የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከስምንት ዓመታት በፊት ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ፣ በመጨረሻ ላይ የታገደውን ዘምዘም ባንክ የምሥረታ ሒደት ለማስቀጠል አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱ ተገለጸ፡፡
ዘምዘም ባንክን በዋና አደራጅነትና ሊቀመንበርነት የሚመሩት ናስር ዲኖ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀድሞም ያላግባብ የታገደው የዘምዝም ባንክ ምሥረታ አሁን በብሔራዊ ባንክ አዎንታዊ ምላሽ በማግኘት የምሥረታ ሒደቱን ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የዘምዘም ባንክን ምሥረታ በድጋሚ ለማቀላጠፍ ላለፉት አሥር ወራት ጉዳዩን በማንቀሳቀስና የተከለከለበትን ምክንያት በማስመርመር በመጨረሻ መግባባት ላይ መደረሱን ያስረዱት ናስር (ዶ/ር)፣ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ አደራጆቹ ከአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር ያደረጉት ውይይት ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡
በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እስላማዊ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም እንደሚቻል መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ወደ አክሲዮን ሽያጭ መግባት የሚያስችላቸውን ደብዳቤ እየጠበቁ መሆናቸውንም ከአደራጁ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በምሥረታ ላይ የነበረው የዘምዘም ባንክ ቢሮ መከፈቱን የጠቆሙት ናስር (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን ላለንበት ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ብሔራዊ ባንክ ያደረጉት ዕገዛ ከፍተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ውሳኔ በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ተከታታይ ደብዳቤዎች በመጻፍ፣ በምሥረታ ላይ የነበረው ዘምዘም ባንክ የታገደበት ምክንያት አግባብ አለመሆኑን የሚገልጹ መረጃዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ያቀረቡዋቸው መረጃዎች ለወራት ተመርምረው ክልከላው ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ተችሏል ብለዋል፡፡
ዘምዘም ባንክ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በሟሟላት እንደሚቋቋም ከብሔራዊ ባንክ እንደተፈቀደ ወደ አክሲዮን ሽያጭ እንደሚገባም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲጀመር የዘምዘም ባንክ አደራጆች ብዙ መድከማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ራሱን ችሎ ባንክ ለማቋቋም ባይችሉም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በባንኮች እንዲሠራበት የሚያስችለውን መመርያ እንዲወጣ አስደርገዋል፡፡ ይህንን ክንውናቸውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹ልፋታችን ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ. በ2008 የፀደቀው የባንክ ቢዝነስ አዋጅ የወለድ ነፃ የባንክ አሠራርን ዕውቅና የሰጠ ሆኖ ወጥቷል፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡
አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ዘምዘም ባንክን ዕውን ለማድረግ ተጨማሪ ሦስት ዓመታትን በፈጀ ያላሰለሰ ጥረት፣ ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታልና 337 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ማስመዝገብ ችሎ የነበረ መሆኑን አደራጆቹ ያወሳሉ፡፡ በወቅቱ ዘምዘም ባንክ 6,800 የአክሲዮን ባለድርሻዎች የነበሩት ሲሆን፣ ከእነዚህ ባለአክሲዮኖች ውስጥ 83 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛውን የአክሲዮን ድርሻ የገዙት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች መሆናቸውን፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች እንደነበሩ አደራጆቹ ይገልጻሉ፡፡
ዘምዘም ባንክ መሥራች ጉባዔውን በማድረግ የቦርድ አባላቱን እ.ኤ.አ. በ2011 መርጦ ነበር፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ባንክ አነስተኛ የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ75 ሚሊዮን ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከፍ በማድረግ፣ በተጨማሪም ዘምዘም ባንክ ሲንቀሳቀስበት ከነበረው ዓላማ ውጪ በወለድም ጭምር እንዲሠራ የሚያስገድድ መመርያ በማውጣት፣ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቋርጡ እንዳደረገ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የዘምዘም ባንክ የምሥረታ ሒደት እንዲቋረጥ የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ ለብሔራዊ ባንክ ገዥ ባስገቡት ደብዳቤ፣ ‹‹ይህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ አግባብ እንዳልሆነ ለማስረዳት የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ብዙ የመንግሥት አካላትን ለማነጋገር የቻልን ቢሆንም፣ ይህን የፖለቲካ ውሳኔ ማስቀልበስ ሳይቻለን ቀርቷል፤›› ብለዋል፡፡
በድጋሚ ለዓመታት የነበረውን ጥያቄያቸውን ይዘው ለመቅረብ ያነሳሳቸው፣ በአገሪቱ በመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ ጥያቄያቸው አግባብ መሆኑን በመረዳት ፈቃድ እንደሚያገኙ በማመን እንደሆነ የሚገልጹት ናስር (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህም ተሳክቶልናል፤›› ብለዋል፡፡ ዘምዘም ባንክ ከወለድ ነፃ የሆነ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የማቋቋም መሆኑን ገልጸው፣ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ አማራጭ ሆኖ የሚቀርብና ለኢኮኖሚውም አጋዥ ይሆናል በማለት ነው፡፡