የወርኃዊ የውኃ ፍጆታ ክፍያን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለማስፈጸም ስምምነት ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በአዲስ አበባ ውኃና ፈሳሽ አገልግሎት መካከል ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በተፈረመበት ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና፣ ወርኃዊ የፍጆታ ክፍያን በባንኩ በኩል መፈጸም የሚያስችለው አገልግሎት መጀመር ደንበኞች ሳይጉላሉና ተጨማሪ ወጪ ሳያወጡ ባሉበት የሥራ፣ የመኖሪያ አካባቢና በአቅራቢያቸው በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፍ መፈጸም ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ ባለሥልጣኑ ወርኃዊ የአገልግሎት ክፍያዎችን በመሰብሰብ ሒደት በርካታ ቅሬታዎች ይቀርብበት እንደነበር አስታውሰው፣ ተቋማቸው ከባንኩ ጋር የሚጀምረው አዲስ አገልግሎት ይህን ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ይፈታል ብለዋል፡፡
የአገልግሎቱ መጀመር ባለሥልጣኑ ቀላልና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም በላይ ዘመናዊ የሆነ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችለዋል ተብሏል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ የክፍያ አገልግሎቱን ለማስጀመር ሁለቱን ተቋማት በኔትዎርክ የማስተሳሰር ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፣ የምዝገባና የመረጃ ማጥራት ሥራዎች በባለሥልጣኑ በኩል በመከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡ የክፍያ አገልግሎቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጭ ማቅረቡ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ስለሚያስችል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ከ560 ሺሕ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ ደንበኞች ከባንኩ ጋር አስቀድመው በሚገቡት ውል መሠረት የውኃ ፍጆታቸው በቀጥታ ከሒሳባቸው ተቀንሶ ገቢ ማድረግ የሚያስችለውን አማራጭ ጨምሮ ሌሎች የባንኩን የክፍያ አማራጮች ተጠቅመው አገልግሎቱን ማግኘት የሚያስችላቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ በፊት ከተለያዩ ተቋማት ጋር አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ያደረገ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከሐረር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲና ከመልቲ ቾይስ ኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ፈጽሞ ወደ ሥራ የገባ መሆኑም ተገልጿል፡፡