Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በቆዳው ዘርፍ ችግሮቻችንን ፈተን ተገቢውን አሠራር ከተከተልን ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠበቀውን ገቢ ማሳካት እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ›› አቶ ወንዱ ለገሠ፣ በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ

አቶ ወንዱ ለገሠ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በዘለቀው የቆዳ ኢንዱስትሪው ተሞክሯቸው አብዛኛውን ያሳለፉት በኢንስቲትዩቱ ቢሆንም፣ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በፈቃዳቸው ተቋሙን ተሰናብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ በመሆን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ከቆዳው ዘርፍ ሳይርቁ በሙያቸው ማገልገሉን እንደመረጡ ይገልጻሉ፡፡ የመልቀቃቸውን ጉዳይ በሚመለከት በተፅዕኖና በግፊት ይሆን ወይ የሚሉ መላምቶች ቢሰነዘሩም፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸውም ሆነ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ያስታወቁት ከዘርፉ ሳይርቁ ነገር ግን በሙያቸው ማገለግልን በመምረጣቸው፣ በአንድ ቦታ ለረዥም ጊዜ ከመቆየት ይልቅ አዳዲስ ልምዶችንና ፈተናዎችን ለመጋፈጥ በማሰብ ጭምር ከመንግሥት ኃላፊነት ለቀለዋል፡፡ እሳቸው ለረዥም ጊዜ የቆዩበት የቆዳ ኢንዱስትሪ በርካታ ስሞታዎችና ወቀሳዎች ሲቀርቡበት ይታያል፡፡ በካይ ፋብሪካዎች አካባቢነት የሚጎዱበት የምርት ሥርዓት፣ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል የውጭ ምንዛሪ አለመገኘቱ፣ የውጭ ባሀብቶች ከአገር በቀሎቹ የበለጠ ትኩረትና ድጋፍ ከመንግሥት እያገኙም የሚፈለገውን ያህል አላስገኙም የሚሉት በአንኳርነት ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲህ ያሉትንና ሌሎችም መሠረታዊ የቆዳ ኢንዱስትሪውን ገጽታዎች በማስመልከት ብርሃኑ ፈቃደ ከአቶ ወንዱ ለገሠ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡– የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን በፈቃድዎ እንደለቀቁ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽዎ የጻፉትን አይቻለሁ፡፡ ለበርካታ ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል፡፡ ይሁንና ሰዎች በተፅዕኖ ወይም በፖለቲካ ምክንያት ኃላፊነትዎን ሳይለቁ እንዳልቀሩ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ስለቀቁበት ጉዳይ ካሰፈሩት ባሻገር በሚዲያ በኩል ምን ሊሉ ይችላሉ?

አቶ ወንዱ፡- ለሚዲያ የምለው በጽሑፍ ያሰፈርኩት እውነተኛ ስሜቴ እንደሆነ ነው፡፡ ቀድሞም በቦታው ስመደብ በተፅዕኖ ወይም ለሌላ ጉዳይ አልነበርም፡፡ ስለዘርፉ የነበረኝን ፍላጎትና ስሜን የተረዱ ኃላፊዎች ለቦታው ይመጥናል ብለው ነው ያስቀመጡኝ፡፡ ለዘርፉ አቅሜ በፈቀደው የቻልኩትን ያህል  ከሚመለከታቸው ኃላፊዎችና ከኢትየጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ጋር በመመካከር ብዙ ሠርተናል፡፡ በጊዜው ውስጤ እንደሚፈልገውና እንዳሰብኩት ዘርፉ ተራምዷል ብዬ አላምንም፡፡ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ባለሀብት ብቻውን አልያም መንግሥት ብቻውን ሳይሆን፣ ራዕይ ያለውና ቢዝነሱንም በሚገባ የሚረዳ ሰው ነው ዘርፉን መቀላቀል ያለበት፡፡ አሁን እንደ በፊቱ አይደለም፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪው ድሮ በተለመደው አካሄድ በፍጹም ሊጓዝ አይችልም፡፡ የተሻለ ዕይታ ያስፈልገዋል፡፡ እኔ በማውቀው የተሻለ ዕይታ በመያዝ ሠርቻለሁ፡፡ ለመንግሥት ፕሮፖዛሎች በማቅረብ የፈጸማቸውም ያልፈጸማቸውም ጉዳዮች አሉ፡፡ የሚቀርበውን ፕሮፖዛል ተቀብሎ ለመተግበርም የሚወስደው ጊዜና ምክንያትም ነበር፡፡ አሁንም ከቆዳው ዘርፍ አልወጣሁም፡፡ የማጠናውም የማነበውም ስለዚሁ ዘርፍ ነው፡፡ በጠቅላላ ሕይወቴ ውስጥ ትልቅነት ያለው ይኼው ዘርፍ ነው፡፡ በበርካታ የሥራ ቦታዎች ተሰማርቼ አገልግያለሁ፡፡ አስቀድሞ አሥረኛ ክፍል ሳለሁ ወደ አየር ኃይል በመግባት አየር መከላከያ በሚባል ክፍል ውስጥ ለሰባት ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ትምህርቴን አጠናቅቄ ለሁለት ዓመታት በአስተማሪነት አገልግለያሁ፡፡ ከዚያም ሞጆ ቆዳ ፋብሪካ በመግባት ለሁለት ዓመታት ከሠራሁ በኋላ፣ ወደ ቆዳ ኢንስቲትዩት በረዳት ኤክስፐርትነት ተቀላቅያለሁ፡፡ ለዘጠኝ ዓመታት በዚሁ ከሠራሁ በኋላ ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመግባት የመምሪያ ኃላፊ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያም በዋና ዳይሬክተርነት ኢንስቲትዩቱን መርቻለሁ፡፡ በጠቅላላው ለ20 ዓመታት በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ስለስኳር ወይም ስለሲሚንቶ ላነብ አልችልም፡፡ የምጽፈውም፣ የምናገረውም፣ የምሠራውም ስለቆዳና ቆዳ ነክ ስለሆኑ ጉዳዮች ነው፡፡ ሆኖም የመንግሥትም የባለሀብቱም ፍላጎት ካለበት ከአመራርነት ቦታው ወጣ ብዬ እንደ ባለሙያ ምን ባግዝ ይሻለኛል የሚል ስሜት አድሮብኝ እንጂ፣ በማንም ተፅዕኖና ጫና አልለቀቅሁም፡፡ እንደውም ከመንግሥትም ከቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበርም፣ ለምን ትለቃለህ የሚል ጥያቄ ቢቀርብልኝም እኔ ግን በራሴ ፈልጌ ነው የወጣሁት፡፡  

ሪፖርተር፡– በ20 ዓመታት ልምድና ተሞክሮዎ የቆዳው ዘርፍ የት ደርሶ አዩት? ከየት ተነስቶ የት ደርሷል ሊባል ይችላል?

አቶ ወንዱ፡- በእኔ ሐሳብና ግምት የቆዳው ኢንዱስትሪ በ20 ዓመታት ውስጥ አድጎ እንጂ ወደ ታች ወርዶ አላየሁትም፡፡ ብዙውን ጊዜ ስለቆዳ ሲነሳ በሰዎች ግምት ቆዳ ሲባል የቆዳ ፋብሪካ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ በቆዳ ዘርፍ ውጤቶቹም ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ እኔ ወደ ዘርፉ ከመምጣቴ በፈት የነበረውን የወጪ ንግድ መጠን ምን ያህል እንደነበርና ከነበረበትስ በምን ያህል ጨምሯል የሚለውን ብናይ፣ በሚፈለገው ደረጃም ባይሆን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተበራክተዋል፡፡ የኢንቨስትመንት መጠን አድጓል፡፡ ጫማ፣ ጓንትና ሌላውንም የቆዳ ውጤት የሚያመርቱ ኢንቨስተሮች በብዛት ገብተዋል፡፡ እነዚህ በሙሉ የመጡት እኔ በምሠራበት ዘመን ነበር፡፡ ዘርፉ ከፍተኛ የሰው ኃይል ቀጥሯል፡፡ በተለይ በፖሊሲ ደረጃ ወደ እሴት ጭመራ ከተሸጋገርን በኋላ በርካታ የሥራ ዕድሎችን አስገኝቷል፡፡ የፖሊሲው ዓላማ ዘርፉ ባለበት እንዲቀጥል ማድረግ ሳይሆን፣ በርካታ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ነው፡፡ በእኔ ዘመን የዘርፉን የወጪ ንግድ አፈጻጸም የሚመሩ የጫማ ፋብሪካዎች የተመሠረቱበት ነው፡፡ እኔ በገባሁበት ወቅት ትልቁ የጫማ የወጪ ንግድ ተብሎ የተመዘገበው መጠን ስምንት ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዛሬ የሁሉንም መረጃዎች ስንመለከት እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር እንደደረሰ እንገነዘባለን፡፡ ይኼ ዕድገት ነው፡፡ ምንም ዓይነት የጓንት ምርት ከማይመረትበት ኢንዱስትሪ ተነስተን በየዓመቱ እስከ ስምንት ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ማስመዝገብ የቻልንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ዓለም አቀፍ መረጃውንም ስንመለከት፣ ሌሎች የቆዳ ውጤቶች የሚባሉትን በዓመት ከ80 እስከ 100 ሺሕ ዶላር ልከን ከምናገኝበት ይልቅ፣ አሁን ሦስትና አራት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ጀምረናል፡፡ የቆዳው ዘርፍ በአብዛኛው በአትዮጵውያን ባለሀብቶች የተያዘ ነው፡፡ ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት የወጡ ወጣቶች ፋብሪካ መሥርተው በአገር ውስጥና በውጭ እየሸጡ፣ በርካታ ሰዎችንም እየቀጠሩ የመጡበት መንገድ በፊት ያልነበረ፣ አሁን ግን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ አካሄድ ነው፡፡ እነዚህን ለውጦች ዓይቻለሁ፡፡ የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያም በርካታ የቆዳ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል፡፡ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችም የቆዳ ሳይንስና ምህንድስና በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ሥልጠና እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመርያ ዲግሪ ደረጃ ስለቆዳ ዘርፍ ያስተምራሉ፡፡ በጫማ ምህንድስና በርካታ ተማሪዎች እየተመረቁ ወደ ፋብሪካዎች እየገቡ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቆዳ ቴክኖሎጂ የሚባል አለ፡፡ እኔ ከመምጣቴ በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት መስክም ብዙ ተሠርቷል፡፡ በፊት የነበረው የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ብቻ ነበር፡፡ በአገር ደረጃ ከ40 በላይ የቴክኒክና የሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተመሥርተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ለእኔ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ዛሬ ስለቆዳ ከሙያና ከዕውቀት ተነስተው በጥልቀት የሚነጋገሩ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡ እንደ በፊቱ ጥቂት ሰዎች ብቻ አይደሉም ዘርፉን የሚያውቁት፡፡ ይሁንና ማፍራት እንደተቻለው የሰው ኃይል መጠን ግን ፋብሪካዎች ተቀይረዋል ወይ ብንል ገና ብዙ የሚቀረው ነገር አለ፡፡ የተማሩ ሰዎች ወደ ኢንዱስትሪው ገብተው በተግባር የሚማሩት መኖር አለበት፡፡ በቆዳ ፋብሪካዎች አካባቢ የሠለጠኑ ሰዎችን በብዛት የመቀበል ችግር አለ፡፡ ከውጭ የመጡት ይሻላሉ፡፡ በርካቶቹ በፋብሪካዎቻቸው ተቀብለው ያሠሯቸዋል፡፡ የአገር በቀሎቹ ተቸግረናል የሠለጠነ የሰው ኃይል የለም ይላሉ፡፡ የሠለጠነ ሰው ግን በብዛት አለ፡፡ እነሱ የሚፈልጉት የ20 እና የ30 ዓመታት ልምድ ካለውም የበለጠ ኃይል ነው፡፡ ይህ በአንድ ጊዜ አይፈጠርም፡፡ ነገር ግን በሁለት ወይም በሦስት ዓመታት ተሞክሮ የሚፈለግበትን ሥራ በሚገባ መወጣት የሚችል የሰው ኃይል መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህ ለእኔ ዕድገት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡– በእርስዎ የአመራር ቆይታ ወቅት አንኳር የሚባሉት ሁለት ወይም ሦስት ሥራዎችዎና ስኬቶችዎ የትኞቹ ናቸው?

አቶ ወንዱ፡- አንዱ የሰው ኃይል ልማት ላይ በከፍተኛ ደረጃ የተሠራበት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ሥልጠናዎች መስጠት ተችሏል፡፡ ኢንስቲትዩቱ አቅም አልነበረውም፡፡ የቆዳ ልማት ኢንስቲትዩት ተባለ እንጂ ስለቆዳ የሚናገር አንድም ባለሙያ አልነበረውም፡፡ ስለጫማ የሚናገር፣ ስለቆዳ ቴክኖሎጂ የሚናገር ባለሙያ አልነበረውም፡፡ ከኬሚስትሪ ምህንድስና ትምህርት ክፍል የምንቀጥራቸው ነበሩ ስለቆዳ ይናገሩ የነበሩት፡፡ ዛሬ ግን ይኼንን አልፈን በቆዳ ቴክኖሎጂ ከ40 በላይ እዚህም ህንድም ተልከው የሠለጠኑ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመሥራት ጭምር ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎችን መፍጠር ተችሏል፡፡ በመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታም ትልቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ልዩ ልዩ የምርት ጥራት ፍተሻዎችን ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ ልከን እናሠራ ነበር፡፡ አሁን ግን በሰው ኃይልና በመሣሪያ አቅማችን በመገንባቱ በአገር ውስጥ መሠራት የሚችሉ የፍተሻ ሥራዎች በርካታ ናቸው፡፡ የመፈተሽ አቅማችን አድጓል፡፡ ጫማ ገዥዎች ከውጭ ሲመጡ የጥራት መፈተሻ እንዳለን ይጠይቃሉ፡፡ ከ86 በመቶ በላይ የጥራት ደረጃን መፈተሽ የምንችለበት አቅም እንደገነባን ስለሚያዩ በቀላሉ ምርቱን ይገዛሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ተሳክቷል የምለው በተለይ በቆዳ ውጤቶች ላይ የታየው ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን ነው፡፡ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች በዘርፉ ተከናውነዋል፡፡ ይኼም እንደ ስኬት የማስበውና በእኔ ቆይታ ወቅት ልጠቅሰው የምችለው ነው፡፡ ከዚህ በላይ መሠራት ነበረበት ግን ደግሞ ይህም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡   

ሪፖርተር፡- እርስዎ በነበሩት ወቅት ከዘርፉ በዓመት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ በተደጋጋሚ ሲታቀድ ነበር፡፡ የዘርፉ አፈጻጸም ግን ከመቶ ሚሊዮን ዶላር ብዙም ገፍቶ አልሄደም፡፡ ዘርፉ እርስዎ በጠቀሱት አግባብ ስኬታማ ሊባል ይችላል፣ ግን ደግሞ ከመንግሥት ዕቅድ አኳያ ዝቅተኛ ገቢ ማስገኘቱ እንዴት ነው የሚታየው? 

አቶ ወንዱ፡- የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲዘጋጅ ሁሉም ነገር ባለበት ሳይሆን፣ በፍጥነት እየተቀየረ ይጓዛል ከሚል ዕሳቤ ነበር ዝርዝር ዕቅዶች የወጡት፡፡ ከዘርፉ ይገኛል የተባለው 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲታቀድም፣ ያሉት ፋብሪካዎች በምን ያህል አቅማቸው እየሠሩ እንደነበርና በምን ያህል እንደሚጨምሩ ታስቦ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱ የአቅሙን 40 በመቶ የሚያመርት አለ፡፡ አንዳንዱም እስከ 30 በመቶ ብቻ ያመርት ነበር፡፡ ይኼንን የማምረት አቅም ወደ 70 ወይም 80 በመቶ እንዴት ማድረስ ይቻላል የሚለው ታስቦ ነበር፡፡ የጫማ ፋብሪካዎች ምን ያህል አሉን? ምን ያህሉስ ከሚሠሩት ስምንት ሰዓት በተጨማሪ በሁለት ፈረቃ ማምረት ይችላሉ? ከውጭ ምን ያህሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስገባት እንችላለን? የሚለው ሁሉ ታስቦ ነው እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል የተባለው፡፡ ይሁንና መሟላት የሚገባቸው ነገሮች ያልተሟሉ ነበሩ፡፡ ባለሀብቱ በሁለት ፈረቃ ለ16 ሰዓታት እንዲያመርት ለማድረግ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ በአገር ውስጥም በውጭም ገበያው መኖር መቻል አለበት፡፡ ሌላው የታሰበው የውጭ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገብቶ ምንም ዓይነት የቢሮራክራሲ ችግር ሳይገጥመው ወደ ምርት መግባት መቻል አለበት፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ግን እንደታሰበው አልተሟሉም፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንቱም በታሰበው መጠን አልመጣም፡፡ በተለይ የእሴት ጭማሪ ፖሊሲው መተግበር ከጀመረ በኋላ የእኛን ቆዳ የሚፈልጉት እዚህ መጥተው ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ አልገጠማቸውም፡፡ በአገልግሎት አሰጣጣችን ውስጥ በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ ገበያው የሚፈልጋቸው እኛ የማናውቃቸውም በርካታ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከሌሎች አገሮች ተምረን ወደ ገቢዎችና ጉምሩክ ሄደን ሌሎች አገሮች እንዲህ ነው የሚሠሩት እያልን ማስረዳት ነበረብን፡፡ ለምሳሌ ያህል ያለቀለት ቆዳ ናሙና ለገዥው ይላካል፡፡ በሌላው አገር ናሙና በተጠየቀ ጊዜ ሁሉ እንደ ልብ ይላካል፡፡ ግዥው ሲካሄድ የተላከው ሁሉ ተቆጥሮ ይካተትና ገንዘብ ይላካል፡፡  በእኛ አገር ግን የመጀመሪያዋ ናሙና ስትላክ አትወጣም ተብላ ትያዛለች፡፡ ይህን ለማድረግ ላኪው ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት አለበት ይባላል፡፡ የውጭ ምንዛሪው መምጣት አለበት ይባላል፡፡ ይኼንን ለመፍታትና በዘርፉ የሚመለከታቸው እንዲረዱት ለማድረግ ረዥም ጊዜ ይፈጅብን ነበር፡፡ አንድ ዓመት አይደለም ሦስትና አራት ዓመታት ይፈጅብን ነበር፡፡ በመጀመርያው ዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ዘመን ያየነው ችግር ወደ ሁለተኛው የዕቅድ ዘመንም ዘልቆ ነበር፡፡ በዕቅድ ሰነዱ የተቀመጠውን ለማሳካት የሚያስፈልጉ ነገሮች አልተሟሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ ዝቅ ሊል ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡– ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ መላክ የሚለው ፖሊሲ እንደወጣ የወጪ ንግድ ገቢው በጣም ወርዶ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩትን ሚኒስትሮች ስንጠይቃቸው ‹‹የገቢው መጠን መቀነስ የሚጠበቅ ነው፡፡ ገዥ አገሮች ፖሊሲውን ሊቃወሙት እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ግን ገቢው ይሻሻላል፤›› ይሉን ነበር፡፡ ገቢው ግን እንደ ታቀደው ሊሻሻል አልቻለም፡፡ በአንፃሩ በከፊል ያለቀለት ወይም ክረስት የሚባለውን የሚያመርቱ፣ ከጥሬ ቆዳ በመጠኑ የተዘጋጀውን ዌት ብሉና ፒክል የተሰኘው ቆዳ እያመረቱ ይልኩ የነበሩ ፋብሪካዎችም የመንግሥትን የእሴት ጭማሪ ፖለሲ ክፉኛ ይቃወሙ ነበር፡፡ ያለቀለት ቆዳ ተልኮም ውጤት አልተገኘም፡፡ በከፊል ያለቀለት ቆዳ ተዘጋጅቶም ፈላጊ ስላጣ ጥሬ ቆዳ እስከመጣል ተደርሷል የሚሉ ቅሬታዎችም ይደመጡ ነበር፡፡ ይህ ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ የመላክ ፖሊሲ ምን አስገኘ? የተጠበቀውን ያህል ውጤት ያላስገኘበትስ ምክንያት ምንድን ነው? 

አቶ ወንዱ፡- መንግሥት የፖሊሲ ለውጡን የፈለገው ካለቀለት ቆዳ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት አይደለም፡፡ የቆዳ ዘርፍ ሲባል የቆዳ ፋብሪካዎቹ፣ የጫማ፣ የጓንት፣ የቆዳ አልባሳትና መሰል ፋብሪካዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ በዚያን ጊዜ የነበረው የመንግሥት ፖሊሲ ከዚህ አኳያ የተቃኘ ነው፡፡ እርግጥ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አንዱ ዓላማው ነው፡፡ ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠርም ዋናው ዓላማው ነበር፡፡ ፒክልና ዌት ብሉ እያመረትክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ መቅጠር አትችልም፡፡ ወደፊት ስንሄድ ከፍተኛ የሰው ኃይል መቅጠርና ለምርቶቻችን እሴት መጨመር እንችላለን የሚል መነሻ አለው፡፡ ለጫማ ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ ያጡትን ያለቀለት ቆዳ ከዚሁ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ እንችላለን፡፡ የወጪ ንግዱ መስፋፋት ያለበት በቆዳ ውጤቶች በኩል እንጂ ቆዳ አልፍተን በመሸጥ አይደለም፡፡ የተለፋ ቆዳ ለውጭ ገበያ ስናቀርብ እኮ ቆሻሻውን እኛው ላይ አራግፈንና አጥበን ነው የምንሰጣቸው፡፡ ዋነኛ ተጠቃሚዎቹ እነሱ እንጂ እኛ አይደለም፡፡ አካባቢያችንን በክለን ነው የምናመርተው፡፡ በፋብሪካዎች አካባቢ የፍሳሽ ማጣሪያ እንዲኖር እንቅስቃሴ የተጀመረው እኮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ ነው የሚለቀቀው፡፡ እስከ 70 በመቶ የሚገመተው ቆሻሻ ከቆዳ ፋብሪካዎች የሚለቀቀው ፒክልና ዌት ብሉ በሚመረትበት ወቅት ነው፡፡ 70 በመቶውን ቆሻሻ እዚህ አራግፈንና አጥበን፣ የሚፈለገውን የሰው ኃይል ሳንቀጥርና የሚፈለገውን የወጪ ንግድ ገቢ ሳናገኝ በዚሁ ሁኔታ መቀጠል አግባብ አይደለም፡፡ የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ላይ ከቀላል ኢንዱስትሪ መስክ የሚመደቡ ናቸው፡፡ በቀላል ኢንዱስትሪው ወደ ፊት መግፋት ሳንችል ወደ ውስብስብና ግዙፉ ማደግ አንችልም የሚል የመንግሥት አስተሳሰብ ነበር፡፡ እኛም በወቅቱ በመንግሥት ሥር የነበርነው ይኼንን አስተሳሰብ እንጋራው ነበር፡፡ ቆዳው ጫማ፣ ቆዳ እየሆነ ይውጣ፡፡ ይህም ባይሆን እንኳ ከፍተኛ እሴት ተጨምሮበት ወደ ውጭ ይላክ የሚል አቋም ነበር፡፡ ፒክልና ዌት ብሉ ማምረት በጣም የሚስማማና ብዙ ልፋት የማይጠይቅ ነው፡፡ ጥቂት ደንበኞች ካሉህ ዓመቱን ሙሉ በኮንቴይነር እያጨቅህ መላክ ነው፡፡ ወዳለቀለት ቆዳ ምርት ስትገባ ግን በርካታ ደንበኞች ይኖሩሃል፡፡ በጣም በርካታ የምርት ናሙና መላላክ የሚጠይቅ፣ የተለየና ውስብስብ አስተዳደር የሚጠይቅ በመሆኑም ጭምር ፋብሪካዎቹ በዚህ ደረጃ መሥራት ይከብደናል ማለታቸው የሚጠበቅ ነበር፡፡

የውጭ ፋብሪካዎች መጥተው እንዴት እንደሚሠሩት ሲያዩና መልዕክቶችን በፍጥነት በመለዋወጥ እንዴት እንደሚሠሩ ስታይ፣ ያለቀለት ቆዳ ማምረትም መነገድም የተለወጠ አስተሳሰብና ማኔጅመንት እንደሚፈልግ ትረዳለህ፡፡ የውጮቹ በዘርፉ  ለዘመናት የካበተ ልምድና ዕውቀት ስላካበቱ ሥራውን በሚገባ ተክነውበታል፡፡ በነበረው ማኔጅመንትና አሠራር መቀጠል ከባድ በመሆኑ በመንግሥት በኩል በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ለመሥራት ሞክሯል፡፡ ፖሊሲው ሲጠናና ሲወጣ ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ይደረጋሉ የተባሉት ነገሮች አልተደረጉላቸውም፡፡ የመሣሪያ ግዥ ለመፈጸም የተለየ የግዥ ሥርዓት ተመቻችቶላቸው ገንዘቡን በአግባቡ ወዲያውኑ አግኝተው ሥራቸውን መሥራት አልቻሉም፡፡ የገበያ ችግር ነበረባቸው፡፡ ገበያው ላይ ከፍተኛ ሥራ ይሠራል የሚል ነገር ተካቶ ነበር፡፡ ግን አልተሠራበትም፡፡ ማሽኑንም ራሳቸው እንዲገዙ፣ ገበያም ራሳቸው እንዲያፈላልጉ ሁሉ ነገር ሲጣልባቸው ችግሩ ተፈጠረ፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ማኔጅመንቱ ከባድ በመሆኑ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ይህም ሆኖ ችግሩ እስኪቀረፍ ወደ ኋላ መመለስ ነው? ወይስ ችግሩን እየተጋፈጡና እያረሙ ወደፊት መሄድ ነው? የሚለው ላይም ክፍተት አለ፡፡ ይህ ሲባል ግን ራሳቸውን በሚገባ ቀይረው የወጡ አሉ፡፡ ችግሩን መውጣት ተስኗቸው የቀሩም አሉ፡፡ በነገራችን ላይ በከፊል ያለቀለት ቆዳ መላክ ስለተከለከለና በፖሊሲው ምክንያት የተዘጉ ፋብሪካዎች አሉ እየተባለ የሚነሳ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን ዌት ብሉና ፒክል በሚልኩበት ወቅትም ይህንኑ መሥራት አቅቷቸው የተዘጉም ነበሩ፡፡ እነዚህን ዛሬ ላይ እያነሳን ለቁጥር ማሟያ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ የዘመኑን አሠራር ባለመረዳት የተዘጉም አሉ፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ግን ያን ጊዜ የተወሰነው ፖሊሲ በጣም ትክክል ነበር፡፡ በመንግሥትና በባለሀብቱ በኩል መሄድ ያለብን ያህል ግን አልሄድም፡፡ በመንግሥትም በባለሀብቱም በኩል መሄድ እስከምንችለው ሄደን ሲያቅተን ወደ ኋላ እንመለሳለን የሚል አስተሳሰብ ይዘን ነው የተራመድነው፡፡ አሁን የሆነውም ይሄው ነው፡፡ በጫማና በጓንት አምራችነት የገቡ አዳዲስ ኩባንያዎች ይህንኑ ፖሊሲ ተከትለው ነው የገቡት፡፡ ጫማውን የሚያስመርቱት ጭምር እዚህ አገር እንዲመረትላቸው ለሚፈልጉት ጫማ ቴክኒሻኖቻቸውን የሰጡን ይህንኑ ፈልገው ነበር፡፡ አሁን ለውጥ በተደረገበት ፖሊሲ ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ የገቡትም እነዚሁ አምራቾችና ገዥዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሆነው በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ እንዲላክ በቅርቡ ስለተፈቀደ ነው ማለት ነው?

አቶ ወንዱ፡- አዎን፡፡ በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ እንዲላክ በመፈቀዱ እዚህ ይመረት የነበረውን ምርት እንደገና ከውጭ ወደ መፈለግ ልንሄድ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ውስጥ ጥሏቸዋል፡፡ በተለይ ጫማ አምራቾችንና ሌሎቹንም የቆዳ ውጤቶች አምራቾችን አደናግጧል፡፡ ከጊዜ በኋላ መጉዳቱ አይቀርም፡፡ በዚያን ጊዜ አብሮ መታሰብ የነበረበት ጉዳይ ግን ገበያ ሲጠፋና መወጣጠር ሲመጣ ማስተንፈሻ ዘዴ መኖር ነበረበት፡፡ ያለቀለት ቆዳ ምርት ገበያ ካላገኘ ፒክልና ዌት ብሉ መከማቸቱ አይቀርም፡፡ ይህንን ችግር በምን እናስተንፍሰው ክምችቱ ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅት እነማን ወደ ውጭ ይላኩት የሚል የመውጫ ስትራቴጂ አልታሰበም ነበር፡፡ እስከ ሰባት ወራት የተከማቸውን ቆዳ እንዴት እናንሳው የሚለው ለእኔ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን ፖሊሲውን ወደ ኋላ መመለስ አግባብነት የለውም፡፡ ይህ መደረጉ በከፍተኛ ደረጃ ያሳስበኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- መንግሥት በከፊል ያለቀለትን ቆዳ ወይም ክረስት ወደ ውጭ መላክ እንዲጀመር በመፍቀድ ብቻ ሳይሆን፣ ዌት ብሉና ፒክልም ጭምር መላክ እንዲጀመር የሚደረግበት እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት በቅርቡ ስለዘርፉ በተደረገ ስብሰባ ላይ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ወንዱ፡- እኔ በመንግሥት አገልግሎት ውስጥ አይደለም ያለሁት፡፡ እንደ ባለሙያና በዘርፉ ውስጥ እንደቆየ ሰው ነው ሐሳቤን የምሰጠው፡፡ ይህ ሐሳብ በተነሳበት ስብሰባ ላይ ዘርፉ ሞቷል፣ ተቀብሯል የሚሉ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ዘርፉ አላደገም ወይም ማደግ በሚገባው ልክ  አላደገ ይሆናል እንጂ ሞቷል የሚያስብል ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ በሚገባው ልክ በፍጥነት አላደገ ይሆናል ግን ዕድገት አሳይቷል፡፡ የቆዳ ውጤቶችና  ቆዳ ፋብሪካዎችም ለውጥም ዕድገትም አሳይተዋል፡፡ ስለቆዳ ፋብሪካዎች ስናወራም በሚያመርቱት መጠን ካየነው እንደሚባለው በጣም የወረደ ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ አጠቃላይ በዋጋ ደረጃ ሲታይ ዝቅተኛ መጠን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ይህ ግን ለኢትዮጵያ ቆዳ ዘርፍ ብቻ የመጣ ችግር ሳይሆን የመላው ዓለም ችግር ነው፡፡ የዓለምን ያለቀለት ቆዳ የሰባት ዓመታት የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ብትመለከት፣ እስከ አሥር ቢሊዮን ዶላር ከነበረው መጠን ወርዶ አሁን ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ኢትዮጵያን ይነካል፡፡ ያለን የጥሬ ቆዳ ጥራት ደረጃ እጅግ እየወረደ መጥቷል፡፡ ይህ ሳያንስ በዚሁ ችግር ላይ እንደገና ዌት ብሉና ፒክል መላክ ማለት ይበልጥ ኪሳራችንን ያባብሰዋል እንጂ ትርፍ አያመጣልንም፡፡ ይልቁኑም ጥራት ያጣውን ቆዳችንን እሴት ጨምረንበት ያለቀለት ቆዳ አድርገን ብንሸጠው ነው የሚጠቅመን፡፡ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ለመብራት፣ ለውኃ፣ ለሠራተኛ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለመሳሰሉት ይከፈል የነበረው የምርት ወጪ አሁን በናበረበት ሁኔታና የመሸጫ ዋጋ በሚቀንስበት ወቅት የተለየ አካሄድ ካልተከተልን በስተቀር፣ ጥሬ ቆዳ ወይም በከፊል የተዘጋጀ ቆዳ በመላክ ችግሩን አናልፈውም፡፡ እኔ ወደ ዘርፉ ስመጣና ሞጆ ቆዳ ፋብሪካ እሠራ በነበረበት ወቅት ጥሬ ቆዳና ሌጦ ወይም ፒክልና ዌት ብሉ ደረጃ ይወጣለት ነበር፡፡ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያለው ቆዳ ከ70 በመቶ በላይ ነበር የጥራት ደረጃው፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የያዘ ጥሬ ቆዳና ሌጦ እስከ 15 በመቶ መጠን ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ መሆኑ ቀርቶ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያለው እየተባለ  የሚቀርበው መጠን 25 በመቶ አይሞላም፡፡ ከአንድ እስከ ሦስት ባለው የጥራት ደረጃ የሚገኘው ቆዳ ከአምስት በመቶ ያነሰ ነው፡፡ የቱ ጋ ቢሠራ ነው ለውጥ የሚመጣው ቢባል የእንስሳቱን የኑሮ ሁኔታ በመቀየር ነው፡፡ የቁም እንስሳቱ በከፍተኛ ደረጃ ለእከክ በሽታ ተጋልጠዋል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ድሮ አሥር ሚሊዮን የበግ ቆዳ ስትገዛ 70 በመቶው ደረጃ ነበረው ካልን፣ ሰባት ሚሊዮን ቆዳው ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት ባለው እርከን ውስጥ ይመደባል ማለት ነው፡፡ ሦስት ሚሊዮኑ አራተኛና አምስተኛ የጥራት ደረጃ ያለው ነው ማለት ነው፡፡ ተቀባይነት ያጣው ቆዳ አምስት በመቶ ገደማ ነው፡፡ ዛሬ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከ55 በመቶ ያላነሰው ቆዳ ተቀባይነት ያጣ ነው፡፡ በዋጋ ቢሰላ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያለውና ያለቀለት ቆዳ የሚባለው በካሬ ጫማ እስከ ሦስት ዶላር ያወጣል፡፡ ከደረጃ በታች የሆነው ወይም ተቀባይነት ያጣው ቆዳ ከአንድ ዶላር በታች ነው የሚሸጠው፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የጥራት ደረጃውን ካሟላው ቆዳ ይገኝ የነበረው 94 ሚሊዮን ዶላር አሁን አምስት ሚሊዮን ዶላር አይገኝበትም፡፡ ይኼንን ልዩነት ያመጣው የቆዳው የጥራት ችግር እንጂ ፖሊሲው አይደለም፡፡

ፖሊሲው እንዲያውም እንደዚህ ዓይነት ቀውስ በመጣበት ወቅት የሌሎች አገሮችን ሁኔታ እንመልከት፡፡ ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ታንዛንያን ብንመለከት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ በምርት ብዛት እየተስፋፋ የማይጨበጥ ሆኖብናል እያሉ የእኛን ነው የሚያልሙት፡፡ እነሱ ጥሬ ቆዳና ሌጦ እየላኩም ቁልቁል ነው የሄዱት፡፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር የኢትዮጵያን ያለቀለት ቆዳ፣ የኢትዮጵያን የቆዳ ጃኬትና ጫማ ጥራት በመመልከት ሲነጋገርበት ቆይቷል፡፡ 30 እና ከዚያም በላይ ፋብሪካዎቻችን ሳይዘጉ በሕይወት የቆዩት በፖሊሲ ምክንያት ነው፡፡ ወዳለቀለት ቆዳ አምራችነት መሄዳችን ከውድቀት አድኖናል፡፡ በከፊል ያለቀለት ቆዳ የሚያመርቱም በመርካቶ ገበያ እንደ ልብ መሸጥ ችለዋል፡፡ ውጭ መሄድ ሳይጠበቅባቸው ገበያው እዚሁ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከውጭ ለመጡ ፋብሪካዎች ማቅረብ ችለዋል፡፡ ሆንግ ኮንግ ወይም ጣሊያን መሄድ ሳይጠበቅባቸው እዚሁ ምርታቸውን ማቅረብ ችለዋል፡፡ ይህ የተፈረው በፖሊሲው ነው፡፡ ቆዳ ፋብሪካ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በተልዕኮና በርቀት ሆኖ ቆዳ ፋብሪካን መምራት አይቻልም፣ ያከስራል፡፡ የፋብሪካ ባለቤት ስለእያንዳንዷ ግብዓት አጠቃቀም መከታተል አለበት፡፡ ኬሚካል ስትመዘን ያላግባብ ጠብ እንዳትል ማድረግ ካልቻለ ለኪሳራ መዳረጉ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያለ የማኔጅመንትና ውጤታማ የምርት ሒደት መከተል ሳንችል ፖሊሲው ችግር እንዳመጣ መኮነን ለእኔ የማይዋጥልኝ ነው፡፡ ፖሊሲው ያመጣቸው ተፅዕኖዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በንግግርዎ ለቆዳው ጥራት መዳከም አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው የእንስሳት ቆዳ በሽታ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ ግን ምን ያህል ነው የዚህ እውነታው?

አቶ ወንዱ፡- ለእኔ ቁጥር አንድ ችግር ይኸው ነው፡፡ በቅርቡ ያነጋገራችኋቸው ባለሙያው አቶ አምዴ አካለወርቅ ወደነበርነበት የጥራት ደረጃ ለመመለስ 12 ዓመታት ይፈጅብናል ያሉት፣ ለጥሬ ቆዳና ሌጦ ወይም ለፒክልና ዌት ብሉ አይመስለኝም፡፡ ይኼንን ጥራት ለማሻሻል ኢንስቲትዩትም አያስፈልገውም፡፡ በቀላሉ ማምጣት ይቻላል፡፡ የጥሬ ቆዳና ሌጦን ጥራት ደረጃን ወደነበረበት ለመመለስ ግን ጊዜ መፍጀቱ አያጠያይቅም፡፡ የከብቱን አኗኗር በማስተካከል የቆዳውን ጥራት ማሻሻል ይቻላል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን እንኳን የእንስሳትና የሰውም አኗኗር ብዙ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ግጦሽ እንደ ልብ ያላገኘ ከብት ቆዳው ፋብሪካ ሄዶ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ ድርቅ ካለበት አካባቢ የሚመጣ ከብት ቆዳ በውስጡ ያለው ድርና ማግ ስለሚላላ በሚዘጋጅበት ወቅት በቀላሉ ይበጠሳል፣ ይቀደዳል፡፡ ስፋቱና ውፍረቱ ቀንሶና ሳስቶ የሚመጣው ቆዳ ገና እንስሳው በቁሙ ሳለ ካልተስተካከለ፣ ቅብብሎሹን በማሳጠር ቄራው ተስፋፍቶ ቆዳው ከእርድ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ቆዳ ፋብሪካ መሄድ ካልቻለ በቀር የጥራት ችግሩ በቀላሉ አይፈታም፡፡ በከብት እርባታ ዘዴውም ቢሆን ከአመጋገብና ከሕክምና አሰጣጥ ጋር መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የውጭ ጥገኛ ነፍሳት፣ እከክና ሌላውም እያስቸገረው ከሚኖር ከብት ነው ቆዳ እየተሰበሰበ ያለው፡፡ ይኼንን ችግር ያመጣው የእሴት ጭማሪ ፖሊሲው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ እንዴት ይሻሻል ለሚለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር በ1991 ዓ.ም. ገደማ ነበር ወዳለቀለት ቆዳ፣ ወደ ጫማ ማምረት መሄድ ሲቻል እንደሆነ ለመንግሥት የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ከተባለ ከ12 ዓመታት በኋላ ነው መንግሥት የእሴት ጭማሪ ፖሊሲን ያመጣው፡፡ በነገራችን ላይ የቆዳ የወጪ ንግድ ለመጀመርያ ጊዜ 100 ሚሊዮን ዶላር የገባው በ2000 ዓ.ም. ነበር፡፡ እርግጥ ፖሊሲው ሲወጣ ወደ 75 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ ወደ 56 ሚሊዮን ዶላርም ወርዶ ነበር፡፡ ይህ እየሆነም ግን በከፍተኛ ገቢነት የተመዘገበችውን የ100 ሚሊዮን ዶላር መጠን እንደሚያልፋት ግን እናውቅ ነበር፡፡ በሦስተኛው ዓመት 112 ሚሊዮን ዶላር አሻቅቦ ነበር፡፡ ወደ 119 ሚሊዮን፣ ወደ 123 ሚለዮን፣ ከዚያም ወደ 135 ሚሊዮን ዶላር ማደግ ችሏል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ታች በወረደበት ወቅትም ዕድገት እያሳየ ነበር፡፡ ጭነቱ እየበዛ ሲመጣና የጫማ ፋብሪካዎች እንደሚፈለገው መጠን ሳይገቡ ሲቀሩ ግን መልሶ እየወረደ መጥቷል፡፡ እውነታው ይህ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- አገር በቀል የቆዳ ፋብሪካዎች መንግሥት ለውጭ ፋብሪካዎች ያደላል ይላሉ፡፡ ይኼንን እንዴት ያዩታል?

አቶ ወንዱ፡- ኢንቨስትመንት ለሁሉም አገር አስፈላጊ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በእኛ አገር ባለው ሁኔታ አሁን የአገር ውስጥ ባለሀብቱም ወደ ቆዳ ዘርፉ አይመጣም፡፡ ወደ ቆዳ ማልፋትና ማለስለስ አይመጣም፡፡ ፖሊሲው አስፈርቶት ሳይሆን በዓለም ላይ የመሸጫ ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ስለመጣም ጭምር ነው፡፡ ቆዳ ያልሆኑ ምርቶች ቆዳን እየተፈታተኑት ነው፡፡ ጫማ በከፍተኛ መጠን ከሰንቴቲክ እየተመረተ ዓለምን እያጥለቀለቀ ነው፡፡ የፔትሮ ኬሚካልና የፖሊመር ምርቶች የቆዳ ምርትን ፈተና ውስጥ ከተውታል፡፡ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ከፍ ያለ ደረጃና በቴክኖሎጂ አቅማቸው የላቁት ትንንሾቹን እየዋጧቸው በመሆኑ፣ አቅም ያላቸውን እንዲህ ያሉትን ኢንቨስተሮች ወደ እኛ ማምጣቱ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሲመጡ የሚያገኙትን ማበረታቻ ለአገር ውስጡ አብልጦ መስጠት ካልተቻለ ግን የእኛ ፋብሪካዎች ውድድሩን ማሸነፍ አይችሉም፡፡ ይህ ግን እስካሁን አልተደረገም፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም ከውጭ የሚመጣ ባለሀብት ያገለገለ ማሽነሪ ይዞ እንዲመጣ ሲፈቀድለት፣ የአገር ውስጡ ባለሀብት ግን ይህ አይፈቀድለትም፡፡ ከጥሬ ዕቃ አቅራቢ በብድር ማምጣት የሚችልበት አሠራር ወይም ሰፕላየርስ ክሬዲት ለውጭ ባለሀብቱ ተመቻችቶለት ያለ ምንም ውጣ ውረድ የውጭ ምንዛሪ ይፈቀድለታል፡፡ ኬሚካል ያስመጣል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ግን ተሠልፎ ነው ዕድሉን የሚያገኘው፡፡ የውጭ ባለሀብቱ ከሰፕላየርስ ክሬዲት በተጨማሪ ከአገር ውስጥ ባለሀብቱም ጋር ተጋፍቶ ለውጭ ምንዛሪ ይሠለፋል፡፡ ያለቀለት ቆዳ የሚያቀርብ አምራች ምርት እንዲያቀርብ በተሰጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ማቅረብ መቻል አለበት፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ባለበት ኬሚካል አምጥቶ መሥራት ካልቻለና እጅግ ጠንካራ ውድድር ካለበት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ማደግ አይችልም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር ባለበት ወቅት የፋብሪካዎቹን ችግር ለማስተንፈስ በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወይም ክረስት በአገር ውስጥ ባለሀብቱ ወደ ውጭ እንዲላክ መደረጉ ሊያስማማ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወደ ቆዳና ሌጦ ደረጃ መውረዱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተከበበ ነው፡፡ ትንፋሽ ለማግኘት ታስቦ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ክረስት ከተፈቀደ ሊያሳምነኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን የዘርፉ ዕድገት በፖሊሲ ምክንያት ተጎድቷል የሚል መነሻ ካለ ግን ትክክል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሦስት ነገሮችን በአጽንኦት እናንሳ፡፡ ከቆዳው ዘርፍ የሚጠበቀው ገቢ አልተገኘም፡፡ አካባቢን በመበከል የተዘጉ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ገንዘብን በሕገወጥ መንገድ ለማሸሽ ምቹ ከሚባሉት ዘርፎች አንዱ የቆዳው ዘርፍ ነው እየተባለ ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች የሚታዩበት ዘርፍ መሆኑ በመንግሥት ልቅ በመደረጉ የመጣ ነው? ወይስ ምንድነው ዘርፉን እንዲህ ተጋላጭ የሚያደርገው? ችግሩ የት ጋ ነው?

አቶ ወንዱ፡- ለሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ወይም ማሸሽ ተግባር የውጮቹ ወይም የአገር ውስጦቹ ናቸው ተጠያቂዎች ብሎ መፈረጅ ችግር አለው፡፡ ሁሉም ይህ ችግር ይመለከተዋል፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ምርትን እንደ ሸጠ ማስመሰልና ጥሬ ዕቃን በከፍተኛ ዋጋ እንደ ገዛ አድርጎ በማቅረብ የሚደረግ ማጭበርበር ሁሉንም ሊመለከት ይችላል፡፡ ነገር ግን ተናቦ ካለመሥራትም የሚመጣ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ የኬሚካል ዓለም አቀፍ ዋጋ ህዳጉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ኢንስቲትዩቱና የገቢዎች ወይም የጉምሩክ አካላት ቢነጋገሩባቸው ቢመካከሩ ችግሩን በቀላሉ መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ ፋብሪካ በዓመት ያመረተው ወደ አገር ውስጥ ካስገባው ጥሬ ዕቃ መጠን ጋር በንፅፅር ምን ያህል እንደሆነ በቀላሉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የትኛው ፋብሪካ ገንዘብ በማሸሽ ተግባር ላይ እንደሚሳተፍ ሊደረስበት ይችላል፡፡ ችግሩ ግን ቆዳው ሲላክ በኪሎ ግራም የነበረው በነጠላ ወይም በቁጥር እየተመዘገበ ይላክ የሚል ክርክር አለ፡፡ የላኩት በኪሎ ግራም ተመንዝሮ ገንዘቡ ይታወቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ይቅርና እያንዳንዱ ካሬ ጫማ ቆዳ በቁጥር ተተምኖ ለገቢዎች እንዲቀርብ በመጠየቁ ፋብሪካዎች ይህን ያህል ካሬ ጫማ፣ ይህን ያህል ኪሎ ግራም፣ ይህን ያህል ነጠላ ቁጥር ያቅርቡ በመባሉ ለአሠራር አስቸግሯል፡፡ ከዚህ ይልቅ ከሰው ንክኪ በሚመራ ሥርዓት መሠረት ወጪና ገቢ ምርቱን መከታተል ይበጃል፡፡ ሥርዓት ሲኖር የትኛው ፋብሪካ አተረፈ ወይም ከሰረ የሚለውን ማወቅ ይቻላል፡፡ ፋብሪካዎች 60 በመቶ አቅማቸው ቢያመርቱ አሁን ባለው ሁኔታ አትራፊ መሆን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ዘርፉ የተደቀነበት ችግር አለ፡፡ ጣሊያን፣ ጀርመንና ጃፓንን ጨምሮ በኢኮኖሚ ያደጉት አገሮችም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዳይሞት የሚከላከሉበት አግባብ አለ፡፡ በተለይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለፋብሪካዎች ቀጥተኛ ድጎማ ያደርጋሉ፡፡ ከባለሀብቱ 20 በመቶ፣ ከመንግሥት 80 በመቶ እየተዋጣ የጋራ ፍሳሽ ማጣሪያ እንዲገነቡ ያግዟቸዋል፡፡ እኔ ወደ ኢንስቲትዩቱ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በሞጆ የጋራ ማጣሪያ ግንባታ ስለማካሄድ ሲነገር ቆይቷል፡፡ እስከ ዛሬ ግን ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ገንዘብ የሚሰጥ አካል ቢገኝም መሬት ግን አልተገኘም፡፡ ጥናት ተጠንቷል፡፡ ለመሬት ካሳ ለመክፈልና መሬቱን ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ ብቻ ከአራት ዓመታት በላይ ፈጅቷል፡፡ በዚህ መካከል ፋብሪካዎች ማጣሪያ ስለሌላቸውና አካባቢ ስለሚበክሉ የሚለቃቸው የለም፡፡ ባላቸው አቅም ለመሥራት ካፒታላቸውን በሙሉ ሥራ ማስኬጃ ላይ ያውሉና ለአካባቢ ጥበቃና መሰል ሥራዎች ሲጠየቁ አቅሙ ስለማይኖራቸው ወደ መዘጋቱ ይሄዳሉ፡፡ ቆዳና ሌጦ እንዲላክ ከመነጋገር ይልቅ እንዲህ ያሉ ማነቆዎችን መፍታቱ ላይ ቢሠራ ጥሩ ለውጥ ይመጣል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተለዋዋጭ ወጪያቸው ከፍተኛ እየሆነና ማትረፍ እያቃተቸው ይሄዳሉ፡፡ እንደ አጥፊና በካይ ማየት ሳይሆን አፋጣኝ መፍትሔ መስጠቱ ነው የሚሻለው፡፡ አካባቢ እንዳይበከል የሚከላከለው አካል የበከሉ ፋብሪካዎችን መዝጋት ነው ሥራዬ ካለ፣  መንግሥት ይህንን ሳይመልስ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ሁሉም ነገር ባለሀብቶች ላይ ይወድቅና ችግር ላይ ይጥላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቆዳው ዘርፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት አይቻልም? እስካሁን በዚህ መስክ የተከፈተ ግንባታ አልታየም፡፡

አቶ ወንዱ፡- ለጫማ ወይም ለቆዳ ውጤቶች ማሰብ ይቻላል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ በቆዳ ውጤቶች ላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ያሰቡ ሰዎች አሉ፡፡ ጆርጅ ሹ፣ ኋጂዬን የተባሉት ፋብሪካዎች ትልልቅ ኢንዱስትሪ ዞኖችን ለመገንባት ያስባሉ፡፡ ባለሀብቶቹ ከውጭ ሲመጡ ይዘውት የሚመጡት አስተሳሰብና እኛ ስለኢንዱስትሪ ያለን ግንዛቤ የማይገናኝ ነው፡፡ የሥራና የኢንዱስትሪ ዲሲፕሊናችን መታየት አለበት፡፡ በዓል ነው እያለ ቤቱ የሚቀር ሠራተኛ ብዙ አለ፡፡ እከሌ ተነካ ብሎም የሚያምፅና ሥራ የሚያቆም አለ፡፡ ከቻይና የሚመጡትም ምናልባት እዚያ እንደለመዱት በስድብና በዱላ ማሠራት የሚቻል ይመስላቸዋል፡፡ ሁሉም በለመደው መንገድ መሥራትም ማሠራትም አይቻልም፡፡ እኛም ብንሆን ችግር ብዙም ያስተማረን አይመስለኝም፡፡ ሥራ ሳይኖረን እየዞርን የምንውል ሆነን፣ ሥራ አግኝተን ደግሞ ደመወዙ ትንሽ ነው ብለን ሥራ ፈት መሆንን የምንመርጥ አለን፡፡ ከታች ወደ ላይ ከመሄድ ይልቅ ከትልቁ ለመጀመር የምፈልግ ብዙ ነን፡፡ ነገር ግን ነገ በጥረትና በሥራ ትጋት ወደ ትልቅ ደረጃና ደመወዝ ማደግ እንደሚቻል ሠራተኞች ማመን አለባቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች በመምጣታቸው በርካታ ዕውቀቶችንና ልምዶችን አግኝተናል፡፡ ከሌሎች የተማርነውን መተግበርና መሥራት ላይ መጠንከር አለብን፡፡ በቆዳው ዘርፍ የውጭ ኩባንያዎች እንደገቡ ሰሞን ሁሉንም የማግበስበስ ችግር ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የተዘጉም አሉ፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ሲመጣ እኛ የምንሠራውን እንዴት ይሠራል የሚባል ነገርም አለ፡፡ ነገር ግን እኛ ከምናመርተውና ከምናመርትበት ዘዴ በተለየና በተቀላጠፈ መንገድ በብዙ ለውጥ እኛው የምናመርተውን ቢያመርት፣ ከእኛ ስለሚሻል እንዲገባ መደረጉ ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዘርፉ ወዴት እያመራ ነው? በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ዘርፉን በሚመለከት የእርስዎ ተስፋስ ምንድነው?

አቶ ወንዱ፡- አሁን ባለው ሁኔታ በዘርፉ የተሰማራው ሰው ማሰብ ያለበት ከባድና ጠንካራ ውድድር ስላለ ለዚህ መዘጋጀት እንዳለበት ነው፡፡ ሁሉ ነገር እንደ በፊቱ ቀላል አይደለም፡፡ አዳዲስ ወጣቶች በዘርፉ እየገቡና ሚሊየነር እየሆኑ ተወዳዳሪነትንም እያመጡ ነው፡፡ ይህ እንዳይቋረጥ መደረግ አለበት፡፡ የውጮቹ ያለቀለት ቆዳ ከውጭ እየገዙም መወዳደር ይችላሉ፡፡ የእኛዎቹ ግን ይኼንን ማድረግ አይችሉም፡፡ የእኛዎቹ  ከሚልኩበት ዋጋ ይልቅ እዚሁ የሚሸጡበት ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን ገበያ በአግባቡ መምራት ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያለባቸውን ችግር እንዲሻገሩ በዓይነትም በገንዘብም ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ብድራቸውን በአግባቡ ሥራ ላይ ያዋሉት ተለይተው ማሻሻያ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህ የሚደረገው ግለሰቦችን ሀብታም ለማድረግ አይደለም፡፡ ነገር የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ለንግድ መስፋፋትና ለሥራ ፈጠራ ያግዛሉ ተብለው መታገዝ አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ወደፊት ያሻግራል ተብሎ መታየትና ለተወዳዳሪነት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከአፍሪካ በዘርፉ የተሻለ ጥሬ ዕቃ አለን ብንልም እነ ቱኒዝያና እነ ሞሮኮ ግን ከውጭ በሚያስገቡት ቆዳና ሌጦ እየሠሩ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኛሉ፡፡ እኛ ግን በራሳችን ሀብት ሠርተንም ይኼንን ያህል ማግኘት አልቻልንም፡፡ ይልቁንም እነዚህን አገሮች ይበልጥ ተጠቃሚ እናድርጋቸው፣ ቆዳና ሌጦውን እናቀብላቸው የሚል አካሄድ እያመጣን ነው፡፡ በአፍሪካ የሚበልጡን አገሮች የተሻለ የእሴት ጭማሪ ማድረግ የቻሉት ናቸው፡፡ የአሥር ዓመታት የዓለም ንግድ ማዕከልን ሪፖርት ብታይ፣ በጫማ ወጪ ንግድ ኢትዮጵያ ከታች ተነስታ ዛሬ ላይ የ54 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት በመቻሏ ከእነ ሞሮኮ፣ ከእነ ቱኒዝያና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ በአራተኛነት የምትጠቀስ አገር ሆናለች፡፡ ይህ በሥራ የመጣ ዕድገት ነው፡፡ በሌሎች የቆዳ ምርቶች አኳያም ከፍተኛ ዕድገት አሳይታለች፡፡ ያለቀለት ቆዳ ግን ወደታች ወርዷል፡፡ ለምን ቢባል የቆዳ ውጤቶች በተበራከቱ ቁጥር ያለቀለት ቆዳ ፍጆታ ስለሚጨምር ወደ ውጭ የሚላከው መጠን ይቀንሳል፡፡ በአገር ውስጥ ያለውን የቆዳ ጫማ ገበያ እንኳ ብንመለከት ከፍተኛ መጠን አለው፡፡ ሰው ግን ወደ ውጭ የሚላከውን መጠን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ ምን ያህል ሰው ቀጥሯል? ምን ያህል ገንዘብ ያንቀሳቅሳል? ተብሎ ሲታይ ዕድገት አሳይቷል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከቆዳው ዘርፍ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊገኝ የሚችለው መቼ ነው?

አቶ ወንዱ፡- ቀደም ብዬ የዘረዘርኳቸው ችግሮች ከተቀረፉና ጥሬ ቆዳና ሌጦ በአግባቡ ጥራቱ ቢሻሻል፣ ምንም የተለየ እሴት ሳንጨምር በከፍተኛ መጠን ማደግ እንችላለን፡፡ ቬትናሞች ባለቀለት ቆዳ ምርት ወጪ ንግድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት ጥሬ ቆዳና ሌጦ በአገር ውስጥ አምርተው አይደለም፡፡ እኛ ቴክኖሎጂው ካለን፣ አካባቢን የሚጠብቅና ለብክለት ምላሽ የሚሰጥ አመራረት ከተከተልን ቆዳና ሌጦ ከውጭም አምጥተን ቢሆን መሥራት አለብን እንጂ፣ ጭራሹኑ ይህነኑ ጥሬ ቆዳና ሌጦ በመሸጥ ተወዳዳሪነታችን ማጣት የለብንም፡፡ ጥሬ ዕቃ የሚልኩት እየወደቁና እየጠፉ ሲሄዱ፣ እሴት እየጨመሩና ወደ ከፍተኛው ደረጃ እያደጉ የሄዱት ገበያውን እየተቆጣጠሩት መጥተዋል፡፡ በቆዳው ዘርፍ ችግሮቻችንን ፈተን ተገቢውን አሠራር ከተከተልን ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠበቀውን ገቢ ማሳካት እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...