Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ያባባሰው የመንግሥት ወጪ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር በመሆን ለዓመታት ዘልቋል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢም በየጊዜው እያሽቆለቆለ መምጣቱም ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በወጪና ገቢ ንግድ መካከል ያለው ልዩነትም በየዓመቱ እየሰፋና እየባሰበት መጥቷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ በመምጣቱም የበርካታ ፋብሪካዎችንና አምራች ኢንዱስትሪዎችን ህልውና ፈተና ውስጥ ከቶታል፡፡  ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በዚሁ ችግር ዙሪያ ባዘጋጀው መድረክ የኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ በገቢና ወጪ ንግዱ መካከል የሚታየው ልዩነት በመስፋቱ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ወደ ሰባት ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል፡፡ በማሳያነት ያቀረቡት መረጃ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. በ2015/16 የተመዘገበው የገቢ ንግድ 16 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ነው፡፡

የወጪ ንግዱ በአንፃሩ ከአሥር ዓመታት በፊት ከነበረበት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ወደ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ቢያድግም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን ወደ ታች እየወረደ መጥቷል፡፡ በተያዘው ዓመት አሥር ወራት ውስጥም ከ2.1 ቢሊዮን ዶላር ማለፍ አልቻለም፡፡ ይህም በመሆኑ በወጪና ገቢ ንግዱ መካከል ያለውን ልዩነት ከአሥር ዓመታት በፊት ከነበረው አኳያ ሲታይ፣ ልዩነቱ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ያመላክታል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ይህንን ልዩነት በተጨማሪ ምሳሌ ሲገልጹት፣ ‹‹የ200 ብር ደመወዝ ተካፋይ ወጪው የ700 ብር ከሆነ፣ ይህንን ይዤ እቀጥላለሁ ወይ፤›› የሚያሰኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ይህ በመሆኑም የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ሊገኝባቸው በሚችሉ ዘዴዎች ሲሸፈን ቆይቷል፡፡ በገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን አባብሷል ያሉት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ለሚታየው የውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያቶች ያሏቸው ነጥቦች ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎችንና የተጓዙበትን መንገድም አብራርተዋል፡፡

መንግሥት የሚከተለው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብና ያሳረፈውን ተፅዕኖም አመላክተዋል፡፡ ተፅዕኖው እንዴት እንደመጣ ካቀረቡት ገለጻ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ እንዲባባስ ከኢኮኖሚ ፖሊሲው የመነጨው ችግር አሁን ተባብሶ ለሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

መንግሥት በ2006 ዓ.ም. የዕድገት ፖሊሲውን ወሳኝ በሚባልና ሊታይ በሚችል መልኩ ለውጦታል፡፡ በዚህ ውሳኔው መሠረት፣ በገበያው መሠረት የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ብዙም ስላልሆነና የግሉ ዘርፍ ለዕድገት የሚኖረው ሚናና አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ቢገባም መንግሥት ጠንክሮ በመውጣትና የኢኮኖሚ አውታሮችን በመቆጣጠር  ዕድገትና ልማት ማምጣት አለበት በማለት፣ ይህንን ለማረጋገጥም ልማታዊ መንግሥት የሚባል ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተል ማስታወቁን የኢኮኖሚ ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡

የልማታዊ መንግሥት እሳቤ ‹‹የመሠረተ ልማቱን ካሟላሁ፣ የግሉ ኢኮኖሚ ኢንቨስት ማድረግ የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል የሚል አመለካከት ነበረው፡፡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተው ኢኮኖሚ ቀስ እያለ አቅርቦት ተኮር ወደ ሆነው ኢኮኖሚ ይሸጋገራል የሚል እምነት ነበር፤›› በማለት የመንግሥትን ንድፈ ሐሳብ አብራርተዋል፡፡

የግሉን ዘርፍ መንግሥት በሚፈልገው መንገድና አቅጣጫ ለመምራት የተነሳው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ፣ ይህንን ሐሳቡን ለማስተባበርም ግብርና ላይ አተኩሮ የከረመው መንግሥት ‹‹ማርሹን ቀይሮ ኢንቨስትመንት መር ኢኮኖሚ እገነባለሁ ብሎ ተንቀሳቀሰ›› በማለት፣ በዚህ መንገድ የተጀመረው ጉዞ መጨረሻ ላይ መንግሥት የኢንቨስትመንትን ትልቅ ድርሻ በመያዝ ኢኮኖሚውን በበላይነት እንዲመራ እንዳበቃው ይገልጻሉ፡፡

ይህ አካሄዱም መንግሥት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍጆታ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ መንግሥት ኢንቨስት የሚያደርግባቸው የመሠረተ ልማት አውታር ግንባታዎችን ለማካሄድ የሚጠቀምባቸውን ግብዓቶች በአብዛኛው ከአገር ውስጥ ይልቅ ከውጭ ለማግኘት መገደዱም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን እያጦዘው እንዲመጣ አስገድዷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መንግሥት ኢንቨስት በሚያደርገው ልክ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ፣ ለእጥረቱ መባባስ ምክንያት እንደሆነም ተነስቷል፡፡  

የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ እንደጠቀሱት፣ 15 ቢሊዮን ዶላር ከደረሰው የገቢ ንግድ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያህሉ የመንግሥት ወጪ ነበር፡፡ ለገቢ ንግድ ከዋለው ከዚህ ገንዘብ  ውስጥ አንድ ሦስተኛውን መንግሥት በመጠቀሙ፣ በውጭ ምንዛሪ የተደረገው የመንግሥት ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የተጠቀመው የውጭ ምንዛሪ መጠን ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ከፍተኛ በሚባለው መጠን ይመደባል ብለዋል፡፡

መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ ለገቢ ንግድ በማዋሉ፣ የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ የፋይናንስ ምንጮችንም ጭምር ለሚገነባቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት ለማዋል በመነሳት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደወሰደም ተጠቅሷል፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያው ገለጻ፣ ባንኩ የሚያሰባስበውን የተቀማጭ ገንዘብ በከፍተኛ መጠን የሚያሟጥጥ ብድር ወስዷል፡፡  

ከዚህ አንፃር ንግድ ባንክ ለብድር ካዋለው ገንዘብ ውስጥ 85 በመቶውን የወሰዱት የፌዴራል መንግሥት ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ባንኩ ለግሉ ዘርፍ ከ10 እና 15 በመቶ ብቻ እንዳበደረ የሚጠቁም መረጃ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ከአንድ ባንክ 85 በመቶውን ብድር መጠቀሙ የግል ዘርፉን ብድር የማግኘት ዕድል በማጥበብ የራሱን ሥራዎች ለማስተግበር እንደተተቀመበት አመላካች ነው፡፡››

ይሁንና ይህ የመንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ፍላጎትና የወጪ መጠን  ከንግድ ባንክ በወሰደው ብድር ብቻ የተገታ አልነበረም፡፡ በ2007 ዓ.ም. የግል ባንኮች ከሚሰጡት ከእያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ በማድረግ ገንዘቡን ለሚፈለገው ዓላማ በመጠቀም፣ የግሉ ዘርፍ ማግኘት የሚገባው ገንዘብ እንዲቀንስበት ጫና አድርጓል፡፡ እስካለፈው ዓመት መጨረሻም ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ በዚህ መንገድ መሰብሰቡን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

እንዲህ ያለው ከፍተኛ የመንግሥት የወጪ ፍላት፣ የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ በተለይ በዋና ተበዳሪነት መንግሥት ለሚያገኘው ገንዘብ የሚከፍለው አነስተኛ ወለድ ከዋጋ ግሽበት አኳያ ሲታይም፣ ከዜሮ በታች የለወድ ምጣኔ ወይም ‹‹ኔጌቲቭ ኢንተረስት ሬት›› በሚባለው ደረጃ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የገንዘብ ፍሰቱንና ወጪውን ጋብ እንዲያደርገው በተደጋጋሚ ለሚቀርብለት ጥያቄም አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ፣ ኢኮኖሚ ላይ ችግሮች እየተፈጠሩ እንደመጡ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እንዲሁም የዋጋ ግሽበት በመከሰቱ፣ ላኪዎች እየተጎዱ መጥተዋል፡፡ የንግድ ሚዛኑም እንዲዛባ እንዲሆን ምክንያት በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የቻለው ሰው፣ ከውጭ ዕቃ አምጥቶ ከዚህ በሚሸጥበት ጊዜ የሚያገኘው ትርፍ ከፍተኛ በመሆኑ አስመጪዎችን የሚያበረታታ እየሆነ መምጣቱ የችግሩ ማሳያ ተደርጓል፡፡  

እንዲህ ያለው የመንግሥት አካሄድ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ ሰፊ ችግር ስለፈጠረ፣ በጥቁር ገበያው የሚመነዘረው የውጭ ገንዘብ፣ ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ ከሁለት በመቶ በላይ እያደገ ሲመጣ ጉዳዩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ሲያብራሩም፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ መካከል ያለው ልዩነት ከ40 በመቶ በላይ በመሆኑ ከአሳሳቢነትም በላይ ሆኖ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡ ወሳኝ ሊባል የሚችል የፖሊሲ አደጋ እንደተደቀነ የጠቆሙት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ይህ አደጋ በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ላይ ሕዝብ እምነት እንዲያጣ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋታቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ልዩነቱ ይበልጥ እየሰፋ ከመጣና በመገበያያ ገንዘቡ ወይም ብር ላይ ዕምነት ከታጣ ወደ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡

የሕዝቡን ዕምነት መልሶ ለማምጣት ከባድ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ በመጠቆም በመፍትሔነት ካሰፈሯቸው መካከል፣ በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት በፖሊሲ ዕርምጃ በቶሎ ማጥበብ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ ካቀረቧቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከልም በጥቁር ገበያው ውስጥ ያሉት አካላት ወደ መደበኛው ኢኮኖሚ እንዲመጡ ለማድረግ፣ በምሳሌነት ያነሱት የምንዛሪ ቢሮዎችን በመክፈት ተቀራራቢ የምንዛሪ ተመን እንዲኖር የማድረግ ሥራን ነው፡፡ ሌላው የምንዛሪ ተመን ለውጥ ነው፡፡ ይህ ሁለት ጊዜ ተሞክሯል ያሉት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ ሌሎች የፋይናንስ ማሻሻያዎችን የሚጠይቁ ሰፊ ጉዳዮች በመኖራቸው፣ እነዚህ ባሉበት ሁኔታ የምንዛሪ ለውጡ አልሠራም ይላሉ፡፡ ሌላው መፍትሔ ግን የመንግሥት ብድር ዕዳን መቀነስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ገበያውን ነፃ ማድረግና የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረግ የሚለው ሐሳብም በመፍትሔነት ቀርቧል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በገበያው አቅርቦትና ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ የሚመራ የምንዛሪ ተመን መከተል ተገቢነት ከተሳታፊዎች ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ቴዎድሮስም (ዶ/ር) አሁን ባለው አኳኋን ምንዛሪውን ለገበያ ክፍት ማድረጉ ጠቃሚ አይደለም ቢሉም፣ አንዱ አማራጭ መፍትሔ እንደሆነ ግን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ክፍት ቢደረግ ምን ሊወጣብን ይችላል የሚል ፍራቻ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ብዙ ዝግጅቶችን ይጠይቃል፤›› በማለት ሁለት ዋና ዋና ያሏዋቸውን ዝግጅቶች ጠቅሰዋል፡፡ አንደኛው የቁጥጥር ማዕቀፍ መዘርጋት ነው፡፡ ማንኛውም ለገበያ ክፍት የማድረግ ዕርምጃ አቻ የሆነ የቁጥጥር ዕርምጃ እንደሚያስፈልገውና በዚሁ እሳቤም የቁጥጥር አቅም ማዳበር ብሎም የማስፈጸም ብቃትን መገንባት እንደሚያስፈልገው አብራርተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪውን በገበያው እንዲመራ ይደረግ ቢባል እንኳ በመጀመርያ  ተዋናዮቹ እነማን እንደሆኑ፣ ግዥ የሚፈጽሙት እነማን እንደሆኑ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ፍላጎቱና አቅርቦቱ በምን አግባብ ሚዛኑ እንደሚጠበቅ በደንብ መታየት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በተለይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቁር ገበያው የሚመጣበትን ጫና ለመቋቋም የሚችልበት፣ በገበያ የሚመራ የምንዛሪ ተመን መፍጠር የሚችልበትና የሚቆጣጠርበት አቅም እስካልተገነባ ድረስ ገበያ መር የምንዛሪ ተመን መከተል ተገቢ እንደማይሆን አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

የመቆጣጠር አቅም ቢፈጠር እንኳ፣ የተዋናዮቹ አቅምና ግንዛቤ ገና በመሆኑ፣ የተቆጣጣሪው አቅም ይበረታና በገበያ ውስጥ ፍራቻ ያነግሳል ያሉት ባለሙያው፣ ለገበያ የሚተወው የምንዛሪ ተመን ፍራቻ እንዳያስከትል የሚያደርግ የመጠባበቂያ መጠን በማዘጋጀትና ይህንን አቅም በመገንባት የሚሠራ ሥራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ‹‹ማዕከላዊ ባንኩ መጠባበቂያውን ይይዝና ሞክሩን ዓይነት ጨዋታ ይጫወታል፡፡ ይህንን የሚያደርገው የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሰጠው ምላሽ ምንድን ነው ብሎ ለመመልከት የሚያስችላቸው በመሆኑ ነገሩን ደረጃ በደረጃ ማስኬድ ይችላል፤›› በማለት ሌሎች አገሮች በምን አግባብ ገበያ መር የምንዛሪ ተመን እንደተከተሉና ውጤታማ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች