Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘ ኢኮኖሚስት በአፍሪካ ገንዘብ የማሸሽና የሕገወጥ ተግባር ላይ ያተኮረ ጉባዔ አሰናድቷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታዋቂውን ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ጨምሮ ከ80 በላይ ልዩ ልዩ ጉባዔዎችን በማሰናዳት የፖሊሲ ክርክሮችና ተፅዕኖችን በመፍጠር ተጠቃሽ የሆነው ዘ ኢኮኖሚስት ግሩፕ፣ በመጪው ወር በአፍሪካ የሕገወጥ ገንዘብ እንቅስቃሴን ብሎም በንግድና ኢንቨስትመንት ሰበብ የሚካሄዱ ገንዘብ የማሸሽ ተግባራት ላይ ያተኮረውንና ‹‹ግሎባል ኢሊሲት ትሬድ›› የሚል ርዕስ የሰጠውን ጉባዔ በአዲስ አበባ ያዘጋጃል፡፡ ጉባዔው ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በትብብር እንደሚሰናዳ ታውቋል፡፡

ጉባዔው በመጪው ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል ለግማሽ ቀን እንደሚካሄድ፣ ዘ ኢኮኖሚስት በድረ ገጹ ካሠፈረው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባገኘው መረጃ መሠረትም በሁለቱ አካላት ትብብር የሚካሄደው የፖሊሲ ውይይት፣ ትኩረቱን ኢትዮጵያ ጨምሮ በአፍሪካ እየተንሰራፋ የመጣውን ገንዘብ የማሸሽና ለወንጀል ተግባራት ድጋፍ መስጫ እየሆነ ስለመጣባቸው መንገዶች የሚያወያዩ የውይይት መርሐ ግብሮች ተካተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርና በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሰበብ ወደ ውጭ በሚሸሽ ገንዘብና ሀብት ተጎጂ ከሆኑ አንዷ እንደሆነች ማሳያዎችን ያጣቀሰው ዘ ኢኮኖሚስት ግሩፕ፣ በተለይም ግሎባል ፋይናንስ ኢንተርግሪቲ የተሰኘው ተቋም ያወጣቸውን አኃዞችም አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ እያጣች ባለችው ሀብትና በሚሸሽባት ገንዘብ ሳቢያ የሚደርስባት ጉዳት የኢኮኖሚዋን (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) 2.2 በመቶ እንደሚነካ አስፍሯል፡፡ ይህም ማለት በየዓመቱ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከኢትዮጵያ እንደሚሸሽ የሚያመላክት ነው፡፡ ይህም ይባል እንጂ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ እንደ አኅጉር በሥውርና በተቀናጀ መንገድ በንግድና በኢንቨስትመንት አማካይነት በሕገወጥ መንገድ የሚሸሽባቸውንና የሚዘረፉትን ሀብት ለመከላከል ሲያደርጉ የሚታዩት ጥረት እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ እንደሚገኝ ዘ ኢኮኖሚስት ይጠቅሳል፡፡

ከአፍሪካ በየዓመቱ ከ50 እስከ 70 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደሚሸሽ በአንድ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመሆን ያካሄዱት ጥናት አረጋግጧል፡፡ ይህ ይባል እንጂ እንደ ግሎባል ኢንተግሪቲ ያሉት ተቋማት ግን ይህንን አኃዝ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያደርሱታል፡፡ በአንፃሩ በመላው ዓለም ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚሸሽና ለሽብር፣ ለሕገወጥ የሰዎችና የአደንዛዥ ዕፆችና ለመሳሰሉት ዝውውሮች እንደሚውል መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣውን የጦር መሣሪያ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ ድርጊቶች ከገንዘብ ማሸሽ ጋር እንደሚያያዙ ዘ ኢኮኖሚስት ካመላከተባቸው መካከል በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ከሱዳን ሲገባ እየተያዘ የሚገኝበትን አግባብ ለመሳያነት ተጠቅሞበታል፡፡ እንዲህ ያለው ክስተት አፍሪካን ዳግም እያንሠራሩ ለሚገኙት የአልቃይዳና የአይኤስኤስ አሸባሪ ድርጅቶች ምቹ ዒላማና መሸሸጊያ እንዲያደርጋት ሥጋቱን ገልጿል፡፡  

በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ቀጠሮ ለተያዘለት ጉባዔ፣ የአፍሪካ መሪዎችና የመንግሥት ተጠሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ አካላት፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻዎች እንደሚሳተፉበት ሲታወቅ፣ እየተስፋፋና እየገዘፈ ለመጣው የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ዝርፊያ የወደፊት መፍትሔን የሚያመላክቱ ሐሳቦችም እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡

በበርካታ አገሮች ገንዘብ የማሸሽ ተግባር ከሚፈጸምባቸው መንገዶች አንዱ የተጭበረበረ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ብሎም የታክስ ማጭበርበር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በገቢና ወጪ ንግድ ዘርፍ የተሠማሩ ወይም ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች፣ የግዥ ሰነዶችን በማጭበርበር ማለትም ለጥሬ ዕቃና መሰል ወጪዎች ከፍተኛ ወጪ እንዳወጡ የሚያሳዩ ሰነዶችን በማዘጋጀት (ኦቨር ኢንቮይሲንግ)፣ በአንፃሩ ወደ ውጭ የላኳቸው ዕቃዎች አነስተኛ ገንዘብ እንዳስገኙ በማስመሰል (አንደር ኢንቮይሲንግ) ገንዘብ የማሸሽ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በተጨማሪም የረዥም ዓመታት የታክስ ዕፎይታና ማበረታቻዎችም ገንዘብ ለማሸሽ ከሚጠቀሱ አመቺ አሠራሮች ውስጥ ይመደባሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች