Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊትምባሆ በሚያጨሱና በሚያስጨሱ ላይ ቅጣት የሚጥለው ሕግ ተግባራዊ ሆነ

ትምባሆ በሚያጨሱና በሚያስጨሱ ላይ ቅጣት የሚጥለው ሕግ ተግባራዊ ሆነ

ቀን:

በመዝናኛና በሌሎች የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች የትምባሆ ምርቶችን በሚያጨሱና በሚያስጨሱ ላይ የገንዘብና የእስራት ቅጣት የሚጥለው ሕግ ተግባራዊ  መደረግ ተጀመረ፡፡

የሲጃራና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን የሚያጨሱና የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህም በኢትዮጵያ የትምባሆ ምርቶችን ማምረት ሥራ ላይ በብቸኝነት የመሰማራት መብት የተሰጠው ለብሔራዊ ትምባሆ ኢንተርፕራይዝ መሆኑ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላቀ፣ በማኅበረሰቡ እምነትና ባህል መሠረት ትምባሆ ማጨስ አፀያፊ መሆኑ ትልቁን ድርሻ አበርክቷል።

ይህ ማለት ግን  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የትምባሆ ምርቶች አጫሾች ቁጥር ከኢትዮጵያ ሁኔታና ከቀጣይ አዝማሚያዎች አንፃር  ሲመዘን ቀላል አለመሆኑን  አኃዞች ያሳያሉ። በየዓመቱ ይፋ የሚደረገው የዓለም የትምባሆ አትላስ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከአሥር እስከ 14 የሆኑ 18,000 ታዳጊዎች በየቀኑ ትምባሆ ያጨሳሉ።

- Advertisement -

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኬረዲን ረዲ (ዶ/ር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ 3.4 ሚሊዮን ሰዎች ትምባሆ የሚያጨሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ 2.2 ሚሊዮን ያህሉ በየቀኑ የሚያጨሱ ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በቤት ውስጥ የሚሠሩ 30 በመቶ ወይም 6.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ገዳይ ለሆነው የሁለተኛ ደረጃ አጫሽነት ተጋላጭ ናቸው፡፡

በመንግሥት ሕንፃዎችና ቢሮዎች 20 በመቶ የሚደርሱ ሠራተኞች፣ 30 በመቶ የሚጠጉ የምግብ ቤቶችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ለሁለተኛ ደረጃ አጫሽነት ተጋላጭ ናቸው፡፡ እንዲሁም በምሽት መጠጥ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች የሚያዘወትሩ ሰዎች ተጋላጭነታቸው 60 በመቶ ይደርሳል፡፡  

የትምባሆ ጭስ ለአምስት ሰዓት በአየር ላይ የሚቆይ ሲሆን፣ በውስጡ የያዛቸው ለካንሰር የሚያጋልጡ ቅንጣቶችም ለሳንባ ነቀርሳና ለከፍተኛ ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የመጋለጥ አደጋን ይጨምራሉ፡፡

በዓለም ትምባሆ የማይጨስበትን ቀን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አሚር አማን (ዶ/ር)፣ ትንባሆ ጭስ ውስጥ ከ7,000 የሚበልጡ ኬሚካሎችና የኬሚካል ውህዶች እንደሚገኙ ተመራማሪዎች ማሳወቃቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 70 የሚሆኑት በተለየ መልኩ ለካንሰር የሚያጋልጡ ኬሚካሎች ስለመሆናቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የትምባሆ ምርቶችን በማጤስ ወይም በመጠቀም በየዓመቱ 16,800 ሰዎች ሕይወታቸውን እያጡ ስለመሆኑ የዓለም የትምባሆ አትላስ ሪፖርት ያስረዳል።

የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም የዓለም ቀዳሚ የጤና ጠንቅ መሆኑን የተረዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እ.ኤ.አ. በ1995 ዓለም አቀፍ ስምምነት አፅድቋል። ይህ ስምምነት በበርካታ አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ይኼንኑ ስምምነት ፈርማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሦስት ዓመት በፊት ያፀደቀች ሲሆን፣ ከጥቂት ወራቶች በፊት ደግሞ ስምምነቱን የሚያስተገብር አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታውጇል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥር ወር 2011 ዓ.ም. ያፀደቀው የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር አዋጅ 1112/2011 ሲሆን፣ አዋጁም ሲጃራና አጠቃላይ የትምባሆ ምርቶች አጠቃቀም የሚያደርሰውን የጤና ጠንቅ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሕግ ግዴታዎችንና ክልከላዎችን ጥሏል፡፡

 ይህ አዋጅ የማኅበረሰብ ጤናን ከመጠበቅ አንፃር የተቃኘ ነው፡፡ ከትምባሆ ምርቶች በተጨማሪ፣ በመድኃኒቶች፣ በአልኮል መጠጦችና በሌሎች ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የታለመ ነው። ነገር ግን የአዋጁን ይዘቶች በተመለከተ በስፋት የተዋወቀው የአልኮል ምርቶች በታዳጊዎችና በወጣቶች እንዳይወሰዱ ለማድረግ ታስቦ፣ የአልኮል ምርቶችን በመገናኛ ብዙኃን እንዳይተዋወቁ የተጣለው ገደብ በአምራቾችና በማኅበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሮበት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል ቢባልም፣ በሌሎቹ የአዋጁ ይዘቶች በተለይም በትምባሆ ምርቶች ላይ የተጣለው ክልከላ እምብዛም ግንዛቤ ያልተፈጠረበት በመሆኑ አዋጁ በሥራ ላይ ውሎም ትምባሆን ማጨስ በተከለከለባቸው ቦታዎች ሳይቀር ትምባሆን ማጨስ በተለመደው መልኩ ቀጥሏል። ይህንን የተገነዘበውና አዋጁን በፌዴራል ደረጃ ተፈጻሚ እንዲያደርግ ሕጋዊ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሰሞኑን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

‹‹ሲጃራና ሌሎች ማናቸውም የትምባሆ ምርቶችን ከበር መልስ ባሉ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ለሚያስጨሱ ወይም እንዳይጨስ የማድረግ ግዴታቸውን ለማይወጡ ድርጅቶች የተሰጠ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ማስጠንቀቂያ፣ በአዋጁ የተቀመጡ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸው በሙሉ ስለአዋጁ ክልከላዎች ሊያውቁት ይገባል ያለውን መረጃ በመገናኛ ብዙኃን አማካይኝነት አስታውቋል።

 የትሞባሆ ምርቶችን ማጨስ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ሲባል በአዋጁ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ማድረግና መፈጸም አዋጁ የሚመለከታቸው ሁሉ  ግዴታ ቢሆንም፣ በተለይ በመዝናኛ የንግድ ዘርፍ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ኃላፊነቶቻቸውን እየተወጡ አለመሆኑን ይገልጻል።

አዋጁን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት የተጣለባቸው በሙሉ የተጣለባቸውን ግዴታ የመገንዘብ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ ባወጣው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የድርጅቶቹን ግዴታዎችና በአዋጁ የተቀመጡ መሠረታዊ ክልከላዎችን  በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

ሲጋራና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን ማጨስን አስመልክቶ የተጣለ ክልከላ

አዋጁ ያስቀመጣቸውን መሠረታዊ ክልከላዎች አስመልክቶ ባለሥልጣኑ ባወጣው መግለጫ፣ ለማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ክፍት የሆኑ እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ ምግብ ቤት፣ መጠጥ ቤትና የምሽት ቤት በመሳሰሉት ማንኛውም ድርጅቶች ውስጥ ወይም በአዋጁ አገላለጽ መሠረት ‹‹ከበር መልስ›› ባሉ ቦታዎች የትምባሆ ምርቶችን እንዲጨሱ መፍቀድ በሕግ የተከለከለ ነው። በተጨማሪም በተጠቀሱትና መሰል ቦታዎች በአሥር ሜትር ዙሪያ እንዲጨስ መፍቀድ እንዲሁም በእነዚህ ቦታዎች ውስጥ የሲጃራ መተርኮሻ ወይም ሌላ የትምባሆ ምርትን ለመጠቀም የሚያገለግል ማንኛውም ዕቃ ማስቀመጥ የተከለከለ ነው፡፡

በጉልህ የሚታይ ትምባሆ ማጨስ ወይም መጠቀም የተከለከለ መሆኑን የሚገልጽ ማሳሰቢያና ይህንኑ የሚገልጽ ጉልህ  ባለቀለም ምልክት በድርጅቱ ውስጥ የመለጠፍ ግዴታም ተጥሏል አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የሺሻ ምርትን ማጨስ ወይም መጠቀምን በተመለከተ በአዋጁ የተቀመጠውን ክልከላ ያስታወቀው ባለሥልጣኑ ሺሻ፣ ከትምባሆ ምርቶች አንዱ መሆኑን በማስታወስ የሺሻ ምርትን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ ማከፋፈል፣ እንዲሁም ማዘዋወርና ማስጨስ ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን አመልክቷል።

ሺሻ በመባል የሚታወቀው የትምባሆ ምርት የሲጃራ ምርት በተለየ ሁኔታ መልካም መዓዛ ያለውና የአጫሾችን ጉሮሮ እንዳይቆጠቁጥ ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ፣ የኒኮቲን መጠኑን ዝቀተኛ እንዲሆን በማድረግ አምራቾች ገበያቸውን የሚያሰፉበትና የኮክ፣ አፕል፣ ማርና ሌሎች አማላይ መዓዛዎችን በመጨመር አዳዲስ አጫሾችን የሚፈጥሩበት አንዱ የትምባሆ ምርት ዓይነት ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአዋጁ አንቀጽ 50 መሠረትም ሲጋራና ሌላ የትምባሆ ምርቶችን ማጨስ የሚከለክለውን ድንጋጌ የማስፈጸም ተቀዳሚ ግዴታ የድርጅቶቹ ስለመሆኑ ባለሥልጣኑ አዋጁን ጠቅሶ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

በድርጅት ባለቤቶች ላይ የሚወሰድ የወንጀልና አስተዳደራዊ ቅጣት

ባለሥልጣኑ በቅርቡ የወጣውን አዋጅ ጠቅሶ እንደገለጸው፣ ሲጋራና ሌላ የትምባሆ ምርት ሲያስጨስ የተገኘ ወይም በማስረጃ ሪፖርት የተደረገበት ማንኛውም ድርጅት፣ ከሦስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት፣ ወይም ከብር አንድ ሺሕ እስከ ብር አሥር ሺሕ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ሺሻ የተባለውን የትምባሆ ምርት በተመለከተ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ደግሞ ማንኛውም ሺሻን ያመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ ያከፋፈለ፣ ያከማቸ ወይም የሸጠ ሰው ከሦስት ወር እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራትና ከብር አንድ ሺሕ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ ብር እንደሚቀጣ የባለሥልጣኑ መረጃ ያመለክታል።

ከጤና ተቆጣጣሪ አካል የብቃት ማረጋገጫ ወስደው የንግድ ፈቃድ ባወጡ እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንትና ምግብ ቤት የመሳሰሉ ድርጅቶች በክልል ወይም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የጤና ተቆጣጣሪ አካል በፈቃዳቸው ላይ ከዕግድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

ማንኛውም ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ ምግብ ቤት፣ መጠጥ ቤት፣ የምሽት ቤትና መሰል ድርጅቶች የተቆጣጣሪ አካላት ወይም ኢንስፔክተሮች ለሚያደርጉት የመቆጣጠርና ሕግ የማስከበር ሥራ የመተባበር ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ በማንኛውም ሁኔታ ትብብር ያላደረገ ሰው በአዋጁ መሠረት ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ቀላል እስራት እንደሚቀጣ መግለጫው ያመለክታል።

ባለሥልጣኑ፣ ይህንን ሕግ የተላለፉ ድርጅቶች በሕጉ የተጣለባቸውን ግዴታ የማይወጡ ድርጅቶችን ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል በመጠቆም ማኅበራዊ ኃላፊነትን እንዲወጣ የጠየቀ ሲሆን፣ ይህንን ዕውን ለማድረግ የጥቆማ መቀበያ ነፃ የስልክ መስመሮችንና ሌሎች ወጪ የማይጠይቁ ጥቆማ የማቅረቢያ መንገዶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን የገለጸ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ ትብብር እንዲያደርግም ጠይቋል።  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...