Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅና የተደቀነው ሥጋት

የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅና የተደቀነው ሥጋት

ቀን:

ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ በፓርላማው የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተዘጋጀው ውይይት፣ የሕገወጥ ጦር መሣሪያዎች ዝውውር መበራከትና ኅብረተሰቡ ከጦር መሣሪያ ጋር ያለው ቁርኝነትና መስተጋብር ለሕጉ እንቅፋት ሊሆን ይችላሉ የሚል አስተያየት ተደምጧል፡፡ በተለይ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከአንድ በላይ የጦር መሣሪያ ሊኖር አይገባም የሚለው ድንጋጌ፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የያዙዋቸውን የጦር መሣሪያዎች እንዳያስመዘግቡ እንቅፋት እንደሚሆን ተወስቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአንድ ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ዋጋ ከ100 ሺሕ እስከ 120 ሺሕ ብር መድረሱን መስማታቸውን በውይይቱ ላይ ያነሱት አንድ ተወያይ፣ ‹‹አርሶ አደሩ በሬውን ሸጦ ድህነትን እየገዛ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ረቂቂ አዋጁ የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸው ግለሰቦች ሊያሟሉ የሚገባቸውን መሥፈርት ሲዘረዝር፣ የዕድሜ መነሻንና አካላዊ ሁኔታን አለማስቀመጡ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ በአገሪቱ ያሉትን የጦር መሣሪያዎች ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ ማስገባት ስለሆነ፣ አስተያየት ሰጪዎች ለግብዓት የሚረዱ ሐሳቦችን አሰምተዋል፡፡

ከሦስት ወራት በፊት የአማራ ክልል ፖሊስ ደረሰኝ ባለው የደኅንነት መረጃና የሕዝብ ጥቆማ በአንድ የክልሉ ፖሊስ ውስጥ በኮማንዶር ማዕረግ የሚጠራ የፖሊስ አባል ቤት ድንገተኛ ፍተሻ ያደርጋል፡፡ ጥቆማው የፖሊስ ኮማንደሩ የሕገወጥ ጦር መሣሪያ አካማችቷል የሚል ነበር፡፡ የክልሉ ፖሊስም ከባህር ዳር እንዳስታወቀው በጥቆማው እውነትም እንደተባለው በፖሊሱ መኖሪያ ቤት ከ400 በላይ ሽጉጦች ተገኝተው ነበር፡፡

ይህ ዜና በወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጥያቄዎችንም አጭሮ ነበር፡፡ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ የሚነሳ ሥጋት እያየለ መጥቷል፡፡ ይህ ሥጋት ደግሞ በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ወዲህ፣ የሕገወጥ ጦር መሣሪያን በተመለከተ ከዜናነት አልፎ እንደ መደበኛ የዕለት ወሬ መሆን ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች ከጎረቤት አገሮች ወደ መሀል አገር የሚገቡት መጠናቸው ሲጨምር ገበያው ደርቷል እየተባለ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዚህ ሥጋት እየናረ መምጣቱን ተከትሎ መንግሥት በሚያዝያ ወር አዲስ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለፓርላማ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ፓርላማውም በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ መጠነኛ ውይይት አድርጎ ለውጭ ግንኙትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም የተመራለትን ረቂቅ አዋጅ በመርመር ላይ ሲሆን፣ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ በረቂቁ ላይ ሕዝባዊ ውይይት ጠርቶ ተወያይቷል፡፡ ምንም እንኳ በውይይቱ ላይ የተገኙት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ውጪ ሌሎች አካላት ባይገኙም የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወኪሎችና የቋሚ ኮሚቴው አባላት ብቻ ነበሩ የተገኙት፡፡

ውይይቱን የመሩት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ሲሆኑ የረቂቅ አዋጁን ዝግጅት፣ ዓላማ፣ አስፈላኒነትና ዝርዝር ድንጋጌዎችን በተመለከተ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተወካዩ አቶ በላይሁን ይርጋ ቀርቧል፡፡ የአቶ በላይሁን ማብራሪያ እንደ ውይይት መነሻ ካቀረበ በኋላ፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላት በረቂቅ አዋጁ ዝርዝር ድንጋጌዎች በጥልቀት ተወያይተዋል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ዝግጅትና አስፈላጊነት ቢስማሙም፣ በርካታ ሥጋቶችንና ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አልቀረም፡፡

በተለይ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ከጎረቤት አገሮች በሕገወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች በገፍ እየገቡና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በመጥቀስ፣ አዋጁ ለመጀመርያ ጊዜ ተዘጋጅቶ መቅረቡን በማወደስ ወቅታዊ ዕርምጃ ነው ሲሉ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ የጦር መሣሪያ ለዓመታት በአርሶ አደሩና በአርብቶ አደሩ እጅ መቆየቱና መከማቸቱ፣ እንዲሁም የጦር መሣሪያ ከኅብረተሰቡ ጋር ካለው ቁርኝትና መስተጋብር አንፃር ሕጉን ለመተግበርም ሆነ ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄም የተለያዩ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል፡፡

በአባላቱ ተለይተው ከተነሱት የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች ውስጥ ለአንድ ቤተሰብ ከአንድ  ሰው  በላይ መሣሪያ የማግኘት ፈቃድ አይሰጠውም የሚለው ነው፡፡ እንዲሁም አዋጁ አስፈላጊ የመሆኑን ያህል በኅብረተሰቡ ውስጥ በቂ ግንዛቤ ሳይፈጠር፣ በችኮላ ሕጉን ማፅደቅ ለምን አስፈለገ የሚለው ይገኝበታል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ዘለቀ መሐሪ የጦር መሣሪያ በአርሶ አደሩም ሆነ በአርብቶ አደሩ ያለው ማኅበራዊ መስተጋብር በአግባቡ ልናየው ይገባል ካሉ በኋላ፣ በአንድ ቤተሰብ ከአንድ መሣሪያ በላይ ሊኖር አይገባም የሚለው ድንጋጌ በአሁኑ ጊዜ አርሶ አደሩ በራሱ ፈቃድ ወደ ሕገ አስከባሪው በመምጣት መሣሪያውን እንዳያስመዘግብ ሊደርገው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ መሣሪያ አሁን እንደ ንብረት ተደርጎ ስለሚቆጠር ኅብረተሰቡን በቀላሉ ማሳመን አስቸጋሪ እንደሚሆን አክለዋል፡፡

‹‹በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ መሣሪያ ቢኖር በአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር መሣሪያህን አምጣ አታምጣ በሚል ክርክር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ በአንፃሩም ደግሞ ለሙስና በር እንዳይከፍት በሩን ልንደፍን ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ዘለቀ በድንጋጌው ላይ ተጨማሪ ዝርዝር ሕግ እንዲካተት አሳስበዋል፡፡

ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ተወክለው የተገኙ አንድ ተወያይም ኅብረተሰቡን እስከ ታች ወርዶ ማወያየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ሕጉ መንግሥት መሣሪያን ሊወርስ ነው የሚል ውዥንብር እንዳይፈጥር አሳስበዋል፡፡ ይኼንኑ የእሳቸውን ሐሳብ የሚደግፉ የቋሚ ኮሚቴው አባል ወ/ሮ ደግሞ፣ ‹‹ኅብረተሰቡ የግድ ሊደግፈው ይገባል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹ለአብነትም ከዚህ በፊት አንድ ግለሰብ ክላሽኒክቮ ጠመንጃና ሽጉጥ ገዝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር በረቂቅ አዋጁ ከአንድ መሣሪያ በላይ መያዝ ከተከለከተለ፣ ግለሰቦች መሣሪያቻው ሊወረስ ነው ብለው ማሰባቸው አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባሏ በረቂቅ አዋጁ የጦር መሣሪያ ተብለው ትርጉም የተሰጣቸውና ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመሣሪያ ዓይነቶችን በተመለከተ ሊካተት ይገባል በማለት ባህላዊ የጦር መሣሪያዎችን አስታውሰዋል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዘመናዊ መሣሪያ በላይ በቀስት በርካቶች እየተገደሉ በመሆናቸው ቀስት በአዋጁ ውስጥ ሊካተት ይገባዋል ብለዋል፡፡ አዋጁ ከዘመናዊ መሣሪያዎች ባሻገር ሌሎች ጉዳት የማያደርሱ የተባሉ ሥለት ነገሮችን ይዘረዝራል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ስለታማ ሴንጢዎች፣ ገጀራዎችና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ከአንድ በላይ መሣሪያ የያዘን ሰው ከመቀማት ይልቅ በሌላ የቤተሰብ አባል ስም ተመዝግቦ ፈቃድ እንዲያገኝ የሚያስችል ድንጋጌ ለምን ማስገባት አይቻልም የሚል ጥያቄም በተወያዮች ቀርቧል፡፡ በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ወንጀል እንዳይበራከት፣ የሕገወጥ መሣሪያ ዝውውርን እንዲያዳክምና በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ መሣሪያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ እንደሚጠቅም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የመሣሪያ ግዥና ሽያጭ በመበራከቱ የገበያ ዋጋው ማሻቀቡን ያወሱት ተወያዮቹ፣ ሕጉ የአርሶ አደሩን ሕይወት ሊታደግ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የአንድ ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ዋጋ ከ100 ሺሕ እስከ 120 ሺሕ ብር መድረሱን እንደሰሙ በመግለጽ፣ ‹‹አርሶ አደሩ በሬውን ሸጦ ድህነትን እየገዛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለሕገወጦች ትልቅ የገንዘብ ማደለቢያ መንገድ እየሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ለአብነትም በባህር ዳር ከ400 በላይ ሽጉጦችን በቤቱ አከማችቶ ስለተገኘው የፖሊስ ኮማንደር አንስተው፣ አንዱን ሽጉጥ በአሥር ሺሕ ብር ቢሸጥ እንኳ ፖሊሱ በአንዴ ሚሊየነር ሊሆን ይችል እንደነበር አቶ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባም በቅርቡ ብቻ በተካሄደ አሰሳ ከአሥር ሺሕ በላይ ሸጉጦችና ከሦስት ሺሕ በላይ የተለያዩ የክላሽኒኮቭ መሣሪያዎች መያዛቸውን አውስተው፣ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ሕጉ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

ነገር ግን ረቂቅ አዋጁ የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸው ግለሰቦች ሊያሟሉ የሚገባቸውን ዝርዝር መሥፈርት ሲዘረዝር፣ የዕድሜ መነሻንና አካላዊ ሁኔታን አለማስቀመጡ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ የጦር መሣሪያ ፈቃድ ለማግኘት መቀመጫውን በተመለከተ በደንብና መመርያ ይወሰናል የሚለውን ተወያዮች ተችተዋል፡፡ ‹‹ለቢራ 21 ዓመት ዕድሜ እያስቀመጥን እንዴት የጦር መሣሪያ በዚህ ዓይነት አዋጅ ውስጥ ለማስገባት ይሳነናል?›› ሲሉ አቶ ዘለቀ ጠይቀዋል፡፡

የአዋጁ አላማ በአገሪቱ ያለውን የጦር መሣሪያ በጠቅላላ ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ ማስገባት በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ የታጠቃቸውን የጦር መሣሪያዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዚህ አዋጅ መሠረት ለተቆጣጣሪው ተቋም የማስመዝገብ ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ከተፈቀደላቸው ዓይነትና መጠን በላይ ሆነው የሚገኙ የጦር መሣሪያዎችን ተቆጣጣሪው ተቋም ወርሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ወይም እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡

ተቆጣጣሪው አካልን በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 2/1/ ትርጉም ክፍል ላይ የፌዴራል ፖሊስ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፣ ራሱን የቻለ ብሔራዊ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የሥራ ክፍል አደራጅቶ የጦር መሣሪያን በተመለከተ በኃላፊነት እንዲመራ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም ተቆጣጣሪው አካል ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል ድረሰ ያለውን የጦር መሣሪያ አያያዝ፣ አጠቃቀም፣ ሥርጭትና የማምረት ሒደት የመምራት ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፣ ተደራሽነትን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ይኼንን አገልግሎት በአካባቢው እንዲያገኝ ከማድረግ አንፃር አንድም አግባብ ነው ብሎ እስካመነው የአገሪቱ አደረጃጀት ደረስ በመውረድ ጽሐፈት ቤት በመክፈት አገልግሎቱን ሊሰጥ ይችላል፡፡

ካልሆነም አግባብ ነው ብሎ ላመነው አካል ውክልና በመስጠት አግልግሎቱን ሊሰጥ ይችላል፡፡ የመከላከያ ሠራዊትና ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎትን በተመለከተ፣ ሕጉ ተፈጻሚ እንዳይሆንባቸው ተደርጓል፡፡ ሁለቱ ተቋማት በዚህ ሕግ ይገዙ የሚባል ከሆነ የጦር መሣሪያን አስመልክቶ የሚያከናውኑት ተግባር ለሦስተኛ አካል ግልጽ እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ ይህ ደግሞ ተቋማቱ ካላቸው ሚስጥራዊነት ባህርይ ጋር አብሮ የሚሄድ አይሆንም፡፡ ስለዚህ አዋጂ በእነዚህ ሁለት ተቋማት ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ሆኖም አዋጁ እነዚህ ተቋማት የሚታጠቁትን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና የአጠቃቀሙንም ሁኔታ በራሳቸው እንደሚወስኑ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአዋጁ ከተቆጣጣሪው ተቋም ጋር በጋራ አስፈላጊ ሆነው በሚያገኟቸው ጉዳዮች ላይ ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡

የጦር መሣሪያ ፈቃድ ገደብ የተደረገባቸው ተቋማትም በአዋጁ ተመልክተዋል፡፡ እነዚህም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሃይማኖትና የእምነት ተቋም፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ማኅበርና የትምህርት ተቋም ናቸው፡፡ ሆኖም ተቋማቱን ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ አገልግሎት የጦር መሣሪያ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ማለት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ላሉ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ እንዲሰጣቸው ተቋማቱ መጠየቅ አይችሉም ማለት ነው እንጂ፣ ተቋማቱን ለመጠበቂያ የሚሆን የጦር መሣሪያ ይሰጣቸዋል፡፡

የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጥበት ሁኔታን በተመለከተ ለግለሰቦችና ለድርጅቶች የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ ዓይነት በሕጉ ላይ የተመለከተው ሲሆን፣ የሚሰጣቸውን የጥይት ብዛት ግን በቀጣይ ተቆጣጣሪው ተቋም በሚያወጣው መመርያ የሚወሰን መሆኑ ተመልክቷል፡፡ መሣሪያውን ለሌላ አካል በፈቃድ ለመስጠት አንዱ መሥፈርት፣ ፈቃድ የተጠየቀበት የጦር መሣሪያ ከዚህ ቀደም በሌላ ሰው ስም ፈቃድ ያልወጣበት መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የፀና ፈቃድ የወጣበት ቢሆንም እንኳን ባለ ፈቃዱ የጦር መሣሪያው ለአመልካቹ ቢሰጥ ፈቃደኛ መሆኑን የሚገልጽ ከሆነ መሣሪያው ለአመልካቹ እንደሚሰጥ ተመልክቷል፡፡ እዚህ ላይ ፈቃድ የወጣበት ቢሆንም፣ ፈቃድ ያወጣበት ግለሰብ ከፈቀደ የሚለው ከላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ እንደ ንብረት ስለሚቆጠር፣ በቤተሰቦች ውስጥ ያለ የጦር መሣሪያን ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ እንዲቻል የሕግ መሠረት ለማስያዝ በማሰብ ነው ተብሏል፡፡

የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚሰጥባቸው መሥፈርቶችን በተመለከተ የጦር መሣሪያ ለመያዝና በሕጋዊ መንገድ ለመገልገል ፈቃድ የሚሰጠው ግለሰብ ማሟላት ያለበትን መሥፈርት ሕጉ በዝርዝር አመልክቷል፡፡ ከእነዚህ መሥፈርቶች መካከል አንዱ በተቆጣጣሪው ተቋም በሚዘጋጅ ወጥነት ያለው መሥፈርት መሠረት የጦር መሣሪያ ለመያዝ በቂና አሳማኝ ምክንያት ያለው ስለመሆኑ የታመነበት ሲሆን ነው የሚል ሲሆን፣ ይህ ድንጋጌ ሁለት ነገሮችን ያመለክታል፡፡ አንዱ የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል የጦር መሣሪያ የሚሰጥባቸውን መሥፈርቶች እንደሚያዘጋጅ የሚያመለክት ሲሆን፣ ሁለተኛው የጦር መሣሪያ እንዲሰጠው የሚጠይቅ አካል የጦር መሣሪያውን የሚታጠቅበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለት ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ያሉ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ ግን የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚጠይቁ ሰዎች ምክንያታቸውን ማስረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለጠየቀ ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያ አይሰጥም ማለት ነው፡፡ የጦር መሣሪያ መታጠቅ የሁሉም ሰው መብት ሳይሆን፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ተቆጣጣሪውን ባለሥልጣን የሚያሳምን ነገር ሲቀርብና መሥፈርቶቹ ሲሟሉ የሚሰጥ ነው፡፡

በአዋጁ አንቀጽ ዘጠኝ ላይ በልማድ የታጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጦር መሣሪያ ፈቃድ አሰጣጠን በተመለከተ የተደነገገ ሲሆን፣ ከላይ በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ እንደተገለጸው የዚህ አዋጅ ዓላማ ከዚህ በፊት ታጥቀው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የጦር መሣሪያ ማስፈታት ሳይሆን፣ ለእነዚህ አካላት ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶ የጦር መሣሪያው የኅብረተሰቡ የጋራ የጦር መሣሪያ እንዲሆን ማደረግና ኅብረተሰቡ በጋራ ሰላምና ደህንነቱን እንዲጠብቅበት ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ራሳቸውን ለመጠበቅና ንብረታቸውን፣ በተለይም ለግጦሽና ውኃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ከብቶቻቸውን ከዘረፋና ከአውሬ ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ የመታጠቅ ልማድ አላቸው፡፡ ይህን በመገንዘብ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የታጠቁት የጦር መሣሪያ ያልተከለከለ ዓይነት እስከሆነ ድረስ በአንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ ውስጥ ተቆጣጣሪው ተቋም በአካባቢያቸው ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ በአካል ቀርበው ፈቃድ መጠየቅና ሕጋዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አዋጁ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈቃድ ጠይቆ ለመውሰድ እንደሚችሉ ፈቃጅ ሆኖ ተቀርጿል፡፡ ሆኖም በጊዜ ገደቡ ውስጥ ፈቃድ ያልወጣበት የጦር መሣሪያ ለተቆጣጣሪው ተቋም ገቢ መደረግ አለበት፣ በቁጥጥር በተገኘም ጊዜ ይወረሳል፡፡ በሌላ በኩል ከሽግግር ጊዜው በኋላ በሒደት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖር ሰው የጦር መሣሪያ ፈቃድ ሲጠይቅ፣ እንደ ማንኛውም የጦር መሣሪያ ፈቃድ ጠያቂ ይስተናገዳል ማለት ነው፡፡ 

የክልሎች ሥጋትና ጥያቄ

በውይይቱ መድረክ ላይ ከሶማሌና ከሐረሪ ክልሎች በስተቀር ሌሎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች ተገኝተው ነበር፡፡ በረቂቅ አዋጁ ከጦር መሣሪያ አያያዝ ጋር በተገናኘ የራሳቸውን ሐሳብ እንዲያቀርቡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዕድል ሰጥተዋቸው ነበር፡፡

