Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ባለሙያዎች በደመወዝና በጥቅማ ጥቅም ችግሮች ከዘርፉ መውጣት እንደሚፈልጉ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ባዶ ቋት በሆነችበት ጊዜ ሠራተኛው የደመወዝ ጥያቄ ማንሳቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቹ

ግብርና ሚኒስቴር ከ70 በመቶ በላይ ባለሙያዎች ከዘርፉ መውጣት እንደሚፈልጉ አጠናሁ ብሏል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበትና ከ1,500 በላይ የግብርናው አመራሮች በተሳተፉበት የሁለት ቀናት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ስብሰባ ላይ፣ አብዛኞቹ የዘርፉ ሠራተኞች በዝቅተኛ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም በትምህርት ዕድሎች ማጣት ከዘርፉ ለመውጣት እንደሚፈልጉ ተገለጸ፡፡

ከየክልሉ የመጡ የወረዳ፣ የቀበሌና የዞን አመራሮች የተገኙበት መድረክ ላይ በባለሙያዎች ተደጋጋሚ ከሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፣ የደመወዝና መሠረታዊ ጥቅማ ጥቅሞች ዕጦት ብሎም በግብርና መስክ ወደ ላይ ማደግና መለወጥ አስቸጋሪ እየሆነባቸው፣ ዘርፉን ወደ ሌላ የሙያ መስክ ለመሄድ በመጠባበቂያነት እንደሚያሳልፉበት በሁለቱ ቀናት ቆይታ ሲገለጽ ተደምጧል፡፡

ቅዳሜና እሑድ ግንቦት 17 እና 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ‹‹ለግብርና ትራንስፎርሜሽን የአመራሩ ሚና›› በተሰኘው ስብሰባ ወቅት፣ ለከፍተኛ ባለሥልጣናቱ  ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የባለሙያዎች የኑሮ ሁኔታና የደመወዝ ጉዳይ በሰፊው ሲደመጥ ነበር፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን የተካሄደውን የውይይት መድረክን የመሩት አቶ ደመቀ መኮንን ምላሽ ከሰጡባቸው ውስጥም፣ ታች ያለው የግብርናው መስክም ሆነ የፖለቲካው ሁኔታ ከባድ ሆኖብናል የሚለው ይገኝበታል፡፡ የአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊ ወጣት አበበ መኮንን፣ ‹‹ታች ያለው አገራዊ ፖለቲካውና የአርሶ አደሩ ችግሮች ከባድ ሆነዋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር የቆዘመውን ሙያተኛ መመልከት አለበት፣ አኩርፏል፡፡ የዞንና የወረዳ ኃላፊዎች ጥያቄያችንን አትመልሱንም እየተባልን ነው፤›› በማለት የግብርና ባለሙያው ድምፅ እንዲደመጥ ጠይቀዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ከሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ፣ ከጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ ከደቡብ ኦሞ ያንጋቶም ወረዳ ግብርናና ከሌሎችም አካባቢዎች ተነስተዋል፡፡ ባለሙያዎች በሥራ ገበታቸው ላይ ለመቆየት የሚያነሳሳና የሚያበረታታ ሥርዓት የለም ያሉት እነዚህ ኃላፊዎች፣ ከደወመዝና ከጥቅማ ጥቅም ክፍያዎች ማነስ ባሻገር፣ በየገጠሩ እየገቡ ከገበሬው ጋር እንደ ልብ ለመሥራትም የመጓጓዣ ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምርያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ ከጥያቄ አቅራቢዎቹ መካከል ናቸው፡፡ ‹‹የግብርና ባለሙያው በተለፋበት ልክ እየተጠቀመና እየጠቀመ አይደለም፡፡ መምህርና ሐኪም ጥያቄ እያነሱ ነው፡፡ እኛም በፉክክር አይደለም የምናነሳው፣ ነገር ግን ከባድ ችግር ስላለብን እንጂ፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ በመነሻ ደመወዝ 2,100 ብር የግብርና ባለሙያው እየተቀጠረ እንደሆነ፣ በየክልሉ ያለው የተለያየ አሠራርና የጥቅማ ጥቅም አከፋፈል ልዩነትም አገሪቱ የምትከተላቸው አሠራሮች ጉራማይሌነት እንዳስቸገራቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኮምጫጫ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ባዶ ቋት ሆና ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል የማትችለበት ደረጃ ደርሳ እንደነበር ተናግረው፣ ‹‹አምና ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ አኳያ በአደገኛ አዘቅት ውስጥ ልትወድቅ ደርሳ ነበር፡፡ የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች መጨረስ ሳንችል፣ የተበደርናቸውን ብድሮች መክፈልና የሠራተኞቻችንን ደመወዝ መክፈል የማንችልበት ወቅት ነበር፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ በተከናወኑ ሥራዎች የበጀት ጉድለት በአራት በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያውም በየትኛውም ዓመት ተገኝቶ የማያውቅ መጠን መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ገና በማገገም ላይ እንዳለች ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በየዘርፉ ጥያቄ የሚያነሱት ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው ወይ?›› እንደሚያሰኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ባዶ ቋት ያላት አገር እንደሆነች እያወቀ የሚጠይቀው ኬንያዊ ነው? ኤርትራዊ ነው? ወይስ ማን ነው? የሚለው ግራ ይገባኛል፤›› በማለት፣ ‹‹ኢትዮጵያን አምጪ ከማለት ይልቅ እንኪ፤›› የምትባልበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

 ለኢትዮጵያ መለወጥና ላሉባት ችግሮች መፈታት ዳያስፖራው በቀን አንድ ዶላር እንዲያዋጣ ተጠይቆ የሰጠው ምላሽ አጠያያቂ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዳያስፖራ አባላት እስካሁን ያዋጡት አራት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለአዲስ አበባ ፅዳትና ውበት አቅሙ ያላቸው እንዲሳተፉ ተጠይቀውም፣ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ በርካታ ቻይናውያን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለጽ፣ ችሎታውና አቅሙ ያለው ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የመስጠት ፍላጎት ማጣቱ እንዳሳዘናቸው የሚጠቁም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ትክክለኛ መሆናቸው በመጥቀስ፣ በሚኒስቴሩ በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም ከ70 በመቶ በላይ የግብርና ልማት ጣቢያ ሠራተኞች ዕድል ቢያገኙ ሥራቸውን መልቀቅ እንደሚፈልጉ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ 80 ቀናት የፈጀ ጥናት ተካሂዶ በታችኛው ዕርከን አመራሮች ከተጠቀሱት ችግሮች የገዘፉ ጉዳዮች መኖራቸው እንደተረጋገጠ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በባለሙያው ዘንድ ያለውን ችግር አንደብቅም፡፡ በጥናት መውጣት ስላለባቸውና እያንዳንዱ ችግር በቅደም ተከተል መፍትሔ ይሰጠዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከአራት በመቶ በታች የደን ሽፋን በሚታይባት ኢትዮጵያ ውስጥ አስደንጋጭ የበረሃማነት ችግሮች እንደሚታዩ ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ በክረምቱ ወራት በተለይም ከሰኔ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ የታቀደው፣ ‹‹40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ›› የተሰኘውና የአራት ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች ተከላ የሚካሄበት ዘመቻ አንዱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም የድርጊት መርሐ ግብር ለሆነው ለዚህ ሥራ ከሕዝብ ጉልበት 45 በመቶ ታሳቢ ተደርጎ እስከ 60 በመቶ ከሕዝብ በሚዋጣ ገንዘብ፣ ቀሪውን መንግሥትና የልማት አጋሮች በሚሸፍኑት የ11.08 ቢሊዮን ብር በጀት በሦስት ወራት ውስጥ እንደሚካሄድ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች