Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኃይል ዕጦት ያነጣቸው ወራት   

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለወትሮው ሄድ መጣ ሲል የከረመው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሰሞኑ ለይቶለት በፈረቃ ወደሚታደልበት አዙሪነት ዳግመኛ ገብቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የኃይል አቅርቦት ከሚቋረጥባቸው ተገልጋዮች መካከል አማራጭ የኃይል ምንጮችን በአብዛኛው ሲጠቀሙ፣ በአብዛኛው በነዳጅ የሚሠሩ ጄነሬተሮችን ሲያንደቀድቁ የሚታዩት የንግድ ተቋማት ነበሩ፡፡

ከፀጉር ቤት ጀምሮ እስከ ትልልቆቹ ሕንፃዎች እንደ አቅማቸው የሚያንጧጧቸው ጄነሬተሮች ወደ መኖሪያ መንደሮችም መዛመት ጀምረዋል፡፡ ውድ ቪላ ቤቶች ብቻም አይደሉም በየመኖሪያ ሠፈሩ ጄነሬቶችን ሲጠቀሙ የሚታዩት፡፡ ኮንዶሚኒየም መንደሮችም የእነዚህ አማራጭ የኃይል ምንጮች ተጠቃሚነት ተርታውን በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ፡፡

እንዲህ ያለውን አስገዳጅ ችግር ያመጣው፣ በአገሪቱ ያሉት ኃይል ማመንጫ ግድቦች የውኃ ዕጥረት ስላጋጠማቸውና በዚህ ሳቢያም የኤሌክትሪክ ኃይል ዕጥረት በመከሰቱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሦስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የውኃ ዕጥረት አጋጥሟቸዋል በማለት ባለፈው ሳምንት መግለጫ የሰጡት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የበልግ ዝናብ በመዘግየቱና የግልገል ጊቤ ሦስት፣ የመልካ ዋከና እንዲሁም የቆቃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ያከማቹት የውኃ መጠን ከዚህ በፊት ከነበረው በመቀነሱ የኃይል ዕጥረት አጋጥሟል፡፡

በአገሪቱ ካሉት 21 ያህል የኃይል ማመንጫ ጣቢዎች እንደሚመነጭ የሚጠበቀው የኃይል መጠን በነዳጅ የሚሠሩ የመጠባበቂያ ኃይል ማመንጫዎች ጭምር ከ4,240 ሜጋ ዋት አይበልጥም፡፡ ከዚህ አቅም ውስጥ እስካሁን ሲመነጭ የቆየው ከ2,500 ሜጋ ዋት ብዙም እልፍ አላለም፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት፣ በውኃ መቀነስ ሳቢያ በተከሰተው የኃይል ዕጥረት ሳቢያ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው ኃይል ከ1,400 ሜጋ ዋት እንደሆነ ይፋ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ሆነ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል እየተሠራጩ የሚገኙ መረጃዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ ‹‹ካለው ነባራዊ ሁኔታ ሳቢያ ከሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 1,400 ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት አይቻልም፡፡ ይህ የኃይል መጠን ከአገሪቱ ፍላጎት አኳያ ሊሸፍንና ሊያስተናግድ የሚችለው 60 በመቶው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኛ ብቻ ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያወጣው መረጃ ለዚህ አስረጅ ነው፡፡

 ግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ከ46 በመቶ በላይ የአገሪቱን የኃይል ምርት ቢሸፍንም፣ ካለፈው ዓመት አኳያ ከ16 ሜትር በላይ የውኃ ክምችቱ በመቀነሱ፣ በአሁኑ ወቅት ከ426 ሜጋ ዋት ኃይል ያላነሰ ኃይል ዕጥረት አጋጥሞታል፡፡ የሌሎቹ ተደማምሮም በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ400 እስከ 1,000 ሜጋ ዋት ኃይል ዕጥረት ማጋጠሙን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡ 

ይህ በመሆኑም በፈረቃ ኃይል ማቅረብ እንደተጀመረና ፈረቃውም ቢያንስ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ እንደሚዘልቅ ይፋ ተደርጓል፡፡ ስለዚህም ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች መካከል ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በየ15 ቀኑ እንዲጠቀሙ ታዘዋል፡፡ ገሚሶቹ ለ15 ቀን ይሠሩና ገሚሶቹ በፈረቃ ይስተናገዳሉ፡፡ የድንጋይ መፍጫ የሚጠቀሙ ወፍጮ ቤቶች የፈረቃ መርኃ ግብሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ ኃይል ከመጠቀም እንዲታቀቡ ታዘዋል፡፡ ሌሎች እንደ ብረታ ብረት ማምረቻዎች ያሉትም አንድ ቀን እያረፉ እንዲሠሩ ተወስኖባቸዋል፡፡ ዕርግጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን የሚያመርቱ፣ ሆስፒታሎች፣ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎትና መሰል ተቋማት ፈረቃው የማይመለከታቸውና ኃይል የማይቋረጥባቸው ስለመሆናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

ዕውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዕጥረቱ የተከሰተው በውኃ ዕጥረት ነው ወይስ በመንግሥት አስቀድሞ የማቀድ ችግር ሳቢያ? የሚል ሙግትም እየተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ናቸው፡፡ አቶ ሞገስ የሚያቀርቡት መከራከሪያ አስቀድሞ የነበረው ትንበያ በመጋቢትና ሚያዝያ ወራት የበልግ ዝናብ እንደማይቋረጥ የሚያመላክት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዝናቡ በመዘግየቱ በተለይ በምሥራቃዊና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በተተከሉት ኃይል ማመንጫዎች ላይ ዕጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ ሌሎቹ የኃይል ማመንጫዎች እንደ ወትሯቸው እያመነጩ ቢሆንም፣ ጊቤ ሦስት መልካዋከናና ቆቃ ግድቦች የውኃ ዕጥረት አጋጥሟቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግርና መቆራረጥ ደቡብ አፍሪካም እያጋጥሟት ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል በኃይል አቅርቦቱ ላይ ጥቂት ተመሳሳይነት ይታያል፡፡ የሁለቱም አገሮች የኃይል አቅርቦትና ሥርጭት የሚተዳደረው በመንግሥት ተቋማት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና በጅምላ ሽያጭ ዘርፉን ይመራል፡፡ ኤስኮም የተባለው የደቡብ አፍሪካ መንግሥታዊ ድርጅትም ተመሳሳዩን ኃላፊነት ይዟል፡፡ ሁለቱም በቂ ኃይል ማቅረብ ባለመቻላቸው የፈረቃ ሥርጭት እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡

እርግጥ በኢትዮጵያ ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥና የፈረቃው ሥርጭት ከደቡብ አፍሪካ አኳያ ሲታይ መጠኑ ከፍተኛ ሆኖ ቢገኝም፣ በሁለቱ አገሮች ውስጥ የተከሰተው የኃይል ዕጥረት ግን የትዬ ለሌ ልዩነት አለው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ያጋጠማት ዕጥረት ከ4,000 ሜጋ ዋት በላይ ሲሆን፣ ይህ መጠን ኢትዮጵያ ያሏት ማመንጫ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ኃይል ቢያመርቱ ሊያስገኙ የሚችሉት መጠን ነው፡፡ በአንፃሩ ኤስኮም ከ34 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል በላይ ያመነጫል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ90 በመቶው በላይ በሙቀት አማካይነት ከሚመነጩ ወይም ከተርማል ኢነርጂ የሚመጭ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚመነጨው ከውኃ ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካውያኑ ‹‹ሎድሼድ›› በሚል ስያሜ የሚጠሩት የፈረቃ ሥርጭት ምንጩ ከሞዛምቢክ ይቀርብላቸው የነበረው 1,000 ሜጋ ዋት ኃይል በአውሎነፋስ አደጋ በመመታቷ መቋረጡ፣ ከ3,000 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የሚያመነጩ በርካታ ጣቢያዎችም በእርጅናና በዕድሳት ዕጦት ሳቢያ ከነጭራሹ ለውድመት እንዳይዳረጉ ለመከላከል ሲባል በተወሰደ ዕርምጃ ወደ ፈረቃ ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በበልግ ዝናብ መዘግየት ሳቢያ ወደ ፈረቃ ገብታለች፡፡

እንዲህ ያለው ችግር መከሰቱ ከተራው ነዋሪ ባሻገር፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ላይ ያሳደረው ጫና ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› እንደሚያሰኘው እየተገለጸ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሠረታዊ የብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ሲፈራረቁባቸው የቆዩትን ችግሮች ሲያስታምሙና ሲያገግሙ የቆዩት ፋብሪካዎች አሁን በተፈጠረው የኃይል አቅርቦት ዕጥረት ሳቢያ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጦት፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር፣ ለውጭ ኩባንያዎች የሚሰጠው ማበረታቻና ሌላውም ድጋፍ ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ባለመሰጠቱ እየተባባሰ የመጣው የፋብሪካዎች ፈርጀ ብዙ ችግርና የህልውና አጣብቂኝ፣ የኃይል እጦት ሲታከልበት በርካቶችን ከሥራ ሊያስወጣቸው የሚችልበት ሥጋት መደቀኑን አቶ ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡

የኃይል ዕጥረቱ ከመምጣቱም ቀደም ብሎ በርካታ አገር በቀል ባለሀብቶች ፋብሪካዎቻቸውን ሸጠው ከዘርፉ የመውጣት አዝማሚያ እያነሱ እንደመጡ የጠቀሱት አቶ ሰሎሞን፣ ፋብሪካዎቹ የወጣላቸው የፈረቃ ሥርጭትም ቢሆን ይብሱኑ ያለ ሥራ እንዲሰነብቱ ያስገድዳቸዋል ብለዋል፡፡ ‹‹የወጣው ፕሮግራም ትልልቅ ማቅለጫና ማሞቂያ ካላቸው ፋሪካዎች አኳያ ምንም አያሠራቸውም፤›› በማለት በተለይ በዋቢነት የጠቀሷቸው የአርማታ ብረት አምራቾችን ነው፡፡ አብዛኞቹ ከሳምንትና ከሁለት ሳምንት በላይ ያልተቋረጠ ኃይል ማግኘት ይፈልጋሉ ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ የወጣው ድልድል ግን ለዚህ አመቺ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በርካቶቹ ፋብሪካዎች ሠራተኞችን ለመቀነስ የሚያስገደዳቸው ደረጃ ላይ የሚጥላቸው ደረጃ ላይ እንዳደረሳቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

እንደ አቶ ሰሎሞን ሁሉ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ የተከሰተው የኃይል ዕጥረትና የወጣው ፈረቃ አብዛኞቹን አምራቾች ያለ ሥራ እንዲሰነብቱ የሚስገድድ ከመሆን አልፎ ህልውናቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተው ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ሥጋት ከሆነም በውኃ ዕጥረት ሳቢያ የተከሰተው የኃይል ዕጥረት ግን ውኃውም ቢገኝ ላይቀረፍ የሚችልባቸው ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ የጥገናና የመለዋወጫ ዕጥረት የሚታይባቸው ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሰኔ 30 በኋላ ኃይል ዳግመኛ በፈረቃ ላለመጠቀሙ የሚሰጡት ማስተማመኛ የለም፡፡ ይህ በመሆኑም መንግሥት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈልግለት፣ በተለይ ፋብሪካዎችና በልዩ ልዩ የምርት ተግባራት ላይ ለተሠማሩ ድርጅቶች ማስተካከያ ማድረግ ስለሚችልበት አግባብ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገርና አቤት ለማለት ኮንፌዴሬሽኑ ዝግጅት መጀመሩንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

ይህን መሰሉን ጉዳይ በመንተራስ ኢኮኖሚያዊ ምልከታቸውን ለሪፖርተር ያጋሩት የኢኮኖሚ ባለሙያውና የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር ተቋም የምርምር ባልደረባ የሆኑት ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የኃይል ዕጥረት ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ ከሚያጋጥሟቸው ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ውስጥ አንደኛው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የዓለም ባንክንና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲን መረጃዎች አጣቅሰው እንደገለጹትም፣ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በመከተል የኃይል መቆራረጥና መጥፋት ሁለተኛውን ከፍተኛ ደረጃ ይዟል፡፡

ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን የኃይል ዕጥረት ችግር በኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ደረጃ ለክቶ ለመግመገም የወጣውን ፈረቃና በፋብሪካዎች ላይ በምን መልኩ እንደሚተገበር በዝርዝር መታየት እንደሚያስያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሆኖ በማደግ ላይ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በኃይል እጦት ሳቢያ የሚደርስባቸው ጫና ከባድ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለምርት ሥራ የሚያስፈልጋቸውን የኃይል ምንጭ ለመትከል የሚያስችል አቅም ስለማይኖራቸው፣ አብዛኞቹ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጉዳታቸው እንደሚያይል አብራርተዋል፡፡ ይህም ሆኖ በነዳጅ የሚጠቀሙ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ስለሚፈጠር፣ የነዳጅ ወጪ ስለሚንር፣ የምርት ወጪን በማብዛትም የኃይል ዕጥረቱ ተወቃሽ ሆኗል፡፡ በዚህ ሳቢያ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ የሚያደርገው አስተዋጽኦም በቴዎድሮስ (ዶ/ር) ዕይታ ሚዛን የሚደፋ ጫና ነው፡፡

አቶ ሰሎሞንና ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ካቀረቧቸው አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል መንግሥት ተገቢውንና ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት ለቅድመ ዕቅድ የሚረዳ እገዛ ማድረግ አለበት የሚለው የኢኮኖሚ ባለሙያው ሐሳብ ነው፡፡ የኃይል አቅርቦቱ ስላሳያቸው ለውጦችና ወደፊት ፈረቃው በምን ወቅት ሊቃለለል እንደሚችልና ይህን የመሳሰሉ መሻሻሎች ሲኖሩም ያልተቋረጠና ዘላቂ መረጃ መስጠትም የመንግሥት የቤት ሥራ ነው፡፡

ይህ የአጭር ጊዜ ወይም በጊዜያዊነት ሊወሰድ የሚችል መፍትሔ ነው ያሉት ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፣ በመካከለኛውና በረጅም ጊዜ ሒደት ግን የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና ወደ ሥራ ለማስገባት መጣር ሲሆን፣ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች በኩልም እንዲህ ያሉትን ክስተቶችና ያስከተሏቸውን ጫና በመለካት ለወደፊቱ የኃይል መቋረጥ ሲኖርና ፈረቃ ሲታሰብ ትምህርት እንዲወሰድበት የሚያበቃ ጥናት ቀምሮና ለክቶ ማስቀመጥ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ መንግሥት እንዲህ ያለውን ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ጉዳትና ኪሳራውን ገምግሞ ለማወቅ የሚችልበትን ዕድል ለመስጠት የኢኮኖሚ ትንታኔዎች እንደሚያስፈልጉት አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች