Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንሳ ሚስጥራዊ ቋቶችቹ ተሰብረው መረጃዎች አፈትልከዋል መባሉን አስተባበለ

ኢንሳ ሚስጥራዊ ቋቶችቹ ተሰብረው መረጃዎች አፈትልከዋል መባሉን አስተባበለ

ቀን:

የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ ሳቢያ በተቋሙ ውስጥ ቁልፍ ሚና በነበራቸውና በለቀቁ በርካታ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በኩል መረጃዎች አፈትልከዋል መባሉን አስተባበለ፡፡

ኤጀንሲው ቁልፍ ሚና የነበራቸው ኃላፈዎችና ሠራተኞች በብዛት መልቀቃቸው ከባድ ጫና እንዳሳደረበት ያመኑት የኢንሳ ተጠባባቂ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ተስፋዬ፣ በተለይ ተቋሙ የሪፎርም ዕርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ ያለፉት ጥቂት ወራት ባልተመለደ ሁኔታ ከባድ ሆነውበት እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሰሎሞን ገለጻ፣ የፖለቲካ ሪፎርም ሒደቱ ለበርካታ ወሳኝ ኃላፊዎች መልቀቅና አብረዋቸው ለወጡ ወሳኝ መረጃዎችና መሣሪያዎች መሸሽ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ኃላፊዎቹ ይዘዋቸው የሄዱት መረጃዎችና መሣሪያዎች ለሳይበር ደኅንነት ወሳኝ ሚና ነበራቸው ብለዋል፡፡ ‹‹የኤጀንሲው ሠራተኞች በብዛት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የተወሰነ ፖለቲካ ቡድን ፍላጎት አራማጅ እንደነበሩ አይካድም፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ በአገሪቱ መካሄድ የጀመረው ፖለቲካዊ ለውጥ በደኅንነት መዋቅር ውስጥ ይንቀሳቀሱ በነበሩ በርካታ አካላት ላይ ከፍተኛ መደናገጥን በማስከተሉ፣ በአንድ ጊዜ በርካታ የደኅንነት አባላት ተገቢ ባልሆነ መንገድ መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ተገቢውን መንገድ ሳይከተሉና የይለፍ ቀልፎችን ጨምሮ እጅግ ጥብቅ መረጃዎችን ሳያስረክቡ ሄደዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከተቋሙ ተሰብረውና ተበርብረው ስላፈተለኩ የኢሜይል መልዕክቶችና መሰል መረጃዎች እየተሠራጩ የሚገኙትን ሐተታዎች፣ ከዚህ አግባብ መመልከት እንደሚገባ አቶ ሰሎሞን አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁንና ሐሙስ ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹SafetyDetective.com›› የተሰኘና ፀረ ቫይረስ ሶፍትዌሮችን የሚገመግም ድረ ገጽ ያወጣው ሪፖርት፣ የኢንሳ 142 አባላት የኢሜይል አድራሻ ተጠልፎና ተበርብሮ መረጃዎች እንዳፈተለኩ አስነብቧል፡፡ የኢንሳ ደኅንነት አባላት በቀላሉ ሊከፈት የሚችል የይለፍ ቁልፍ መጠቀማቸውን ሲያብራራም ‹‹P@$$word›› የሚል የይለፍ ቃል መጠቀማቸውን ድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ ድረ ገጹ ለክፍያ በማይሠራ የምርምር ላቦራቶሪው አማካይነት የኢንሳን የመረጃ ቋት በመበርበርና የኢሜይል ልውውጦችን በመጥለፍ፣ ጠቃሚ መረጃዎችን እንደመነተፈ ይገልጻል፡፡ ይህ የሆነው ኢንሳ አሁንም ድረስ ጥቅም ላይ ያሉ የ300 አባላቱን የኢሜይል አድራሻዎችና የይለፍ ቃላት ለመቀየር በሚሯሯጥበት ወቅት ነው፡፡

ፖለቲካዊ መነሻ ያላቸው ብርበራዎች አዲስ ነገር እንዳልሆኑ፣ በርባሪዎች የደኅንነት ኤጀንሲን መረጃ መዋቅር በቀላሉ ሊሰብሩ ይችላሉ ያለው ድረ ገጹ፣ የኢንሳ ግን አሳሳቢ ነው ከማለቱም ባሻገር ችግሩን በጣም የከፋ የሚያደርገውም በኢንሳ አገልግሎት ላይ የዋሉት የይለፍ ቁልፎች የመጀመሪያ ደረጃ ወይም በቀላሉ ሊሰበሩ የሚችሉ መሆናቸው ለማመን የሚከብድ ነው ሲል ሁኔታውን ይገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ300 የይለፍ ቁልፎች ውስጥ 142 ‹‹P@$$word›› የሚለውን የይለፍ ቃል ይጠቀሙ እንደነበር፣ ሌሎች 62 የይለፍ ቁልፎችም ‹‹123›› ቀጥሮችን በመደዳ ይጠቀሙ እንደነበር፣ እነዚህንም ለመበርበር በእጅጉ ቀላል ሆነው እንደተገኙ አሥፍሯል፡፡ ይኸው የበርባሪው ድረ ገጽ ሪፖርት፣ የተቋሙ ሰርቨሮች ባይበረበሩ እንኳ የቀደሙትን ተጋላጭ የይለፍ ቁልፎች ለመተካት የዋሉትም ቢሆኑ በቀላሉ ሊበረበሩ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ የኢንሳ የቴክኒክ ክፍል ባልደረባ በበኩሉ፣ አፈትልከው ወጡ የተባሉት መረጃዎችና የተበረበሩ ኢሜይሎች እንደሚባለው ሳይሆን፣ ሆን ተብለው ለመረጃ ቅርበት በነበራቸውና ባደረባቸው ቅሬታ ከአንድ ዓመት በፊት ተቋሙን በለቀቁ አባላት የተሠራጩ ናቸው በማለት ገልጿል፡፡

‹‹አንዳንድ የቀድሞ ሠራተኞች ከነበራቸው የሥራ ኃላፊነት አኳያ ያገኙ የነበሩትን መረጃ ይዘው ሄደዋል፡፡ ለዚህ ነው አሁን የምናየው ድርጊት እየተፈጸመ ያለው፤›› በማለት ወጣቱ የመረጃ ባለሙያ ይናገራል፡፡ የወጡት መረጃዎችም መረጃውን ከሚያስተዳድረው ዋናው አካል የተቀዱ እንጂ፣ እንደሚባለው ከተበረበረ ኢሜይል የተገኙ አይደሉም በማለት የተጠቀሱት የኢሜይል አድራሻዎችም የቀድሞ አባላት እንደሆኑ አብራርቷል፡፡

ምንም እንኳ በድረ ገጹ ይፋ የተደረጉት ቀላልና በቀላሉ የሚበረበሩ የይለፍ ቃላት ከተምዶ አሠራር ውጪ ባይሆኑም፣ አዲስ የኢሜይል አድራሻ በሚፈጠርበት ወቅት አብረው የሚወጡ ከመሆናቸው ባሻገር በሞባይል ስልክ ፎቶ እየተነሱ የተሠራጩትና የተበረበሩ ኢሜይሎች እየተባሉ የሚጠቀሱት ግን ጊዜ ያለፈባቸውና ከዋናው የመረጃ ምንጭ የተቀዱ እንደሆኑ የቴክኒክ ባለሙያው ይደመድማል፡፡

ተቋሙ አፋጣኝ የጥገና ዕርምጃዎችን ባይወስድ ኖሮ ከዚህም የበለጠ መረጃ ሊወጣ ይችል እንደነበር አቶ ሰሎሞን ይገልጻሉ፡፡ ተቋሙ የሪፎርም ዕርምጃዎቹን እያጠናከረ በሚመጣበት ወቅትም፣ ከዚህም የባሰ ጉዳይ ሊያጋጥመው እንደሚችል ሥጋታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከአሁኑ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን በማስቀረት በሙያዊ ብቃትና ክህሎት ላይ የተመሠረተ አካሄድ መከተል ጀምሯል የተባለለት ኢንሳ፣ ወደፊት የፖለቲካ ረፎርሞች ጫና ውስጥ እንዳይከቱት የሚያስችሉ አካሄዶችን እየተገበረ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ በተለይም የሚከተላቸው አሠራሮች ግለሰብ ተኮር እንዳይሆኑና በሰዎች ላይ ጥገኛ እንዳያደርጉት ቅድሚያ የተሰጣቸው ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...