Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተስፋ የሰጡ የለውጥ ዕርምጃዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከቱ የሪፎርም እንቅስቃሴዎች ኢንዱስትሪውን ከተለመደ አሠራሩ የሚሻሻልበትን መንገድ እንደሚጠርጉለት የዘርፉ ተዋንያን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን አላላውስ ያሉ ሕግጋትን የሚያፍታቱ ማሻሻያዎች ሲደረጉ መታየታቸው ተስፋ እንደሚያጭር የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡

ገደብም ክልከላም ተጥሎባቸው ሳይተገበሩ የቆዩ አሠራሮች ነፍስ እንዲዘሩ የሚያደርጉ ውሳኔዎች ሲተላለፉ መታየታቸው በለውጡ እየታዩ ከመጡ በጎ ጅምሮች ውስጥ ይጠቀሳል የሚሉት ባለሙያዎች፣ ሪፎርሙ ሊመለከታቸው ይገባል፣ መስተካከል አለባቸው በማለት በተደጋጋሚ ሲነሱ ከነበሩትና ምላሽ እንደተሰጠባቸው ከሚወሱት አንዱ ትውልደ ኢትዮጵያውን በባንክ መስክ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው ረቂቅ ሕግ ለመጨረሻው የውሳኔ ሒደት መቅረቡ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አላላውስ ይሉ የነበሩ መመርያዎችም እየተስተካከሉ ነው፡፡ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለማቅረብ በማሰብ ለዚሁ ሥራ ባንክ እያደራጀ በነበረበት  ወቅት በመጨረሻው ምዕራፍ አይቻልም የተባለው ዘምዘም ባንክ፣ በዚህ እገዳው ተነስቶለት ባሰበው መንገድ ዳግም ለመጓዝ ይሁንታ ማግኘቱ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው መስክ ከታዩ ጉልህ ለውጦች አንዱ ተደርጓል፡፡

ከዘምዘም ባንክ አደራጆች ለመገንዘብ የተቻለው ‹‹ለጥያቄያችን የተገኘው አወንታዊ ምላሽ›› አማራጭ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት መንግሥት የቀደመ አቋሙን እንደቀየረ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ትክክለኛ ሪፎርም መታየት ጀምሯል የሚለውን የመስኩን ተዋናዮች አመለካከት ያጠናከረው ሌላው ነጥብ፣ በቅርቡ መንግሥት ለግል ባንኮች 100 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁና ሌሎችም ማስተካከያዎችን ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተነሳሽነት በአብዛኞቹ የግል ባንኮች ዘንድ ሙገሳ እያተረፈለት ነው፡፡ ከቆንጣጭና አይቻልም ባይነት ወደ ይፈቀዳል የመጣ አካሄዱን አሞካሽተዋል፡፡ በአንፃሩ አሁንም የባንኩን አካሄድ በጥርጣሬ የሚመለከቱም አሉ፡፡

ለግል ባንኮች የተፈቀደው 100 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ ምንዛሪ ፍላጎት መናርና ለየባንኮቹ ከቀረበው ጥያቄ አንፃር ግን እዚህ ግባ የማይባል፣ ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› እንደሆነ የሚገልጹትም ቢሆኑ፣ ከሩብ ክፍለ ዘመን ወዲህ ባለው የግል ባንኮች ጉዞ፣ የውጭ ምንዛሪ ተለቆላቸው አያውቅም ነበርና ጅምሩ ትልቅ መልዕክት እንዳለው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስታገስ መንግሥት የሚያቀርበው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለግል ባንኮችም መስጠቱ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡

ይህ አካሄድ የፖሊሲ ለውጥ ሊያስብለው እንደሚችል የሚጠቅሱም አልታጡም፡፡ በውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ላይ የተቀመጠው መመርያና ሌሎችም የማያፈናፍኑ ሕጎችን ለመለወጥ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንደተረዱ የገለጹት የግል ባንክ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ዘርፉን የከረሙ ችግሮች ለመቅረፍ ተስፋ የሚሰጥ ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ የባንኩ የለውጥ ዕርምጃ በጅምር እንደማይቆም ተስፋ በማድረግ፣ በውድድር ሜዳው ላይ ይብዛም ይነስም የግል ባንኮች ያለ ልዩነት የሚስተናዱበት ጅምር እየመጣ ለመሆኑ አመላካች የሚያደርጉትም አሉ፡፡

አንድ የግል ባንክ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ ለአንድ ወገን ያደላ ጠባይ የነበራቸው መመርያዎችን ሲተገብር የቆየው ገዥው ባንክ፣ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትን ለማረጋጋት በሚል ሰበብ ገንዘቡ በንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንዲያልፍ ማድረጉን በዋቢነት አንስተዋል፡፡ ይህን አሠራር በመለወጥ የግል ባንኮችም ለውጭ ምንዛሪ ታሳቢ መደረጋቸው ብቻም ሳይሆን፣ ‹ችግራችሁ ምንድነው፤ ምን ይሻሻልላችሁ›  ተብለው ምክርና ሐሳብ እንዲሰነዘሩ ዕድል ማግኘታቸውም ከዚህ በፊት ያልነበረ በመሆኑ እንደ መልካም ጅምር ታይቷል፡፡

የግል ባንኮች አሁንም መሻሻል አለባቸው በማለት የጠቀሷቸው መመርያዎችና አሠራሮችን ፊት ለፊት ቀርበው መግለጽ የቻሉበትን መድረክ ማግኘታቸውም የለውጥ አጥቢያ ተስፋን እንዳስጨበጣቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህም ሆኖ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ሪፎርሙ ሊመለከታቸው የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ያሳስባሉ፡፡ ለውጥ ይሻሉ የተባሉ ጉዳዮች በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተንፀባረቁ ሲሆን፣ በመድንና በባንኮች ማኅበራት በኩልም መሻሻል አለባቸው የተባሉ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ ትክክለኛ ተወዳዳሪነት እንዳይኖር ያደረጉ አሠራሮችና መመርያዎች መስተካከላቸው የፋይናንስ ዘርፉን በተለይም የባንክና የመድን ተቋማትን ወደፊት ሊያራምዱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙት የባንክ ባለሙያዎች፣ ወደፊትም ቢሆን ተወዳዳሪነትን የማያገናዝቡ መመርያዎች መፈተሽ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

የባንኮችና የመድን ድርጅቶች ኃላፊዎች ያቀረቧቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች የተቀበለው ብሔራዊ ባንክ፣ የመጨረሻ ምላሹን በቅርቡ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በተለይም ገዳቢ መመርያዎቹ ጊዜ ሳያሳጣቸው ማስተካከሉ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ኃላፊዎቹ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የግል ባንኮች ከበላይ የሚተለፍባቸው መመርያ ነበረባቸው የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ የግል ባንኮች አስፈላጊነት ላይ የነበረው ምልከታ የተዛባ ስለነበር፣ በገዥው ባንክና በግል ባንኮች መካከል የነበረው ግንኙነትም የአዛዥና ታዛዥ ነበር ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ብዙውን ጊዜ የአንድ ወገን መመርያዎችን በማውጣት ባንኮችን ሲጫን ቆይቷል በማለት እንደ ፖሊሲ አውጭነቱ ማስፈጸም እንጂ ፖሊሲው የግል ባንኮች ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ተፅዕኖ ብዙም ግድ እንዳልነበረው  ይገልጻሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮችና የመንግሥት ባንኮችን የሚመለከትበት መነጽር የተዛባ ነው በማለት የቀድሞውን የገዥውን ባንክ አሠራሮች ባንኮች ተትተዋል፡፡

መንግሥት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቁጠባ ሒሳብ በንግድ ባንክ ብቻ እንዲወሰን ማድረጉ በግል ባንኮች ዘንድ የሚነሳ የገዥው ባንክ የአድሎ አሠራር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግሥት ቢዝነሱ ውስጥም በመግባት የመቆጣጠር አዝማሚያውን ያሳያል ያሉት ባንኮች፣ ይህም በተለይ የግል ባንኮችን ያገለለ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ቁጠባ የግል ባንኮች እንዳይሳተፉ የተደረገው፣ አቅም የላቸውም በሚል ምክንያት ነበር፡፡ ‹‹እንደአቅማችሁ መጠን ተሳተፉ ቢባሉ እንኳ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ስለዚህ በፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ ውስጥ አግላይ አሠራር ነበር፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

አሁን የተጀመረው፣ መደማመጥ የታከለበት ሪፎርም ብዙ መንገድ ይቀረዋል የሚለውን አመለካከት ባንኮች እንዲያንፀባርቁ ያስገደዳቸው ሌላው ጉዳይ፣ ንግድ ባንክ ለብቻው እንዲሠራበት የተደነገገውና የግል ባንኮች አሁንም ድረስ እንዳይሠሩ የታገዱበት ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ወደ ቻይና የሚላከው የውጭ ንግድ ነው፡፡ የግል ባንኮች ከቻይና ገበያ እንዲገለሉ በመደረጉ፣ ወደ ቻይና የሚሄድ ማንኛውም የውጭ ንግድ፣ በንግድ ባንክ በኩል መሆኑ የውድድር ሜዳውን አባጣና ጎርባጣ እንዳደረገው ባንኮች ይጠቅሳሉ፡፡ መንግሥት የራሱን ባንክ በማጠናከር የግል ባንኮችን ችላ ያለበት አካሄድ እንደነበር በመግለጽ፣ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ሪፎርም እንዲህ ያሉትንም ያፈነገጡ አሠራሮች እንዲመለከታቸው ገዥው ባንክ እየጠየቀ ነው፡፡

በአንድ የንግድ መስክ ላይ በሚተውኑ አካላት ላይ የመንግሥትና የግል በሚል ልዩነት፣ መመርያዎችን ተፈጻሚ ማድረጉ ሲያስተቸው የኖረው ብሔራዊ ባንክ፣ ራሱ ባወጣው ሕግ መሠረት የተቋቋሙ ሆነው ሳለ፣ በተለይ የግል ባንኮች እስኪነስራቸው የመቆጣጠርና ስህተት ከፈጸሙም መቀጣጫ የማድረግ አካሄድ እንጂ እንዲያድጉ፣ እንዲስፋፉና እንዲጠነክሩ የማገዝ ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነበር ያሉት የግል ባንኮች አመራሮች፣ አሁን ግን ይህ ችግር ይቀረፋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ብድር 27 በመቶ ተሠልቶ ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድደው መመርያ ንግድ ባንክን የማይመለከት መሆኑ በአንድ የንግድ ሥራ መስክ ለሚወዳደሩ መንግሥታዊና የግል ባንኮች የተቀመጠ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ጫና ውስጥ የሚጥል እንደሆነ በአስረጅነት ያቀርባሉ፡፡ የገዥውን ባንክ ምልከታንም ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱት ውስጥ በጉልህ እንዲታይ ያደርገዋል ይላሉ፡፡

የዚህ መመርያ መውጣት ዋነኛ ዓላማ ከግል ባንኮች የሚሰበሰበው ገንዘብ መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የልማት ሥራዎች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ብድር እንዲመቻችላቸውና ገንዘብ እንዲያገኙ ለማገዝ ነው፡፡ እስካሁን ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ ባንኮቹ ለቦንድ ግዥ ያዋሉ ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ በአግባቡ ሥራ ላይ ዋለ የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዓላማው ልማት እስከሆነ ድረስና በትክክል እንዲተገበር እስከተፈለገ ድረስ ግን ሁሉም ባንኮች ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው ተብሏል፡፡ በተለይም ንግድ ባንክ ከሚያንቀሳቅሰው ሰፊ ገንዘብ ውስጥ መንግሥት ለልማት ሥራ የሚያውለው ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት ይችል ነበር፡፡

ስለዚህ የዚህ መመርያ መሻሻል ጥያቄ ባይኖረውም እንደነበር ይቀጥል ቢባል እንኳ፣ በግል በሌላ መመርያ አፈጻጸሙ እስካሁን በተካሄደበት መንገድ መሆን እንደሌለበት በማመን ይህ መመርያ መስተካከል እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት አግላይ አሠራሮች ኢንዱስትሪውን አያሳድጉም፡፡ የውድድር ሜዳው እኩል መሆን አለበት፡፡ የውጭ ባንኮች ይግቡ ቢባል እንዲህ ዓይነት መመርያዎች ቦታ አይኖራቸውም፤›› በማለት የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች ሁሉንም በኩል ማስተናገድና መግዛት የሚችሉ ሆነው መቀረፅ እንዳለባቸው የባንክ ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር በኩል በግልጽ ከቀረቡ ጥያቀዎች መካከል በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ባለአክሲዮኖች የባለቤትነት ድርሻቸው ላይ የተጣለባቸው ገደብ መነሳት አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህንን ሐሳብ ባንኮችም ይጋሩታል፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ አንድ ባለአክሲዮን ሊኖረው የሚገባው የአክሲዮን ድርሻ ከጠቅላላው ካፒታል አምስት በመቶ በላይ መብለጥ አይችልም የሚለው መመርያ፣ ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ ባለሀብቶችን የሚገፋ ነው በመባሉ እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡

ይህ መመርያ ትርጉም አይሰጥም የሚሉት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላ፣ ‹‹ገንዘብ ያለው ሰው የፈለገውን ያህል ኢንቨስት ቢያደርግ ለምን እንደሚከለከል አይገባኝም፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያለው መመርያ መስተካከል ያለበት በመሆኑ ማኅበሩ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ ተቋማት የቦርድ አባላት ቁጥር ዘጠኝና ከዘጠኝ በላይ መሆን አለበት የሚለው ድንጋጌም ተገቢ መስሎ ስለማይታያቸው፣ የቦርድ አባላቱን ቁጥር የሚወስነው የብሔራዊ ባንክ መመርያም መለወጥ አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡

በዚህ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ ዛሬ ውጤታማ የሚባል ቦርድ ሦስትም አምስትም ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶች የሚያመለክቱ አነስተኛ ቁጥር ያለው ቦርድ ውጤታማ ሥራ ሊሠራ ይችላልና የቦርድ አባላት ቁጥሩ ከሦስት ጀምሮ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ የንግድ ሕጉም ቢሆን የተቋማትን የቦርድ አመራሮች ከሦስት ያላነሱ በማለት የሚያስገድድ በመሆኑ፣ በዚሁ መልኩ መቀጠል እንደሌለበትና እንዲሻሻል ጥያቄ ስለመቅረቡ መዘገብ ተችሏል፡፡ ስለዚህ የቦርድ አባላት ቁጥር ብዛትን አግባብ አለመሆኑን በማመላከት ብሔራዊ ባንክ ሊያስተካክለው እንደሚገባ ማኅበሩ አቋም መያዙን አስታውቀዋል፡፡ በኢንሹራንስ ማኅበሩ ምልከታ መሠረት አንዳንዶቹ መመርያዎች ለባንኮች ተብለው ቢወጡም፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም እንዲገዙበት የሚደረግበት አሠራርም እንዲፈተሽ አቶ ያሬድ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሌላው የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ለማስተዳደር ከወጡ መመርያዎች ውስጥ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማዋል ያለባቸውን የኢንቨስትመንት መጠንን የሚመለከተው ነው፡፡

በመመርያው መሠረት አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ከሰበሰበው አረቦን ለተለያዩ የኢንቨስትመንቶች ላይ ማዋል የሚችለው 35 በመቶ ነው፡፡ ይህም ቢሆን የተወሰነውን ለባንክ፣ የተወሰነውን ለሪል ስቴት እያለ የሚያካፍል ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ በአቅማቸው ኢንቨስት እንዳያደርጉ የሚገደድባቸው በመሆኑ መጠኑ እንዲስተካከል ተጠይቋል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው የመድን ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ሥራ ሁኔታ የሚደነግገው መመርያ ቁጥር SIB/25/2004 ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ከማርች 2004 ጀምሮ በሥራ ላይ ውሎ ይገኛል፡፡ መመርያው የኢንቨስትመንት ሥራዎችን በሁለት ቋቶች (Funds) ዓይነቶች የሚከፍላቸው ሲሆን፣ እነዚህም የአጠቃላይ ኢንሹራንስ ፈንድና የሕይወት ኢንሹራንስ ፈንድ አጠቃቀም ብሎ በሁለት ከፍሏቸዋል ያሉት አቶ ያሬድ በሚከተለው ሰንጠረዥ የኢንቨስትመንት መጠኑን አቅርበውታል፡፡  

ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው

በመሆኑም በመቶኛ የሚሠላው ከኩባንያው ተቀባይነት ያለው ሀብት (Admitted Asset) ብቻ ሲሆን፣ በተለይም በ‹‹ሀ›› የተቀመጠው ምጣኔ 65/50 በመቶ ቢሆንም፣ በአንድ ባንክ ውስጥ በማናቸውም ጊዜና ሁኔታ ከ25 በመቶ በላይ ሀብት ማስቀመጥ እንደማይቻል ድንጋጌው ማስቀመጡን በማመላከት ለውጥ እንደሚያስፈልገው አብራርተዋል፡፡

ይህን መሰሉ የማስተካከያ ዕርምጃ የሚወሰድ ከሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለያየ አዋጭ ኢንቨስትመንቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ እርሱንም ኢኮኖሚውንም ማገዝ የሚችሉ በመሆኑ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች