Tuesday, May 21, 2024

በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል የሀብትና የገቢ ክፍፍል ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እየተዘጋጀ ያለው የሕግ ማዕቀፍ ምን አዲስ ነገር ተልሟል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፌዴራሊዝም የፖለቲካ ሥርዓት ሥልጣንን ያልተማከለ ከማድረግ በዘለለ፣ ሥርዓቱ ከተተገበረበት አገር የሚመነጭ አጠቃላይ ሀብትና ገቢ ለሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የተመጣጠነ ዕድገት ባልተማከለ መንገድ የሚከፋፈልበትን መንገድ ማበጀትና ይኼንንም ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።

በመሆኑም በፌዴራል የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ ልዕልናን ተላብሰው የተዋቀሩ መንግሥታት በአስተዳደር ወሰናቸው ውስጥ ያመነጩትን ሀብትና ገቢ፣ በአስተዳደር ወሰናቸው አስቀርተው ለብቻቸው የሚጠቀሙበት ሳይሆን፣ በዕድገት የተሻሉት በዕድገት ወደ ኋላ ለቀሩት የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታትና ሕዝቦች ሀብታቸውን የሚያቋድሱበትን ዕድል ይፈጥራል።

ይህ መሆኑ በፌዴሬሽኑ ወይም በአገሪቱ ተጠቃለው ለሚኖሩ ሕዝቦች የተመጣጠነ የሀብት ተጠቃሚነትን የሚፈጥር ቢሆንም ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ባለቤትነትን ወይም አሳታፊነትን ባማካለ መንገድ ያልተቀረፀ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት ሳይኖር ክፍፍሉን በተመለከተ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በፌዴሬሽኑ አባላት መካከል አለመግባባትን፣ መካረርን ብሎም ከፌዴሬሽኑ የመውጣት ፍላጎትን ሊያጭር እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በሕግ ከተመሠረተበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ያልተማከለ የሀብት ክፍፍል ትግበራ ላለፉት 27 ዓመታት እየተፈጸመ ነው። ይህ የሀብት ክፍፍል የሚመራበትና የሚተገበርበትን መርህ በተመለከተ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ግልጽ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል።

ሕገ መንግሥቱ የሀብት ክፍፍሉ ዓላማና ክፍፍሉ የሚፈጸምበት ቀመርን በተመለከተ ከደነገጋቸው መርሆዎች መካከል የሚከተሉት መሠረታዊያን ናቸው።

የመጀመርያው መርህ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41(3) የሚመነጭ ሲሆን፣ ይኸውም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመንግሥት ገንዘብ ከሚካሄዱት ማኅበራዊ አገልግሎቶች እኩል የመጠቀም መብት እንዳለው የሚያመለክት ነው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እንዲሻሻልና እኩል ዕድል እንዲኖረው መንግሥት ሀብትን በፍትሐዊነት የማከፋፈል ግዴታ እንዳለበት የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 89(2) ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ መርህን የያዘ ድንጋጌ ነው።

ሦስተኛው መርህ በዚሁ በአንቀጽ 89 ውስጥ የተካተተውና የፌዴራል መንግሥት በዕድገት ወደ ኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት የሚደነግገው የሀብት ክፍፍሉ የሚፈጸምበት መርህ ነው።

 ሌላው ደግሞ በአንቀጽ 94(1) ላይ የተቀመጠው መርህ ሲሆን፣ ይኸውም የፌደራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት የየራሳቸውን ወጪ የመሸፈን ኃላፊነትን የሚያመላክት ነው፡፡ በአንቀጽ 94(2) ደግሞ የፌዴራል መንግሥት የተመጣጠነ ዕድገትን በማያፋልስ ሁኔታ ለክልሎች ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት የሚደነግገው መርህ፣ በአንድነት ተደምረው የሀብት ክፍፍሉ ዓላማና ግብን የተመለከተ ማዕቀፍ እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል።

የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት እንቅፋት ካልሆነ በስተቀር ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ፣ ለመልሶ ማቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ ዕርዳታ ሊሰጥ እንደሚችል የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 (2)፣ እንዲሁም በአንቀጽ 98 ሥር የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል እንደሚከፋፈሉ የሚገልጸው ድንጋጌና በአንቀጽ 55 (6) ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ሲባል በፌዴራል መንግሥት ሕግ እንዲወጣላቸው የሚያስገድዱ ለመሆናቸው፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የታመነባቸው የፍትሐ ብሔር ሕጎችን እንደሚያወጣ የተቀመጠው ድንጋጌ የሀብት ክፍፍሉ ማስፈጸሚያ ቁልፍ ድንጋጌዎች ናቸው።

