የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በ2011 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት ውስጥ በነዳጅ ላይ ከተጣለው የመንገድ ፈንድ ታሪፍ ገቢና ከሌሎች ምንጮች ከ2.16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰቡን አስታወቀ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በ2011 ዓ.ም. በዘጠኝ ወራት ሪፖርቱ እንዳመላከተው፣ ዘንድሮ ከዕቅዱ በላይ ገቢ አሰባስቧል፡፡ ከዕቅድ በላይ ገቢ ካሰባሰበባቸው ዘርፎችም በቀዳሚነት የተቀመጠው በነዳጅ ላይ ከተጣለው የመንገድ ፈንድ ታሪፍ የተገኘው ተጨማሪ ገቢ ነው፡፡ ከነዳጅ ገቢ ባሻገር በዘይትና በሞተር ቅባት ላይ የተጣለው የመንገድ ፈንድ ታሪፍ፣ ከመንገድ ተገልጋይነት የሚገኝ ገቢ፣ ከግምጃ ቤት ሰነድ የሚገኝ ወለድና ክብደትን መሠረት ካደረገ የመንገድ ፈንድ ዓመታዊ ተሽከርካሪ ማደሻ ክፍያ በጠቅላላው ለማሰባሰብ ያቀደው የገቢ መጠን 1.97 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በመሆኑም የዕቅዱን 110 በመቶ ማከናወን መቻሉን ያሳያል ብሏል፡፡
ከዕቅዱ በላይ ገቢ ቢያሰባስብም ገቢውን በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ በማዋል በኩል ሰፊ ክፍተት እንዳለበትም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙ እንደሚያሳየው፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር ክፍያ ለመፈጸም አቅዶ የ869.3 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽሟል፡፡ ይህም የዕቅዱን 48 በመቶ ብቻ እንዳከናወነ የሚያሳይ ነው፡፡ የክፍያ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሆነው ክፍያ የሚፈጸምላቸው አካላት የክፍያ ሰርተፍኬት በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻላቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በዓመቱ ዘጠኝ ወራት በጽሕፈት ቤቱ በተፈቀደው ሒሳብ መሠረት የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ እንዳቀረበው፣ 18,657.49 ካሬ ሜትር የመንገድ ጥገና ለማድረግ ታቅዶ 12,329.78 ኪሎ ሜትር ወይም የዕቅዱን 66 በመቶ ማከናወን ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ ባገጠመው የፀጥታ ችግር ሳቢያ አፈጻጸሙን ዝቅ ማለቱም ታይቷል፡፡
የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ፣ ከ70 የመንገድ ኤጀንሲዎች ለቀረቡለት ዓመታዊ የመንገድ ጥገና ዕቅዶችን በዕቅድ አተገባበር መከታተያ ስልት መሠረት ተገምግመው ግብረ መልስ እንደተሰጣቸው ይጠቅሳል፡፡ የ25 መንገድ ኤጀንሲዎች ሪፖርት በሩብ ዓመቱ በመቀበል በታዩ ክፍተቶች ላይ ግብረ መልስ ስለመሰጠቱም ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ ከመንገድ ኤጀንሲዎች የቀረቡ 501 የክፍያ ሰርተፍኬቶች በዕቅድና በውሉ መሠረት መሠራታቸውን በማረጋገጥ ክፍያ መፈጸሙን፣ በ12 የመንገድ ኤጀንሲዎችና በመንገድ ጥገና ፕሮጀክቶች ላይም የመስክ ምልከታና ግምገማና በማድረግ በአሠራር ክፍተቶች ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ሐሳብ ማቅረቡን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቀዋል፡፡
በ12 ነዳጅ ኩባንያዎች የሚሰበሰበው ገቢ በየወሩ በሚቀርበው ሒሳብ ሪፖርት መሠረት መገምገሙንና ከ27 መንገድ ኤጀንሲዎች ውስጥ በኦዲተሮች የቀረበው የ2010 ዓ.ም. ሒሳብም ተገምግሟል ተብሏል፡፡ የመንገድ ኤጀንሲዎች የውስጥ ኦዲት የ2011 ዓ.ም. በሒሳብ ዓመት የድርጊት መርሐ ግብር እንዲያቀርቡ በተላለፈው የስምምነት ሰነድ መሠረት፣ ከ30 የመንገድ ኤጀንሲዎች ለጽሕፈት ቤቱ የቀረቡለት ሲሆን ሌሎቹም እንዲቀርቡ ክትትል ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የ2010 ዓ.ም. የ66 መንገድ ኤጀንሲዎች የሒሳብ ሪፖርትንም ገምግሟል፡፡
የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋናነት ለመንገድ ጥገና ፈንድ የማሰባሰብ፣ የተሰበሰበን ፈንድ የማስተዳደር፣ ለመንገድ ኤጀንሲዎች የማከፋፈልና የሚከፈለው ገንዘብ ተገቢና ትክክለኛ አገልግሎት መገኘቱን የማረጋገጥ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች በጽሕፈት ቤቱ ለዚሁ ዓላማ የተዘረጋው የክትትልና ድጋፍ ሥርዓትን ተከትሎ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የፈንዱ ተጠቃሚ የሆኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የዘጠኝ ክልሎች የገጠር መንገዶች ባለሥልጣናትና እንዲሁም አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ የተመረጡ ከተሞች የመንገድ ጥገናን የሚያከናውኑ ተቋማት በአጠቃላይ 71 ተቋማት በጽሕፈት ቤቱ የፋይናንስና ቴክኒክ ኦዲት ይደረግባቸዋል፡፡ የፋይናንስ ኦዲት ሥራ በኦዲት ባለሙያዎች የሚከናወን ሲሆን፣ የቴክኒክ ኦዲት ሥራው ደግሞ በኢንጂነሮች የሚከናወን ነው፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በቀጥታ ኦዲት ከሚያደርገው በተጨማሪ የውጭ ኦዲተሮችን በመቅጠር የፋይናንሺያል ኦዲት የሚያስደርግ ሲሆን፣ የክሊክ ኦዲት ሥራው እያንዳንዱ ኤጀንሲ ቀጥሮ የሚያሠራቸውን ኮንሳልታንቶች (አማካሪ ድርጅቶች) አማካይነት የሚከናወን ነው፡፡