አብዛኞቹ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች የሕጉን አስፈላጊነት ቢደግፉትም፣ በሕጉ አጠቃላይ አተገባበርና ከየክሎቻቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጋሯቸው ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ያህል የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሕጉ ለአገሪቱም ሆነ ለክልላቸው የጦር መሣሪያን በመቆጣጠርና በማስተዳደር ያለው ጠቀሜታ ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በግለሰብ የጦር መሣሪያ ፈቃድ አሰጣጥና አመዘጋገብ ላይ የክልላቸው አርብቶ አደርን ባህሪ ጠቅሰው ሥጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በእኛ አካባቢ መሣሪያ ሀብት ነው፡፡ ወንድ ልጅ ሲወለድ ግመል ተሸጦ መሣሪያ ተገዝቶ ይቀመጥለታል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አሁን በክልሉ ያለውን የመሣሪያ ቁጥጥርና ምዝገባ በተመለከተ ሲያስረዱ አንድ ግለሰብ ክላሽና ሽጉጥ ሊኖረው ይችላል፡፡ ፈቃድም ሲያወጣ ለሁለቱም ነው ያሉት የአፋር ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ‹‹ከዚህ በኋላ በዚህ ሕግ መሠረት አንዱን ተመዝግበህ ፈቃድ ውሰድ ሌላውን መሣሪያ ይወረሳል ብንለው ወደኋላ በመሄድ መሣሪያውን ለመግዛት ማሰቡንና ስለመሸጡ ስለሚያስብ ይህ ጉዳይ ቀላል ላይሆን ይችላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደ ሚካኤልም እንዲሁ የክልላቸውን ነባራዊ ሁኔታ በሦስት ከፍለው ገልጸዋል፡፡

‹‹የእኛን አካባቢ በሦስት ከፍዬ እገልጻለሁ፡፡ ክልላችን ከኬንያና ከደቡብ ሱዳን ይዋሰናል፡፡ ድንበሩን የሚጠብቀው ደግሞ አርብቶ አደሩ ነው፡፡ መንግሥት ድንበር እንዲያስጠብቅ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ሰሚ አላገኘንም፡፡ ስለዚህ እነዚህን አርብቶ አደሮች በቀላል መሣሪያ ጠብቁ ብንል አስቸጋሪ ነው፤›› በማለት፣ በረቂቅ ሕጉ ለግለሰቦች የሚከለከለውን የመሣሪያ ዓይነት በተመለከተ ድጋሚ ሊታይ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በተደጋጋሚ ከአርሶ አደሮቹም ሆነ ከአርብቶ አደሮች መሣሪያን ለመውሰድ ሳይሆን ባለበት ይዞታ ለማስተዳዳር ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ነገር ግን የፖሊስ ኮሚሽነሮችም ሆኑ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ለሚቀጥለው ሳምንት ለመገናኘት ሐሳብ ቀርቦ፣ ተወያዮችም በዚሁ ተስማምተው በረቂቅ አዋጁ ላይ ለመወያየት በቀጠሮ ተለያይተዋል፡፡

በተለይ ፌዴራል ፖሊስ በቀላሉ ለመቆጣጠር በማይችልባቸው ሥፍራዎች ሥርዓተ አልበኞች እንዳይነግሱ ለማድረግ፣ የክልል ፖሊስ ሚና በአግባቡ በሕጉ ቢካተት ይሻላል ሲሉም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ፖሊስ ኮሚሽነሮችም እንዲሁ ከጎረቤት አገሮች ከደቡብ ሱዳንና ከሱዳን የሚገቡ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን በተመለከተ ያሉባቸውን ችግሮች ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽነር ጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን በአራት ቦታ የመሸጋገሪያ በሮች እንዳሉ፣ ሁለቱ ሲጠበቁ ሁለቱ ግን አይጠበቁም ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተጠበቀ ድንበር መሣሪያ ሲገባ መነሻውን ጋምቤላ ያደረገ ሕገወጥ መሣሪያ ተያዘ ተብሎ ዜና ሲሠራብን ያመናል፤›› ሲሉ ከድንበር የመጣውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ረቂቅ አዋጁ ቀላል መሣሪያን ብቻ ለግለሰቦች መፈቀዱ በአብዛኞቹ የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተቀባይነት ላይኖረው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ በተደጋጋሚ ሕጉ መሣሪያ ከአርሶ አደሮችም ሆነ ከአርብቶ አደሮች ለመውረስ ሳይሆን፣ ባለበት ይዞታ ለማስተዳደር ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...