 በዚህም መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው ድጎማ በክልሎች መካከል የሚከፋፈልበትን ቀመር የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ በተመሳሳይ ለክልሎች የሚሰጠውን የድጎማ ቋት ጨምሮ አጠቃላዩን አገራዊ በጀት የማዘጋጀትና የማፅደቅ ኃላፊነት ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠ ነው፡፡

ከላይ የተገለጹት ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን ለማጣጣም ከፍተኛ ብልኃት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የሀብት ክፍፍሉ የፌዴራል ሥርዓቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እየተፈጸመ ነው።

 የሀብት ክፍፍል ሥርዓቱ ትግበራን በራሱ እንደ አንድ ትልቅ ተግባር መቁጠር ያለበት ቢሆንም፣ ፍትሐዊነት ተጠቃሚነትና ተጠያቂነትን ያረጋገጠና የሀብት ተጋሪዎቹን በሚያረካ መንገድ ሲፈጸም ቆይቷል ለማለት እንደማይቻል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፊስካል ፌዴራሊዝም ተመራማሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሰሎሞን ንጉሤ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

ጉዳዩን በተመለከተ በርካታ ምርምሮችን ያደረጉት ተመራማሪው እንደሚያስረዱት፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ስለመኖሩ ለመገንዘብ ውስብስብ የሆነውን አሠራር በደንብ መረዳት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

የሀብት ክፍፍሉ የሚፈጸመው በሦስት መንገዶች ሲሆን፣ እነዚህም የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው ጥቅልና በሁኔታ ላይ የተገደበ (General and Specific Grant) ድጎማ የመጀመሪያው ሲሆን፣ የጋራ ገቢዎች ክፍፍልና የፌዴራል በጀት ለመሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት የሚያደርገው ወጪዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።

የአገሪቱ ሀብት የማመንጨት አቅም ምንም ይሁን ምን የፌዴራል መንግሥት በጥቅል ድጎማ የሚመድበውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያዘጋጀው ቀመር አማካይነት በየዓመቱ የሚከፋፈለው የጥቅል በጀት ድጎማ፣ የተሻለ ፍትሐዊነት እንዳለው መናገር እንደሚቻል ያምናሉ።

የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ ከሚመድበው በጀት ውስጥ በጥቅል ድጎማ መልክ ለክልሎች የሚከፋፈለው የሀብት መጠን ከአጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት በጀት ውስጥ እስከ 35 በመቶ የሚደርስ መሆኑን በማሳየት፣ የፍትሐዊነት ሚዛኑ የተሻለ ሊባል እንደሚችል ያመለክታሉ።

የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊነት የሚታይበት ሌላ ሰበዝ፣ የፌዴራል መንግሥት ወደ ኋላ የቀሩ አካባቢዎች በሀብት ክፍፍል ሥርዓት ውስጥ ትኩረት እንዲያገኙ ተደርገው መካተታቸው መሆኑን ያወሳሉ።

ይህ ቢሆንም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 98 መሠረት የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ገቢዎች ተብለው የተለዩ ገቢዎች የሚከፋፈልበት ሒደት፣ ግልጽነት የጎደለውና ፍትሐዊነት የማይታይበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የጋራ ተብለው የተለዩት ገቢዎች የሚከፋፈሉት ከ20 ዓመታት በፊት በወጣ ሕግ መሆኑን የተናገሩት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ በዚህ ሕግ የሚደረገው የሀብት ክፍፍል መርህ አልባ እንደሆነና ከክልሎች ይልቅ ለፌዴራል መንግሥት የሚያደላ መሆኑን ያስረዳሉ።

ይኼንንም በምሳሌ ሲያስረዱ በቅጥር ገቢ ላይ ከሚጣል ግብር፣ በኩባንያዎች ላይ ከሚጣል የትርፍ ግብር የሚገኘው ገቢ 50 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት፣ ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ ግብር የተጣለበት ተቀጣሪ ወይም ኩባንያ ለሚገኝበት በሌላ አነጋገር ገቢው ለተሰበሰበበት ክልል ድርሻ መሆኑን ያስረዳሉ። በተመሳሳይ ከተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) የሚገኝ ገቢ የሚከፋፈለው 70 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት፣ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ የቫት ገቢው ለተሰበሰበበት ክልል መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የዚህ አሠራር ኢፍትሐዊነት የሚመነጨው በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች የሚያመርቱት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት በክልሎች ውስጥ ሆኖ፣ ዋና መቀመጫና ምዝገባቸውን የሀብት ክፍፍሉ በማይመለከታትና ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚያደርጉ በመሆኑ ገቢ ሙሉ ሙሉ ወደ ፌዴራል መንግሥት እንዲሆን ማድረጉን ያስረዳሉ።

ምንም እንኳን ጉዳዩ የፖሊሲ ምርጫ ቢሆንም በአገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች የሚከናወኑት በፌዴራል መንግሥት በተቋቋሙ ኩባንያዎች አማካይነት መሆኑ፣ ከዚህ የሚፈጠረው ገቢ ወደ ፌዴራል እንዲሄድ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ። የፌዴራል መንግሥት በዚህ መንገድ የሚያገኘውን ትልቅ ድርሻ መልሶ ለክልሎች የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት እንደሚያውለው ቢከራከርም፣ ይህ የሚፈጸምበት አሠራርና የክፍፍል ድርሻ ግልጽነት እንደሌለው ይገልጻሉ።

ይህ በመሆኑም ክልሎች በፌዴራል መንግሥት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ የማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የሚገልጹት ባለሙያው፣ ባለፉት ዓመታት የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ግንኙነት በመርህና በእኩልነት ላይ የተመራ አለመሆኑ አንዱ ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል የፖለቲካው አካሄድ በማዕከላዊነት መመራቱ ሒደቱን ተዓማኒነት እንዲጎለው ማድረጉንም ያክላሉ።

ወደ መፍትሔው ያነጣጠረ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ

የሀብት ክፍፍሉ የሚመራበትንና የሚተገበርበትን ሥርዓት የሚያሻሽል አዲስ የሕግ ማዕቀፍ፣ በአሁኑ ወቅት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካይነት ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት ነው።

በተዘጋጀው አዲስ የሕግ ማዕቀፍ የመጀመርያ ረቂቅ በመግቢያ ክፍሉ ላይ የሕግ ማዕቀፉን ለማዘጋጀት ምክንያት የሆኑ ሐሳቦች ሠፍረው ይገኛሉ። እስካሁን የፌዴራል መንግሥት የሚመድበውን የድጎማ በጀት ለክልሎች የሚደለድልበትም ሆነ የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት የአሠራር ሥርዓት ወጥነትና ቅንጅት የጎደለው ከመሆኑ የተነሳ፣ በክፍፍሉ ሚዛናዊነትና ውጤታማነት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋሉ የመጡ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ገቢራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ምክንያት መሆኑን የረቂቁ መግቢያ ያመለክታል።

በተጨማሪም የክፍፍሉ ሒደት የበለጠ ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና ተጠያቂነት ይሰፍንበት ዘንድ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር በማስፈለጉ የሕግ ማዕቀፉ እንዲዘጋጅ ምክንያት መሆኑን ያስረዳል።

በረቂቅ የሕግ ማዕቀፉ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ በተመለከተ ሁለት የድጎማ ዓይነቶች ተሰይመዋል። አንደኛው የድጎማ ዓይነት ለጥቅል ዓላማ የሚውል ድጎማ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያለውን መርህ ተከትሎ በቀመር የሚከፋፈል ነው።

ሌላኛውና ማሻሻያ የተደረገበት የፌዴራል መንግሥት ለውስን ዓላማ ማስፈጸሚያ በማለት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ ዓይነት ነው። ይህ የድጎማ ዓይነት የሚሰጥበት መንገድና አሠራሩ ግልጽነት የጎደለው እንደሆነ የሚገልጹት ተመራማሪው፣ ሰሎሞን ንጉሤ (ዶ/ር) በማሻሻያው ትኩረት ማግኘቱን በበጎነት ዓይተውታል።

ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ይኼንን የድጎማ ዓይነት አንድ የተወሰነ ወይም የተገደበ ዓላማን ለማሳካት ታስቦ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ ስለመሆኑ ይገልጻል። ውስን ዓላማ ያለው ድጎማ የሚሰጥበት መርህ በረቂቁ ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ወሰን ውስጥ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ለሚገቡ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም፣ በአንድ ክልል የሚሰጥ አገልግሎት በሌላ ክልል ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ምክንያት የሚያስከትለውን ወጪ ለማካካስ፣ የሴቶች እኩል ተጠቃሚነትን፣ ለዘላቂ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለማጥበብ የሚሉት ይገኙበታል።

ይህ ውስን ዓላማ ያለው ድጎማ የሚከፋፈልበትን መርህ ረቂቁ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ድጎማው ከመሰጠቱ በፊት ተጠቃሚ ክልሎች ዓላማውን በተመለከተ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስምምነት እንዲፈጽሙ ይጠበቅባቸዋል።

 የሥራ አፈጻጸምና የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነት፣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት የውስን ዓላማ ድጎማው ማከፋፈያ መርሆዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

ረቂቅ የሕግ ማዕቀፉ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ስለሚሰጠው የድጎማ ዓይነትና ክፍፍሉ የሚፈጸምባቸውን መርሆች አስመልክቶ ከያዛቸው ድንጋጌዎች በተጨማሪ፣ ትልቅና የነበረውን የፍትሐዊነት ችግር ይፈታል ተብሎ የሚጠበቀው ማሻሻያ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ገቢዎቻቸውን የሚከፋፈሉበትን መርህና ሥርዓት በተመለከተ የተካተተው ማሻሻያ ነው።

አዲስ የተረቀቀው የሕግ ማዕቀፍ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል የክልሎችንም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱን የወጪ ፍላጎቶችና የገቢ አቅማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሆንና መሠረታዊ መርሆቹም የገቢ ምንጭ፣ የነፍስ ወከፍ እኩልነትና የማመጣጠኛ መርሆዎችን ባማከለ መንገድ እንደሚሆን ያመለክታል።

ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት መፈጸም እንዲችሉም በብቃት የተደራጀ ተቋማዊ አሠራር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የክፍፍል ሥርዓቱን ለሚቀይሰው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርግ፣ የድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ኮሚሽን እንዲቋቋም ረቂቁ ማቋቋሚያ ድንጋጌዎችን አካቷል።

 በጋራ ገቢዎች ላይ ያለውን የፍትሐዊነት ጥያቄ ለመመለስ ጉዳዩ የሚመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነቱን ወስዶ ማሻሻያውን ለማድረግ መንቀሳቀሱ፣ ክልሎችም በዚህ ሒደት እንዲሳተፉ መደረጉን የሚያደንቁት ሰሎሞን (ዶ/ር)፣ ሒደቱ የሚያለፋ ቢሆንም መጨረሻ ላይ መተማመንን ለመፍጠር የሚረዳ እንደሚሆን ገልጸዋል።

 ይህ ማሻሻያ ከጋራ ገቢዎች ላይ የፌዴራል መንግሥትና የክልሎች ድርሻ በፍትሐዊነት እንዲሰላ የሚያደርግ መሆኑን ያስረዳሉ።

 ለአብነትም የቫት ገቢ የሚመነጨው አምራቹ በሚገኝበት ክልል ብቻ ሳይሆን፣ ምርቱን ከገዙት በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ ሸማቾች የመነጨ ገቢ በመሆኑ ክፍፍሉም ይኼንንኑ መሠረት በማድረግ፣ የፌዴራልና የተለያዩ ክልሎች ገቢ እንዲሆን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተመሳሳይም አዲስ አበባ ውስጥ ዋና መሥሪያ ቤታቸውን አድርገው በክልሎች ከንግድ እንቅስቃሴያቸው በሚያመርቱ ኩባንያዎች ላይ የሚገኝ የትርፍ ግብርም ሆነ የቅጥር ግብር ገቢ፣ ለፌዴራል መንግሥት ብቻ ሲገባ የነበረበትን አሠራር በማስቀረት ፍትሐዊ ክፍፍል የሚደረግበትን ሥርዓት እንደሚያበጅ ያምናሉ።

ይህ ሥርዓት የተሻለ የተፈጥሮ ሀብትና ሌሎች ሳቢ ሀብቶችን የያዙ ክልሎች፣ እንዲሁም የተሻለ መሠረተ ልማትና ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመያዛቸው ምክንያት በርካታ ኩባንያዎችን ማስጠለል ለቻሉ ክልሎች የተሻለ የገቢ ዕድል የሚፈጥር ቢሆንም፣ ይህ ሊፈጥር የሚችለውን መዛባት ከጥቅል ገቢ ድጎማውና ለውስን ዓላማ ከሚውለው የድጎማ ሥርዓት ጋር በማቆራኘት መቅረፍ የሚቻልበት አሠራር እንደሚኖር አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -