Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎት የነበረው የአሀዱ ኤፍኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ በዋስ ተለቀቀ

ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎት የነበረው የአሀዱ ኤፍኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ በዋስ ተለቀቀ

ቀን:

ከአምስት ወራት በፊት ሠርቶ ባስተላለፈው የምርመራ ዘገባ ምክንያት ከግንቦት 16 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በፖሊስ ታስሮ የነበረው የአሀዱ ኤፍኤም 94.3 ሬዲዮ ጋዜጠኛ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ከፖሊስ ጣቢያ በቀበሌ መታወቂያ ዋስ ተለቀቀ፡፡

ጋዜጠኛው ታምራት አበራ ለሦስት ቀናት ታስሮ የቆየው በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንደፋ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ነው፡፡

የሬዲዮ ጣቢያው አድራሻ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከመሆኑና የንግድ ፈቃዱና አገልግሎቱ የሚሠራቸው የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዴት ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ ሊታሰር እንደቻለ ጋዜጠኛውን ሪፖርተር አነጋግሮ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ታምራት እንዳብራራው፣ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ምሽት ላይ ስቱዲዮ ገብቶ ዜና እያነበበ ነበር፡፡ የተቋሙን የጥበቃ ሠራተኞች በማስፈራራት አልፈው ወደ ውስጥ የዘለቁ ታጣቂ ፖሊሶች፣ ‹‹የምታስመልጡ ከሆነ እንመታዋለን፤›› እያሉ ዜና የሚያነብበት ስቱዲዮ ድረስ ዘልቀው መግባታቸውን ተናግሯል፡፡ ‹‹በተገኘበት ቦታ ተይዞ ይቅረብ፤›› የሚል መቀመጫው ወይም ዋና ማስቻያ ቦታው ሰንዳፋ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው በኦሮሚያ ልዩ ዞን በርህ ወረዳ ፍርድ ቤት የተጻፈ መያዣ ደብዳቤ መያዛቸውን እንዳሳዩት ታምራት ተናግሯል፡፡ የጣቢያው ሠራተኛ በወቅቱ ግራ ስለተጋባ፣ ‹‹እሱ መያዝ የለበትም፡፡ ተጠያቂ መሆን ካለበትም ዋና አዘጋጁ ነው፡፡ እሱ ደግሞ ለሥራ ወደ ሌላ ቦታ ስለሄደ እስከሚመጣ ታገሱን፤›› በማለት ቢለምናቸውም፣ ኃይል በመጠቀም በማስፈራራት ይዘው ለመሄድ ሲሞክሩ ግርግር በመፈጠሩ በቅርብ ወደሚገኘው ሲኤምሲ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ይዘውት እንደሄዱም አክሏል፡፡ ጣቢያው እንደ ደረሱ የጣቢያው ፖሊሶች ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው ከመግለጽ ባለፈ እንዳመነጫጨቁትና የማይገባ ምላሽ እንደሰጡት የገለጸው ታምራት፣ የመውሰድ ሥልጣን የላችሁም ብለው ሊከላከሉለት ሲገባ ከክልል የመጡትን ፖሊሶች ማገዝ በመምረጣቸው እሱም ለመሄድ መቁረጡን አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ይዘውት በመጡት የቤት መኪና ሰሌዳ ባለው መኪና ውስጥ እንዲገባ ሲነገረው ተከትለውት ጣቢያ ድረስ የሄዱት የሥራ ባልደረቦቹ፣ ‹‹መሄድም ካለበት በፖሊስ መኪና እንጂ በግለሰብ መኪና የት እንደምትወስዱት አይታወቅም፤›› በማለት በመቃወማቸው፣ ከብዙ ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ ተደርሶ ሊሄድ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የጣቢያው ዋና አዘጋጅ አቶ ጥበቡ በለጠን ጨምሮ ሌሎች በምርመራ ዘገባው ውስጥ ተካተው የነበሩ ግለሰቦች ጭምር አብረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው የገለጸው ጋዜጠኛው፣ በዕለቱ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ላይ እሱ ብቻ ሰንዳፋ ፖሊስ ጣቢያ መድረሱን ገልጿል፡፡ እንደ ደረሰ ዕለታዊ ቃል ተቃባይ አጭር ቃለ መጠይቅ ካደረገለት በኋላ፣ ቀበቶና የጫማ ክሩን ፈትቶ ከእስረኞች ጋር መቀላቀሉን አክሏል፡፡

በጣቢያው ውስጥ ከአራት ወራት በላይ ፍርድ ሳያገኙ ታስረው የሚገኙ በርካታ እስረኞች መኖራቸውን የጠቆመው ጋዜጠኛው፣ አራት በአራት በሆነች ጠባብ ቦታ ላይ ተፋፍገው ከመታሰራቸውም በተጨማሪ፣ እስከ ሦስት ቀናት ውኃ ሳያገኙ እንደሚከርሙ፣ አንዳንዶቹ ጠያቂ የሌላቸውና ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን በቆየባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ መገንዘቡን ገልጿል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ሰንዳፋ ከተወሰደና ካደረ በኋላ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቃሉን እንዲሰጥ ፖሊስ ሲጠይቀው፣ ‹‹ያለ ጠበቃዬ ቃሌን አልሰጥም፤›› ብሎም እንደነበር ተናግሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በማያውቀው ቋንቋ ቃሉን መስጠት ካለበት ትክክለኛ አስተርጓሚ መኖር እንዳለበት፣ ቃሉን ሰጥቶ ሲጨርስ በትክክለኛ መመዝገቡን የሚተረጉምለት ታማኝ ሰው ወይም የሕግ ባለሙያ መኖር ስላለበት መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም እሱ የሚያምነውን የራሱን ሰው ማቅረብ እንደሚችል ተፈቅዶለት ቃሉን እንደሰጠም አክሏል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር በዋለና በታሰረ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ሲደነግግ፣ የተያዘበት ቦታ ለሚታሰርበት ጣቢያ ርቀት ካለው ግምት ውስጥ የሚያስገባ ቢሆንም እሱ ከተያዘበት 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ ከተማ በተያዘ በዕለቱ መድረሱ እየታወቀ፣ ለሦስት ቀናት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ መቅረቱን አስረድቷል፡፡ ይኼ ደግሞ ሕገ መንግሥቱንና ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕጓ አካል ካደረገቻቸው ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች አንፃር የሰብዓዊ መብትና የሕግ ጥሰት እንደተፈጸመ ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ለአንድ ዓመት አንድም ጋዜጠኛ ባለመታሰሩ፣ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነትን አመቺ በማድረግ ከነበርችበት ደረጃ በ40 ደረጃ ማሻሻሏ ከተገለጸ አንድ ወር ሳይሞላ እሱንና ሌሎች ጋዜጠኞች ላይ እስርና መንገላታት መጀመሩ አሳዛኝ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ጋዜጠኛ በሠራው ዘገባ መታሰር እንደሌለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ እየተናገሩ ባለበት ወቅት፣ ያለ ምንም ጥፋት ሕግን ተላልፎ ወራት ባለፉት ዘገባ መታሰሩ ሐሳብን በነፃነት የመናገርና የመግለጽ አፈና መሆኑንም አክሏል፡፡ ታምራት ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡት ጥያቄ እያቀረበ ሳለ፣ ‹‹ወደፊት ተጠርተህ መምጣትህ አይቀርም፤›› በማለት በመታወቂያ ዋስ መለቀቁን አስረድቷል፡፡

ለእስር ያበቃው የምርመራ ዘገባ ምን እንደሆነና መቼ እንደተላለፈ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ ጋዜጠኛው እንዳብራራው፣ ጉዳዩ አሥር ዓመት ሆኖታል፡፡ ወ/ሮ ደብሪቱ ፋና አቦ የሚባሉ ሴት ከጣፎ አለፍ ብሎ 44 ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ በውርስ ያገኙት ይዞታን ይመለከታል፡፡ ሴትየዋ ከ63 ዓመታት በፊት የአውራሻቸው የጉዲፈቻ ልጅ ናቸው፡፡ አውራሻቸው አያታቸው ሲሆኑ ንብረታቸውን ሲያውርሷቸው፣ ወራሽ ለመሆናቸው ማረጋገጫ በጋዜጣ ማሳተማቸውንና የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም እንደተሰጣቸው ገልጿል፡፡

ሴትየዋም ንብረታቸውን እያስተዳደሩ እያሉ በ2001 ዓ.ም. የወንድማቸው ልጆች ንብረቱ የእነሱ እንደሆነ በመግለጽ እንዲያስረክቧቸው፣ ታምራት በተጠራበት ፍርድ ቤት ክስ መመሥረታቸውን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱም ማስረጃዎቹን ያይና ሰነዶች በሙሉ የሚያረጋግጡት ይዞታው የሴትየዋ መሆኑን ስለሆነ እነሱን እንደማይመለከት ገልጾ መዝገቡን እንደዘጋው አስረድተዋል፡፡ እነዚያው ከሳሾች ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ በ2010 ዓ.ም. ስማቸውን በመቀየርና ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት በተመሳሳይ ንብረት፣ ተመሳሳይ ክስ፣ በተመሳሳይ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸውን ታምራት ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱ ሲቀርብለት ቀደም ብሎ መቅረቡንና መዘጋቱን፣ እንዲሁም በአንድ ጉዳይ ተመሳሳይ ክስ ሁለት ጊዜ መቅረብ እንደማይችል (ሬስጁዲካታ) ገልጾ፣ መዝገቡን እንደመዝጋት ተሰይሞ ጉዳዩን በማየት ለከሳሾች እንደፈረደላቸው ጠቁሟል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግራ ያጋባቸው ወራሾች ጉዳዩን ወደ አሀዱ ኤፍኤም 94.3 ሬዲያ ጣቢያ ሲያመጡ የምርመራ ሥራውን መጀመሩን የገለጸው ታምራት፣ ውሳኔ ያስተላለፉትን የፍርድ ቤቱን ፕሬዚዳንት፣ ሌሎች ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አካላትና ጠበቆች በማነጋገር ከሁለት ወራት የምርመራ ሥራ በኋላ ከአምስት ወራት በፊት ዘገባውን እንዳስተላለፈው አስረድቷል፡፡ የፍርድ ቤቱን ፕሬዚዳንት ቃለ መጠይቅ ባደረገባቸው ወቅት እንዳያስተላልፍ እንዳስጠነቀቁትና እንዳስፈራሩት፣ እንዲሁም በአጭር የስልክ መልዕክት ስድብ አዘል ማስጠንቀቂያ ልከውለት እንደ ነበር ገልጿል፡፡ በዛቱት መሠረትም ሕግን ተከትለው (Rule of Law) መጠየቅ ያለባቸውን ነገር መጠየቅ እየቻሉ፣ ‹‹ኅብረተሰቡ በእኛ ላይ አመኔታ እንዲያጣ አድርገሃል፤›› በማለት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው እንዲታሰር ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...