፍየል ሌጦ ደረጃ መውረድ እንደማይገባው ያሳስባሉ፡፡ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉትና በቆዳው መስክ አንጋፋ ልምድ ያላቸው አቶ አምዴ አካለወርቅም፣ የቆዳና ሌጦ ለወጪ ንግድ እስከመጨረሻው በቋሚነት መፈቀድ እንደሌለበት ይስማማሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች