Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ70 ሚሊዮን በታች የሆኑ ግብር ከፋዮች ቫት ገቢ የሚደርጉበትን ጊዜ ወደ ሦስት ወራት የሚያራዝም የሕግ ረቂቅ ቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየወሩ ሽያጭና ገቢ ማሳወቅን የሚጠይቀውን ነባር አዋጅ እንዲሻሻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ሕግ፣ ዓመታዊ ሽያጫቸው 70 ሚሊዮን ብር በታች ለሆኑ ነጋዴዎችና ድርጅቶች የቫት ማሳወቂያና ገቢ ማድረጊያ ጊዜ ወደ ሦስት ወራት እንዲራዘምላቸው የሚጠይቀውን ጨምሮ ሌሎችም ማሻሻያዎች የተካተቱበትን የሕግ ረቂቅ ሊያጸድቅ ነው፡፡

ምክር ቤቱ የተወያየበት ይህ ረቂቅ ሕግ፣ በየወሩ ለታክስ ባለሥልጣኑ ወይም ለገቢዎች ሚኒስቴር የሚቀርበውን የንግድ ሥራ እንቅስቃሴና የገቢ ማሳወቂያ ሪፖርት ወደ ሦስት ወራት ከፍ እንዲል፣ በካፒታል ዕቃዎች ላይ የተከፈለ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሁም ከተከፋይ ሒሳብ ላይ በገዥው ተቀንሶ የሚያዘው የተጨማሪ እሴት ታክስ አያያዝና አከፋፈል ላይ መደረግ አለባቸው በተባሉ ማሻሻያዎች ላይ መክሯል፡፡

በመሆኑም በየወሩ ይቀርብ የነበረው የተጨማሪ እሴት ታክስ ሪፖርት ወይም የሒሳብ ጊዜ ማሳወቂያ በተለምዶ ዜድ ሪፖርት፣ በታክስ ከፋዩም ሆነ በታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ላይ ችግር ሲያስከትል መቆየቱን አብራርቷል፡፡ በተለይም ምንም ዓይነት የሽያጭ እንቅስቃሴ ያላከናወኑ አነስተኛና መካከለኛ ግብር ከፋዮች ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያስከትል እንደቆየ በመግለጽ፣ ይህንን ችግር ለማቃለል የሒሳብ ጊዜው አንድ ወር ከሚሆን ይልቅ ወደ ሦስት ወራት እንዲራዘም የሕግ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ቀርቦለታል፡፡ ዓመታዊ ሽያጫቸው ግን ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ግብር ከፋዮች በየወሩ ቫት እንዲያሳውቁና ገቢ እንዲያደርጉ ረቂቅ ሕጉ አስቀምጧል፡፡

ከዚህ ባሻገር በካፒታል ዕቃዎች ግዥ ላይ የተከፈለ የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ፣ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ መሠረት ከቀረጥና ከታክስ ነፃ ከሚገቡ ዕቃዎች በስተቀር ሌሎች ቫት የሚከፈልባቸው የካፒታል ዕቃዎች ላይ ለሚከፈል ቫት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሒሳቡ ለባለሀብቶቹ ተመላሽ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡ በማዕድንና ነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለተሰማሩ ኩባንያዎች በተለይ የከፈሉት ቫት በአንድ ወር ውስጥ ተመላሽ እንዲደረግ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ የቀረበ ሲሆን፣ በተለይም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ሥራ ላይ የሚያውሉ ባለሀብቶች በካፒታል ዕቃዎች ላይ የሚከፍሉት ቫት በአንድ ወር ውስጥ ተመላሽ እንደሚደረግላቸው የሕግ ማሻሻያው አመላክቷል፡፡

ይህ ማሻሻያ በነባሩ አዋጅና እስካሁን በነበረው አሠራር መሠረት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ሥራ ላይ ያዋሉ ባለሀብቶች መሥሪያ ካፒታላቸው ሊመለስላቸው በሚገባው ቫት ምክንያት ታስሮባቸው ሲቸገሩ እንቆዩም በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የሚገቡትን ሳይጨምር፣ የከፈሉት ቫት ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ታክሱን በከፈሉ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተመላሽ እንዲደረግላቸው መታሰቡን ረቂቅ ሕጉ አስፍሯል፡፡

በተጨማሪም ከተከፋይ ሒሳብ ላይ በገዥው ተቀንሶ ሲያዝ የቆየው ቫት እስካሁን በነበረው አሠራር መሠረት፣ መቶ በመቶ ለታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ተከፋይ የሚደረግበትን አሠራር በማሻሻል ወደ 50 በመቶ ዝቅ እንዲል ረቂቅ ሕጉ ጠይቋል፡፡ ይህም ያስፈለገው፣ ቫት የሚሰበስበው ግብር ከፋይ የከፈለውን ታክስ ለማቀናነስ የሚያስችል ቫት መሰብሰብ ባልቻለበት ጊዜ ተመላሽ እንዲደረግለት የሚያቀርበውን ጥያቄ ለመቀነስ ያስቻላል ተብሎ ስለታመነበትና እንደ ኬንያ ያሉ አገሮችም ተመሳሳይ አሠራር የሚከተሉ በመሆናቸው፣ ተቀንሶ የሚያዘው ሐሳብ ላይ ይከፈል የነበረው የመቶ በመቶ የቫት ሒሳብ ወደ 50 በመቶ ዝቅ እንዲል የማሻሻያ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በመሆኑም በነባሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 (እንደተሻሻለ) መሠረት ማሻሻያ የተደረገባቸው አንቀጾች የአዋጁ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1፣ ከአዋጁ አንቀጽ ሁለት ሥር ስለካፒታል ዕቃዎች የሚደነግግ አዲስ ንዑስ አንቀጽ በማካታተትና ሌሎችንም በመሻር መጠነኛ ማሻሻያዎችን ያካተተበት የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀርቦ፣ ለተጨማሪ ዕይታ ተመርቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች