Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ሺሕ ፋብሪካዎች እንደሚገቡ ይጠበቃል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአሥር የውጭ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል

በኢትዮጵያ እየተገነቡ ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ በሆነው በቂሊንጦ የመድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከአንድ ሺሕ ያላነሱ ፋብሪካዎች ለተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚውሉ መድኃኒቶች እንዲያመረቱና ከአገር ውስጥ አልፈውም ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ መታቀዱ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከ1,000 በላይ አምራቾች በመድኃኒት አምራችነት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

የግንባታ ሥራው ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሙሉ በሙሉ ለመድኃኒትና ለተያያዥ ምርቶች የሚውል ሲሆን፣ በ279 ሔክታር ክልል ውስጥ ግንባታው እየተጠናቀቀ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅትም ከ85 በመቶ በላይ ግንባታው እንደተገባደደ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዓለም ባንክ በሰጠው የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ግንባታው በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ዓምና ሥራ እንደሚጀምር ይጠበቅ የነበረው ይህ የመድኃኒት ማምረቻ ፓርክ፣ ግንባታው መዘግየት ቢታይበትም አቶ ተመስገን በዚህ እንደማይስማሙ ጠቅሰው፣ እንደ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሁሉ ከይዞታና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ሲነሱበት እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከ85 በመቶ ያላነሰውን የመድኃኒት አቅርቦቷን ከውጭ የምታስገባበትን ሒደት በከፍተኛ መጠን በአገር ውስጥ በማምረት ለመተካት ያስችላል ተብሎ የሚጠበቀው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለመሥራት ፍላጎት ካሳዩ አሥር የውጭ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች መፈረማቸውን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን አስታውቀዋል፡፡ ትልልቅና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸውን አምራቾች በመምረጥ የአገር ውስጥ ፍጆታን የሚያሟላ፣ እንዲሁም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ምርት እንደሚመረት ገልጸዋል፡፡

ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድና ሁለት፣ ቂሊንጦና የኢይቲ ፓርክን በአንድ ያካተተና በዙሪያቸው የሚኖረውን ማኅበረሰብ ባለበት የሚያቅፍ ትልቅ የኢንዱስትሪ ከተማ እንደሚፈጠር የገለጹት ተመስገን፣ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሰው ልጅ ከሚውል መድኃኒት ባሻገር የእንስሳት መድኃኒት፣ የምርት ማሸጊያዎችና ሌሎችም ተጓዳኝ የሕክምና ምርቶች የሚፈበረኩበት በአዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ የሚገነባ ግዙፍ ፓርክ ነው ብለዋል፡፡ 

ከመነሻው በ337 ሔክታር መሬት ላይ እንዲያርፍ ታቅዶ የነበረው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ማሻሻያዎች ታክለውበት፣ ይዞታው ወደ 279 ሔክታር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በቀን 14 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት እንደሚኖረው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል፡፡ 

በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመድኃኒት ግዥ የምታውለው ኢትዮጵያ፣ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይም ውጭ ሄደው ለሚታከሙ ሕሙማን ታወጣለች፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት 22 የውጭና የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች በኢትዮጵያ ውስጥ ቢንቀሳቀሱም፣ መሸፈን የቻሉት ከ20 በመቶ ያነሰውን የመድኃኒት አቅርቦት ፍላጎት እንደሆነ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ በአገር ውስጥ መድኃኒት የሚያመርቱ ኩባንያዎችን ለማበረታታት የአሥር ዓመታት የመድኃኒት ዘርፍ ስትራቴጂና የድርጊት መርሐ ግብር መቀረፁን ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ መንግሥት በቅርቡ ወደ ሥራ ያስገባው የግልና የመንግሥት አጋርነት ማዕቀፍም በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና፣ በአገልግሎት አቅርቦት መስክ በተለይም በከፍተኛው የሕክምና አገልግሎት መስክ ለመሠማራት የሚችሉበትን ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 200 የመድኃኒት አስመጪዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ልዩ ልዩ መድኃኒቶችን በማስመጣት እንደሚያከፋፍሉ የጤና ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት ውስጥም 15 በመቶውን የመድኃኒት አቅርቦት እያሟሉ የሚገኙት የአገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ እስከ 70 በመቶ እንደሚደያድግ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

መንግሥት በኢትዮጵያ በመድኃኒት አምራችነት ለሚሳተፉ ኩባንያዎች እስከ 14 ዓመታት የሚቆይ የኩባንያ የገቢ ግብር ዕይታ እንደሚሰጥ ሲታወቅ፣ በግለሰብ ገቢ ግብር ዕፎይታም ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ታሳቢ የሚደረጉበት አሠራር ዘርግቷል፡፡ አዲስ መድኃኒት ለሚቀምሙና ለሚያዘጋጁም እስከ 12 ዓመታት የሚፀና የታክስ ዕፎይታ ይሰጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች